Monday, 28 January 2019 00:00

ለዘንድሮው የኦስካር ሽልማት የታጩ ፊልሞች ታወቁ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 ዘንድሮ ለ91ኛ ጊዜ ለሚከናወነው ታላቁ የአለማችን የፊልም ሽልማት ኦስካር የታጩ ፊልሞች ዝርዝር ባለፈው ማክሰኞ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ “ሮማ” እና “ዘ ፌቨራይት” እያንዳንዳቸው ለ10 ጊዜ በመታጨት ቀዳሚነቱን ይዘዋል፡፡
“ኤ ስታር ኢዝ ቦርን” እና “ቫይስ” እያንዳንዳቸው ለ8 ጊዜያት በመታጨት በሁለተኛነት ሲከተሉ፣ብዙ ሲባልለት የከረመውና የአመቱ ምርጥ ፊልም ዘርፍን ጨምሮ  7 ጊዜ የታጨው “ብላክ ፓንተር” በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ከ“ብላክ ፓንተር” ጋር በአመቱ ምርጥ ፊልም ዘርፍ የታጩት ሌሎች ፊልሞች “ብላክክላንስማን”፣ “ቦሜን ራፕሶዲ”፣ “ዘ ፌቨራይት”.፣ “ግሪን ቡክ”፣ “ሮማ”፣. “ኤ ስታር ኢዝ ቦርን” እና “ቫይስ” የተሰኙት ፊልሞች ናቸው ተብሏል፡፡
ክርስቲያን ቤል፣ ዊሊያም ዴፎ፣ ራሚ ማሌክና ቪጎ ሞርቴንሴን በምርጥ መሪ ተዋናይ ዘርፍ ለዘንድሮው ኦስካር ሽልማት ሲታጩ፤ በምርጥ ተዋናይት ዘርፍ ደግሞ ያሊዛ አፓሪኮ፣ ግሌን ክሎዝ፣ ሌዲ ጋጋ፣ ኦሊቫ ኮልማንና ሜሊሳ ማካርቲኒ ታጭተዋል፡፡
በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው የኦስካር ምርጥ ዳይሬክተር ዘርፍ ለሽልማት የታጩት የፊልም ዳይሬክተሮች ደግሞ ስፓይክ ሊ፣ ፖዌል ፖሊኮውስኪ፣ ዮሮጎስ ላንቲሞስ፣ አልፎንሶ ኳሮንና አዳም ማኪይ መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በመጪው ወር መጨረሻ የሚከናወነው የኦስካር ሽልማት ስነስርዓት በኤቢሲ ቴሌቪዥን ጣቢያ በቀጥታ እንደሚሰራጭና በመላው አለም በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ይመለከቱታል ተብሎ እንደሚገመትም ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
በዘንድሮው ኦስካር በብዛት በመታጨት ቀዳሚነቱን የያዘው የፊልም ስቱዲዮ ታዋቂው ዋልት ዲዝኒ ሲሆን፣ ዲዝኒ ለ17 ጊዜያት ለሽልማት መታጨቱ ተነግሯል፡፡

Read 886 times Last modified on Saturday, 26 January 2019 15:56