Monday, 28 January 2019 00:00

የለውጡ ትሩፋትና ያጣመምነው ጉዞ!

Written by  (ደ.በ)
Rate this item
(2 votes)

የሰማሁት አንድ ታሪክ- በእጅጉ መሥጦኝ ሳሰላስል፣ የኛን ሀገር የቅርብ ጊዜ ታሪክ እየመሰለኝ መጣ፡፡ ሰውየው፤ አንድ ሺህ ብር የማይሞላ ደሞዝ የነበረውና ኑሮውን በመከራ የሚገፋ ነው፡፡ ታዲያ ፈጣሪ ከሰማይ አየውና፣ ብዙ ሚሊዮን ብሮች የሎተሪ ዕጣ ወጣላት። ይሁንና ይህ ገንዘብ ለሰውየው ፀጋ ብቻ አልነበረም፤ ግራ መጋባትም ጭምር እንጂ፡፡ ስለዚህም ብሩን ተቀብሎ መኪና ገዛ፡፡ መኪናውን ሲገዛ ግን መንጃ ፈቃድ አላወጣም፡፡ ችሎታም የለውም፡፡ እናም ብር የሚያመጣው ድፍረት ደፈነውና መኪናውን በጉልበት ያሽከረክር ገባ። መኪናውን ባሽከረከረ ቁጥር አደጋው በዛ። ባጃጆች እየገጨ፣ ገንዘብ እየከፈለ እያሠራ ከቆየ በኋላ የባሰው ጉድ መጣ፡፡ ዕድለኛው ሰው መንገደኛ ገጨና እሥር ቤት ገባ፡፡ የሎተሪው ዕድለኛ - ዕድሉን በርጋታ መጠቀም ስላቃተው አሁን ማረሚያ ቤት ይገኛል፡፡
አንዳንዴ በድንገት የሚመጡልንን ያልተጠበቁ ዕድሎች በወጉ መጠቀም ካቃተን የሚገጥመን ዕዳ ቀላል አይደለም፡፡ ምናልባትም ሁለመናችንን ልናባክነው እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣው ለውጥ ለእሥረኛው፤ አሸባሪ ለተባለው ፖለቲከኛ፣ ቤተሰቦቹ ለተጎዱበት፣ ንብረቱን ለተቀማና ለሁላችንም ያልተጠበቀ በረከት ነው፡፡ በገዛ ሀገራችን ፖሊስ ባየን ቁጥር የምንበረግግበት፣ ባልታወቀ ሰውና ሁኔታ ቤት ንብረታችን የሚቀማበት፣ በዘር አድልዎ የምንገለልበት፣ በቋንቋ የምንገፋበት ጊዜ አልፎ “እንደ ልብ” ተናገሩ፤ ሃሳባችሁን ግለጡ፣ የተሰደዳችሁ ሀገራችሁ ግቡ” ሲባል ህልም የመሰለን ብዙ ነበርን፡፡
ይሁን እንጂ (በአብዛኛው) አያያዙን ያወቅንበት አንመስልም፡፡ አንዳንዶቻችን “እኛ እያለን እነዚህ እንዴት ሥልጣን ይይዛሉ” የሚል ቅናት ቢጤ የተሰማን ይመስላል፡፡ በዚህም የተነሳ ሀገሪቱን ከማዳንና ለውጡን ከማስገስገስ ይልቅ ድንጋይ ለማንሳት ጐንበስ እያልን ነው፡፡
ሌሎቻችን ከዚህ ቀደም በነበረው መንግሥት አሮጌ አሠራር ውስጥ የደረሰብንን በደል እየቆጠርን፣ ዛሬ በዚህች ዕድል ሥልጣን መናጠቅ፣ ቁጭታችንን መበቀል አለብን ብለን ተነስተናል፡፡ ስለዚህም መራራ ዋጋ ከፍለውና በእሳት ተቀቅለው የታገሉልንን ሰዎች እንደ ባላንጣ ማየት ጀምረናል፡፡ ምናልባትም  እነዚህ ሰዎች ያንን ዋጋ ለመክፈል ባይቆርጡ ኖሮ፣ ዛሬ ሥልጣን ለቅቀው በየአቅጣጫው ጥፍራቸውን አርዝመው የሚቧጭሩን ሰዎች የት ያደርሱን ነበር? ብለን አናስብም፡፡ በደረሰን ሎተሪ ዕድሉን ተጠቅመን፣ በአንድ ሀገር በእኩልነትና በፍትህ፤ በወንድማማችን ለመኖር ሥነ ልቡናዊ ዝግጅት አናደርግም፡፡ ይልቅስ አሁንም ከዚህ ቀደም አባቶቻችን ባለማወቅ እንዳደረጉት፣ አንዳችን ለአንዳችን መቀበሪያ ጉድጓድ እንቆፍራለን፡፡
ሌሎቻችን ደግሞ ይህንን ዕድል ተጠቅመን፣ የሠፈራችንን ድንኳን ለመሙላት አጋጣሚውን ለሽሚያ መጠቀም ይቃጣናል፡፡ የትግሉ መሪዎች እንደሚነግሩን፤ የትግሉ ዓላማና ግብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት፣ በፍትህና በሠላም የሚኖሩባትን የጋራ ሀገር መፍጠር ነው፡፡
ከዚህ በፊት የነበሩ ስህተቶችን ሳንደግም፣ አንዱ ሲዘፍን ሌላው የሚያለቅስበትን፣ አንዱ ሲጠግብ፣ ሌላው የሚራብበትን ማህበረሰብ ለመፍጠር ሳይሆን ሁሉም እኩል የሚሆንባትን የበለፀገች ኢትዮጵያ ለትውልድ ለማውረስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህን እውነት ለመቀበል ያልተዘጋጀና ያልሰለጠነ አእምሮ ያላቸው ተንሳፋፊዎች፣ የትናንት ጥብቋቸውን አውልቀው፣ ዛሬም ከባለ ጊዜ ጋር በመለጠፍ፣ “ጊዜው የኛ ነው” የሚል መዝሙር እየዘመሩ እንደሆነ፣ ከየሥራቸው ያንሾካሾኩት ወሬ በአደባባይ እያጋለጣቸው ነው፡፡ ጊዜው የማንም አይደለም፤ ጊዜው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው!! ጊዜው የኦሮሞ ነው! ጊዜው የትግራይ ልጆችም ነው! ጊዜው የአማራ፣ ጊዜው የሲዳማም ነው! ጊዜው ዘርና ጐራ አይመርጥም! የኢትዮጵያ ነው! ጊዜው!!
“ኦዴፓ” የታገለው ለሁላችንም ነው፡፡ እኛም ከጐኑ የቆምነው የብሔር ወኪላችን በመሆኑ አይደለም፡፡ በቀጣይ ምርጫ” “ኦዴፓ”ን ለመምረጥ ኦሮሞ መሆን የለብኝም፡፡ “ኦዴፓ” የኦሮሞ ሕዝብ ፓርቲ ቢሆንም የኛም የነፃነት ጠበቃ፣ የዛሬው ብርሃን አድማስ ነው፡፡ ስለዚህ ለውጡን በሚጠቅመንና ለተሻለ ዕድል ብንጠቀምበት ለሁላችንም ይበጀናል፤ ባይሆንና ብናበላሸው ግን የሁላችንም ዕድል ይበላሻል፡፡
አሁን ያለንበት ጊዜ ወደ ቀጣዩ ሕልማችን የሚያደርሰን መነሻ መንገድ ስለሆነ በተጀመረው ሀገራዊ አንድነት፣ የፍቅርና መተሳሰብ፣ የምህረትና ይቅርታ መንገድ ተያይዘን፣ ወደ በለፀገች ኢትዮጵያ እንጓዝ፡፡
ክልሎችም ሕገ-መንግሥቱ በሰጣቸው ሥልጣንና መብት መጠቀም ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም መብት አክብረው፣ በመተሳሰብ፣ የተሻለች ሀገር ለመፍጠር፣ የራሳቸውን ሚና መጫወት  ይጠበቅባቸዋል፡፡ በነጠላ ከመታገል ይልቅ በቡድንና በህብረት መሥራት ውጤት እንደሚያመጣም ሊያስተውሉ ይገባል፡፡ በጆንሲ  ማክስዌል የተጻፈ አንድ መጽሐፍ ላይ ያነበብኩት ነገር ይህን ሃሳብ ያጠናክራል፡፡
በጋዜጣው ጀርባ ላይ ቀልቤን የሳበው አንድ ማስታወቂያ፣ የቅርጫት ኳስ አሰልጣኝ የሆነውን የጆን ውድን ምስል ይዟል፡፡ የምስሉ ርዕስ “በቅርጫቱ ውስጥ ኳሷን ያስገባው ወጣት ባለ አሥር እጆች ነው” ይላል፡፡ ይህንን ያሉት በአመት ውስጥ አሥር ጊዜ የሀገሪቱ ሻምፒዮን ስለሆነ ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ ውጤት የተአምር ያህል ነበር፡፡ ይህ ብልጫ ጠንካራ ልምምድን የጠየቀና በስልጠና የተገኘ ቢሆንም፤ ዐቢዩ ጉዳዩ ግን የአሰልጣኝ ጆን ውድን የቡድን ሥራ መሥራት ነው፡፡
ከመጽሐፉ ማጠቃለያ የምንረዳው፤ አሰልጣኙ፣ ሁሉም ተጫዋቾች በተሰለፉበት ቦታ በሚገባ እንዲጫወቱና በአንድነት ታላቅ ቡድን እንዲፈጥሩ መትጋታቸውንና ያንንም ማሳካታቸውን ነው፡፡ የስኬታቸውም ምስጢር ይኸው ነው፡፡
ይህ ምሳሌ ለሀገራችን ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ይመስለኛል፡፡ አንዳችን ለአንዳችን ሀይል ነን፤ አንዳችን ለሌላችን አጋር ነን፡፡ ይህንን ጠብቀን ከሄድን ብቻ ነው በዓለም ላይ ታላቅ የሆነች ሀገርን መፍጠር የምንችለው፡፡ አለበዚያ ደግሞ እንደፈረሱት ሀገራት ፈርሰን፣ የሞቱት እየሞቱ፣ የተረፍነው በየሀገራቱ እርጥባን እንለምናለን፡፡
በተለይ በአንድነትና በፍቅር ጉዳይ ላይ ስናወራ፣ ግንባር ቀደሙን ሚና መጫወት የነበረባቸው የእምነት ተቋማትና የኪነጥበብ ሰዎች ናቸው፡፡ ይሁንና ባለፉት ዓመታት በተሰራው ቀናነት የጐደለው ሥራ ሁላችንም በጐራ ተከፍለን፣ የፈጣሪን አንድነትና የፍቅር ሃሳብ ከመስበክ ይልቅ በእጅጉ ምድራዊና ዐለማዊ ሆነን፣ ጐጣችንን ስንሰብክ ኖረናል፡፡ በቅርቡ አቶ ለማ መገርሳ በአንድ መግለጫቸው እንደተናገሩት፤ “በአንድ እጃችን መጽሐፍ ቅዱስ በሌላ እጃችን ሌላ ነገር ይዘናል፡፡ በእሳት ላይ ውሃ ከመድፋት ይልቅ ነገር የምንጭርበት ክብሪት ታጥቀናል፡፡ ለመሆኑ የትኛው አምላክ ይሆን በዘር ለይተህ፣ ሌላኛውን አጥፋ ብሎ ያስተማረው? በቅዱስ መጽሐፍት ዓለምን መመዘን የሚገባቸው ሰዎች በመጽሐፉ ሲመዘኑ ዜሮ ሆነዋል፤ ወድቀዋል፡፡ ቢሆንም መጽሐፉ የሰጣቸው የይቅርታ ተስፋ ስላለ፣ የመመለስና በቀናው መንገድ እየተጓዙ፣ ቀና መሥራትና ሕዝብን ወደተሻለ ህይወት የማድረስ ዕድሉ አላቸው፡፡
ስፖርተኞችና ስፖርት ከዚህ ቀደም ስናውቀው፣ የአንድነትና የሰላም ባንዲራ የሚውለበለብበት መንደር ነበር፡፡ ዘርና ሃይማኖትን፣ የቀለም ልዩነትን ሁሉ ያሸነፈ ነበር። አሁን የምንሰማው ግን አስደንጋጭ ነው። ሰሞኑን “ስፖርት ዞን” በተሰኘው የሬዲዮ ፕሮግራም የሰማሁት ነገር በእጅጉ ገርሞኛል፡፡ ጉዳዩ አንድ ለረጅም ዓመት በብሔራዊ ቡድን የተጫወተ፣ በተለይም በመካከለኛውና ምሥራቅ አፍሪካ ውድድር ጊዜ፣ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ልዩ ትዕዛዝ በቻርተር አውሮፕላን የተጓዘ፣ በኋላም የእግር ኳስ አሰልጣኝ የነበረ ሰው ወደ ግብርና ሙያ ሊገባ መገደዱን ጠቅሰው የተረኩት ነገር ነበር፡፡ ስፖርተኛው የሥልጠና ሰርተፊኬቶች ያሉትና ብዙ ልምድ ያካበተ ቢሆንም የክልል ክለቦች ግን “የራሳችንን ሰው እንቀጥራለን” በማለት እንደማይፈልጉት ነግረውታል፡፡ ይሄ የሚያሳየን ከእንግዲህ ሰው በችሎታው ሳይሆን በብሔሩ ብቻ እንደሚመዘን ነው፡፡ ለመሆኑ ይህንን ማድረግ ለማን ይጠቅማል? “ብሔር አምላኪዎችስ” ቢሆኑ ችሎታ ባለው ሰው ቡድናቸውን አሰልጠነው፣ የሚያመልኩትን ብሔር ባለ ውጤት ቢያደርጉት አይሻልም? በየአደባባዩ በሽንፈት ከመፈጥፈጥ ባለሙያን ተጠቅሞ ባለክብር መሆን አይመረጥም? እንኳን የሀገራችንን ልጆች የውጭ ሀገር አሰልጣኝ በውድ ዋጋ እያመጣን ለበርካታ ዓመታት ለውጤት ተጠቅመን የለ እንዴ? ሳስበው ሁላችንም እያበድን ነው፤ ወይም ረጅም ስካር ውስጥ ነን፡፡ ስንነቃ ይቆጨናል፡፡
ሌሎቻችን የለውጡን መንግሥት በመተቸት ሥራ ላይ ተጠምደናል፡፡ የትችታችን ምክንያት ደግሞ ተጨባጭ ባለመሆኑ፣ ሰውን ግራ ከማጋባት ያለፈ ፋይዳ አላስገኘም፡፡ የስነ አመራር ምሁሩ ጆን ማክስዌል እንደሚሉት፤ መሪነት ከሚያስከፍላቸው ዋጋዎች አንዱ የትችት በረዶን መቀበል ነው፡፡ የሞቀ ስሜትን ለማቀዝቀዝ፣ ከፍ ያለ የለውጥ ሃይልን ለማሽቆልቆል የሚሞክሩ ሰዎች መኖራቸው የግድ ነው፡፡ የሰው ልጅ በተፈጥሮው ለትችት ፈጣን ቢሆንም እንደኛ ማበረታታትና ማመስገን እርም የሆነበት ሀገር ያለ አይመስለኝም፡፡ እኛ ትልቁ ራስ ምታታችን፤ ሰዎችን ማመስገንና አጥፍቶ ይቅርታ መጠየቅ ነው፡፡
በየትኛውም ሀገር፣ በየትኛውም ዘመንና ሁኔታ ለውጥ ሲመጣ፣ ጥቅማቸው የሚነካባቸው ወገኖች፣ ያንን በተፃረረ መልክ ተሰልፈው የሚችሉትን ማድረጋቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ የእኛ ሀገር የሚለየው ከጐዳቸው ይልቅ ሰንሰለታቸውን የበጠሰላቸውና ቀንበራቸው ከጫንቃቸው ላይ የወረደላቸው ወገኖች ብሰው መገኘታቸው ነው። በየመንገዱ በግፍ ከመገደል፣ ያለ ምክንያት ከመታሰር፣ በገዛ ሀገር ከመሳቀቅ የተረፉ ከለውጡ በተቃራኒው ቆመው፣ ሌላ ጉድጓድ እየቆፈሩ፣ በታላቅ ተጋድሎና መስዋዕትነት የተገኘውን ድል አፈር ሊመልሱበት እየደከሙ  ነው፡፡
እንደኔ እንደኔ፤ ለሁላችንም የሚያዋጣን ፍቅርና ይቅርታ ብቻ ነው፡፡ ያለፈውን ዘመን ቂም እያሰላሰልን ሌላ የበቀል ጉድጓድ የምንምስ ከሆነ፣ ሁላችንም እዚያው ጉድጓድ ውስጥ እንገባለን፡፡ የሺህ ዓመታት የእምነትና የሃይማኖት ታሪክ አለን የምንል ኢትዮጵያውያን፤ እርስ በርስ ለመጠፋፋት ሰይፍ ስንመዝዝ ብንገኝ፣ ዓለም ሁሉ ባንድ ድምጽ ይስቅብናል፡፡
ታሪክና ሥልጣኔ በገቢር ሲሰፈር ባዶ ሆኖ ከተገኘ፣ ውጤቱ ሀፍረትና ውድቀት ነው፡፡ ስለዚህ በአንድ ድምጽ በተባበረ ልብ፣ ኢትዮጵያን ታላቅ ለማድረግ፣ መሥራትና ከስግብግብነት  መውጣት አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡
ገጣሚው አሌክስ አብረሃም ለሀገራችን የተመኘውን እኔም ልመኝ - በእሱ ስንኞች፡፡
ካገር ማድጋችን ውስጥ
የጥላቻ እርሾ የቂም ቡኮ ይፍሰስ
ኑሮ የደቆሰው ደሳሳ ጐጇችን በባርኮት ይታደስ።
እንደ አደይ ድምቀት - ፈገግታችን ይፍካ፣
የተራቆተ ኪስ ይሙላ በፈራንካ
የታመሙት ነፍሳት በገፍ ይፈወሱ፣
የጤና እንስሳት በምድራችን ፊት ላይ ዘላለም ይንፈሱ
ሁላችንም ሀሳባችንና ሕልማችን ወደተሻለ ህይወትና ብልጽግና ቢሆን፣ እኛና ቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር አይተን፣ በተረጋጋ ኑሮ፣ ታላቂቱን ኢትዮጵያን በዓለም ፊት እናሳያለን፡፡
ልብ ላለውና ላስተዋለ ሰው፤ ይህ ታላቅ ዕድል ከፈጣሪ የተሰጠ፣ የሎተሪን ያህል አስደሳች ክስተት ነው፡፡ ይህንን ዕድል ባንጠቀምበት፣ ዕጣ ፈንታችን ለቅሶና መከራ ነው፡፡ ምርጫችንና መንገዳችን እንዲስተካከል ምኞቴና ፀሎቴ ነው።  

Read 4783 times