Monday, 28 January 2019 00:00

ቃለ ምልልስ ከሚጣሉ ፕላስቲኮች ፋብሪካና ኢንዱስትሪ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“… ዛሬ የውሃ መስመሮች በሙሉ በፕላስቲክ ቱቦ እየተተኩ ነው፡፡ መኪናዎች በአብዛኛው በፕላስቲክ ነው የሚሰሩት፡፡
አውሮፕላን 80 በመቶ ፕላስቲክ ነው፡፡ ኮምፒውተር፣ ስልክ፣ ጠረጴዛ፣ ወንበር … ሁሉም ፕላስቲክ እየሆነ ነው፡፡…”

    በኬሚስትሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ያገኙት አቶ ሲሳይ ክፍሌ፤ የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት በሂልኮ ኮሌጅ
ተከታትለዋል፡፡ ሁለተኛ ድግሪያቸውን ደግሞ በሥራ አስተዳደር አግኝተዋል፡፡ ከሣይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በምርምር ስራ ላይ እንደሚሳተፉ
የሚናገሩት አቶ ሲሳይ፤ ለረዥም ዓመታት ትኩረታቸውን በፕላስቲክ ጥናትና ፈጠራ ላይ አድርገው መቆየታቸውን ይገልጻሉ። በአሁኑ ወቅት
ጅግዳን ከተባለ ኮሌጅ ጋር በመተባበር በፕላስቲክ የፈጠራ ስራዎች ላይ ስልጠና የሚሰጥ የሙያ ት/ቤት ከፍተዋል፡፡ በቅርቡ የፕላስቲክ ውዳቂን ወደ ጥቅም በመቀየር የአካባቢ ብክለትን መቀነስ” የሚል በፕላስቲክ ውዳቂ አያያዝና አጠቃቀም ላይ ያተኮረ መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ አቶ ሲሳይ ክፍሌ፤ በመጽሐፋቸውና በውዳቂ ፕላስቲኮች ትሩፋቶች ላይ እንዲሁም በወደፊት ዕቅዳቸው ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል፡፡ እነሆ፡-

    የፕላስቲክ ውዳቂን ወደ ጥቅም በመቀየር ላይ ያተኮረ መፅሐፍ አሳትመዋል፡፡ መጽሐፉን ለማዘጋጀት ያነሳሳዎት ምንድን ነው?
መፅሐፉን ለመፃፍ ያነሳሳኝ አንድም የሙያ ግዴታዬ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፕላስቲክ በመጠቀም ሂደት ውስጥ የሚታዩ የግንዛቤ ችግሮች ናቸው፡፡ የተጠቀምንባቸውን ፕላስቲኮች እንዲሁ በየመንገዱ በየሜዳው እንደ አልባሌ ነው የምንጥላቸው፡፡ እነዚያ የተጣሉ ፕላስቲኮች በዝናብ ወቅት ከጎርፍ ጋር የመንገድ ቱቦዎችን እየደፈኑ፣ መንገዶች እንዲበላሹ ሲያደርጉ እንታዘባለን፡፡ ከዚህ አንፃር ሰው ስለ ፕላስቲክ ምንነት በቂ ቅንዛቤ ቢያገኝና ቢጠቀምበት፣ይህ ሁኔታ ሊቀየር ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ለህብረተሰቡ ትምህርት ለመስጠትም ነው አላማው፡፡
ፕላስቲክ አካባቢ በካይ እንደሆነ ነው የሚታወቀው፡፡ እርስዎ ደግሞ በመጽሐፍዎ ፕላስቲክ ጠቃሚ መሆኑን ጽፈዋል፡፡ እስቲ ያብራሩልን …
ፕላስቲክን በአግባቡ አልተረዳንም እንጂ ዘላቂ እድገትን ያለ ፕላስቲክ ማሰብ አይቻልም። ሳይንስ በምርምሩ የፈጠረው ፕላስቲክ፤ ለሰው ልጅ መሰረታዊ ጥቅም ያለው ነው፡፡ ልክ እንደ ምግብ፣ መጠለያ ልብስ ነው የሚቆጠረው። ፕላስቲክ፤ እንጨትን ብረትንና ሌሎች አላቂ የሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶችን መተካት የሚችል ነው። ፕላስቲክ በጤናው፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ በህክምናው ብንመለከት እንኳ በቀዶ ጥገና ሰውነታችን ውስጥ የምንተካቸው አይን፣ ቆዳ፣ እግር፣ ልብ ሌሎችም ከፕላስቲክ ይሰራሉ፡፡ አርቴፊሻል ደም ሁሉ እየተሰራበት ነው ያለው - ፕላስቲክ። በኮንስትራክሽኑ ደግሞ ከቤት ግንባታ ጀምሮ እስከ ቤት እቃ ድረስ ፕላስቲክ በርካታ ድርሻ አለው፡፡ ፕላስቲክ የማያገለግለው ነገር የለም ማለት ይቀላል፡፡
የኛ ማህበረሰብ ደግሞ ለፕላስቲክ ያለው ግምት አነስተኛ  ነው?
ይሄን መፅሐፍ ለመፃፍም ያነሳሳኝ አንዱ ጉዳይ ይሄ ነው፡፡ ፕላስቲክ ቀላል ክብደት ስላለው ቢያንስ ሰብስቦ አንድ ኪሎ እንኳ ለመሙላት ከባድ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሁሉም ማህበረሰብ ፕላስቲክን ወደ ገቢ ምንጭነት መለወጥ አይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በፅዳት ስራ ላይ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ቢያንስ በስራቸው አጋጣሚ ስለሚያገኙት፣ እንዴት ወደ ጥቅም መቀየር እንደሚችሉ በቀላሉ መረዳት ይችላሉ። ተጠቃሚው ወይም ፕላስቲክን የሚጠቀመው ማህበረሰብ ደግሞ ቢያንስ ከመፅሐፉ ስለ ፕላስቲክ ግንዛቤ አግኝቶ፣ ፕላስቲክን እላዩ ላይ በሰፈረው ቁጥር መሰረት ማጠራቀም እንዲችል ይረዳል፡፡ ይሄ ለፅዳት ሰራተኞች በጣም ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ፕላስቲክ ተፈጭቶ እንደገና ወደ ምርት መለወጥ ይችላል። ፕላስቲክ ሳንፈጨውም በቤታችን ለተለያየ ተግባር ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡ እኛ ሃገር ያለው ችግር፣ ትንሽ የመሰለ ነገር ትልቅ ዋጋ ያለው መሆኑን ያለመረዳት ነው። ሳንቲም ተጠራቅሞ ነው ብር የሚሆነው፡፡ የፕላስቲክም ነገር እንደዚያው ነው። በሌላ በኩል፤ መንግስት ህብረተሰቡ ፕላስቲክን እንዳይጠቀም ከልክሏል። ግን ህዝቡም መጠቀሙን አልተወም፤ ፕላስቲክ ፋብሪካዎችም ማምረት አላቆሙም። ፕላስቲክ በእርግጥም አካባቢን ይበክላል፤ ነገር ግን እንዳይበክል ተደርጎ በላቀ መልኩ መጠቀም ይቻላል። ምናልባት የውሃ ቱቦና መንገድ ላይ መጣል በህግ ሊከለከል ይችላል እንጂ በአጠቃላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለውን ፕላስቲክ በጥቅሉ መጠቀም መከልከል ተገቢ አይሆንም፡፡
በርካታ አገራት ፕላስቲክ መጠቀምን በህግ ከልክለዋል…
አዎ፤ መከልከል የሚሞክሩ ሃገሮች አሉ። እነ ኬንያ፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ… ለመከልከል ሞክረዋል፤ ግን አልቻሉም፡፡ ፕላስቲክ ማምረት ከቆመ ወደ እንጨትና ሌሎች ተፈጥሮአዊ ሃብቶች ይገባል። ተፈጥሮአዊ የሆኑ ነገሮች ደግሞ ወደድንም ጠላንም ማለቃቸው አይቀርም፡፡ አብዛኞቹ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በፕላስቲክ የሚመረቱ ናቸው፡፡ ምናልባት እንደ ወረቀት የሚበሰብስ ፕላስቲክ መስራት ይቻላል፤ ተሰርቶም ተሞክሯል። ፕላስቲክ፤ እንጨትና ብረትን ተክቶ ስለሚጠቅም እንዳይመረት ማድረግ አይቻልም፡፡ ፕላስቲክ በማንኛውም ዘርፍ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኝ ነው። በእርሻ፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት----በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ ጥቅም እየሰጠ ነው። በተለይ በኮንስትራክሽንና በጤና ዘርፍ ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ ጉሉኮስ፣ የህክምና ማሽኖች፣ የተተኪ አካላት ቁሳቁስ ይመረትበታል። በሃገራችን ከ700 በላይ የፕላስቲክ ፋብሪካዎች አሉ፡፡ እነዚህ ምን ያህል ያመርታሉ የሚለው ሌላ ጉዳይ ሆኖ አብዛኞቹ ግን በትንሽ ደረጃ ነው ያሉት፡፡ የስድስት ፋብሪካዎች አጠቃላይ ዋጋ ምናልባት አንድ ቪ8 መኪና ቢገዛ ነው፤ ስለዚህ ሴክተሩ ምንም ፋብሪካ የለውም ማለት ይችላል። በተለይ ጥራቱ ቁጥጥር ተደርጎበት፣ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ቢመረት ትልቅ ጥቅም የሚሰጥ ነው፡፡ ዛሬ የውሃ መስመሮች በሙሉ በፕላስቲክ ቱቦ እየተተኩ ነው፡፡ መኪናዎች በአብዛኛው በፕላስቲክ ነው የሚሰሩት፡፡ አውሮፕላን 80 በመቶ ፕላስቲክ ነው፡፡ አንድ ሰው በቤቱ ያሉትን እቃዎች ትኩረት ሰጥቶ ቢመለከት፣ አብዛኛው ፕላስቲክ ነው፡፡ ኮምፒውተር፣ ስልክ፣ ጠረጴዛ፣ ወንበር… ሁሉም ፕላስቲክ እየሆነ ነው፡፡
ቤቶችም በፕላስቲክ እየተሰሩ እንደሆነ ይታወቃል ----
ምርምር ሁልጊዜ ሲሰራ ቀጣይነቱ ወሳኝነት አለው፡፡ የፕላስቲክ ቤት በህንድ ነው መሰራት የጀመረው፡፡ በኛም ሃገር መሰራቱ ተነግሯል፡፡ ግን አንድ ከተማ በፕላስቲክ መገንባት ይቻላል? ቀጣይነት ያለው ነው? የሚለውን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ለኔ ትልቁ ቁምነገር ፕላስቲክን ወደ ላቀና ቀጣይነት ወዳለው ጥቅም መቀየሩ ነው፡፡ ከፕላስቲክ ፖሊስተር ክር ተሰርቶ ልብስ ይሆናል፡፡ ፈጠራ ለኔ ይህ አይነቱ ነው፡፡ እንደዚህ ዘላቂ የሆነ ነገርን ማሰብ ያስፈልጋል። ፕላስቲክን ፈጭተው ወደ ውጪ የሚልኩ አሉ። “ውዳቂ ፕላስቲኮች ወደ ውጪ ስለሚላኩ፣ የምናመርተው ጥሬ ዕቃ አጣን፤ ይከልከልልን” የሚል አቤቱታ በአንድ ወቅት ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ቀርቦ ነበር፡፡ በእርግጥ ፕላስቲክ ፈጭቶ ወደ ውጭ በመላክ ምናልባት 1 ዶላር ሊገኝ ይችላል፤ ነገር ግን የፕላስቲክ ጥሬ እቃን በ10 እና 20 ዶላር መልሰን እንገዛለን፡፡ ወደ ውጪ ፈጭቶ ከመላክ ይልቅ እዚሁ ቢመረት ትልቅ የገቢ ልዩነት ነው የሚፈጠረው፡፡ ዋናው ጥሬ እቃ ከነዳጅ ተረፈ ምርት ስለሚገኝ እሱ ላይኖረን ይችላል፤ ነገር ግን ቢያንስ ውዳቂ ፕላስቲክ ፈጭቶ ወደ ውጪ ከመላክ አስፈላጊውን ማሽን አስገብቶ፣ ሙሉ ምርት እዚሁ ማምረት የተሻለ ይሆናል። ቤት መስራት ምናልባት እንደ ጥበብ ሊሆን ይችላል እንጂ ብዙ ጥቅም የለውም። ትልቁ ነገር ቋሚ ዘላቂ ነገር ላይ ማዋል ነው። በውጪ ሃገርም ለገና ዛፍ፣ ለአበባ፣ ለቤት እቃዎች ይውላል፡፡ እኛ ሃገርም በፕላስቲክ ቤት ከምንሰራ ምናልባት እንጨትን እየጨረሰ ያለውን የኤሌክትሪክ ስልክ ምሰሶ የሚተካ የፕላስቲክ ምሰሶ ብንሰራ የተሻለ ይሆናል።
በሀገራችን ለፕላስቲክ የተሰጠው ግምት ዝቅተኛ ነው ተብሏል፡፡ ከመንግስትም ሆነ ከሌሎች ባለድርሻዎች በዚህ ረገድ ምን ይጠበቃል?
መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ የፕላስቲክ አጠቃቀም ህግ ማውጣት አለበት፡፡ ህግ ከወጣ በኋላም አፈፃፀሙን ጠንካራ ማድረግ ይገባዋል። አምራቾች ደግሞ ለምሣሌ ፕላስቲክ ቁጥር አለው። ለምሳሌ 1 ቁጥር የተፃፈበት ፕላስቲክ፣ የውሃ ጠርሙስ የሚሠራበት ነው፣ 2 ቁጥር ደግሞ Low Density Poultry ይባላል፡፡ በዚህ መልኩ ቁጥርና ስም ተሰጥቷቸዋል፤ስለዚህ አምራቾቻችን ይሄን ቁጥር በአግባቡ ማስቀመጥና ህብረተሰቡን ማስገንዘብ አለባቸው፡፡ መንግስት በዚህ መስፈርት መሠረት ጠንካራ የጥራት ቁጥጥር ማበጀት አለበት። አምራቾችም እንደ ሀገር አስበው፣ ደረጃውን የጠበቀ ምርት ማቅረብ አለባቸው፡፡
የአካባቢ ተቆርቋሪ ቡድኖች፤ ህብረተሰቡ ፌስታልን ጨምሮ የፕላስቲክ እቃዎች እንዳይጠቀም ይመክራሉ፡፡ ይሄን ጉዳይስ እንዴት ትመለከተዋለህ?
ብዙ ጊዜ ከፕላስቲክ ይልቅ ወረቀት ተጠቀሙ ይላሉ፡፡ ነገር ግን ወረቀት ራሱ የራሱ ችግር አለው፡፡ ከፕላስቲክም የበለጠ ችግር አለው፡፡ ወረቀት የሚመረተው ከእንጨት ነው፡፡ ለወረቀት ምርት የሚፈለገው ጥሬ እቃ ፕላስቲክ ለማምረት ከሚፈለገው የበለጠ ዋጋና ብዛት ያለው ነው። ሁለተኛ አመራረቱን ብንመለከት፣ የፕላስቲክና የወረቀት አመራረት በጣም ይለያያል፡፡ ወረቀት ሲመረት ካርቦንዳይኦክሳይድን ጨምሮ በርካታ ተረፈ ምርት ነው ያለው፡፡ ከፍተኛ የአየር ብክለትን የሚያስከትል ነው አመራረቱ፡፡ ፕላስቲክ ግን በመጽሐፌም እንዳመለከትኩት፤ አመራረቱ በጣም ቀላልና ለአካባቢ ብክለትም ከወረቀት አመራረት አንፃር ያለው ድርሻ አነስተኛ ነው፡፡ በአመራረትና በምርት ሂደት፣ ከፕላስቲክ ይልቅ ወረቀት የበለጠ አካባቢ በካይ ነው፡፡ ፕላስቲክን ደጋግሞ መጠቀም ይቻላል፡፡ ወረቀትን ግን ድጋሚ ለመጠቀም አይቻልም፡፡ አንድ የፕላስቲክ ወንበር ሲመረት፣ ቢበዛ 10 ደቂቃ ቢፈጅ ነው። ወረቀት ግን ብዙ ውሃ ጨርሶ፣ ጊዜ ፈጅቶ ነው የሚመረተው፡፡ አቀማመጡን በተመለከተም 1ሺህ ፕላስቲኮችን በአንድ አነስተኛ ጣሳ ማስቀመጥ እንችላለን። በተመሳሳይ ወረቀትን ለማስቀመጥ ግን ምናልባት 10 ጣሳዎች ያስፈልጉናል። ወረቀትን ለማምረት የሚያስፈልገውን ጥሬ እቃ፣ የማሽን ውድነትና ብዛት ስንመለከት ደግሞ ከፕላስቲክ አንፃር ፈጽሞ የሚወዳደር አይደለም፡፡ ቢቻል ከፕላስቲክም ከወረቀትም በተሻለ የጨርቅ ዘንቢሎችን ብንጠቀም፣ ካልሆነ ግን ከወረቀት ይልቅ የፕላስቲክ ዘንቢል መጠቀሙ የተሻለ ነው፡፡
መፅሐፍህን ለሽያጭ ሳይሆን በነፃ ነው ያቀረብከው ----ለማን እንዲደርስ ነው ያለምከው?
አዎ! መፅሃፉን ትርፍ ለማግኘት አይደለም ያሳተምኩት፡፡ ዋነኛ አላማዬ ለአዲስ አበባ ከንቲባ ወይም መልሶ ማልማት ክፍል በነፃ መስጠት ነው። በነፃ የምሰጠው በዋናነት በከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉ 537 የቆሻሻ ፅዳት ማህበራት እንዲደርሳቸው በማሰብ ነው፡፡ ማህበራቱ ይሄን የፕላስቲክ ጥቅም የሚያስረዳ መፅሐፍ ካገኙ በኋላ ከተቻለ ስልጠና መስጠት እፈልጋለሁ፡፡ እንዴት ፕላስቲክ መሰብሰብ፣ መፍጨትና ወደ ሌላ ጥሬ ዕቃ ወይም ምርት መቀየር እንደሚቻል ማህበራቱ ከተረዱ በኋላ በቀጣይ የራሳቸውን የመፍጫ ፋብሪካ እንዲያቋቁሙ ነው የምፈልገው፡፡ ትልቁ አላማዬ፤ እነዚህ ማህበራት ቆሻሻን ወደ ኢንዱስትሪ ምርት እንዲቀይሩ ማገዝ ማበረታታት ነው፡፡ በሃገሪቱ 80 ያህል የውሃ ፋብሪካዎች አሉ፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች ቢያንስ በአንድ ፈረቃ ከ100ሺ ጠርሙስ በላይ ውሃ ያመርታሉ፡፡ በሶስት ፈረቃ ደግሞ እስከ 20 ሚሊዮን ጠርሙስ ውሃ ያመርታሉ፡፡ ይሄን ጠርሙስ ወደ ኢንዱስትሪ እንቀይር ከተባለ ደግሞ 1 ሊትር የሚይዝ የውሃ ኮዳ፣ 1 ሱሪ ማምረት ይችላል፡፡ የውሃ ኮዳውን ወደ ክር፣ ወደ ፖሊስተር ክር በመቀየር ልብስ ማምረት ይቻላል። ፖሊስተር ክር ከተመረተ ለማንኛውም ልብስ መስሪያ ይሆናል፡፡ ፖሊስተር ክር  የሚመረተው ከፕላስቲክ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄን የፖሊስተር ክር ማምረቻ እንዲከፈቱ፣ ከፍ ሲልም የልብስ ፋብሪካ እንዲከፈቱ ማድረግ ነው ፍላጎቴ፡፡ በዚህ መንገድ በዋና ዋና ከተሞች ቢያንስ አንድ አንድ ፋብሪካ ቢቋቋም፣ ፕላስቲክ ተራ ሳይሆን እጅግ ተፈላጊና ጠቃሚ ይሆናል ማለት ነው፡፡
መፅሐፉን በማሳተም ረገድ ማን እገዛ አደረገልዎ?
ይሄን መፅሐፍ ለማዘጋጀት የረዱኝ በርካታ አካላት አሉ፡፡ አዋሽ ኢንሹራንስ፣ ጣፎ ፕላስቲክ ፋብሪካ፣ ፓክትራ፣ ሮተሪ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ጎማ ቁጠባ፣ ኤይር ሊንክ የጉዞ ወኪል፣ አፍሮ ጀርመን ኬሚካል፣ ክሩዝ ት/ቤትና ሌሎችም ይገኙበታል። በዚህ አጋጣሚ እነዚህን ተቋማት አመሰግናለሁ፡፡   

Read 553 times