Print this page
Monday, 28 January 2019 00:00

ኢትዮጵያዊቷ ወጣት በቻይና እስር ቤት ትገኛለች

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

ጓደኛዋ አድርሺልኝ ያለቻት ሻምፑ አደንዛዥ ዕፅ ሆኖ ተገኘ
                
    ከአምስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምህንድስና ሙያ ተመርቃ፣ በጥሩ ደመወዝ በመስራት ላይ የነበረችው ናዝራዊት አበራ፤ እንደ ነፍሷ የምትወዳትና አጥብቃ የምታምናት አብሮ አደግ ጓደኛ አለቻት። ይህቺው ጓደኛዋም “ቻይናን ጐብኝተን እንምጣ” የሚል ግብዣ ስታቀርብላት፣ ናዝራዊት ግብዣውን የተቀበለችው በደስታ ነበር፡፡
የተለያዩ አገራትን ልምድና ተሞክሮ ማየት ለስራዋም ሆነ ለግል ህይወቷ የሚኖረውን ከፍተኛ ጠቀሜታ በማሰብ፣ ለጉዞ መዘጋጀት ጀመረች፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በሆስተስነት ለዓመታት ከሰራች በኋላ ሥራዋን ለቃ ወደተለያዩ አገራት በመዘዋወር፣ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራችው ጓደኛዋ፤ ቻይናን ጨምሮ ወደተለያዩ አገራት በየጊዜው በመመላለስ በቂ ልምድ ያላት በመሆኑ ጉዞአቸው አዝናኝና ቆይታቸው አስደሳች እንደሚሆን ደጋግማ ነግራታለች፡፡ የመሄጃቸው ጊዜ ሲደርስ ግን ጓደኛዋ፣ አባቷ በድንገት ስለሞቱባት ወደ ቻይና አብራት ለመሄድ እንደማትችል ነገረቻት። ነገር ግን ሁሉም ነገር ዝግጁ እንደሆነና ምንም እንግድነት እንደማይሰማትም ነግራ አሳመነቻት። እናም መሃንዲሷ ናዝራዊት ወደ ቻይና ለብቻዋ ለመጓዝ ተነሳች፡፡ ለጉዞው ያነሳሳቻት ጓደኛዋ፤ ወደ ቻይና ለሰው የምትልከው ዕቃ እንዳለና አየር መንገድ መጥታ እንደምታቀብላትም ነገረቻት ለቀናት በቻይና የምታደርገውን ጉብኝትና ቆይታ አጠናቃ፣ ከገና በዓል በፊት ወደ አገሯና ወደ ቤተሰቦቿ ለመመለስ ያቀደችው ናዝራዊት፤ “እዛው ቻይና ለሚኖር ሰው የሚላክ ነው እዛ  መድረስሽን ኦንላይን ስታሳውቂኝ ያረፍሽበት ሆቴል ድረስ መጥተው እንዲቀበሉሽ አደርጋለሁ፡፡ አንቺ በማታውቂው አገር መጉላላት የለብሽም ተብሎ በጓደኛዋ የተነገራትን አምና አድርሺ የተባለችውን 5 ሻምፖና ሁለት ሂዩማን ሔር ይዛ ወደ ቻይና አቀናች፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ምንም አይነት እንግልትና መጉላላት ሳያጋጥማት፣ ቻይና በሰላም የደረሰችው ናዝራዊት ከአየር መንገዱ ከመውጣቷ በፊት የያዘቻቸው ዕቃዎች በቻይና አየር ማረፊያ ውስጥ ሲፈተሽ እጅግ አስደንጋጭ ነገር ተከሰተ፡፡
በ5 የሻምፑ ዕቃዎች ውስጥ የተሞሉና እጅግ በረቀቀ መንገድ በፈሳሽ መልክ የተዘጋጁ ሄሮይንና ሌሎች አደገኛ አደንዛዥ እፆች ሆነው ይገኛሉ፡፡ ስለ ጉዳዩ ምንም አይነት ዕውቀት የሌላት ወጣት ሁኔታው እጅግ አስደነገጣት፡፡ ከአየር መንገዱ ሠራተኞችም ሆነ ከአገሪቱ ፖሊስ የሚቀርቡላትን ጥያቄዎች መመለስ አልተቻላትም፡፡ “ከጓደኛዬ ተቀብዬ ነው፡፡ ለማን እንደምሰጠው አልነገረችኝም፤ እዛ ስትደርሺ የሚቀበልሽ ሰው ያለሽበት መጥቶ ይወስዳዋል ነው ያለችኝ” ስትል ምላሽ ሰጠች፡፡ ይህ ምላሽ ግን ለቻይና ፖሊሶች አልተዋጠላቸውም፤ ናዝራዊት በእጇ ተገኘ ከተባለው ኤግዚቢት ወደ እስር ቤት እንድትገባ ተደረገ፡፡
በዚህ ዜና የተደናገጡት ቤተሰቦቿ፤ ወጣቷ የደረሰባትን ለማወቅና አሁን ያለችበትን ሁኔታ ለማየት ወደ ቻይና ተጉዘው ጉዳዩን ቢጠይቁም ወጣቷ ጥብቅ ክትትል በሚደረግበት እስር ቤት ውስጥ እንደገባችና ማንንም ማግኘትም ሆነ ከማንም ጋር መገናኘት እንደማትችል ይነገራቸዋል፡፡
በቻይና የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተወካይ የሆነ ሰው ያለችበትን ሁኔታ ማየት እንዲችል ከመፈቀዱ ውጪ ወጣቷን ለማየትና ለማነጋገር ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ሆነ፡፡
የወጣቷ ቤተሰቦች እንደሚናገሩት፤ ናዝራዊት አሁን ያለችበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢና አስደንጋጭ ሲሆን ህይወቷም አደጋ ላይ ይገኛል፡፡
ለወጣቷ ሻምፑዎቹን የሰጠቻት አብሮ አደግ ጓደኛዋ፤ አሁንም እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፤ የናዝራዊት ቤተሰቦች ሻምፑዎቹን የሰጠቻት እሷ መሆኗንና ቻይና ውስጥ ለሚገኝ አንድ ሰው እንድታደርስላት እንደጠየቀቻት የሚገልጽ መረጃ በእጃቸው ላይ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡ “ምንም በማታውቀውና በሌለችበት ጉዳይ ልጃችን ህይወቷን ሊያሳጣት በሚችል ከፍተኛ አደጋ ውስጥ መውደቋን ህዝብና መንግስት እንዲያውቅልንና ህይወቷን ለማትረፍ የሚቻልበትን መንገድ እንዲፈልግልን” ሲሉ ቤተሰቦቿ ይማፀናሉ፡፡ የዚህችን ወጣት ህይወት ለማትረፍ ሁሉም ወገን የበኩሉን ድጋፍ ያድርግልን ሲሉም ተማጽኖአቸውን ያሰማሉ፡፡
በቻይና ህግ አደገኛ ህፆችን መጠቀም፣ ማዘዋወር፣ መሸጥና ህፃናትን በዚህ ጉዳይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ የሞት ቅጣት ሊያስከትል የሚችል ወንጀል ነው፡፡ ቻይና እ.ኤ.አ በ2017 ዓ.ም ከ140 በላይ አደገኛ እጽ አዘዋዋሪዎችን በሞት ቀጥታለች፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጉዞ ተርሚናሎቹ ውስጥ ያለው ቁጥጥርና ፍተሻ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ይህቺ ወጣት የኢትዮጵያ አየር መንገድን አልፋ ነው ቻይና ላይ የተያዘችው፡፡

Read 1459 times