Monday, 28 January 2019 00:00

ነቢይ ፍለጋ

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

‹‹ረስተው - ተዘንግተው - ሺህ አመት አንቀላፉ፡፡››
              
   አዎን ትልቅ ነበርን!!!
አየሩን የመላ ከአቻምና የተጋባ ህያው ትውፊት አለ
ልዕለ ስብዕናው ባንዳች ቢስ ተሰልቦ
ከትናንትና አልፎ ዛሬ ላይ ያልዋለ
በእጅ እማይዳሰስ ጥርሱን ነክሶ እሚኖር
ያልሞት ባይ ተጋዳይ ህያው ጥላማ አለ፤
የስንቱን ወጥቶ አደር ፣ ታጋይ፣ ሽፍታ፣ ፋኖ
የዜጋ ደም በልቶ አጥንቱን አንክቶ በነበር ያዋለለ፤
እማይርብ እማይጠማው በምዕታመታት ጠኔ ዛቻ ያልተነነ
መለኸቱ እስኪነፋ በተስፋ እሚዋትት
ከምድር አጽናፍ አጽናፍ እየተንቀዋለለ፤
ታሪክ እማይክደው፤ ዘመን የማይንደው
መከራ እማያርደው፤ እማይሞት እማይበርደው
ጦሙን ሳያከፍል በእጦት እየገረረ
እንደተደገገ የዋለ ያደረ አንድ እውነትማ አለ!!! . . .

በጥምቀት ክብረ በአል መነሻ፤ ኢትዮጵያ፣ በአዲስ ኪዳን የተገኘውን ጥምቀት፣ በብሉይ ኪዳን ከነበረው (መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 3፡3 የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ ተከተሉት።) ትእዛዝ ጋር ሕብር ፈጥራ (ባለንበት ዘመን በርካታ የውጪ ሀገራት ዜጎችን በአመታዊ ጎብኚነት፤ (ከዚያም ባሻገር በሚያስደንቅ ሁኔታ  በቅዱስ ታቦት አጃቢነትና የክብር ስጋጃ አንጣፊነት በሚያሳትፍ መልኩም) የጥምቀትን ጸጋ ለመላ ምእመናኑ በሰፊው ለማቋደስ በሚፈቅድ መንገድ፣ እጅግ በደማቅ ሁኔታ ስናከብር፤ ኢትዮጵያ የብሉይ ኪዳንን ስርአት አዲስ ኪዳን ዘመን ድረስ ይዛ ከመዝለቋ አንጻር፤ ከልዕለ ኃያሏ ምድር ሕዝቦች ከአሜሪካዊያን የስልጣኔ ድርሳን ዋቢ እንጥቀስ ብንል፤ አሜሪካዊያኑ በተለይ ለፖለቲካዊ ጉዳዮቻቸው America’s political system እና ለሌሎችም ሀገራት መትረፍ ለቻለው ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰባቸው ምሰሶ ከሆኑላቸው ተጽዕኖዎች መካከል ይኸው ሀገራቸው ከመመስረቷ በፊት የነበረውን የብሉይና አዲስ ኪዳናት ጥምር እምነት መከተላቸው መሆኑን ይመሰክራሉ . . . The American system of government owes much to other nations and civilizations. One of the major influences upon American political thought has been the Judeo-Christian religious tradition which was found in the Middle East over a thousand years before America was discovered. (An Introduction to American Civilization - 1967.)

ወኔውን ቀን ሰልቦት አቅሉን አገርጅፎት እምቢ አልሞትም ያለ
‹‹ወድቆ›› የሚፎክር ቆስሎ እሚንከላወስ ‹‹በድኑ›› አለሁ እያለ፤
ደግፎ እሚያቆመው አንሺ እጅ የሚሻ፤
አቻምና ላይ ወድቆ ተዘርሮ የቀረ፤
ለቀብር፣ ለፍታት፣ ተርፎም እንደሁ ለማንሳት ቦዩን ለመከተል
የተቋጠረበት፣ የተበጠሰበት ምልክት ያልተው፤
በየትኛው ዘመን እምን ቦታ ጠፍቶ ወዴት እንደቀረ
ማወቅ ያልተቻለ
ግዘፍ ነስቶ ዘወትር ምድሩን እንደፀለለ
የኖረ ፣ እሚኖር ፣ ኗሪ - አንድ አውነትማ አለ!

ሀገራችን ኢትዮጵያ በአይሁድና ክርስትና እምነቶች ታሪክ ውስጥ እንደነበራት ቀዳማይ ጸጋ ሁሉ፤ በእስልምና ኃይማኖትም እንዲሁ ከዓለም ሁሉ በፊት የነቢዩ መሀመድ (ሰዐወ) መልእክተኞችን ተቀብላ ማስተናገዷንና ከሕዝቦቿም መካከል በነቢዩ አስተምህሮ ማመናቸውን አብሮም በነቢዩ ሕይወት ውስጥ ጎልተው የሚጠቀሱትን ኢትዮጵያዊያን ኡሙ አይመን አል ሀበሺንና ለአዛን የተመረጠውን ጥቁሩን ሙአዚን ቢላል አል ሀበሺን  . . . ወዘተ. የበርካታ ሙስሊም ኢትዮጵያዊያንን ኃይማኖታዊ ገድል በክብር እናስታውሳለን፡፡ የመጀመሪያዎቹ የነቢዩ ሱሀባዎች ማረፊያ ስፍራ የነበረውን የአል ነጃሺን እፁብ ድንቅ ታሪካዊ ቅርስነት ለማስጠበቅ በረዥም ዘመን የተደረገ ክብሩን የሚመጥን ሥራ ግን አለመኖሩንም እዚህ መጥቀስ ግድ ይላል፡፡
ከቀዳማይዋ ሂጅራ በወደረኛነት ከምንዘከርበት
ወደ ለአዛን በኩሩ ቢላል አል ሀበሺ ከይር ምድር አብነት
‹‹ሂዱ በሰላም ኑሩ፤ ሀበሽን አትንኩ››ን በመከሩ አንደበት
በነቢዩ (ሰዐወ) ፈቃድ በክብር ለመሰንበት፤
ወገኖች ከቁሬይሽ ተሰድደው የአልነጃሺን መስጂድ ካቆሙበት
በንጉሥ አርማህ ችሎት ፍትኃዊ ቅንነት
‹‹አርሂቡ›› ተብለው በአማን ካረፉበት . . .

ኢትዮጵያ ሀገራችን ገና በቂ ጥናትና ምርምር ከሚሹት፤ በርካታ ጥንታዊና ዘላቂ፤ ያልተደረሰባቸው እውቀት ወ ጥበባት የቋጠሩ፤ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የነባርና የሀገር በቀል  እምቅ፣ ድብቅ፣ ጥልቅና ረቂቅ ... ባህላዊና ‹‹ተፈጥሯዊ›› አንጡራ የእምነት ቅርስ ቱሩፋቶቿ ጋር፤ አስቀድሞ በህገ ልቦና እና ሕገ ኦሪት፤ ከዚያም በሦስቱ የአለም አበይት ኃይማኖቶች በአይሁድ፣ክርስትና እና እስልምና ኃይማኖቶች እንዳላት፣ ቀዳማዊና ጉልህ ድርሻ፤ እንደዚሁ ከአፍሪቃ ምድራቸው በግፍ ተዘግነው JESUS OF LUBECK ‹‹ኢየሱስ እስኪመጣ›› የሚል የላቲን ጽሑፍ በሰፈረበት በአይጠየፌው የቅኝ ገዢዎች መርከብ ተጠቅጥቀው ተወስደው፤ በደቡብ አሜሪካ የሸንኮራ እርሻ ውስጥና በከባድ የጉልበት ስራዎች እንደ እቃ ተቆጥረው፣ በክፉ ጭቆና ሲዳክሩ፣ በባርነት ጭለማ ሲማቅቁ የኖሩ ጥቁር ሕዝቦች፤ የሙሴን ዘ ጸአት ተምሳሌት አድርገው፣ ከአዲስ ኪዳን ገላትያ 5፡1 ጋር ‹‹ በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ።›› አሰናስለው ነጻ ለመውጣት ላደረጉት እልህ አስጨራሽ እርምጃ ተፈጻሚነት፤ በተስፋ ሲጠባበቁት በኖሩት ነጻ አውጪው ነቢይ የመሰሏቸውን ንጉሥዋን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን እና  ምስራቅ አፍሪቃዊ ሉአላዊ ምድሪቱ ለሰው ልጆች ከቀንበር የማምለጥ ታሪካዊ ክስተት በነቢይነት አምሳልና በተስፋ ምድርነት የመገለጧን፤ የኢትዮጵያን ለራስታፋሪያኒዝም ኃይማኖት መነሻነት እዚህ ይጠቅሷል፡፡
ኢትዮጵያዊያን፤ የራሳችንን ኢትዮጵያዊ ጳጳስ እስክንሾም በግብጽ ጳጳሳት ስር ለ1625 አመታት ስንንከላወስ መኖራችን ቁጭቱ ቢያንገበግብም፤ ያም ሆኖ ግን ደሞ ክርስትናን በመንግሥት ደረጃ በይፋ መቀበላችን የሌሎች ሀገራት ሕዝቦች ክርስትናን ወደ ገዢዎች እስኪያሰርጹ በዘመነ ሰማዕታት የከፈሉትን ያህል መራር መከራ ከማስተናገድ ተርፈናል፡፡ እንዲያውም አጼ ካሌብ ክርስቲያን ሰማዕታትን ለመታደግ ናግራን ድረስ እንደዘለቀው (ከኢየሱስ ከሄሮድስ ሽሽት ጀምሮ) ለግፉዐኑ  ከለላ ለመሆን ተመርጠናል፡፡ ምንም እንኳ ከለላው በተለይ እኛው ብርቱ በትር ያሳረፍንባቸውን የኛኑ ደቂቀ እስጢፋኖስንና በኦሪት እምነታቸው የተደቆሱትን ኢትዮጵያዊያን አይሁድ ወገኖቻችንን፣ ለወንጌሉ የቆሰሉትን እንዲሁም ሌሎቹንም በተለያዩ ኃማኖቶቻቸው፡ በልዩ ልዩ አምልኮዎቻቸው ...ወዘተ ባጠቃላይ የመረጡትን እምነታቸውን በነጻነት ለማራመድ የተኮደኮዱትን ወገኖቻችንን ባይጨምርም፡፡ . . .

እንዲህም ይላል ደሞ ትውልዱ ሲያጠይቅ መልሶ መላልሶ . . .
ምናልባትስ ቢሆን የካቻምናን ክብር ያጣው የኦሪት ሕዝብ
ሽፍታ ያበረረው ሰው ሲኖር ተለሳልሶ፤
ባልጠና ጉተናው ከሻጠው አስኬማ
ከባዕዱ ቱሩጅማን ቃል ሀረግ ተውሶ፤
በመንበረ ማርቆስ የፍትሐ ነገሥት ገጽ እግረ ሙቅ ህግጋት
ጽኑ ተኮድኩዶ ሳያየው ፈትኖ በቅጡ ፈትሾ
ሀርቤን ያስመረረ ጠይባን ያመነነ ሀገር ያተከነ ማነቆ ቋጠሮ
በአመት ሁለት አመት ሥራ ፈት ዜጋን ለምድሩ አንበሽብሾ፤
የሀበሻ ሊቃውንት ለሀበሻ አያሻምን የእሾህ አክሊል በሰጠው
በእስክንድርያ ዳና ሺህ ስድስት መቶ አመት ምድሩ ተውለሽልሾ
ከሜሮኤ ኑቢያ የተቆራረጠው ብፁዑ ወገኔ በበተነው እርሾ
ለዬህም ብፁዕ ሆኖ ለ‹‹በአፈ ገጽከ›› ትዕዛዝ ተቅለሽልሾ?! . . .
ለመላው ምድር ቅድመ ስልጣኔን እንዳካፈለና ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲል ሆኖ የአርነት ብርሃን እንደፈነጠቀ፤ ሉአላዊ ሕዝብ ሲሰላና የኢትዮጵያዊያንን የረዥም ዘመናት ኃይማኖታዊ የታሪክ ባለቤትነት በቅኝ ግዛት ውስጥ ኖረው፣ ቅርብ ጊዜ ነጻነታቸውን ከተቀዳጁት ከአፍሪቃዊያን ሕዝቦች አንጻር ስናጤነው ደግሞ፤ መጀመሪያ ዘወትር ኋላ ለመቅረታችን ዋቢ አድርገን የምንጠቅሰውን ጊበን GIBBON የተባለ የታሪክ ጸሐፊ ስለ እኛ፤ ‹‹ኢትዮጵያዊያን አለምን ረስተው እነርሱም በረሱት አለም ተዘንግተው ለሺህ አመታት አንቀላፉ›› ያለውን፡፡
በንጉሡ ዘመን አልጋ ወራሹ ለቢቢሲ ያወጉትን፤ ‹‹ሌሎች አፍሪቃዊያን ከቅኝ ግዛት ተላቅቀው ሲመነደጉ፣ ኢትዮጵያዊያን ግን ዛሬም ድረስ ባለንበት ‹እንንፏቀቃለን›. . .!››ቁጭትም ያስታውሰናል ...ይህን ቁጭት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ታጋይ መለስ ዜናዊም ሲደግሙት ሰምተናል፤ ‹‹ጥንት አክሱምን፣ላሊበላን፣ፋሲል ግምብን የሰራን ሕዝቦች ዛሬ አክሱም ሀውልት ከተወሰደበት ተመልሶ ሲመጣ መልሰን መትከል አቃተን!›› ... ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ሰለሞን ዴሬሳም እንዲሁ ግራ በመጋባት ጠይቆ ነበር፤ ‹‹እኒህን መሰል ከአንድ ድንጋይ ተፈልፍለው የወጡ የእፁብ ድንቅ ቤተ መቅደሶች ኪነ ህንጻ በቆመበት፣ ሮሀ አምባ በላሊበላ መንደር ዙሪያ ያሉ መኖሪያ ቤቶች ምን እንዲህ ጭርቁስቁስ አደረጋቸው ታዲያ!›› ሲል፡፡ እናም አሁንም በ21ናው ክፍለ ዘመን ላይ ሆነን፣ ከዚህ ሁሉ ሺህ ዘመናት ነቢይ ጥበቃ በኋላ ዛሬም ቁልቁል አቀርቅረን እያየን፤ ለሦስት ሺህ ዓመታት በበሬ ያረስንበትን ለውለታው ምላሽ ክብር ሲገባው ንቀትን ያከናነብነው ጠይቡ ቀጥቃጭ ሳይታክት ተግቶ የሚኮችምልንን ያችኑ አንዲቷን ማረሻ ታቅፈን፣ ተኮራምተን፣ የማይነጥፍ ተስፋ እናንጎራጉራለን . . .

ረቢ በመጣ? ምሳሌ እሚነግረን . . .
ረቂቁን አጉልቶ ኃይሉን ቃል በውበት፤
ስለ ሰማይ እውነት፣ ስለ ምድር ወረት
ስለዛገው ብረት ገበሬው አፈሩን ስለሚገምስበት
‹‹ሞፈሩ ቀንበሩ የሀበሻ ማረሻ እግር ያላወጣበት
ሺህ አመታት ተንፏቅቆም ጋት ፈቅ ያላላበት
ሌማት ጎተራዋ አውድማዋ ጦቢያ
ቀን እየጠበቀ እሚደነግጥበት፤
በባዕድ ርጥባን እሚሳቀቅበት
ነባር ጸጋ ክብሩ ምን ጉድ ነው የመጣበት?››
ብለን እምንጠይቀው ነቢይ ባፈራ ቤት . . .

(ስንኞቹ ከ ‹‹እፍኝ የድንጋይ እርሾ›› 2005 ዓ.ም- ተራኪ ግጥም
 የተቀነጫጨቡ ናቸው - የፀሐይ ገበታ - ያልታተመ፡፡)

Read 1010 times