Monday, 28 January 2019 00:00

“ሎሚ ጣሉባት በደረቷ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)


     እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሎሚ ጣሉባት በደረቷ
የጨዋ ልጅ ነች መሰረቷ
የምትል ነገር ነበረች፡፡ ዘንድሮ ብዙ ሎሚ ውርወራ አልነበረም አሉ፡፡ እንዴት ሊኖር ይችላል! በፊት እኮ በሽልንግ ኪስ ሙሉ ሎሚ ይዞ መሄድ ይቻል ነበር…የዛሬን አያድርገውና! አሁን ለገበታ እንኳን ጠፍቶ ‘ደረት’ እንዴት ትዝ ይበል!
እናላችሁ… ሎሚ ‘እንደማባበያ’ 
እኔ የምለው…ይሄ ከአምስት ዓመት በላይ ያገለገለ መኪና እንዳይገባ ሊደረግ ነው የሚባለው ነገር እውነት ነው እንዴ! ለምን አያሳሳስበን….አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች አካባቢ ‘ሶሻል ክራይሲስ’ ሊፈጥር ይችላላ! ልጄ… መኪና እኮ በ‘ጊፍት ፔፐር’ አትጠቅለል እንጂ የስጦታ እቃ ከሆነች ከረመች እኮ! እኛ የቶርታ ኬከ ስጦታ ለመስጠት ከአራት ወር በፊት መቆጠብ እንጀምራለን እዛኛው ሰፈር መኪና ‘ኮምፐልሰሪ’ ሆናለች፡፡
“አሁን ለእኔ ቪትዝ ለመግዛት ትልቅ ነገር ሆኖ ነው ለምኚኝ የምትለው!”
በማግስቱ ለእሷዬዋ ስልክ ይደወልላታል። “ስሚ፣ በሰባት ሰዓት እንትን ክትፎ ቤት እፈልግሻለሁ፡፡”
ሰዓት ደርሶ ክትፎ ቤት...እናላችሁ እሱዬው ኮሽኮሽ እያደረገ ከኪሱ ያወጣና ጠረጴዛ ላይ ሆጭ ያደርገዋል፡፤
“ያውልሽ…”
“ምንድነው እሱ?”  (ሰውየው ብሎ፣ ብሎ የቤቱ ጠባቂ ሊያደርግኝ ነው እንዴ!)
“ቪትዝ፣ ቪትዝ እያልሽ ስትጨቅጭቂኝ አልነበረም! ያውልሽ የቪትዝሽ ቁልፉ፡፡”
“እኔ አላምንም…”
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ ይቺ “እኔ አላምንም!” የሚሏት ነገር… አለ አይደል… “ዋው” እንደሚሉት ነገር ማለት ነው፡፡ በቃ “እኔ አላምንም…” የሚባለው መባል ስላለበት ወይም መባል ያለበት ስለሚመስለን ይመስላል፡፡
እናማ…ይሄ ከተወሰነ ዓመት በላይ ያገለገሉ መኪናዎች አለመግባታቸው ‘የመኪና ባለቤትነት ተዋጽኦውን’ እንዳያበላሸውማ! (ቂ…ቂ…ቂ…) ደግሞ እኮ ትናንት ቪትዝ ትገዛበት የነበረው ዋጋ አሁን እኮ ለባጃጅ የሚጠየቅ ሆኗል አሉ፡፡ ሀሳብ አለን… የቦሌ መንገድ ለባጃጅ ይፈቀድልንማ!
እንደዛ ከሆነ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… ዓመት ሳይሞላ፣ አንደኛ በቦሌ መንገድ ባጃጆችና የሌሎች መኪኖች ብዛት መሳ መሳ ለመሳ ይሆናል፣ ሁለተኛ የስጦታ እቃዎች የሚሸጡ ሱቆች “ለሚወዷቸው በስጦታ የሚያበረክቷቸው ባጃጆች ማስመጣት መጀመራችንን በደስታ እንገልጻለን. የሚሉ ማስታወቂያዎች መለጠፍ ይጀምራሉ፣ በተጨማሪ በጥቂት ወራት ውስጥ ባጃጅ ሁለት መቶ ምናምና ሺህ ትገባለች፡፡
“እሷ እንዴት አይነት ሀብታም ሆናለች መሰለሽ!”
“የት አየሻት?”
“ቦሌ መንገድ ላይ በባጃጅ ፈልሰስ ስትል አላያት መሰለሽ!”
“ባጃጅ ያዘች! ቢል ጌትስ ገንዘብ ልኮላት መሆን አለበት፡፡”
በቀደም በበዓሉ ዕለት በቴሌቪዥን ሎሚ ወረወራችሁ ወይ ተብለው የተጠየቁ ወጣቶች… “አሁን የመኪና ቁልፍ ሆኗል…” ምናምን አይነት ነገር ሲሉ ነበር አሉ፡፡ የምር ግን እዚህ አገር እኮ ብዙ ነገሮች ላይ  የምንሄድበት ጥግ የጉድ ነው፡፡ እናላችሁ…በተለይ ገንዘብ የጎረፈ እንደሁ፣ ስልጣን የመጣ እንደሁ… አለ አይደል… በአምስተኛ ማርሽ እንገባበታለን እንጂ ደረጃ በደረጃ ብሎ ነገር የለም፡፡ እናም…የስጦታ ነገርም እንዲሁ ይመስላል፡፡ እንደውም በተለይ ለእንስቶች ስጦታ መስጠቱ እንደ ፉክክር አይነትም ሆኗል ሲባል ነበር፡፡
እናላችሁ…አንድ ሰሞን አንዱ ነጋዴ ጠዋት ላይ የሆነች አሪፍ መኪና ገዝቶ ሱቁ ወይም  ድርጅቱ ፊት ለፊት ካቆመ፣ ጎረቤቱ ያለው ደግሞ ከሰዓት በኋላ ወይ የዛችው አይነት ካልሆነም የተሻለች አይነት ገዝቶ ይመጣል ሲባል እንሰማ ነበር። በቅርብ ጊዜያት ደግሞ “እከሌ ለእንትና እኮ እንዲህ የሚባል አይነት መኪና ሰጣት፣” ሲባል ሌላኛው ደግሞ በእሱ በኩል ላለችው የተሻለ የሚባል መኪና ይገዛል አሉ፡፡ ባስ ሲል ደግሞ ጂ ፕላስ ምናምን አለላችሁ፡፡
በቀደም ቢል ጌትስ በርገር ሊገዙ ተሰልፈው በማህበራዊ ሚዲያ ስናያቸው፣ ለብዙዎቻችን እንግዳ ነበር፡፡ የተሰማን ስሜት “የዓለም ሀብታሙ ሰው ይሰለፋል! ያውም የምናምን ናይንቲ ናይን ሀምበርገር ለመግዛት!” አይነት ነገር ነበር፡፡ ከመሰለፉ ሌላ ተከታዩ ጥያቄ… “ግን እሱ ምን አጣና ነው ሀምበርገር የሚመገበው?” ይሆናል፡፡ ሀብታም ሰው እንደ እኛ እንደ ተራዎቹ እንዲሆን አይጠበቅማ! እኛ የሆነ በሚሊየነርነት ወይም ቢሊየርነት ስሙን የምንሰማው (“በተግባሩ የምናውቀው” ማለት ስላሰቸገረ ነው!) ሰው ‘እንትን ቆሎ’ ሊገዛ ተሰልፎ ብናየው፣ “አሁን ወደ አእምሮ ሀኪም የሚወስደው ዘመድ አጥቶ ነው!” እንላለን እንጂ እንደ ቢል ጌትስ አናጨበጭብለትም፡፡ እኛ አገር ሀብታም የሆነ ሰው ሀብታምነቱን ማሳየት አለበት፡፡ አይደለም እኛ እግረኞቹ፣ ባለመኪኖቹም ለእሱ መንገድ መልቀቅ አለባቸው፡፡
ቢል ጌትስ እኮ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘቡን ለበጎ ተግባር በማዋሉ በርካታ ሚሊዮኖች፣ የጤና እንክብካቤ አግኝተዋል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናት ትምህርት ቤት መሄድ ችለዋል፡፡
እናማ የመኪናውንና የቤቱን ስጦታ በየዓመቱና በየሁለት ዓመቱ ለተለያዩ እንትናዬዎች የሚረጩት ሰዎች፤ እንደው የዛን አንድ አስረኛ ያህሉን ለወላጅ አልባ ህጻናት፣ ለአቅመ ደካሞችና ለተለያዩ እርዳታ ለሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ቢያውሉት ምን ይቀንስባቸዋል!
የምር እኮ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… እዚህ አገር ችግረኛ በጣም እየበዛ ነው። ነገሮቹ ኩልና ምናምን አይነት ላይ ላዩን እየተቀባቡ ‘ሁሉም ምቹ፣ ሁሉም ዝግጁ’ አይነት መምሰላቸው በስተኋላ “ምነው በእንቁላሉ በቀጣሽኝ…” ዓይነት ነገር ሊያመጡ ይችላሉ። ገንዘብ በምንም መንገድ ይገኝ፣ ከምን መጣ የማይሉት ‘አውሎ ነፋስ’ ነገር… አለ አይደል… ‘ብን’ አድርጎ ሊያጠፋው እንደሚችል ያለፉት ወራት በጣም በትንሹም ቢሆን ምልክቶች ሰጥተውናል፡፡ ጤፍ በጆንያ ውድ በሆነበት ጊዜ ‘ብር በጆንያ’ ርካሽ ሲመስል የሆነ በጣም፣ እጅግ በጣም የተበላሸ ነገር አለ ማለት ነው፡፡
እናላችሁ …አይደለም ሀብታሞቻችን ራሳቸው… ከእነሱ ቅርብ የሆኑት ሁሉ ዘጠኛው ሰማይ ላይ ለመውጣት ነው የሚሞክሩት። በነገራችን ላይ አሁን፣ አሁን አጠቃላይ እይታችንን ሊያበላሽ የሚችል አስተሳሰብ አልፎ፣ አልፎ ያለ ይመስላል… ሀብት ሁሉ የሚገኘው በትክክለኛው መንገድ ሳይሆን በተሳሳተው መንገድ ነው የሚል፡፡ ይቺ አገር ብዙ፣ በጣም ብዙ ጥረው ግረው፣ በላባቸው ሀብት የሰበሰቡና እየሰበሰቡ ያሉ ዜጎች አሏት፡፡
እኔ የምለው…በስንት ጊዜ አንዴ ቺቺንያ ብቅ ስትሉ የነበራችሁ ወዳጆቼ…ነገርዬው አሁንም ጭርታ እንደበዛበት ነው እንዴ!
ሎሚ ጣሉባት በደረቷ
የጨዋ ልጅ ነች መሰረቷ
የሚሏት ነገር ነበረች፡፡ የሎሚው ‘ስትራቴጂ’ እርፍናው ምን መሰላችሁ …ለፉክክር አይመችም።
“ስማ እንትና እኮ እንትናዬን ሦስት ሎሚ ደረቷ ላይ አይወረውርባት መሰለህ!” ቢባል ይህኛው… አለ አይደል… “ምን አለ በለኝ… እኔ አስር ሎሚ ባልወረውርባት!” አይልም፡፡ አሀ… ከአንድና ከሁለት ሎሚ በላይ የፍቅር መግለጫ መሆኑ ቀርቶ አካላዊ ጥቃት ይሆናላ!
እናማ…የመኪና ስጦታ መስጠቱ አንድም መኪና በመወደዱ፣ ሁለትም ዘንድሮ ‘ዓይን መግባቱ’ እንደ ሌላው ጊዜ ስለማያስፎክር፣ ሀሳብ አለን…ወደ “ሎሚ ጣሉባት በደረቷ…” ተመለሱልንና ሁላችንም ‘እኩል’ እንሁንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1279 times