Saturday, 26 January 2019 15:32

በኢትዮጵያ ጽንስን ስለማቋረጥ የተሻሻለው ሕግ አስተዋጽኦ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

  ጽንስን የማቋረጥ ፍላጎትና ድርጊትን በሚመለከት የወጡት ሕጎች እንደሚያመላክቱት በተሸሻለው ሕግ መሰረት ብዙ ወጣቶች ከጉዳት እራሳቸውን እያዳኑ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የተሸሻለው ሕግ ለወጣቶች ደህንነቱ የተጠበቀ እና ሕጋዊ የሆነ ጽንስን የማቋረጥ ተግባር እንዲያከናውኑ የሚያስችላቸው ሲሆን ይህንን ጥያቄም የጤና ተቋማቱ በተገቢው መንገድ እንዲያስተናግዱ መንገድ ይመራል፡፡    
ኢትዮጵያ ህገወጥ በሆነ መንገድ የሚካሄደውን የጽንስ ማቋረጥ ተግባር በመገደብና ወደህጋዊ አፈጻጻም እንዲቀየር በማስቻሉ ረገድ ሂደቱን ካሳኩ ጥቂት ሀገራት መካከል የምትጠቀስ መሆንዋን Guttmacher Institute እና Ipas ያወጡት መረጃ ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ ቀደም ባለው ጊዜ የሚሰራበት ሕግ ጽንስን ማቋረጥን በህጋዊ መንገድ የሚፈቅደው የአረገዘችውን ሴት ሕይወት ወይንም የአካል ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ብቻ ነበር፡፡ የተሸሻለው ሕግ ግን…፤
ተገዶ በመደፈር ምክንያት የሚፈጠር እርግዝና ፤
እርግዝናው ያጋጠመው ዘመድ ከሆነ ሰው ከሆነ፤
እርግዝናው ቢቀጥል ለጽንሱም አደገኛ ሁኔታ ካለው፤
ወይንም ያረገዘችው ልጅ እድሜዋ  ከ18/አመት በታች ከሆነ እና፤
ያረገዘችው ሴት የአእምሮ ወይንም ልጅ ወልዶ ለማሳደግ የማያስችል የአካል ጉዳት የደረሰባት ከሆነ ፤
በሕጋዊ መንገድ ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ እንዲተገበር ህጉ ይፈቅዳል፡፡
ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በ2014/እንደውጭው አቆጣጠር 64% የሚሆኑት ጽንስ ማቋረጦች በወጣቶች የተከናወነው በጤና ተቋማት ነው፡፡ እድሜያቸው ከወጣትነት የዘለለው ሴቶች ማለትም እድሜያቸው ከ25-29 (46%) እና እድሜያቸው ወደ 35/አመት የሚሆኑትም (22%)  ጽንስ ያቋረጡት በሕጋዊ እና በሰለጠነ የሰው ኃይል ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ ነው። ከዚህ ውጭ የተደረጉት ጽንስ ማቋረጦች ግን ሕገወጥ መሆናቸው እርግጥ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ጥናት ካደረጉት መካከል ዮሐንስ ዲባባ እንደሚመሰክሩትም ኢትዮጵያ ጽንስን በማቋረጥ ተግባር የደነገገችው ህግ በተለይም ወጣቶቹ በሕገወጥ መንገድ ጽንስ ሲያቋርጡ የሚደርስባ ቸውን የህይወት መቀሰፍ እና አካል መጎዳት ለመቀነስ አስችሎአል ብለዋል በ Guttmacher- Institute እና Ipas የጥናት ውጤት ሰነድ ፡፡  
በኢትዮጵያ በህገ ወጥ መንገድ የሚካሄደውን የጽንስ ማቋረጥ ተግባር ለማቋረጥ ሲባል የተሸሻለውን ህግ ወደጎን በመተው አሁንም ሕጋዊ ባልሆነ እና ባልሰለጠኑ ሰዎች አማካኝነት ለምን ጽንስን ማቋረጥ አስፈለገ የሚለው ጥያቄ መልስ የሚያሻው ድርጊት ነው፡፡ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው በተለይም እድሜያቸው ከወጣትነት የዘለለው ሴቶች ሕገወጥ የሆነውን መንገድ የሚጠቀሙ መሆናቸውን ነው። ለምሳሌም ያህል በ2014/ የወጣው መረጃ እንደሚ ያሳየው ከሆነ እድሜያቸው እስከ 19/አመት የሚደርሱ 64%...//እድሜያቸው ከ20-24/አመት የሚሆኑ 61%...//እድሜያቸው ከ 25-29/አመት የሚሆኑት 46%...//እድሜያቸው ከ30-34/አመት የሚሆኑት 26%...//እድሜያቸው 35/አመት የሚሆናቸው ደግሞ 22%/ ጽንስን በህጋዊ መንገድና በሰለጠነ የሰው ኃይል በጤና ተቋማት እንዳቋረጡ ጥናቱ ያሳያል፡፡
በተጨማሪም ጥናቶች እንደሚያሳዩት ወጣቶችም አንዳንድ ጊዜ ከሚፈጠሩ የተለያዩ ችግሮች ማለትም ጽንስ በማህጸን እያለ ሕይወቱ ቢቋረጥ ወይንም አንዳንድ ጊዜ ሊደብቁት የሚፈልጉት አላስፈላጊ ነገር ሲኖር በእድሜ ከፍ እንዳሉት ሴቶች ከአራቱ አንዱ ወደ ሕገወጥ ጽንስ ማቋረጥ ድርጊት እንደሚሄዱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ምናልባትም ህጋዊ በሆነው መንገድ ጽንስን ከሚያ ቋርጡ ወጣቶች ጋር ሲነጻጸር ጽንስን በድብቅ የሚያቋርጡት ወጣቶች ብዙ ጊዜ ያገቡ ወይንም በትምህርት ዝቅ ያሉ አለበለዚያም እርግዝናው በድጋሚ የተከሰተባቸው ሴቶች ናቸው፡፡ ስለ ሆነም ሕጋዊ በሆነው መንገድ ጽንስን ስለማቋረጥ በትምህርት ዝቅተኛ ወይንም በጋብቻ ውስጥ ያሉትን እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች ያሉዋቸውንም እንዴት ማስረዳትና ማሳመን እንደሚቻል ቀጣይ ስራዎች ሊኖሩ ይገባል እንደጥናቱ ፡፡
ጽንስን የማቋረጥ ድርጊት ከሁሉም እድሜ ሲነጻጸር የወጣቶች ዝቅተኛ ነው እንደ Guttma- cher Institute ጥናት ቡድን መሪዋ Elizabeth Sully ምስክርነት፡፡ በወጣቶች የሚከሰተው ወደ ግማሽ ያህል የሚጠጋው እርግዝና ሳይታቀድ ወይንም ሳይፈለግ የተከሰተ ነው። በዚህም ዙሪያ ምናልባት ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል መውሰድ የሚገባቸውን መከላከያ አቅርቦትና የባለሙያዎች ድጋፍ ከምን ደረጃ ላይ እንዳለ መፈተሸ ሊያስፈልግ ይችላል እንደ Elizabeth ማብራሪያ፡፡  
ጥናት አድራጊዎች እንደሚገምቱት በኢትዮጵያ ከፍተኛው ያልታቀደ እርግዝና የሚከሰተው በወጣቶች ሲሆን እሱም ከ (1‚0000-176/) ከአንድ ሺህ ሴቶች 176/ ያህል ይሆናል፡፡ ሲነጻ ጸርም ባጠቃላይ ያልታቀደ እርግዝና እድሜያቸው ከ15-49/ አመት በሚደርሱ ከ(1‚000-101) ከአንድ ሺህ ሴቶች አንድ መቶ አንድ ይሆናሉ፡፡ ምንም እንኩዋን ወጣቶች በእድሜያቸው ከፍ ካሉ ሰዎች ጋር እኩል ወይንም በብልጫ ወሲብ የመፈጸም አጋጣሚ ይኖራቸዋል ባይባልም ነገር ግን ያልተፈለገ እርግዝና መከላ ከያ የማግኘት እድላቸው አነጋጋሪ ይሆናል፡፡  
ጽንስን ማቋረጥ በ2014/እንደተመዘገበው ወደ 96‚243/ ያህል በየአመቱ በወጣቶች የሚፈጸም ሲሆን ይህም የሚያሳየው በማንኛውም እድሜ ባሉ ከሚፈጸመው ዝቅተኛው ማለትም ከ1‚000/ ሴቶች /20/ ያህሉ ባነሰ የተመዘገበ ነው፡፡ ጥናት አቅራቢዎቹ የጠቆሙት ወጣቶች በተሟላ ሁኔታ ያልተፈለገ እርግዝናና የምክር አገልግሎት ለወጣቶች ቅርብ በሆነ መንገድ እና ጥራቱን በጠበቀ ደረጃ እንዲቀርብላቸው ነው፡፡    
ከላይ የተጠቀሰው የጥናት ውጤት እንደሚጠቁመው ሕገ ወጥ የጽንስ ማቋረጥ እንዲፈጸም ምክንያት ለሚሆኑ ነገሮች ምንጊዜም መንገዱ ላይ ጥላ በመፍጠር ለማጥፋት መሞከር ተገቢ ነው፡፡ ይህ ከተደረገ በተለያዩ ምክንያቶች ተደብቀው በህገወጥ መንገድ ጽንስን ለማቋረጥ የሚያስቡ ወጣቶችንም ሆነ በማንኛውም እድሜ ላይ የሚገኙ ሴቶችን አስተሳሰብ ወደሕጋዊ እና የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲሁም ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ አገልግሎት ለማግኘት እንዲያስቡ ማስቻል ጠቀሜታ አለው፡፡
ወጣት ሴቶች ባላሰቡት መንገድ ለእርግዝና የሚያጋልጣቸው ምንም ምክንያት ቢፈጠር እራሳ ቸውን ለመሸሸግ ሳይሞክሩ  ሊጠቀሙበት የሚችሉት ህግ በኢትዮጵያ የተደነገገ መሆኑን ልብ ሊሉ እና ሕይወታቸውን እንዲሁም አካላቸውን ሊጠብቁ ወደ ሚችሉበት ሕጋዊ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ እንዲመሩ ለማድረግ የተቻለው ሁሉ መደረግ አለበት ፡፡   
በ2017/በ Guttmacher Institute የቀረበው መረጃ ከጽንስ ማቋረጥ ጋር የተያያዘ ዝርዝር ነገሮችን ለንባብ ብሎአል፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የጽንስ ማቋረጥ ሁኔታ ምን ይመስላል?
የጽንስ ማቋረጥ ድርጊት መቼ የት …ወዘተ ምን ይመስላል?
ያልተፈለገ እርግዝና እና የታቀደ እርግዝና በኢትዮጵያ ምን ይመስላል?
ሕጋዊ ጽንስ ማቋረጥ ተግባር እና ጽንስ ከተቋረጠ በሁዋላ ያለው አገልግሎት በኢትዮጵያ ምን ይመስላል?
ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ምን ያስከትላል?
የሚሉትን እና ተያያዥ ነገሮችን በሚቀጥለው እትም እናስነብባችሁዋለን፡፡

Read 676 times