Monday, 28 January 2019 00:00

የጅጅጋ ወቅታዊ ፖለቲካ

Written by  መስከረም አበራ
Rate this item
(4 votes)

 (ከአብዲ ኢሌ እስከ ሙስጠፋ ኡመር)
                  

    ለሃያ ሰባት አመታት የዘለቀው ኋላቀር ፖለቲካችን፣ የሃገራችንን ክልሎች ሁሉ ሲያንገላታ የኖረ ቢሆንም የሱማሌ ክልል ደግሞ ከሚብሱት በባሰ ችግር ውስጥ የቆየ፣ በሁለት ሶስት ለበቅ ሲገረፍ የኖረ ክልል ነው፡፡ የዚህ ክልል ህዝብ ከሌላው ህዝብ በተለየ መከራው እንዲብስ ያደረገው በሁለት በኩል እሳት የሚነድበት መሆኑ ነው፡፡ በአንድ በኩል የመለስ ዜናዊ ምልምል የሆነው አብዲ ኢሌ “ኦብነግን ትደግፋላችሁ” እያለ ህዝቡን ወደ እስር ቤት አጉሮ፣ ሊያልፉበት ቀርቶ ሊያደምጡት  በሚያስቸግር መከራ ውስጥ ይዶላል፡፡ በስሙ ጦስ ህዝብ በአብዲ ኢሌ ለበቅ የሚገረፍለት ኦብነግ በበኩሉ፤ አብዲ ኢሌን ፈርተው ይሁን አላማውን ተቃውመው ያልተባበሩትን የክልሉ ነዋሪዎች “አብዲ/የመለስ መንግስት ደጋፊዎች ናችሁ” እያለ ያንገላታል፡፡ በዚህ ላይ ክልሉ እምብዛም ያልለማ ከመሆኑም በላይ ያለው የፀጥታ ችግር ተደምሮ ህዝቡ በሶስተኛው ለበቅ (በኢኮኖሚ ችግር) እንዲገረፍ አድርጓል፡፡
የአብዲ ኢሌ አረመኔነት በህዝቡ ላይ ያደረሰው የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ እኛን የሃገራቸውን ሰዎች ቀርቶ ምዕራባዊያንን ያሳሰበ ነበር፡፡ በስተመጨረሻው እንደውም አሜሪካ፣ አብዲ ኢሌን ከተፈላጊ ወንጀለኞች አንዱ አድርጋ ታድነው ሁሉ ነበር፡፡ የህወሃት/ኢህአዴግን ገመና ለመክተት ተብሎ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፤ ዓለምን ጉድ ያሰኘ እርኩሰት ወደሚሰራበት ወደ ሶማሌ ክልል ትውር ብሎ አያውቅም፡፡ ቱሪስትም መናኝም መስለው ገብተው፣ በክቡሩ የሰው ልጅ ላይ አብዲ ኢሌ እና አለቆቹ  ይሰሩት የነበረውን ግፍ የሚያጋልጡት ባዕዳኑ ምዕራባዊያን ነበሩ። የአቶ አዲሱ ገብረእግዚአብሄር መስሪያ ቤት  በፈረንጆቹ  ስለ ጉዳዩ ሲጠየቅ፤ “ወደዚያ ክልል ሄጄ አላውቅም” ሲል በምቾት ነበር፡፡
ታዛቢ በሌለበት ተከድኖበት ሲንተከተክ የኖረው የሶማሌ ህዝብ፤ አምላክ በቃህ ብሎት፣ አብዲ ኢሌ የተባለው ሰውዬ ከትከሻው ተነስቷል፡፡ አብዲ ሲነሳ የተተኩት አቶ ሙስጠፋ ኡመር ደግሞ ለበደሉ በካሳነት የተቀመጡ የሚመስሉ ሰው ናቸው፡፡ አቶ ሙስጠፋ ጥሩ በሚከፍሉ ዓለም ዓቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ተቀጥረው፣ ባህር ማዶ የሚኖሩ ምሁር ነበሩ፡፡ የተመቸ ኑሯቸውን ጥለው በአመፅ ስትታመስ የኖረችውን የሱማሌን ክልል ለማቅናት፣ በጄ ማለታቸው ያስመሰግናቸዋል፡፡ የተረከቡትን ሃላፊነት በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚገርም ቅንጅት፣ አመርቂ በሆነ ሁኔታ ለመወጣት እያደረጉት ያለው ጥረት ያስደንቃል፤በብዙዎች ዘንድም ተወዳጅነትን አትርፈውበታል፡፡
አቶ ሙስጠፋ በኢህአዴግ ፖለቲካ ውስጥ የኖሩ ሰው አይደሉም፤ክልሉን የሚመራው ሶህዴፓ አባልም አይደሉም፡፡ ይልቅስ የእርስ በርስ ጦርነት ወደ ፍርስራሽነት የቀየራቸውን የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራትን ህዝቦች በእርዳታ ለመታደግ በሚሰሩ የረድኤት ድርጅቶች ውስጥ ሲያገለግሉ የኖሩ የተግባር ሰው ናቸው፡፡ በስራቸው ምክንያት የእነዚህን ሃገራት አሳዛኝ እጣ ፈንታ ያዩት አቶ ሙስጠፋ፤ ኢትዮጵያም እንደ ሃገር እስካልቆመች ድረስ የሶሪያና የየመን እጣ እንደሚጠብቃት ተገንዘበው፣ አገራቸውን ከዚያ ዓይነት ቀውስ ለመታደግ  መስራት እንደሚፈልጉ ለአውስትራሊያው SBS ሬዲዮ በሰጡት ቃለ ምልልስ ገልፀዋል፡፡
ሙስጠፋ የኢህአዴግ ካድሬነት ታሪክ ስለሌላቸው የሰሩትን የመዘከሩ የፕሮፓጋንዳ ጥማት አይፈትናቸውም፤ በክልሉ ያለውን የፖለቲካ ችግር መጠኑን በሚወክል ሁኔታ ተረድተው በአፋጣኝነቱ መጠን ይሰራሉ እንጂ እንደ ሌሎቹ የክልል ባለስልጣናት በችግሩ ዙሪያ አይዞሩም፡፡ ስልጣን ላይ ከተቀመጡ ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ክልሉ ያልለመደውን የሰላም አየር እንዲስብ አድርገዋል፡፡ የዘር ፖለቲካ ሃገሪቱንም ሆነ ሱማሌ ክልልን እንደማይጠቅም በግልፅ የተናገሩ የመጀመሪያው የሃገራችን ባለሥልጣን ሙስጠፋ ኡመር ናቸው፡፡ ቋንቋ መግባቢያ እንጂ ማግለያ እንዳልሆነ ለማስመስከር፣ ዘር ሳይቆጠር፣ ሶማሊኛ የሚናገር ኢትዮጵያዊ ሁሉ በሱማሌ ክልሉ እንዲያገለግል አድርገዋል፡፡ በአብዲ ኢሌ የመጨረሻ የሥልጣን ቀናት፣ የክልሉ ነዋሪዎች ዘር፣ ሃይማኖት ቆጥረው፣ የተጋደሉ ለማስመሰል የተደረገውን ክፉ ስራ ለማርከስ የክልሉ ተወላጆች ባያጠፉ እንኳን “ጥፋቱ የተደረገው በእኛው ስም ስለሆነ ወንድሞቻችንን ይቅርታ መጠየቅ፣ የጠፋባቸውን ንብረት ምትክ እንዲያገኙ ማድረግ፣ በስነ-ልቦና በማፅናናት ወገንተኝነታችንን ማሳየት  አለብን” የሚል በጎ አካሄድ እንዲፈጠር የሙስጠፋ አመራር ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡
በጎሳ ተሸንሽኖ ለመባላት አንድ ሃሙስ ቀርቶት የነበረውን የሶማሌ ክልል፣ በጎሳዎች መካከል ያለውን ፍጥጫ ሳይቀንሱ ስለ ሱማሌ ክልልም ሆነ ስለ ኢትዮጵያዊነት ማውራት አይቻልም በሚል እሳቤ፣ በጎሳዎች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር፣ የሃገሩን ባህላዊ የእርቅ መንገድ ተጠቅመው በጣም ባጭር ጊዜ አመርቂ ስራ ሰርተዋል - አቶ ሙስጠፋ፡፡ ከክልሉ መጠሪያ ጀምሮ እስከ ባንዲራው ድረስ በህዝቡ ዘንድ የነበረውን ቅሬታ አዳምጠው፣ ህዝብ በሚፈልገው መንገድ መፍትሄ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ሙስጠፋ እንዲህ ባለው ብቁ አመራራቸው፣ እጅግ ያሰጋኝ የነበረውን የሶማሌ ክልል ፀጥታ አረጋግተው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በትርምስ ይታወቅ የነበረውን ክልል፣ በአሁኑ ወቅት ምናልባትም ከሌሎች ክልሎች በተሻለ ሰላም ላይ የሚገኝ ክልል አድርገውታል፡፡ ሃገራችን እንዲህ ያሉ ወደ ስራው ያመዘኑ፣ ስራቸው ራሱ አፍ አውጥቶ የሚያወራላቸው እንጂ የፕሮፓጋንዳ አጀብ የማይጠሩ መሪዎች  ያስፈልጓታል፡፡
የአቶ ሙስጠፋ አስተዳደር በሱማሌ ክልል ሰላምና መረጋጋት ላይ ላስመዘገቡት ስኬት የኦብነግ ድርሻም ላቅ ያለ ነው፡፡ ኦብነግ በትጥቅ ትግል የህወሃት/ኢህአዴግን የግፍ አገዛዝ ከመንበሩ ለማውረድ ከሚታገሉ ብረት አንጋች ታጋዮች መካከል በቀድሞው ጠ/ሚ አቶ መለስ በጥብቅ ይፈራ ነበር፡፡ ኦብነግን ላቅ አድርገው ይፈሩት እንደነበር የክልሉን  ልዩ ሃይል ለማቋቋም ያፈሰሱት በጀት፣በኦብነግ አጋርነት  በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ ይፈፀም የነበረው የተለየ ጭካኔ፣አብዲ ኢሌን ይዘውበት የነበረው የወዳጅነት ትስስር ጥብቀት  ማስረጃ ነው፡፡ በተጨማሪም ኦብነግን ወደ ሌላ ፍጥረት በሚጠጋ አረመኔነትና ሰላም ያለመፈለግ አመፀኝነት የመፈረጁ የፕሮፓጋንዳ ናዳ  ድርጅቱን በጥብቅ ከመፍራት የመጣ  ነው።
በህወሃት/ኢህአዴግ በኦብነግ ላይ በተነዛው ፕሮፓጋንዳ ሳቢያ ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ሲመጡ “መደመር” ለሚለው ፍልስፍናቸው ትልቅ ፈተና ሊጋርጥ የሚችለው ኦብነግ ሊሆን ይችላል የሚል ፍርሃት ነበር፡፡ የሆነው ግን ሌላ ነው፡፡ ምናልባትም ኦብነግ ከአብዛኛዎቹ የኦዴፓ አመራሮች በተሻለ የዶ/ር ዐቢይ የመደመር ፍልስፍና አጋር ሳይሆን አልቀረም፡፡ ጭራሽ የአቶ ሙስጠፋን መንግስት ለመበጥበጥ በአቶ አህመድ ሽዴ እየተመራ ያለውን የሶህዴፓ እና የኦዴፓ ጥቂት አመራሮች ቡድን አደብ እንዲገዙ፣ በክልሉ ሰላም ላይ ያነጣጠረ እኩይ ስራቸውን እንዲያቆሙ እያስጠነቀቀ ያለው ኦብነግ መሆኑ፣ የሃገራችን ፖለቲካ እንዴት ባለ የግልምቢጥ ዘመን ላይ እንዳለ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡
የቀድሞው ኢህአዴግ የቀኝ እጅ የነበሩት አቶ አህመድ ሽዴ፤ የአቶ ሙስጠፋ አስተዳደር ላይ ታች ብሎ ፈር ያስያዘውን የሶማሌ ክልል ሰላም ለማደፍረስ፣ የአቶ አብዲ ኢሌን ዘመን አስተዳደር ለማምጣት እየሰሩ እንደሆነ የክልሉ የህግና ሰብዓዊ መብት አማካሪ  አቶ ጀማል ድርየ፣ በግልፅና ቀጥተኛ  ቋንቋ ለኢሳት ተናግረዋል፡፡ ይህ ግልፅነት ፌደራል መንግስቱን ጨምሮ ሌሎችም የክልል አስተዳደሮች ሊከተሉት የሚገባ አካሄድ ነው፡፡ የኢህአዴግ ባለስልጣናት እንደ ብልህነት የሚያዩት የበዛ ማስመሰልና መሸነጋገል፣ ለተገዳዳሪ የመፈርጠሚያ ጊዜ ይሰጥ ይሆናል፤ የችግሩንም ጥልቀት ይጨምር ይሆናል እንጂ የትም አያደርስም፡፡ ይህ የተገለፀላቸው የሱማሌ ክልል ባለስልጣናት፣ የአረመኔውን አብዲ ኢሌን አገዛዝ ትንሳኤ ለማምጣት ላይ ታች የሚሉ የሶህዴፓ ሹማምንትን (በዋናነት አቶ አህመድ ሽዴን) በስም ጠቅሰው፣ “ከድሮ እስከ ዘንድሮ ቅንጣት ያህል የህዝብ ወገንተኝነት የሌላቸው፣ ስልጣንና ጥቅም አምላኪ ተላላኪዎች” እንደሆኑ  አቶ ጀማል ድርየ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ዛሬ ለምን ሰላም ወረደ ብለው በጥባጭ የሆኑት አቶ አህመድ ሽዴ፤ በቅርቡ ኦብነግን በበጥባጭነት ሲከሱ የነበሩ ሰው ናቸው። ዛሬ ደግሞ ሸሽተው ቱርክ ኢስታምቡል ከገቡ የአብዲ ኢሌ ግብረአበሮች ጋር ግንባር በመፍጠር፣ ክልሉን ለማረጋጋት ደፋ ቀና የሚሉ ሰዎችን ለማደናቀፍ እየሰሩ ነው፡፡ አሁን የማን ምንነት እየለየ ነው፡፡ አሁን በሹመት ላይ ሆነውም በመከራ የተረጋጋውን ክልል ለማመስ እየሞከሩ ያሉት አቶ አህመድ ሽዴ፤ ድሮም አሁንም የሶማሌ ክልል ሰላምና የህዝቡ እጣ ፈንታ የሚያስጨንቃቸው ሰው እንዳልነበሩ ነው ከሰሞኑ ስራቸው መገንዘብ የሚቻለው፡፡ በአንፃሩ ትናንት በአመፀኝነት ሲከሱት የነበረው ኦብነግ፤ ሳይሾም ሳይሸለም፣ “አመራሮቼ በክልሉ አስተዳደር ላይ ይሾሙልኝ” ሳይል፣ ለህዝብ ሰላም ስለሆነ ብቻ በቂ ነው ብሎ አደብ ገዝቶ መቀመጡ ሳያንስ፣ እነሱኑ እንዲታገሱ እየመከረ ነው፡፡ አልፎ ተርፎም በሃገራችን የዘር ፖለቲካ አብቅቶ የዲሞክራሲ ዘመን እንዲመጣ ለመስራት እንደሚፈልግ ጠቁሞ፣ ለዚህም  ራሱን ወደ ህብረ-ብሄራዊ ፓርቲነት ሊቀይር እንደሆነ በይፋ ተናግሯል፡፡ ይህ ያልገረመው አይገኝም መቼም!
የኦብነግ ጨዋነት ትናንት ትጥቅ ያስነሳው በህዝብ ላይ ሲደረግ የነበረው ግፍ ብቻ እንደሆነ አስመስካሪ ነው፡፡ ይህ የኦብነግ ብስለት የተሞላበት ፖለቲካዊ ጨዋነት፣ ለሶማሌ ክልልም ሆነ ለሃገራችን መረጋጋት እጅግ አስፈላጊ ግብዓት ነው፡፡ በአራቱም ማዕዘን በሰላም ውላ በማታድረው ሃገራችን ፖለቲካዊ ትኩሳት ላይ ኦብነግም እንደ ኦነግ ለጠብም ለፍቅርም የማይመች ቢሆን ኖሮ፣ ፈተናችን ይከብድ ነበር፡፡ አብዲ ኢሌን ሲወጋ የነበረው ኦብነግ፤ አቶ ሙስጠፋንም ለመውጋት አልተነሳም፡፡ በአንፃሩ ብዙ አመት ታገልኩ የሚለው ኦነግ፤ አቶ አባዱላን/አቶ ሙክታርን ለመውጋት አልሆንልህ ባለው ጦሩ፣ አቶ ለማ መገርሳን የመሰሉ ሰው ሊወጋ ይገለገላል፡፡
የኦብነግ የአዋቂ እርምጃ፣ የአቶ ሙስጠፋ ድንቅ አመራር፣ ከሱማሌ ህዝብ የሚበጀውን አዋቂነት ጋር ተደማምሮ፣ የጅጅጋ ፖለቲካ ሙክክ ብሎ እንዲበስል አድርጎታል፡፡ አሁን በእነ አቶ አህመድ ሽዴ ቆስቋሽነት የተነሳው የለውጥ ቅልበሳ ሴራ የሚናቅ ባይሆንም፣ ህዝባዊ ድጋፍ ስለማይኖረው እምብዛም ሩቅ የማይሄድ ግን ደግሞ በአንክሮ ሊታይና መላ ሊባል የሚገባው ችግር ይሆናል፡፡ አቶ አህመድ ሽዴ ከዚህ በኋላም በዶ/ር ዐቢይ እልፍኝ እንዲሽሞነሞኑ ሊፈቀድላቸው አይገባም፡፡ ሌላ ሰው የማይገባው የኢህአዴግ ካድሬዎች ጠላትን አጠገብ በማድረግ የሚከናወን የፖለቲካ ጨዋታም ቢሆን፣ እንዲህ ነገሮች ፍርጥ ብለው ከወጡ በኋላ የሚያመጣው ጥቅም ያለ አይመስለኝም፡፡
ይልቅስ አጋጣሚውን ተጠቅሞ የወዳጅ ጠላትን ማጥፋቱ የተሻለ ይሆናል፡፡ አደገኛ ጠላትን አጠገብ አድርጎ መሾም መሸለሙ፣ በክልሉ የተጠላ ካድሬን ፌደራል ወንበር ላይ ቂብ አድርጎ፣ ረዥም እጁን ወደ ተወለደበት ክልል ፖለቲካ እንዲሰድ የመልቀቁ የኢህአዴግ ካድሬዎች ዘይቤ፣ ኢህአዴግ ላልሆኑት አቶ ሙስጠፋ ግርታን መፍጠሩ አይቀርም፡፡ የሆነ ሆኖ አቶ ሙስጠፋ ዑመር፤ ድምፃቸውን አጥፍተው፣ በአጭር ጊዜ ላስመዘገቡት ድንቅ አስተዳደራዊ ብልጫ መመስገን ያለባቸው ሲሆን ያለንበትን ዘመን የሚመጥን ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሊደግፋቸው ይገባል፡፡ በሃገር ደረጃ ሳይቀር ትልቅ ስራ የመስራት ችሎታ ያላቸው፣ ብስልና የተግባር ሰው ናቸው - አቶ ሙስጠፋ ኡመር፡፡          

Read 1166 times