Print this page
Monday, 28 January 2019 00:00

የእነ አቶ በረከት ስምኦን እስር አወዛጋቢ ሆኗል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)


 - “የአቶ በረከት መታሰር የለውጥ ኃይሉ የህግ ማስከበር ሂደቱን ወደፊት እየገፋበት መሆኑን አመላካች ነው” - ፕ/ር መረራ ጉዲና
 - “የእነ አቶ በረከት መታሰር ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው - አቶ ጌታቸው ረዳ
 - አሁን ብዙዎች ጥሩ አየር መተንፈስ ይችላሉ” - አና ጐሜዝ


     የህዝብ ሃብት በማባከን ተጠርጥረው የታሰሩት የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣናት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ትናንት ፍ/ቤት ቀርበው የ14 ቀን ተጨማሪ ቀጠሮ የተሰጠባቸው ሲሆን ተጠርጣሪዎች ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት ጉዳያችን በፌደራል ፍ/ቤት ይታይልን የሚል ጥያቄ በፍ/ቤቱ ውድቅ ተደርጓል። በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ስም ያለ ሀብትና ንብረት ታግዷል፡፡ ሁለቱም ተጠርጣሪዎቹ ጉዳያቸው ቤተሰቦቻቸው በቅርበት በሚገኙበት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንዲታይላቸው እንዲሁም የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ጉዳያቸውን በውጪ ሆነው እንዲከታተሉ የጠየቁ ቢሆንም ፍ/ቤቱ ሁለቱንም ጥያቄዎች ውድቅ በማድረግ ጉዳዩን ለየካቲት 1 ቀን2011 ዓ.ም ቀጥሮታል፡፡
አቃቤ ህግ ተመዘበረ ከተባለው ሃብት አንፃር ጉዳዩ ዋስትና የማያሰጥ ነው የሚል መከላከያ ያቀረበ ሲሆን ምስክሮች በአማራ ክልል ስለሚገኙና ወንጀሉም የተፈፀመው በአማራ ክልል በመሆኑ ጉዳዩ ሊታይ የሚገባው በባህርዳር ነው የሚል መከራከሪያ አቅርቧል፡፡  
እነ አቶ በረከት በዋናነት የተጠረጠሩት በጥረት ኮርፖሬት ስር ከሚገኙ 6 ኩባንያዎች የአክሲዮን ግዥና የአንድ ኩባንያ ሽያጭ ጋር በተያያዘ በተፈፀመ የገንዘብ ብክነት የአሠራር ጥሰት መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በአጠቃላይ ግለሰቦቹ የጥረት ቦርድ ኃላፊዎች በነበሩ ወቅት ከህግ አሠራር ውጪ በመንቀሳቀሳቸው፣ ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲባክንና እንዲመዘበር ሆኗል ይላል ክሱ፡፡
በቀጣይም በሁለት ኩባንያዎች ማለትም በዳሽን ቢራ እና በጁቬንቱስ ኩባንያ ላይ የሚደረገው የኦዲት ምርመራ ሲጠናቀቅ፣ በግለሰቦቹ ላይ ተጨማሪ ክስ ሊቀርብባቸው ይችላል ተብሏል፡፡
የግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር መዋል ተከትሎ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የግለሰቦቹ ለህግ መቅረብ እንዲያውም የዘገየ ቢሆን እንጂ ተገቢ ውሣኔ ነው ብሏል፡፡ መንግስት በቀጣይም የአገርን አንድነት ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ፣ በህዝብ መካከል ጥላቻ፣ ግጭትና አለመተማመንን የሚያነግሱ፣ የህዝብን ሃብትና ንብረት የዘረፉ ወገኖችን  ለህግ እንዲያቀርብ ንቅናቄው ጠይቋል፡፡
በአማራ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት የፈፀሙ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ አገርን የዘረፉና የመዘበሩ ግለሰቦችን መንግስት በቀጣይ ለህግ እንደሚያቀርብ ተስፋ እናደርጋለን ያለው አብን፤ በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ዝርዝር የፍትህ አሰጣጥ ሂደቱ ለህዝብ በግልጽ እንዲያሳውቅም ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) ሊቀ መንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ “የሁለቱ የቀድሞ ባለስልጣናት እስር፣ በኢህአዴግ ውስጥ ያለው ሽኩቻና አለመተማመን እያየለ መምጣቱን ያሳየኛል፤ ጉዳዩን የህግ የበላይነት ማስከበር ብቻ አድርጌ አልወስደውም” ብለዋል፡፡
“ወደ ትክክለኛ የህግ ማስከበር ይገባ ከተባለ፣ አሁን በከፍተኛ አመራር ላይ ከሚገኙት መካከልም የአብዛኞቹ ማረፊያ ወህኒ ቤት ይሆን ነበር ብለዋል፡፡ በእነ አቶ በረከት ላይ የቀረበው ክስ፤ የፖለቲካ ውሣኔ የፖሊሲ አቅጣጫና ሲስተም የፈጠረውን ችግር ያሳያል ባይ ናቸው - ኢ/ር ይልቃል፡፡
አቶ በረከትን በምርጫ 97  በተለየ ሁኔታ እንደሚያስታውሷቸው የጠቆሙት ፕ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው በተለይ የብአዴን መስራች፣ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አጥማቂና የቀድሞ ጠ/ሚ አቶ መለስ የቅርብ ሰው የነበሩ ከመሆናቸው አንፃር በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የለውጥ ሃይሉ የህግ ማስከበሩን ጉዳይ ወደፊት እየገፋበት መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል፡፡
የኢህአዴግን የፖለቲካ እምነትና መስመር ከቀየሱ ሰዎች አንዱ አቶ በረከት ናቸው የሚሉት ፕ/ር መረራ አሁን በጥፋት ተጠርጥረው መታሰራቸው ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡ ሠርተውታል ተብለው የተጠረጠሩበት ወንጀል ምን ያህል አሳማኝ ነው የሚለው በሂደት በፍ/ቤት የሚረጋገጥ እንደሚሆን ጠቁመዋል - ፕ/ሩ፡፡
የህወኃት ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ፤  ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት፤ የእነ አቶ በረከት በሙስና ተጠርጥሮ መታሰር እንዳስደነቃቸው ተናግረዋል፡፡ አቶ በረከት ስምኦንም ሆኑ አቶ ታደሰ ካሣ ከሙስና አንፃር ስማቸው ሊነሳ የማይችል ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፤ እስሩ ፖለቲካዊ ነው ብለው እንደሚያምኑ ጠቁመዋል፡፡
የእስሩ ሌላኛው ምክንያት በግልጽ እንዲነገር የጠየቁት አቶ ጌታቸው፤ የሁለቱ የቀድሞ ባለስልጣናት መታሰር ፈጽሞ ያልጠበቁት መሆኑንም በመግለጽ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን በድጋሚ ተመልክተው ያስተካክላሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም አስረድተዋል፡፡
አንድ ሰው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በማድረጉ ወይም የክልል አሊያም የፌደራል መንግስትን በመተቸቱ ለእስር የሚዳርግ ከሆነ፣ ግለሰቦቹ ተገቢውን ፍትህ ያገኛሉ ብሎ መጠበቅ አይቻልም ብለዋል - አቶ ጌታቸው ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት፡፡
በ97 ምርጫ የኢትዮጵያ የአውሮፓ የምርጫ ታዛቢ ልኡክ መሪ የነበሩትና በወቅቱ “ምርጫ ተጭበርብሯል” የሚል ሪፖርት ያቀረቡት፤ አና ጐሜዝ በቲውተር ገፃቸው ባሠፈሩት አስተያየት፤ “በመጨረሻም ወንጀለኛው በረከት ስምኦን ታስሯል፤ ብዙዎች አሁን ጥሩ አየር መተንፈስ ይችላሉ” ብለዋል፡፡
አቶ በረከት ስምኦንንም በተደጋጋሚ “ኢትዮጵያዊው ጐብልስ” ሲሉ የአዶልፍ ሂትለር የቀኝ እጅና ከፍተኛ አማካሪ ከነበረው ጐብልስ ጋር ያመሳስሏቸዋል - አና ጐሜዝ፡፡  

Read 9421 times