Monday, 28 January 2019 00:00

“የኦነግና የመንግሥት እርቅ ተጨማሪ ውይይትና መተማመን ይፈልጋል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 የኦነግና የመንግሥት (ኦዴፓ) እርቅ የበለጠ ሊጠናከር እንደሚገባው የተገለፀ ሲሆን በአባገዳዎች የሚመራው 71 አባላት ያሉት የአፈፃፀም ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ ስራውን በይፋ ጀምሯል፡፡
ሁለቱ አካላት እርቅ የፈፀሙበት የሽምግልናና የአባገዳዎች የእርቅ ስነ ስርአት ሂደት በሃገሪቱ ያሉ ሌሎች መሰል ችግሮችን ለመፍታት ሊውል እንደሚገባው የገለፁት የፖለቲካ ልሂቃን፤ በዚህ ረገድ የሃገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡
አባገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች ያከናወኑት የእርቅ ስርአት በቀላሉ ውጤታማ ሆኗል ያሉት አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ የሽምግልና ባህላችን ተገቢውን ቦታ እየያዘ መምጣቱ በእጅጉ ተስፋ ሰጪ ነው ይላሉ፡፡
የሽምግልና ስርአታችን ባልና ሚስት ብቻ ከማስታረቅ አልፎ ሁለት ጦር የተማዘዙ አካላትን ማስታረቁ የኦሮሞ ህዝብ ጥንት ሲጠቀምባቸው የነበሩ የአባ ገዳና የሃደ ሲንቄ የእርቅ ስርአቶች ተመልሰው መምጣታቸውን ያመላክታል ብለዋል፡፡ እርቁ በቀጣይም በሌሎች የተጋጩ ወገኖች ዘንድም ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት ተናግረዋል - ዶ/ር ነጋሶ፡፡
አባ ገዳዎች፤ የኦነግ እና የኦዴፓ የአስመራ ውይይትን በመሃል ተገኝተው ቢከታተሉና ቢታዘቡ ኖሮ አሁን ለእርቅ የተቀመጡበት ግጭት አይፈጠርም ነበር ያሉት ፖለቲከኛው፤ ሌሎች የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶችም ንግግር ሲያደርጉ በመሃከላቸው አባገዳዎችን በታዛቢነት ቢጠቀሙ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡
የተደረገው እርቅ ዘላቂ ውጤት ያመጣል የሚል እምነት ያላቸው ዶ/ር ነጋሶ፤ በተለይ 71 አባላት ያሉት የጋራ ኮሚቴ በቀጣይ የሚያከናውናቸው ተግባራዊ ስራዎች ወሳኝ መሆናቸውን አስምረውበታል፡፡
ስምምነቱን ከሁለቱ ወገን የጣሰ አካል ያለበትን ተጠያቂነት የሚያስቀምጥ ሰነድ መኖር አለበት የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ፤ ህዝቡም በዚያ መሰረት ጉዳዮን መታዘብ ይችላል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ስምምነቶቹ በግልፅ ለህዝብ፣ ለመገናኛ ብዙኃንና ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ይፋ መደረግ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡
ግጭቱን በአባገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች የሽምግልና ስርአት ለመፍታት የተደረገው ጥረት ለሌላውም አስተማሪ ነው በሚለው የዶ/ር ነጋሶ ሃሳብ የሚስማሙት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ም/ሊቀ መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው፤ በዚህ ስምምነት ዘላቂ ተፈፃሚነት ላይ ግን ጥርጣሬ እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡
በኦነግ እና በኦዴፓ መካከል ያለው የፖለቲካ ቁርሾ በተጨማሪ ስምምነቶች ሊጠናከር ይገባዋል ያሉት አቶ ሙላቱ፤ በእርቅ ስነ ስርአቱም ላይ ቢሆን ልዩ ትኩረት ሰጥተው የኦዴፓ ሊቀ መንበርና ም/ሊቀ መንበር ሊገኙ ይገባ ነበር ብለዋል፡፡ ጉዳዩን በፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ ደረጃ ብቻ ማስተናገዳቸው ተገቢ አልነበረም ያሉት አቶ ሙላቱ፤ በቀጣይ ግን የኦነግ አመራሮችና የኦዴፓ ሊቀ መንበርና ም/ሊቀመንበር ተጨማሪ ውይይትና መተማመን መፍጠር አለባቸው ይላሉ፡፡
ቀጣዩ የእርቁና የስምምነቱ ፈተና በአባገዳዎች ጫንቃ ላይ የወደቀው የኦነግ ሰራዊት እጣ ፈንታ ነው ያሉት የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር፤ የተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ በዚህ ረገድ የበሰለና ጠንካራ ውሳኔ ይጠበቅበታል ብለዋል። ግጭቱ በነበረባቸው የምዕራብ ወለጋና ሌሎች አካባቢዎች ላይም የህዝብ ውይይት መደረግና የበለጠ ጠንካራ መተማመን ካልተፈጠረ ስምምነቱ ዘላቂ ውጤት ላያመጣ ይችላል የሚል ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡
ኦነግ በየቦታው ቢሮ ሊከፍት የሚያደርገው እንቅስቃሴ፣ ሰራዊቱን መልሶ የማቋቋም ሂደትና ኦነግ በህዝቡ ውስጥ የሚያደርገው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች የግጭት ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው - አቶ ሙላቱ፡፡
የኦነግን አካሄድ በፅኑ ሲተች የሰነበተው አክቲቪስቱ ጀዋር መሃመድ በበኩሉ፤ በመጨረሻ አቶ ዳውድ ኢብሳ የወሰኑት ውሳኔ መልካም ነው ብሏል፡፡
በተለይ ጦሩን ለአባ ገዳዎችና ለህዝብ አስረክቤያለሁ የሚለው ቃላቸው ጠቃሚ ነው፤ በቀጣይ አባገዳዎች ለኦነግ ሰራዊት የተኩስ አቁም ጥሪ ማቅረብ፣ የጦር ኃይሉ ወደ ህዝቡ የሚቀላቀሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ ጦሩ ወደ ካምፕ እንዲገባ ጥሪ ማቅረብ፤ በመጨረሻም ለተመለሰው የጦር ኃይል ተገቢውን ስልጠና እንዲሰጥ ማመቻቸት ይገባል ብሏል፡፡ እነዚህ ሂደቶች ከተፈፀመ እርቁ ሙሉ ውጤት ያመጣል የሚል እምነት እንዳለው አቶ ጀዋር ገልጿል፡፡
በእርቁ እለት የተቋቋመው ኮሚቴ በበኩሉ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ የመጀመሪያውን የህዝብ እርቅ መድረክ በአምቦ ከተማ በማከናወን ስራውን መጀመሩ ታውቋል፡፡ በእርቅ ስነ ስርአቱ ላይ የኦነግ እና የኦዴፓ የእርቅ ስምምነት ለህዝብ ይፋ ተደርጓል፡፡
በኦነግ የጦር ሰራዊትን ትጥቅ ለማስፈታትና ሰራዊቱን ወደ ካምፕ ለማስገባት የተደረሱ ስምምነቶችን ለማስፈፀም የተቋቋመው ኮሚቴ፤ 11 ምሁራን፣ 54 አባ ገዳዎች፣ 3 የኦዴፓ እንዲሁም 3 ከኦነግ አባላት የተካተቱበት ነው ተብሏል፡፡

Read 4885 times