Monday, 28 January 2019 00:00

በሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ላይ “መፈንቅለ ስልጣን” ለማድረግ ሞክረዋል የተባሉ 6 አመራሮች ተባረሩ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 በድሬደዋ የተቀላቀለውን ግጭት ተከትሎ 84 ተጠርጣሪዎች ታስረዋል


      ከሰሞኑ በምስራቅ ኢትዮጵያ የጅግጅጋ እና ድሬደዋ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ የሶማሌ ክልል መንግስት 6 ከፍተኛ አመራሮን ከስልጣን ያባረረ ሲሆን የድሬደዋ አስተዳደር ደግሞ 84 የወንጀል ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ታውቋል፡፡
በሶማሌ ክልል/ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፋ ኡመር ላይ የማጥላላት ዘመቻ በመክፈት የመፈንቅለ ስልጣን ሙከራ አድርገዋል በተባሉ ስድስት የክልሉ መንግስት የካቢኔ አባላት ናቸው ከትናንት በስቲያ ሐሙስ የተባረሩት፡፡
በዚህም መሰረት የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ የነበሩት አቶ ጉሌድ አዋለ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት አማካሪ አቶ አብዲ ሃኪ፣ የክልሉ ልዩ ፖሊስ ኢንተርፕራይዝ ምክትል ኃላፊ አቶ ሃሰን አሊ፣ የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ኃላፊ አቶ አብዲ ሀኪም አሊ፣ የክልሉ የከተማ ስፋ ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲ ኢሌ አብዱላሂ እና የክልሉ የውሃ ልማት አማካሪ አቶ አብዲ ሙሃመድ ኡስማን ከካቢኔው መሰናበታቸውን የክልሉ መንግስት አስታውቋል፡፡
እነዚህ አመራሮች በዋናነት በእስር ላይ የሚገኙትን የቀድሞውን የክልሉን ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሃመድን አላማ ለማስፈፀምና በሰብአዊ መብት ጥሰትና በአስተዳደር ብልሹነት ከስልጣኑ የተነሳውን ስርአተ መንግስት ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ ነበር ተብሏል፡፡
የክልሉን መንግስት ከቀድሞ አስተዳደር ትስስር እና ስውር መዋቅር የማፅዳቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ መንግስት አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ከጥምቀት በአል አከባበር ጋር በተያያዘ በጅግጅጋ እና በድሬደዋ ከተማ በተለምዶ ሄጎ እየተባሉ የሚጠሩ ቡድኖች ግጭት ለመፍጠር መንቀሳቀሳቸው የተገለፀ ሲሆን ይህን ተከትሎም የድሬደዋ አስተዳደር ፖሊስ 84 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉ ተገልጿል፡፡
በድሬደዋ ከተማ ከሰኞ ጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት እና አለመረጋጋት እስከትናንት በስቲያ መቀጠሉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የአካባቢው ምንጮች ለአዲስ አድማስ እንዳረጋገጡት በገንዳ ቆሬ፣ ጎሮ፣ ደቻቱ አካባቢ ሐሙስ እለት ተቃውሞና ግጨት እንደነበር ያስታውቁ ሲሆን ፖሊስም በርካታ ተጠርጣሪዎችን ሲያስር እንደነበር አስታውቀዋል፡፡
በከተማው ተቃውሞ የተፈጠረው በዋናነት የአስተዳደር ለውጥ ጥያቄን መነሻ አድርጎ መሆኑን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በተለይ በከተማ አስተዳደሩ ፍትሃዊ የሆነ የስልጣን ድልድል ይደረግ 40 በመቶ በኦሮሞ 40 በመቶ በሶማሌ እና 20 በመቶ በሌሎች ብሔር ተወላጆች አስተዳደሩ መደልደሉ አድሎአዊ እና 1ኛ እና ሁለተኛ ዜጋን የሚፈጥር ነው የሚለው የተቃውሞ ዋነኛ ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል፡፡
አለመረጋጋቱ እና ግጭቱ እስከትናንት ድረስ የቀጠለ ሲሆን በንግድ እንቅስቃሴዋ ሞቅ ደመቅ የምትለው ድሬደዋ ባለፉት አምስት ቀናት ተቋሟቶቿ ከአገልግሎት ውጪ ሆነው ከርመዋል፡፡
በግጭቱ የአካል ጉዳቶች ከማጋጠማቸው ውጪ እስከ ትናንት ድረስ በሰው ህይወት ላይ ያጋጠመ ጉዳት አለመኖሩን የሆስፒታል ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

Read 5513 times