Monday, 28 January 2019 00:00

ዞን እንዲሆን የተወሰነው የኮንሶ ወረዳ አከላለል ቅሬታ አስነሳ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  በቅርቡ በደቡብ ክልል የወረዳ እና የዞን አደረጃጀት ለውጥ ሲደረግ ራሱን የቻለ ዞን እንዲሆን የተወሰነው የኮንሶ ወረዳ አከላለልና አስተዳደር ሁኔታ ቅሬታ የፈጠረ ሲሆን የኮንሶ የህዝብ ተወካዮች አቤቱታቸውን አዲስ አበባ ለሚገኘው የሰላም ሚኒስቴር አቅርበዋል፡፡
ህዝቡ በአሁኑ ወቅት በዋናነት በምንፈልጋቸው በምናምናቸው ሰዎች እንመራ እንዲሁም በ1 ወረዳ የሚኖር የኮንሶ ህዝብ ወደ ሌላ ዞን እንዲከለል መደረጉ አግባብ አይደለም የሚል ጥያቄ ይዞ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱን የኮንሶ ህዝብ ኮሚቴ አባል አቶ ገመቹ ገንሳ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
ህዝቡ ይሄን ጥያቄ ወደ ፌደራል ይዞ ከመምጣቱ በፊት በተደጋጋሚ ለደቡብ ክልል ብሔራዊ መንግስት ማቅረቡን ነገር ግን ምላሽ የሚሰጥ አካል መታጣቱን የጠቆሙት አቶ ገመቹ ከወራት በፊት በኮንሶ ላራት ከተማ 2መቶ ሺ ያል ሰው አደባባይ ወጥቶ ጥያቄውን ማቅረቡን አስታውቀዋል፡፡
በወቅቱም የክልሉ አመራሮች አደባባይ የወጣውን ህዝብ ለማረጋጋት በሚመስል ሁኔታ ጥያቄያችሁ ሁሉ ምላሽ ያገኛል የምትፈልጓቸውን አመራሮች በፅሁፍ በኮሚቴ በኩል አሳውቁን እንዲሁም ያሏችሁን ተጨማሪ ጥያቄዎች በተመሳሳይ አቅርቡ ብለው ህዝቡን ተሰናብተው ወደ መጡበት መመለሳቸውን ያስታወሱት አቶ ገመቹ በፅሁፍ የቀረበላቸውን ጥቄ ግን ሊቀበሉን አልቻሉም ብለዋል፡፡
ህዝቡ በዚህ አካሄድ በመሰላቸቱ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የሰላም ሚኒስቴር ከ5 መቶ በላይ ተወካዮቹን ማክሰኞ እለት መላኩን አስታውቀዋል፡፡
የተጓደሉ መረጃዎች ይሟሉ፣ ህዝብ የሚፈልጋቸው አስተዳደሮች ይምሩን የሚለው የህዝቡ ጥያቄም ለሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዘይኑ ጀማል ማቅረባቸውን ያስታወቁት አቶ ገመቹ ሚኒስትር ዴኤታውም በቀጣይ ማክሰኞ ጥር 21 ቀን ወደ ስፍራው አቅንተው ህዝብን በማወያየት ጊዜ ወስደው ችግሩን ለመፍታት ቃል መግባታቸውን አቶ ገመቹ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡

Read 6028 times