Monday, 28 January 2019 00:00

የጠ/ሚኒስትሩ ዕረፍት አልባ የአውሮፓ ጉብኝት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 “ለዓለም ህብረተሰብ መተማመንን የሚፈጥር ማብራሪያ ሰጥተዋል”


    ባለፈው ሰኞ ጥር 13 የአውሮፓ ጉብኝታቸውን ከጣሊያን - ሮም የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ በሮም ከጣሊያኑ አቻቸው ጋር ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን ከአዲስ አበባ ምፅዋ የሚዘረጋውን የባቡር መስመር ጨምሮ ጣሊያንና ኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቀጣይ ግንኙነቶች ላይም መክረዋል፡፡
በጣሊያን ከሚገኙ ባለሀብቶችና የታላላቅ ኩባንያ ባለቤቶችና ዋና ስራ አስፈፃሚዎች ጋር በኢትዮጵያ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ተነጋግረዋል፡፡ የጣሊያን ጉብኝታቸውን እንዳጠናቀቁ የካቶሊክ ጳጳስ መቀመጫ የሆነችውን ቫቲካንን የጎበኙ ሲሆን ከፓፕ ፍራንሲስ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል፤ የአቢሲኒያ ቤተክርስቲያንንም ጎብኝተዋል፡፡
ረቡዕ በተጀመረው የዳቮስ የዓለም የኢኮኖሚ ጉባኤ ላይ ንግግር ካደረጉ የዓለም መሪዎች አንዱ የነበሩት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ወራት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና አካባቢያዊ ዲፕሎማሲ ላይ ያደረገቻቸውን ማሻሻያዎችና ለውጦች በስፋት አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ መደመር በተሰኘ ፍልስፍና እየተመሩ ሁሉን አካታች የሆነ የፖለቲካ ንጣፍ ለመዘርጋት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ያወሱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በኢኮኖሚው ረገድም ቴሌ እና አየር መንገድን ጨምሮ በመንግስት በብቸኝነት ተይዘው የነበሩ ኩባንያዎችን በሙሉ እና በከፊል ወደ ግል ለማዘዋወር መንግስታቸው በቁርጠንነት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከጉባኤው ጉን ለጎንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የታላላቅ ኩባንያ መሪዎችንና የኢኮኖሚ ባለሙያዎችንም አግኝተው ተነጋግረዋል፡፡ ከዱባይ ኢንቨስትመንት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ጋር በመጀመሪያው የዳቫስ ቆይታቸው የተወያዩት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ኩባንያው በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርግ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ ኩባንያውም ግብዣውን ተቀብሎ በቅርቡ ጥናት እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም መስራች የሆኑትን ፕሮፌሰር ክላውስ ሸዋብን ያገኙት ዶ/ር ዐቢይ፤ ኢትዮጵያ የ2020 የዓለም ኢኮኖሚ ፎረምን እንድታዘጋጅ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ብቻ ሳያበቁ የማይክሮሶፍት ባለቤትና የዓለም ቁጥር ሶስት ቢሊየነሩ ቢል ጌትስ እንዲሁም ቻይናዊው የአሊባባ ግሩፕ ኃላፊ ቢሊየነሩን ጃክ ማን አነጋግረዋል፡፡ በውይይታቸውም የቴክኖሎጂ ከተማን መገንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተነጋግረው ባለሀብቱም ግብዣውን ተቀብለዋል፡፡
የሳይንስ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጆይ ካሰርንም በኢነርጂ ዘርፍ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጠ/ሚኒስትሩ ጠይቀዋቸዋል፡፡
ባለሀብቶችንና የታላላቅ ኩባንያዎች ኃላፊዎችን ከማነጋገራቸው ጎን ለጎን ታዋቂውን የCNN የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ፋሪድ ዘካሪያንም አግኝተው መወያየታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአውሮፓ ቆይታቸው ያለእረፍት ባተሌ ሆነው ከሰነበቱ በኋላ የመጨረሻ ጉብኝታቸውንም በቤልጅየም ብራሰልስ አድርገዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ከዚህ ቀደም ይደረጉ ከነበሩት በተሻለ የተሳካ እንደነበር የጠቆሙት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ፤ የሃገሪቷን ገፅታ በማስተዋወቅና ለኢንቨስተሮች መተማመን በመፍጠር ረገድ የጉብኝታቸው አስተዋፅኦ የላቀ ነው ይላሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚከተሉትን የመደመር ፍልስፍና በከፍተኛ ሁኔታ ለማስተዋወቅ መሞከራቸው እንዲሁም ሃገሪቱ በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ላይ መሆኗን ያስረዱበት መንገድ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም ያሉት ምሁሩ፤ ኢኮኖሚውን እናደርጋለን፣ ፖለቲካውን እያረጋጋን ነው ማለታቸውና ሃገሪቱ ለቢዝነስ ክፍት መሆኗን ማስረዳታቸው ለዓለም ህብረተሰብ መተማመንን ይፈጥራል፤ ጠ/ሚኒስትሩ ለሃገራቸው ያላቸውን ትልቅ ራዕይና ግብም ያንፀባርቃል ብለዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በኢኮኖሚውና በፖለቲካው ሃገሪቱ ያለችበትን ደረጃ በአካል ተገኝተው በትልቁ የኢኮኖሚ ጉባኤ ላይ ማስረዳታቸው ለኢንቨስተሮች ትልቅ መተማመን የሚፈጥር ነው የሚለውን የዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ሃሳብ የሚጋሩት የቢዝነስ ፕላን አማካሪው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በበኩላቸው፤ የውጪ ኢንቨስትመንት ወደ ሃገር ውስጥ ለመሳብ ኢትዮጵያ በዓለም ተወዳዳሪ ሆና ለመቅረብ የሚያስችላትን ተግባር ለመፈፀም ችለዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያገኙትን እድል ተጠቅመው ወሳኝና የዓለም ታላላቅ ኩባንያ ባለቤቶችን አግኝተው በተናጥል ማነጋገራቸውም ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውና ለኩባንያዎቹም ያላቸውን አላማና ግብ የሚያስረግጥላቸው ነው ብለዋል አቶ ዘመዴነህ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአውሮፓ ቆይታ በኢንቨስትመንት በኩል ለሃገሪቱ መልካም እድሎችን ያመጣል የሚል ሙሉ መተማመን ያላቸው ምሁራኑ፤ በዚያው ልክ ስጋቶችም እንዳሉ ይጠቅሳሉ፡፡
የውጭ ኢንቨስተሮች በአንድ ሃገር ኢንቨስትመንት ለማከናወን እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚጠይቁት በሃገር ውስጥ ያሉ የባንኮች የማበደር አቅምን ነው የሚሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ በቀጣይ መንግስት በባንክ ጉዳይ አዳዲስ የፖሊሲ አማራጮችን መዘርጋት አለበት ይላሉ፡፡
ለዚህም አንዱ የመፍትሄ አማራጭ የውጭ ሃገር ታላላቅ ባንኮች ወደ ሃገር ቤት መጥተው እንዲሰሩ ማድረግ ነው ብለዋል፤ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ የበርካታ ሃገራትን ልምድ በማሳያነት በመጥቀስ፡፡  

Read 5128 times