Saturday, 19 January 2019 00:00

ሪሃና “ያለ አግባብ በስሜ ነግዷል” በሚል ወላጅ አባቷን ከሰሰች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ታዋቂዋ አሜሪካዊት የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ሪሃና የቤተሰቡ ስያሜ የሆነውን ፌንቲ የሚል ቃል ለኩባንያው ስያሜነት በመጠቀምና የኩባንያው ባለድርሻ ወይም የስራ አጋር እንደሆንኩ በማስመሰል ዝናዬን ተጠቅሞ በስሜ በመነገድ ያልተገባ ጥቅም አግኝቷል በማለት በወላጅ አባቷ ሮቢን ፌንቲ ላይ ክስ መመስረቷ ተነግሯል፡፡
ፌንቲ የሚለውን ቃል ለንግድ ምልክትነት ወይም ለኩባንያ መጠሪያነት የመጠቀም የባለቤትነት መብቱ የሪሃና እንደሆነ የዘገበው ቢቢሲ፤ ወላጅ አባቷ ግን በ2017 ፌንቲ ኢንተርቴይንመንት የተባለ የመዝናኛው መስክ ኩባንያ ከማቋቋም አልፎ እሷ በማታውቀው መልኩ በስሟ የሙዚቃ ጉዞ ለማዘጋጀት ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የድብቅ ድርድር እስከማድረግ መድረሱንና ድምጻዊቷም በዚህ ድርጊቱ አባቷን መክሰሷን አመልክቷል፡፡
አባትዬው የድምጻዊቷን የንግድ ምልክት ከመጠቀም ባለፈ ታዋቂነቷን ተጠቅሞ እሷ በማታውቀው ሁኔታ በስሟ የንግድ ድርድር ማድረጉ ህገወጥ ድርጊት እንደሆነ በግለሰቡ ላይ የተመሰረተው ክስ ያስረዳል፡፡
አለማቀፍ ዝናን ያተረፈቺው ድምጻዊቷ ሪሃና “ፌንቲ ቢዩቲ” እና “ሳቬጅ ኤክስ ፌንቲ”ን ጨምሮ በፌንቲ የንግድ ምልክት ስር ባቋቋመቻቸው የተለያዩ የንግድ ኩባንያዎች ትርፋማ ስራዎችን ስታከናውን እንደቆየችም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 1514 times