Saturday, 19 January 2019 00:00

“የጥምቀት በዓል አከባበር በኢትዮጵያ……..”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

በኢትዮጵያ አመታትን ጠብቀው የሚከበሩ ሀይማኖታዊ በዓላት ከእምነት ፋይዳቸው ባለፈ በውስጣቸው በያዙት መስህባዊ ተፈጥሮ ምክንያት በርካት የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ይስባሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ደግሞ የጥምቀት በዓል ነው። የስነ መለኮት ምሁራን ጥምቀት ለሚለው ቃል መነከር፣ መታጠብ፣ መረጨትና  የመሳሰሉትን ትርጓሜዎች ይሰጡታል፡፡ የጥምቀት ዋዜማ ከተራ ይባላል፡፡ የከተራ እለት /ጥር 10 ማለት ነው/ ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ በሚሰማው የደውል ጥሪ ታቦታቱ፤ የተለያዩ ህብረ ቀለማት ያላቸው አልባሳት በለበሱ ህዝበ ክርስቲያን ታጅበው ጉዞአቸውን ወደ ጥምቀተ ባህር ያደርጋሉ፡፡
በሀገራችን ታቦት ተሸክሞ፣ ወንዝ ወርዶ የክርስቶስን በዓለ ጥምቀት ማክበር የተጀመረው በአፄ ገብረመስቀል ዘመነ መንግስት እንደሆነ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ ይህንን ታሪክ በመከተል አፄ ነዖድም (1486 – 1500 ዓ.ም) ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ሁሉ ታቦተ ህጉ ወደ ጥምቀተ – ባህሩ በሚወርድበት ጊዜ እና ከጥምቀተ – ባህሩ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ መውረድና መመለስ እንዳለበት አዋጅ አስነግረው ነበር፡፡ በአዋጁ መሰረትም ህዝቡ በየአመቱ ታቦተ ህጉን በማጀብ ወንዶች በጭፈራና በሆታ፣ ሴቶች ደግሞ በእልልታ ሲያከብሩ ኖረዋል ፤ አሁንም እያከበሩት ይገኛል፡፡
በከተራው ዕለት ድንኳን ተተክሎ፣ ዳሱ ተጥሎና ውኃው ተከትሮ ሁሉም ነገር ከተስተካከለ በኋላ፤ ታቦተ ህጉ የሚንቀሳቀስበት ሰዓት ሲደርስ የየቤተ መቅደሱ ታቦታት በወርቅና በብር መጎናፀፊያ እየተሸፈኑ፤ በተለያየ ህብር በተሸለሙ የክህነተ አልባሳት በደመቁ ካህናትና የመፆር መስቀል በያዙ ዲያቆናት ከብረው፣ ከቤተ መቅደስ ወደ አብሕርት /መጥማቃት/ ለመሄድ ሲነሱ መላው አብያተ ክርስቲያናት የደውል ድምፅ ያሰማሉ፡፡ ምዕመናንም ከልጅ እስከ አዋቂ በአፀደ ቤተ ክርስቲያን እና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ እንደሚባለው ያማረ ልብሳቸውን ለብሰው በዓሉን ያደምቃሉ፡፡
ታቦታት ከቤተ መቅደሳቸው ወጥተው በህዘበ – ክርስቲያኑ ታጅበው ማደሪያ ቦታቸው ይደርሳሉ። በዚያን ጊዜ ዳቆናትና ቀሳውስት በባህረ ጥምቀቱ ዙሪያ ሆነው ከብር የተሰሩ መቋሚያና ፅናፅን እንዲሁም ከበሮ ይዘው በነጫጭና በወርቅ ቀለም ባሸበረቁ እጥፍ ድርብ አልባሳት አምረውና ተውበው፤ የክርስቶስን የጥምቀት ታሪክ የሚያወሱ ወረብና መዝሙሮችን ጣዕም ባለው ዜማ ያቀርባሉ። ሌሊቱን ስብሀተ – እግዚአብሔር ሲደርስ አድሮ ከዚያም ስርዓተ ቅዳሴው ይፈፀማል፡፡ በወንዙ /በግድቡ/ ዳር ፀሎተ- አኩቴት ተደርሶ 4ቱ ወንጌላት ከተነበቡ በኋላ ባህረ ጥምቀቱ በብፁዓን አባቶች ተባርኮ ለተሰበሰበው ህዝበ – ክርስቲያን ይረጫል፡፡ ለዚህ በዓል ህዝበ ክርስቲያኑ ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ ምክንያቱም በዓሉ እየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ የተጠመቀበትን ተምሳሌት በማሰብ ስለሚከበር፡፡
የጥምቀት በዓል ሀይማኖታዊ ስርዓቱን ከባህላዊ ወግና ስርዓት ጋር አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ በዚህም በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ህብረ – ቀለማዊ የሆነ ጨዋታቸውን በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ያቀርባሉ፡፡ በዓሉን ለማክበር ወደ ጥምቀተ ባህር የሚሄዱ ሰዎች ከበዓሉ በፊት ተዋወቁም አልተዋወቁም በዚያን ዕለት በጋራ ሆነው ጥዑም ዜማዎችን ያንቆረቁራሉ፡፡ ይህ ዕለት ማንም ሰው ሳያፍርና ሳይሸማቀቅ የውስጡን የሚገልፅበትና በጋራ የሚጫወትበት ዕለት ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በጓደኝነት ለመተጫጨት ለሚፈልጉ ወጣቶች መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡ ህዝበ – ክርስቲያኑ ይህንን በዓል ዘርና ቀለም ሳይለዩ በአንድነት ያከብሩታል፡፡ በመሆኑም በዓሉ ህዝብን ያቀራርባል፤ የመረዳዳት ባህልንም ያሳድጋል፡፡
የጥምቀት በዓልን ለማክበር የተለያዩ ሀገር ዜጎች፣ ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮችና ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም የቤተክርስቲያን አባቶችና ምዕመናን ይታደማሉ፡፡ ይህ በዓል በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚከበር ቢሆንም በተለይ በአፄ ፋሲል መዋኛ፣ በላልይበላ፣ በመቀሌ ፣ በአክሱምና በአዲስ አበባ ከተሞች በተዘጋጀላቸው የክብር ቦታ ህዝበ – ክርስቲያኑ ከውጪ ከሚመጡ ቱሪስቶች ጋር በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ያከብሩታል፡፡ ታዲያ በዚህ በዓል ላይ ያስገረማቸውን ነገር በማስታወሻነት ለማስቀመጥ የተለያዩ ሰዎች የፎቶና የቪዲዮ ካሜራዎቻቸውን ደግነው እያነሱና እየቀረፁ ያስቀራሉ፡፡  በመጨረሻም በሀገራችን የሚከበሩ ሀይማኖታዊ በዓላት የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህልን ያዳብራሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር አገሪቱ ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው ተጠቃሚ እንድትሆን ያስችሏታል፡፡ ስለዚህ ተገቢውን ትኩረት ልንሰጣቸው ይገባል፡፡
(ከተስፋዬ አበበ ፌስቡክ የተወሰደ)

Read 5518 times