Saturday, 19 January 2019 00:00

ዳግማዊ ቴዎድሮስ - የኢንዱስትሪዉ አብዮት ዘመነኛ

Written by  ቴዎድሮስ ዘርፉ
Rate this item
(0 votes)

  መግቢያ
አጤ ቴዎድሮስ ከዛሬ ሁለት መቶ ዓመት በፊት በበጌምድር አውራጃ በጎንደር አቅራቢያ በምትገኝ ዳዋ በተባለች ሰፈር ከእናቱ ከወ/ሮ አትጠገብና ከአባቱ ኃይሉ ወልደ ማርያም፣ በ1811 ዓ.ም  ጥር 6 ቀን ተወልዶ፣ ስርዓተ ክርስትናው በአብየ እግዚእ ቤተ-ክርስቲያን ከተከናወነ በኋላ የክርስትና ስሙ  ገብረ ኪዳን ተብሏል፡፡ አጤ ቴዎድሮስ በተወለደና ባደገበት ወቅት ኢትዮጵያ በመሳፍንትና በጉልበተኞች ቅርጫ ወድቃ ነበር፡፡ ይህንን የተመለከተው ልጅ ካሳ፤ ሀያሏን ኢትዮጵያ አለመ፤ እንደመሻቱም ሆነለት። ለዚህ ይመስለኛል ፕ/ር ባህሩ ዘውዴ፤ በዘመነ መሳፍንት ተወልዶ በዘመነ መሳፍንት ማርከሻ  ኮሶ የሆነ የሚሉት፡፡ አጤ ቴዎድሮስ የዘመኑ መሳፍንትን ተፈፃሚነት ቀብር ካረጋገጠ በኋላ ከፊት ለፊቱ የሚጠብቀውን የመዘመን ጥያቄ ለመመለስ በእጅጉ ደክሟል፤ ያሳካቸውም ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ትምህርት ቤት (የእጅ ሙያ) መክፈት፣  የጦር ሰራዊቱን ዘመናዊ ማድረግ፣  መድፍ፣ መኪናና ጋሪ፣ መርከብ (የጦር ሀይል ማቋቋም)፣ መንገድ የመሳሰሉትን-- ጋፋት የምትባል የመጀመሪያዋን የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ከተማ በማደራጀት የተሳካለት ሊባል የሚችል ስራ ሰርቷል፡፡ ለዚህም ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመነኛ እለዋለሁ። በጠቅላላው አጤ ቴዎድሮስ ሁለት ግቦች ነበሩት፤ እነርሱም- ውህደትና ዝመና፡፡
ቀዳሚ ግብ፡- ውህደት
ከተፈፃሜተ መንግስት ተክለ ጊዮርጊስ እስከ ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ መነሳት መካከል የነበሩት ዘመናት፤ መሳፍንቱና መኳንንቱ እንደየ ጉልበታቸው መጠን ሲያስገብሩና ሲገብሩ የነበረበት ዘመን እንደ መሆኑ መጠን የዘውዱ ክብር ተዋዶ፣ መሳፍንቱ ያሻቸውን የሚያነግሱበትና ያሻቸውን ወህኒ አምባ በሚልኩበት በዚያን ወቅት የሀገሪቱ ሀገርነት እንኳን ጥያቄ ውስጥ በገባበት፤ የግል ድሎትና ምቾት መኳንንቱንና መሳፍንቱን አቅል በነሳበት፣ በመሳፍንቱ የፌሽታ ዘመን፣ ቴዎድሮስ የሚሆን ህፃን በጎንደር ተወልዷል፡፡ በአውሮፓ የአጤ ቴዎድሮስ ዘመነኛ (Contemporary) የነበረው አቶቫን ቢስማርክ፣ ጀርመንን ለማዋሀድ በተነሳበት በዚያን ዘመን፣ የጀርመን ጥያቄ ይላል ቢስማርክ፣ የሚመለሰው በአውጫጭኝ ጭብጨባ (majority vote ) እና በርዕቱ እንደበት (by speach) አይደለም፡፡ ጥያቄው የሚመለሰው በደም (blood)  እና በጠመንጃ (iron) ነው፡፡ በማለት ነበር የፐርሽያን ፓርላማ (Prussian legislative) ቁርጡን ያሳወቀው፡፡ ለዚህም ነበር ቴዎድሮስ የዘመነ መሳፍንት ማርከሻው ኮሶ፣ አምቻና ጋብቻ አይደለም በማለት ድንጋይ ትራሴ ቅጠል ቁርሴ ብሎ ወደ ቋራ በርሃ የሸፈተው፡፡
ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ እንዲል ማቴ 21፡42 ፍየል ጠባቂ ቆለኛ፤የኮሶ ሻጭ ልጅ ሙጭልጭልላ  እያሉ በጦር ብዛታቸው የተዘባነኑትን መሳፍንት በሙሉ ያለ አንዳች ሽንፈት አንበረከካቸው፤ የዘውዱንም ክብር ወደ ነበረ ቦታው መለሰው፡፡
ካልዕ ግብ፡- ዝመና
አጤ ቴዎድሮስ በተዋሀዳቸው ሀገር ላይ ዋናው አላማቸው ስርዓት መትከል ነበር፡፡ (ይህ የሥርዓት ጉዳይ በኋላ በ20ኛው መጀመሪያ የተነሱት ልኂቃን ዋነኛ ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል) አጤ ቴዎድሮስ ስርዓትን ለማፅናትም የተለያዩ አዋጆችን አናግዋል፡፡ የዝመናውን አይነትም ቁሳዊና መንፈሳዊ ብለን ልንከፍለው እንችላለን፡፡ አጤ ቴዎድሮስ መንፈሳዊውን ዝመና ለማጣትና ማህበረሰቡ ከወደቀበት የግብረ-ገብ መላሸቅ ለመታደግ የተለያዩ መንግስታዊ ስርዓትን ፈጥረዋል፡፡ ተቀዳሚው በአርያ ስላሴ የተፈጠረን ሰው ባሪያ ብለህ የምትሸጥና የምትገዛ ተውኝ፣ የገዛህም የገንዘብህ ባለዕዳ እኔ ነኝና ነፃ ልቀቅ፡፡ እያለ የባሪያን ንግድ በማስቆም  የጀመረው አጤው፤ በሁለተኛ ደረጃ የተቃወመው ከአንድ በላይ ሚስት ውሽማና ቅምጥ በሚል እርስ በእርስ ይደዳሩበት የነበረውን (polygamy) ስርዓት ነበር፡፡
ሌላኛው ለኋላ ውድቀት ምክንያት ጉድጓድ የቆፈረለትንና ነገር ግን አሁንም ድረስ ቤተ-ክህነት እየተጠቀመችበት ያለውን ስርዓት ተከለ፡፡ ይህም በአንድ ደብር አምስት ወይም ሰባት ሰሞነኛ በቂ ነው ብሎ አዋጅ አስነገረ፡፡ ቀሳውስቱ በአዛዥ በጎዝጎዥ፣በቄስ በገበዝ የያዙትን መሬት ለቀው ወደ ስራ እንዲሰማሩ አዘዘ፡፡
የአጤ ቴዎድሮስ የቁስ ዝመና ተቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው የጦር ኃይሉን የደመወዝ ተከፋይ ከማድረግ በዘለለ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ ማድረግ ነበር፡፡ ስለዚህም ተልዕኳቸው ከባህር ማዶ ተሻግረው የመጡትን ሰላዮችና ተጓዦች በሙሉ የጋፋት ልጆች በማለት በመቅደላ አቅራቢያ በምትገኝ ጋፋት በተባለች ሰፈር የመጀመሪያውን የኢንዱስትሪ ከተማ መሰረቱ፡፡ የዚህችም ከተማ የስራ ውጤት የሆነውን መድፍ፣ አለቃ ተክለ እየሱስ ዋቅጅራ እንዲህ ይገልጹታል፡-
አጤ ቴዎድሮስ ያማቱን ሀዘን ጨርሶ ጎራድ ጥድ ላይ ሰፈረ፡፡ ቦቦ የሚባል ትልቅ መድፍ አሰርቶ ነበር፤ መድፉም አፈ ሰፊ ሰው ገብቶ የሚጠርገው ነበር። ሰሪዎቹ እንግሊዞች ናቸው፡፡ ሌላም ፈረንጆች እነ ዋልት ማየር ነበሩ፡፡ መድፉ የተሰራው ከጎንደር በተዘረፈ ንዋየ ቅድሳት ነቅሰ ባለው መስቀልና ቃጭል በብረት ናስ ነው፡፡
መድፍም ባለ መንኮራኩር በአቀበት የሚሳብ፣ በቁልቁለት የሚገታ የዝሃ ጀመሬ ገመድ የሚይዘው %% ሰው ነበረው፡፡ ያን ጊዜ የጨጨሆን በር በዲናሚት ደንጋውን እየፈለጠ ደልድሎ መድፉን መቅደላ ሰደደው (ሰርገው ገላው፤ ገፅ 230 ተመልከት) ከአለቃ ተክለየሱስ ፅሁፍ እንደምንረዳው፤ መድፉን ከማሰራታቸው ባሻገር ለመድፉ መጓጓዣ መንገድ ማሰራታቸውን ነው። ከዚህም በፊት መናገሻ ከተማቸው ደብረታቦርን ከጎንደር፤ ከጎጃምና ከመቅደላ ጋር በአውራ ጎዳና ለማገናኘት ጀምረው ነበር፡፡ በተያያዥነትም በዚያን ወቅት ሳል ሙለር የሚያሰራውን የቤተ ሐራን መንገድ ሊጎበኙለት ሔዱ፤ ከዚያም እንደደረሱ ሳልሙለር የሚረዳኝ አጥቼ ብቻየን ሆንኩ ብለው ለአጤ ቴዎድሮስ አመለከቱ፣ ይህን የሰሙት አጤ ቴዎድሮስ በጣም ተቆጥተው፣ ይህ ከሩቅ አገር መጥቶ ሲሰራ ያገሬ ሰው እንቢ ሊል ብለው የዋድለውን ምሳለኔ ይመር ጎዳና የተባሉትን ገርፈው አሰሉት፡፡ (አለቃ ዘነብን ተመልከት)
በጣም የሚገርመው በዚሁ ወቅት ለሳል ሙለር የራሳቸውን በቅሎ መሸለማቸውና የጨጨሆን መንገድ ለሚሰራው ለፍላድ 300 ብር መስጠታቸው ለዝመና ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር በደብዳቤያቸውም እንደሚሉት፤ ሰለሞን በኪራም ጫማ እንደ ወደቀ እኔም ጥበብን በመሻት እግርዎ ጫማ እወድቃለሁ (ለቪክቶሪያ) እያሉ የሚገልፁት በመሆኑ አይደንቅም፤ አንገብጋቢው ጥያቄና አስገራሚው ነገር በዚህ መንገድ የሚነዳው ከብት ወይስ ጋሪና መኪና? ጳውሎስ እንዲህ ይለናል፤ ሚሲዮናውያኖቹ መንገድ ከመስራታቸው ሌላ ባሰሩት መንገድ እቃ የሚያመላልስ ጋሪም ሰርተው ነበር፡፡ (አጤ ቴዎድሮስ ገፅ 170 ተመልከት)
ሌላኛው የአጤ ቴዎድሮስ ቁሳዊ ዝመና የመርከብ ስራ ነበር፡፡ በወቅቱ ከሆምሩዝ ራስም ጋር አብሮ የመጣው ሄነሪ ብላንክ (ዶ/ር) ስለዚህ ጉዳይ ሲያብራራ፤ እንዲያውም ፓድል እስቲመር ፈልስፈው ሰርተው ነበር፡፡ ዳሩ ግን ሎኮሞቲቭ ሳይሰራ ቀረ፤ ጀልባዋን የሚያንቀሳቅሰው ሁለት መንኮራኩር በጣም ትልቅ ስለነበር ወደ ውሃው ውስጥ ጠልቆ እንዲገባ ለማድረግ በመቶ የሚቆጠር ሰው ያስፈልግ ነበር (ዳኛው ወልደ ስላሴን ትርጉም እስራት በሀበሻ ምድር ተመልከት) በማለት ያብራራልንን ሆምሩዝ ራሳም፤ ሁለቱ መርከቦች ከተሞከሩ በኋላ የባህር ኃይል እንዲያቋቁሙለት እንደጠየቁት በማስታወሻው ገልፆአል፡፡
የአጤ ቴዎድሮስ የዝመና አቀባበል translational adoption (ሀገርኛ ወይም ሀገር በቀል አድርጎ መቀበል) እንደነበር ፋንታሁን አየለ (ዶ/ር) revisiting the history gafat በሚል ጥናቱ አመላክቶናል፤ስለሆነም መደምደሚያችን የሚሆነው የ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ሊቅ በሆነው በአንዱ በነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ይሆናል፡፡
“የአጤ ቴዎድሮስ ሀሳብ ግን አልተፈፀመም እንጅ አልሞተም፤ አባ ታጠቅ ለራሱ ቢከፋው የማይረሳውን ስም ተክሎ ሞተ፤ እውነት ነው የመነኮሳቱ ሀይል ገና አላላችም፤ ሹሞቹም ብርቱ ተቆጣጣሪ ገና አልወጣላቸውም፤ እስካሁን ድረስ የተሸሙበትን በገንዘባቸው እንደገዙት ርስት ያዩታል።” (አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ ገፅ 13 ተመልከት)
(200ኛ ዓመት የልደት በዓሉን በማስመልከት የቀረበ ፅሁፍ)

Read 192 times