Saturday, 19 January 2019 00:00

ነቢይ ፍለጋ

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(5 votes)


     አዎን!
ትልቅ ሕዝብ ‹‹ነበርን››!!!
‹‹መቸስ ምን እንላለን›› . . .
በተለዋዋጭ መልኳ በተፈጥሮ ህግ ተገድበን
ከእጃችን ያመለጠችውን አዱኛ ወረት ታዝበን
ከነግ ተስፋ መድረስ ጓጉተን እየቋጨን የጥንቱን
ዘመን
ኗሪውን ማእዘን ሳንሰለች በጽናት ዛሬ እንፈልጋለን
መቸስ ምን እንላለን  . . .
ሳይንስ፤ ሕይወት ከሦስት ቢሊዮን አመታት በፊት በውኃ ውስጥ ተጀመረ ይለናል፡፡ ምድር ከተመሰረተች 4.5 ቢሊዮን አመታት ነው የሚሉት የሳይንስ ምሁራኑ፤ ቀደምቶቹ ህያው ክስተትም፣ ራሳቸውን የማባዛት ተፈጥሮ የነበራቸው ቅንጣቶች (Molecules) ቆይተው ወደ ረቂቃን ነፍሳት (Bacteria)፤ ከዚያም ከዛሬ 1 ቢሊዮን አመታት በፊት ዘር (nucleus) ወደ ቋጠረ ህዋስነት ደረሱ። በባክቴሪያነትና በጥንታዊው አልጌነት እርስ በርስ እየተቆራኙ ባለ ብዙ ህዋስ ቅርጾችን ፈጠሩ፤ ከዚያም  ወደ የውሀም የብስም ፍጥረት (amphibians) ወደነ እንቁራሪትነት ደረሱ፡፡ በደረቁ የብስ ላይ ከራርመው ደግሞ ወደ ተሳቢ ፍጥረትነት (reptiles) መለወጡን ተያያዙት፡፡ ከጥቂት ሚሊዮን (‹‹ጥቂት - ሚሊዮን!››) ዓመታት በኋላም አጥቢ ፍጡራን ሆኑ፡፡ አጥቢዎቹ ከዛሬ 30 ሚሊዮን አመት ጀምሮ በምድር ዙሪያ ተስፋፉ፡፡ በቺፓንዚና ጉሬላነት አልፈው መጡ የሚባሉቱ ጥንታዊያኑ የኛዎቹ ምንጅላቶች የሆኑት ቀደምት የሰው ዘሮች (Hominids) 15 ሚሊዮን አመታት በፊት፡፡ ድንቅነሽ (ሉሲ) እና የሷ ዝርያዎች በአድማሱ ጫፍ ብቅ ብለው የታዩት በጣም አርፍደው የዛሬ 4 ሚሊዮን  አመት ገደማ፤ ዘመናዊው የሰው ልጅ አንድ ሚሊዮን አመት ይላሉ። ምንም እንኳ ‹‹የሰውን ዘር ከጥንታዊ ማንነቱ የሚያስተሳስረው ሰንሰለት›› የሚሉት ጉዳይ ጥርት ያለ ሀቁ ከራሳቸው ከተመራማሪዎቹም ቋጠሮ ውሉ ገና የተሰወረ  መሆኑና ዛሬም ድረስ ፍለጋው መቀጠሉ እሙን ቢሆንም (THE MISSING LINK - IT IS STILL MISSING!)  የዝግመተ ለውጡን Evolution ሂደት መቋጫ፤ የሰው ዘርን መነሻ አፋር (አፍሪቃ) ሀዳር ሸለቆ ያደርሱታል - ከእኛዋ ኢትዮጵያ ምድር፡፡የጉዲፈቻ መጠሪያዋን በቢትልስ ዜማ እየተውረገረጉ ሰይመውልን . . . ‘’Lucy on the sky with diamonds.’’
ከሳይንስም ማጀት ጦጣና ዝንጀሮም ሰብዕ
ከሆኑበት
ከተሸራረፉት የጠጠሮች ቅንጣት ሉሲ ቅልልቦሽ
ካጫወተችበት
እንፈልገው እስቲ
የጥንቱ ልዕልና የመሸገበትን ያን የከበረ አለት . . .
ታሪክ፤ የሰው ልጅ፡ ከተፈጥሮ ጋር ከነበረውና ካለው ጥብቅ ቁርኝት በመነሳት የዙሪያውን ጸጋ የሚቸረውን አንድ ልዩ ኃይል ለማወቅ ጥረት ማድረግ መጀመሩን ይተረክልናል፡፡ እናም፤ እንደ ሳይንሱ ሁሉ የኃይማኖታዊው ዝግመተ ለውጥ (Religious Evolution) በበኩሉ፤ አምላክ ራሱን የሚገልጥባቸው መንገድ ነው ከሚል እምነት (Natural Theology) የሰው ልጅ ባካባቢው ላሉት ነገሮች ለእያንዳንዳቸው የራሳቸውን አምላክ እየሰየመ መኖር ሲቀጥል ያሳየናል፡፡ ይህ አይነቱ እሳቤ ዛሬም በምንኖርበት አለም በሚከናወኑ አንዳንድ ኃይማኖታዊ ስርአቶች የቀጠለ ቢሆንም፤ በቅድመ ጅማሮው የአማልእክት አይነቶችን በየደርዙ አሰባጥረው በማደራጀት በታሪክ ጎልተው የሚጠቀሱቱ ሳምራዊያን ህዝቦች ናቸው። እነርሱን ተከትለው ባቢሎናዊያን፣ አሶራዊያን፣ ከዚያም ሜሶፖታማዊያን፣ ከነአናዊያን፣ ግብጻዊያን ... ሌሎችም ይቀጥላሉ ... የውኃ አምላክ፣ የጦርነት አምላክ፡፡ የዘር መቀጠል፣ የአዝመራ ልምላሜ፣ የፀሐይ አምላክ ... ወዘተ እያሉ፡፡ አሁንም ታዲያ አንዳንድ የታሪክ ምሁራን በተለያዩ የታሪክ ዘመናት ኢትዮጵያዊያን ግብጽን፣ ግብጾችም ኢትዮጵያን መግዛታቸውን በመጠቆምና እንደ ፒያንኪ፣ ታርሐቃና ሻ ባካ፣ ሻባቶ ካ መሰል የግብጽ 25ኛ ሥርወ መንግሥት ገዢዎች ጥቁር ፈርዖኖች እንደነበሩ፣ አንዳንዱም ተመራማሪዎች የፈርዖኖችን ረዣዥም የአገጭ ጢም ከኢትዮጵያዊያን ሕዝቦች የኦሮሞ ጢም አስተዳደግ የተወረሰ መሆኑን በማመላከትም ይሞግታሉ፡፡ የጥንቱ የሰውና አምላክ በከባቢ ተፈጥሮ ቁርኝት ውስጥ መገለጥን ማመንም፣ አሻራው በመደብዘዝ ላይ ቢገኝም፣ እኛም ዘንድ መኖሩንም እንዲሁ ይጠቁማሉ፡፡ የዚሁ የተፈጥሮ (ባለቤቱ) ህልውና በሰፊው ህዋ ውስጥ ግዘፍ ነስቶ የመገለጡ ማሳያ ምልክቶች (Manifestation of a self-existing universe) ‹‹አምላክ በሁሉም አለ፤ ሁሉምም አምላክ ነው›› (Pantheism?) ማሳያም  ቀስ በቀስ እየደበዘዘ ቢሄድም በኢትዮጵያዊያን ሕዝቦች ነባር፣ ሀገር በቀል ባህላዊ ...እምነቶች ውስጥ ዛሬም ድረስ  አለ ይላሉ፡፡ የአምላከ አማልእክቱ ወኪሎች፤ የቀዬው ጠባቂ፣ የልምላሜና የመራባት አማልእክቷ፣ ልጆችን ሰጪዋ፣ ለሰብል፣ ለከብቶች፣ ለሀብት፣ ለጦርነት . . .ወዘተ፡፡

አፈር ድሜ የቃመ ከወርቅ ዕንቁ የከበረ የተተወ
ብረት እንደተቀበረ
ለረመጡ ጠኔ ‹‹አግሉኝ? አቅልጡኝ?
ቀጥቅጡኝ?›› እያለ
ተከብሮ በኖረ በአፍቃሬ መዶሻ ጡሩር ከታጠረ
ከጥንቱ የጸጋና የጦር አማልዕክቱ ከሣ-ራ ፡ አቴን
፡ አሽታር
ምድረ ልዕልና ፡ ዘርፈ ብልጽግና ግብሩ ያልቀጠለ
ያም ይሁን ይኼ መልክ ብቻ ትናንት አለ . . .

ምሁራን፤ ‹‹የሰው ልጅ የነገረ ፍጥረትና የነገረ ህላዌ እንቆቅልሾችን (cosmological and ontological questions) ለመመለስ የሞከረበት፡ እየተመሰቃቀለ ለሚያስቸግረው ዓለም ህልው ሥርዓት (cosmic order) ለማበጀት የባተለበት እምነታዊና ፍልስፍናዊ ጥበብ ነው፡፡›› በሚሉት (Mythology) ውስጥ፤የሰው ልጅ በፈጠራቸው መናፍስትና አማልእክቱ ያለው የእምነት መልክ በተከተቡባቸው ድርሣናቸው ከሚታወቁት (GREEK GODS, ROMAN GODS, INDIAN GODS, EGYPTIAN GODS  . . . ወዘተ) ጥቂት የዓለም ሀገራት መካከል ለመቆም የሚያስችለንን የራሳችንን ነባርና ሀገር በቀል ጥንታዊ እምነቶች ጽፈንና በወጉ አደራጅተን ለማስቀመጥ ያልታደልን መሆናችን የታሪካችን አንዱ አሳዛኝ ገጽታ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከብሉይና ባመዛኙ ከክርስትናና እስልምና ኃይማኖታዊ ገድልና ከነገሥታቱ ዜና መዋዕል ጋር አስታክከንም ቢሆን ታሪካችንን መመዝገብ የጀመርነው ከረዥም ዘመናት ታሪካችን አኳያ እጅግ በጣም ዘግይተን ነበርና፡፡ የታሪካችንን ዳና ፍለጋ ዛሬም የምእራቡን ዓለም መዛግብት ደጅ መጥናት የማይቀርልን ነንና። እነርሱው መልሰው ለኛው Geez is the future  እንዳሉን ሰሞኑን፡፡

እንፈልግ ካልን የወል አቁማዳ አዝለን ጉዞ
ሳናናጥብ
ዘመናችን መሀል ጎልታ እምትታይ የብርሃን
እንጎቻ
ጽልመት ጠል ጮራ ሰናፍጭ ታህል ቅጥብ
ለዘር የተረፈች ቀቢፀ ተስፋችን ላይ ፀዳል
እምታሽት ተስፋን እምትቋጥር
ያቻምናን ውብ ዘመን የፀሐይ ገበታ እፍኝ እርሾ
ቁንጥር፤
እነሆ እንቀጥል . . .

‹‹ጥንታዊ ስልጣኔ ከኢትዮጵያ ወደ ግብጽ - ባቢሎን - ግሪክ - ሮም ከዚያም ወደ ተቀረው የምዕራቡ አለም ተዳረሰ›› የሚሉ ቢኖሩም፤ ግሪካዊያን የዓለምን ታሪክ ለመጻፍና ለመደጎስ በቀደምትነት ሲጠቀሱ ይኖራሉ፡፡ ከዚያም ጋር ዘወትር አብረው የሚነሱት የጥንቱ ዓለም የታሪክ አባት የሚሰኘው ግሪካዊው ሔሮዶቱስና ባለቅኔው አይነስውሩ ሆሜር እንዲሁም ሌሎችም በርካታ የጥንቱ አለም የታሪክ ጸሐፍት ስለ ኢትዮጵያ ምድራዊ ልምላሜ፣ ስለ ሕዝቦቿ እውቀትና ውበት በተለይም ‹‹በባህርያቸው እንደ እግዚአብሔር ናቸው›› አይነት ላቅ ያለ ውዳሴያቸውን አዝንበዋል። እናም ግሪካዊያን ከሁሉ በተሻለ ደረጃ የጥንቱን አለም ታሪክ በፔሪፒለስ (በእኛው ብራና እና በግብጻዊያኑ ፓፒረስ አይነት) ጥቅልል ላይ ሲከትቡ በመኖራቸው፤ ከራሳቸው አልፎ ለመላው ምድርና ለሰው ልጅ ሁሉ ተርፈዋል፡፡ ከኒሁም መካከል፡- በግሪክ የአማልእክት ድርሳን (ሜቶሎጂ) የአማልእክቱ ሁሉ ፈላጭ ቆራጭ ገዢ ሆኖ የተሳለው አምላከ፣ አማልእክቱ ዜዩስ ጥልቅ አርምሞ እናም ፈንጠዝያ ሲሻ (‹‹ነቢይ ፍለጋ?››) ከኦሊምፐስ ተራራ እየከነፈ አሽከሮቹን አስከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ምድር ይመጣና በተትረፈረፈው የኢትዮጵያዊያን ነፃ ጥንታዊ ማዕድ ‹‹የፀሐይ ገበታ›› ግብዣና ፌሽታ በሀሴት ሰክሮ፣ በጥቁሩ ልእለ ሰብእ በኤዞፕ ጣፋጭ ወጎች በእጅጉ ይመሰጥ፡ በዜማው ዳንኪራ ይቦርቅ ነበር ሲሉም አስፍረዋል፤ የታሪክ ጸሐፍቱ፡፡ የኛውን የታሪክና ኪነ ጥበባት ሊቅ ጉምቱውን ኢትዮጵያዊ ባለቅኔ ጸጋዬ ገብረመድኅንን AETHOP ግጥም ያስታውሷል፡፡ እግረ መንገድም ጥንታዊ ትውፊታችንን ከዛሬው ማንነታችን እያሰናሰለ ያጠየቀው ‹‹የኤዞፕ ምድር›› ድራማም በዚሁ ተራኪ ግጥም ንሻጤ የተጻፈ መሆኑን እዚህ መጥቀስ ግድ ይላል፡፡ . . . Come! Rise ... your poet for tomorrow’s resurrection of new constellation እንዳለውም ምናልባት። ኤዞፕ ለረዥም ዘመናት በአለም ዙሪያ በስፋት የሚታወቀው በግሪካዊነቱ እንጂ በኢትዮጵያዊ ዜግነቱ አለመሆኑንም እንዲሁ በቁጭት ማስታወስ የሚያሻን ይመስላል፡፡... ‹‹ነቢይ ባገሩ...›› የታከተ ተረታችንን እየጠረቅን እና በ‹‹እንትን›› እያወራረድን።
‹‹በእንግዳ ተቀባይ የካቻምና ማጀት የፀሐይ
ገበታ ምድርን ባጠገበ
የሰው ዘርን ቀርቶ አማልእክት ባስጠለለ
ሆሜር፤ ሄሮዱተስ፡ ዳዮደረስ . . .ወዘተ
ወዘተ ወዘተ . . . ›› የታሪክ ሊቃውንት ፡ ጸሐፍቱን
ባስደመመ
ዝናው በገነነ፤
አዎን ትልቅ ነበርን . . .
        
አልፎ አልፎ የሚታየውን የሳምራዊያንን የእምነት ፍንጥቅጣቂዎች ከብሉይ ኪዳን ድርሣናቸው ውስጥ ፍጹም ማስቀረት ባይችሉም፤ የአምላክ ህልውና ከተፈጥሮ መሳ የተሰፋበትን ነባር እምነት በመተው፤ በነገረ ፍጥረት (Creation) አንድምታ አምላክን ፈጣሪ፣ ተፈጥሮንና ፍጥረትን ተፈጣሪ አድርገው የማመን ኃይማኖታዊ ስርአትን (Biblical Theology) የጀመሩት ደግሞ እብራዊያን ሕዝቦች  ነበሩ፡፡ ታዲያ በዚሁም የስነ ፍጥረት የታሪክ ድርሣን ውስጥ ገና በብሉይ ኪዳን ሁለተኛ ምእራፍ ላይ፤ እግዚአብሔር በመልኩና በአምሳሉ የፈጠራቸው አዳምና ሄዋን፤ በገነት መካከል ካለው ዛፍ እንዳይበሉ የተከለከሉትን የእፀ በለስ ፍሬ በልተው ወደ ምድር እስኪባረሩ ድረስ፤ ይኖሩበት ዘንድ የሰጣቸውን ኤደን ገነትን እንዲያጠጡ ካፈለቃቸው አራት ወንዞች፣ የሁለተኛውን ወንዝ መገኛ የኛኑ ሀገር ያደርጋታል፡፡ ‹‹ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር፤ ከዚያም ለአራት ክፍል ይከፈል ነበር። የአንደኛው ወንዝ ስም ፊሶን ነው እርሱም ወርቅ የሚገኝበትን የኤውላጥ ምድርን ይከብባል፤ የዚያም ምድር ወርቅ ጥሩ ነው፤ከዚያም ሉልና የከበረ ድንጋይ ይገኛል። የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል።›› (ኦሪት ዘፍጥረት 2፤ 10-13)
ከአባታችን አዳም፤ እፍ የተባለበት የአምላክ
እስትንፋስ
እሣት፡ ውሃ፡ ነፋስ ፡ አፈሩ ገላችን ከተዘገነበት
ከምስራቅ ኤድን አጸድ ገነት ዛፍ ጥላ ስር
በግዮን ወንዝ ዳር ስትወናኝ ሄዋን ቁጢጥ
ካለችበት፤

በአንድ አምላክ ብቻ ማመንን ተከትሎ፤ ከኖኅ ልጆች መካከል ከካም ዘር በኩሽ ነገድ የሚቀጥለውን ትስስር ለጥቁር ሕዝብ ሰፊ ግዛትና የረዥም ዘመናት ገናና ስልጣን መነሻነት (ዘፍ. 10፡6 የካምም ልጆች ኩሽ፥ ምጽራይም፥ ፉጥ፥ ከነዓን ናቸው።) እያጣቀስን፤ እግዚአብሔር ሕዝቤ ብሎ በመረጠው ወገን በኩል ከሰው ልጆች ጋር ግንኙነት ማድረግ ሲጀምርና አብራምን ከኡር ምድር አውጥቶ የተስፋ ቃሉን ሲሰጠው፤ ከዚያም ቆይቶ እግዚአብሔር እስራኤል ብሎ የጠራው ያእቆብና ቤተሰቡ ከገጠማቸው የከፋ ድርቅ ለመጠለል መጥተው መኖር በጀመሩበትና በባርነት ከከረሙበት ምድር፤ ሙሴ እስራኤላዊያንን ከግብጽ ባርነት እንዲያወጣ እግዚአብሔር ሲገለጥለት እናስተውላለን፡፡ እግዚአብሔርም የተገለጠለትና (ዘጸአት 3፡5 ‹‹የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ››) ያለውና ሕዝቡን ከባርነት ነጻ ያወጣ ዘንድ ለነቢይነት እንዲነሳ ያዘዘውም እዚሁ ሀገራችን ኢትዮጵያ ምድር መሆኑን፡፡ በተለይም ሙሴ በምድያሙ ካህን በዮቶር ታዛ በስደት ተጠልሎ ኢትዮጵያዊቷን ሴት ልጁንም ሲፓራን አግብቶ ፍሬ ማፍራቱን እናነብባለን፡፡

ከተናቀው አፈር ከጠይባኑ አምባ ደምቢያ ጥዱ
ሞረት
ያልካስናት ሸክለኛ በእንባዋ አቡክታ ያገር ጥምን
መክያ ጋን ከምትሰራበት፤
ከሲጳራ ገንቦ አዝላው በጀርባዋ ውሃ ልትቀዳ
በወረደችበት
ከእንግዳው እብራዊ ከተያየችበት
ከተጫጨችበት፤
ከአማቹ ዮቶር ደጃፍ ከምድያም ምድር መልስ
ስደተኛው ነቢይ ሙሴ የአምላኩን ኪዳን
በግራር ሳንቃ እንጨት በወርቅ ለብጦ በክብር
ካኖረበት፤

ምንም እንኳ በሌላው አለም ክፍል ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች አንዳንድ የብሉይ መጽሐፍትንና ነቢያትን ላለመቀበል ወደ ኋላ ቢሉም፤ ኢትዮጵያ ግን ተሰውረው የኖሩ እንደ መጽሀፈ ሔኖክና ኩፋሌ ያሉ ቅዱሳን መጻሕፍትንም በምድሯ በማኖር ትታወቃለች፡፡ ኢትዮጵያ እግዚአብሔር መሻቱንና ትእዛዛቱን ለማስተላለፍ ይጠቀምባቸው በነበሩት በነቢያቱ አንደበትም በተደጋጋሚ ስትጠቀስ ትገኛለች፡፡ ሙሴ ሕዝቡን ወደ ከነአን ምድር ከመራ በኋላም ኢትዮጵያ በተለይም እግዚአብሔር ‹‹እንደ ልቤ›› ብሎ የጠራው ንጉሥ ዳዊት (ከክ.ልበ በ1ሺ1መቶ)  በመዝሙሩ (መዝ፤68፡31 ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።) ማለቱን ስናይ፤ ኢትዮጵያ በእግዚአብሔርን መንግሥት ያላትን የማያቋርጥ መለኮታዊ ጥሪ ያስታውቀናል። ከዳዊት በኋላ የነገሠውን ልጁን ንጉሥ ሰለሞንን የውድ ስጦታዎች ገጸ በረከት ይዛ ጥበቡን ለመቅሰም የጎበኘችው ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ መሆኗም እንዲሁ፡፡ (ስለዚሁ ጥንታዊ ታሪካዊ ገድል የኛው ሀገር በቀል ድርሣን በበኩሉ፤ ንግሥት ሳባ ንጉሥ ሰለሞንን ስትጎበኝም፤ እርሱ በትንቢት ይመጣል የተባለው መሢህ ስለመሆኑ ጠይቃው እንደነበረና አስቀድሞ የግብዣ ጥሪ ያቀረበላት፣ በታላቅ ክብር ተቀብሎ ያስተናገዳትና ‹እነሆ በረከቱንም› ጨምሮ በከፍተኛ ልግስናም የሸኛት ንጉሥ ሰለሞንም በምላሹ፤ እርሱ አለመሆኑንና መሲሁ ከድንግል ሴት በመንፈስ ቅዱስ ተጸንሶ እንደሚወለድ እንደነገራት ይተርክልናል፡፡) ይህም ኢትዮጵያዊያን የነቢያትን ትንቢት በተስፋ ይጠባበቁ እንደነበር አመላካች ነው። ‹‹የአንድን ሕዝብ ሥነ ጽሑፍ ንገረኝና ስለዚያ ሕዝብ ማንነት እነግርሀለሁ›› እንዲል ቻይናዊው ፈላስፋ ኮንፊዩሸስ፡፡

የተዳፈነው እሣት የተገፋው መዳፍ
‹‹ባላዋቂ የምላስ ቅርስ›› ተሳቅቆ እየኖረ፡
ክንዱን ጎምዶ አዳሜ አፉን እያሾለ
የተንጠራወዘ የነዳይ ዘምቢሉ የተወለወለ
ተጠዋሪ መልኩ በዘኬ ያማረ፡
የምንዱባን ሮሮ የኔ ቢጤ ዜማው እለት ተዕለት
ስር ሰድዶ
አድሮም ለተማጽኖ እየተንደባለለ  ባዕዳን እግር
ስር እየተንከባለለ
ለስንቱው መጤ ‹‹ውል›› ክፍት ውሎ እንዳደረ፡
ወይ እጁን ሰብስቦ ራሱን ያልቻለ
እምቡጥ ጋሜ ሳለ በእምቡቡ ጎልምሶ በእንኮኮ
አድጎ አርጅቶ
ጠውልጎ ወርዝቶ የተንዘላዘለ!!!

ፈጣሪ ለሰው ልጆች ሲል ሰው ሆኖ ወደ ምድር በመምጣቱም ጊዜ፤ (ማቴ 2፡12 ‹‹ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።›› ተብለው በመጽሐፍ ቅዱስ አሁንም የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ ቀድመው ለማብሰር ከተጠቀሱት ሰብአ ሰገል መካከል ኢትዮጵያዊያን ነገሥታት መኖራቸውም፤ በብሉይ የነበረውን መሲሁን/ነቢዩን የመጠበቅ ቀጣይነትን ማሳያ ነው።) ኢትዮጵያ ልክ እንደሌሎቹ ነባር ድንቅ ሁነቶች ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እውቅና ለመስጠት በመመረጥም ቀዳማይ መሆኗን ይመሰክራል፡፡
ነቢይ ፍለጋ በጽኑ የቃተተው ኢየሱስን በዮርዳኖስ ያጠመቀው መጥምቁ ዮሐንስም ጭምር ነበር ‹‹የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?›› ብሎ ከወህኒ መልእክት በላከበት ጊዜ፤ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ ዕውሮች ያያሉ አንካሶችም ይሄዳሉ፥ ለምጻሞችም ይነጻሉ ደንቆሮችም ይሰማሉ፥ ሙታንም ይነሣሉ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው።›› ኢየሱስ በሰጣቸው መንፈሳዊ ጸጋ ሐዋርያቱ ማጥመቅ ሲጀምሩ፤ ጥምቀት ገና ከኢየሩሳሌም አቅራቢያ ባሉ ከይሁዳና ከሰማርያ አካባቢ ሳይወጣ በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ በሌላ ምድር ለሚኖሩ ሕዝቦች የመድረስ እድል ሲያገኝ፤ የአዲስ ኪዳንን 2/3ኛ የጻፈው ሓዋርያው ጳውሎስ እንኳ የጌታ ምህረት ሳይደርሰውም በፊት፤ ከአለም ሁሉ አስቀድሞ፤ያውም በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ እጅ፤ ኢትዮጵያ አሁንም እንደ ልደቱ ሁሉ ለጥምቀቱም ቀዳማይ ትሆን ዘንድ መመረጧን እናያለን፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 ቁጥር 27 ላይ እንደሰፈረው . . .
‹‹የጌታም መልአክ ፊልጶስን ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደ ሆነ መንገድ ሂድ አለው። ተነሥቶም ሄደ። እነሆም፥ ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋም ሁሉ የሠለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤ ሲመለስም በሰረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር። መንፈስም ፊልጶስን ወደዚህ ሰረገላ ቅረብና ተገናኝ አለው። ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን? አለው። እርሱም፦ የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? አለው። ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው። ያነበውም የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፥ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል?ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ፦ እባክህ፥ ነቢዩ ይህን ስለ ማን ይናገራል? ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለ ሌላ? አለው።ፊልጶስም አፉን ከፈተ፥ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት። በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው። ፊልጶስም በፍጹም ልብህ ብታምን፥ ተፈቅዶአል አለው።  መልሶም ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ አለ። ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም።ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፥ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና።››

ጃንደረባው ባኮስ ቅድስቲቱ ምድር ከነአን ተገኝቶ
ለአምላክ ቤተ መቅደስ መስዋዕት አበርክቶ
ከኢየሩሳሌም መልስ በኤል ሃኒዬ መንገድ
ተአምር ተከስቶ
ፊደል በቀረፀች የምድሩ ብራና የህያው ቃል
ድርሣን
በኢሣይያስ ትንቢት በንባብ ተመስጦ
ከቀዬው ቢርቅም ደሙን በተጣባው እንግዳን
መቀበል ለጽድቅ ተመርጦ
ሓዋርያ አስተናግዶ ወልድን አገልግሎ
መሰስ ካለበት በህንደኬ ንግሥት ምቹ ሠረገላ
ፊሊጶስን ጭኖ
ከጋዛ ዳርቻ ሳይነጠቅበት በቃሉ አምኖ ድኖ
ከሓዋርያው ጳውሎስም ለጥምቀቱ ቀድሞ፡፡

ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ኢየሩሳሌም ሰግዶ በመመለስ ላይ መሆኑ፤ ኢትዮጵያዊያን ‹‹የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ ዘንድ፥ ለእስራኤል ምስክር ሊሆኑ የእግዚአብሔር ነገዶች ወደዚያ ይወጣሉ። የሚወዱሽ ቢኖሩ ይለምልሙ›› (መዝ. 122፡ 4/6) ተብሎ ስለ ኢየሩሳሌም የተጻፈውን ቃል ይተገብሩ እንደ ነበር ያመለክታል፡፡  የንግስቲቱ ሹም በሰረገላው ላይ ተቀምጦ ጮክ ብሎ ያነበው የነበረው የኢሣይያስ መጽሐፍም ፤ ኢትዮጵያዊያን የትንቢቱን ቃል በማንበብ የተጠመዱና ‹‹ነቢይ ፍለጋ›› በመቃተት ላይ እንደነበሩ ማስረጃ ይሆናል። ባንጻሩ ኢየሱስ በምድር ከተመላለሰበት እድሜው ከአንድ አመት በኋላ በ34ኛው ዓመተ ምህረት ጥምቀትን ብናገኝም እስከ ኢዛና ዘመን መንግስት ክርስትናን በይፋ ለመቀበል ከ300 አመታት በላይ ማለፋቸውን በ‹‹ለምን ይሆን እና እንዴት›› ተጠየቅ ከማውጠንጠን ከቶም ባናርፍም፡፡ ውሎ አድሮም አበው በደጎሱልን በየመጻሕፍቱ ገጾች መካከል፤ የአለቃ ሀሴቱ አፈ ንጉሥ ነሲቡ ችሎት ቀርበው ‹‹እርስዎም ዘመን የወለደውን፣ንጉሥ የወደደውን ኃይማኖት እስከዛሬ ካልተቀበሉ ይቀጡ በቃ።›› ትችት አይነት ድርሳን ስናጨነቁር፤ ነቢይ ፍለጋ መቃተቱና ተግዳሮቱ እየተንከባለለ ወይም የውርርሱ ድልድይ አንድ ቦታ ላይ ተሰብሮ ስንጥቃቱ እቅርቡ ዘመን ድረስም ታይቶ እንደነበር ጠቋሚ እሚሆነን ለዚህ ሳይሆን ይቀራልን?  ‹‹ወይስ ሌላ እንጠብቅ?›› መቀጠሉን፡ ‹‹ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን?››  ... ወዘተ. እምናመነዥክ - በወተት ጥርስም ቢሆን። በ‹‹ሁሉን ፈትኑ መልካሙን ያዙ›› ስንጥር ታክል ምርኩዝ ተደግፈን እናም ተደግገንም ምናልባት፡፡ (Pride V’s Vain pide!)
ብቻ ግን የሆነው ሁሉም ሆኖ፤ ምንም እንኳ እስተ ወዲያኛው ጥም ባይቆርጥም፤ የወል ተግባር ይሻልና ገና በምሉዕ ሀሴት ባያጠምቅም፤ ለዚህም ሆነ የትዬለሌ ክፍተት የተመሉ ጉዳዮቻችን፤ ለኢትዮጵያዊያን ከታሪክና ዘመን መሷረፍ ምላሽ ያጣንላቸው ተጠይቆቻችን መጽናኛ ይሆነን ዘንድ፤ ኢትዮጵያን ከዓለሙም ሁሉ፡ ታሪክም፡ ከጊዜም አልቀው ከማመንና ከመግለጥ የማይደክማቸው የታሪክ ተቆርቋሪና ቅን አሰላሳዮች መኖራቸው እሙን ነው፡፡
እናም እኒህን መሰል ስብራት ጠጋኝ፣ ተስፋ ፈንጣቂ፣ ለጥልቅ ፍለጋ አትጊ፣ ኮርኳሪ ህያው ምስክርነቶች በድንገቴ ግጥምጥሞሽ ስናገኝም እንደመማለን፤ ላፍታም ቢሆን ከቁጭታችን እናገግማለንም፡፡ ለምሳሌ (ለቀን ህብስታችን ስንኳትን የተጋራነው - እነሆ ያጋራነውም!) ፕሮፌሰር ሙጬ እንዲህ ይላሉ፡- “The World fears time, Time fears history , History fears Ethiopia.’’ አሜን፡፡ እሰይ! ደግ! ይሁንልና!  መልካም አውደ አመት፡፡ ‹‹ነቢይ ፍለጋ›› ይቀጥላል . . .
(ስንኞቹ  ከ‹‹እፍኝ የድንጋይ እርሾ››  ተራኪ ግጥም 2005 ዓ.ም- የተቀነጫጨቡ ናቸው - ‹‹የፀሐይ ገበታ›› መድበል - ያልታተመ፡፡)

Read 1363 times