Saturday, 19 January 2019 00:00

‹‹ለመሆኑ ቅኔ ፍልስፍና መሆን ይችላል?››

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 (ለብሩህ ዓለምነህ የተሰጠ መልስ)
                   መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር


     ብሩህ ዓለምነህ ‹‹ፍልስፍና ፫፡ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የወደ ፊት ፈተና ምንድን ነው?›› በሚል ርእስ በስድስት ክፍሎችና በዐሥራ ዐምስት ርእሶች አዋቅሮ ያሳተመው መጽሐፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሁሉም ርእሶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከቱ ጉዳዮችን የያዘ ነው፡፡ ከእነዚህ ርዕሶች ውስጥ የመጀመሪያው ክፍል ‹‹ቅኔና ፍልስፍና›› የሚል ሲሆን፣ በዚህ ክፍል ውስጥ ከገጽ 5-18 የምናገኘው ‹‹ለመሆኑ ቅኔ ፍልስፍና መሆን ይችላል?›› የሚለው ርዕስ፣ ስለ ቅኔና ፍልስፍና ግንኙነት ወይም ቅኔ ፍልስፍና ሊባል ይገባል ወይስ አይገባም በሚለው ክርክር ላይ የራሱን አቋም አቅርቧል፡፡
በመጀመሪያ፣ ብሩህ በኢትዮጵያ የፍልስፍና ታሪክ ውስጥ የራሱን አሻራ ለማኖርና የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት በሚያደርገው ትጋት በጣም እደንቀዋለሁ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› የሚለውን መጽሐፉን ከተማሪዎቼ ጋር ሰፋ ያለ ውይይት አድርገንበታል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› ላይ ያለኝን አስተያየት ለሌላ ጊዜ ላቆየውና ለዛሬ ግን ‹‹ፍልስፍና ፫›› መጽሐፉን አንብቤ አስተያየት ለመስጠት እግዚአብሔር ረድቶኛል፡፡
ብሩህ ‹‹ፍልስፍና ፫›› ብሎ በሰየመው መጽሐፉ ‹‹ለመሆኑ ቅኔ ፍልስፍና መሆን ይችላል?›› ብሎ ላነሣው ጥያቄ የሰጠው መልስ አሉታዊ ነው፤ ማለትም ‹‹ቅኔ ፍልስፍና መሆን አይችልም›› የሚል ነው፡፡ የደረሰበትን ድምዳሜ ሲያስረዳም ‹‹እኔ ‘ቅኔ ፍልስፍና መሆን አይችልም፤ የኢትዮጵያን ፍልስፍናም ከቅኔ ውስጥ ማግኘት አይቻልም፤ ቅኔን ወደ ፍልስፍና ማጠጋጋት ሳያስፈልግ፣ በራሱ ውበት እንደ አንድ የሥነ ጽሑፍ ዘውግነት መታየት አለበት’ ብለው ከሚከራከሩ ሰዎች ውስጥ ነኝ›› ይላል (ገጽ11)፡፡
ለዚህ ድምዳሜ ምክንያት አድርጎ ያቀረባቸው ደግሞ ሁለት ማስረጃዎች ናቸው፡፡ አንድኛው፣ የቅኔ ትርጕም ሲሆን ቅኔን እንደ ግጥም ብቻ በመተርጎምና በትርጉሙ ላይ ብቻ በመመሥረት ‹‹ቅኔ ፍልስፍና ሊሆን አይችልም›› የሚል ሐሳብ አቅርቧል፡፡ በሁለተኛነት መሠረታዊ ብሎ የጠቀሰው ምክንያት ደግሞ ‹‹ቅኔያችን የተለያዩና የተበታተኑ (ብዙ ጊዜም እርስ በእርስ የሚጣረሱ) ሐሳቦችን መያዙ ነው›› የሚለው መከራከሪያ ነጥብ ነው፡፡
ምንም እንኳን እኔ የፍልስፍና ተማሪ ባልሆንም በሥነ መለኮት፣ በማኅበረ ሰብ ሳይንስ (ሶሽዮሎጂ)፣ በሕግና በአፍሪካ ጥናት ትምህርት ባለፍኩባቸው ጊዜያት የወሰድኳቸው የፍልስፍና ትምህርቶች፣ ይልቁንም ጉዳዩ የተሻለ አውቀዋለሁ ከምለው ከቅኔ ትምህርት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ምክንያት አስተያየት ለመስጠት በጣም ተገፋፍቻለሁ፡፡ ምንም እንኳ ለዛሬ አስተያየት የማቀርበው ከቅኔ ጋር ለተያያዘው ርዕሰ ጉዳይ ቢሆንም፣ በሂደት ግን በሁሉም የመጽሐፉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ አስተያየት ይኖረኛል፡፡
የግእዝ ቅኔ ትምህርት የግጥም ትምህርት ነውን? ወይስ ቅኔ ግጥም ብቻ ነውን? የሚለው ሐሳብ በጣም መሰረታዊ ስለሆነ ጥያቄያችንን ከእሱ እንጀምር፡፡ ስለ ግእዝ ቅኔ ትምህርት ስንናገር፣ ስለ ግእዝ ቋንቋ ትምህርትና ስለ ሥርዐተ ትምህርቱ እንዲሁም ስለ ማስተማሪያ ዘዴው (methodology) አጠቃላይም ስለ ትምህርት ፍልስፍናው እየተናገርን ነው፡፡ በቅኔ ትምህርት ውስጥ ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ዜማ፣ ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያዊ ማንነት ጭምር አለ፡፡ በዚህም የተነሳ ቅኔ የትምህርት ሥርዐት እንጂ ግጥም አይደለም፡፡ ‹‹ቅኔ ቤት›› ሲባልም ‹‹ግጥም ትምህርት ቤት›› ማለት አይደለም፡፡
እኔ እስከ ማውቀው ድረስ ብሩህ በመፅሀፉ ውስጥ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ የሰጡትን ትርጉም ጠቅሶ ማርዬ ይግዛው ያቀረበው ‹‹ቅኔ አንድ ሰው ስለ አንድ ነገር ወይም ድርጊት ያገኘውን ዕውቀት ወይም ምሥጢር ምሳሌ መስሎ፣ ምስጢር ወስኖ፣ቃላት መጥኖ በአዲስ ግጥም የሚያቀርብበት ድንገተኛ ድርሰት ነው›› (ገጽ 10)  የሚለው ትርጕም ቅኔን ለመግለጥ በቂ አይደለም፡፡ ይህ ትርጉም፣ የቅኔ ድርሰትን እንጂ ራሱን ቅኔን አይተረጕምም፡፡ የአንድ ሰው ትርጕም መሆኑ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የግእዝ ቅኔን የማይገልጥ ጠባብ ትርጕም ነው፡፡
የግእዝ ቅኔ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እንደሚረዱት ቋንቋን፣ ሃይማኖትን፣ ባህልን፣ ትምህርትን፣ የሰው ልጅ አስተሳሰብን፣ወዘተ የያዘ አንድ ራሱን የቻለ የትምህርት ይዘት፣ ሥርዐተ ትምህርትና የማስተማር ዘዴ ያለው ሥርዐት (Sysytem) እንጂ ግጥም አይደለም፡፡ በድርሰትነቱ ሲታይ፣ ግጥምነቱ በድርሰት ጊዜ ወጥ የሆነ የዜማ ስልት እንዲኖረው ለማድረግ ታስቦ የተሠራ የዜማ ልክ ያለው ስለሆነ እንጂ ቅኔና የቅኔ ትምህርት የተለካ ግጥም ብቻ መሆኑን አያመለክትም፡፡ አስቀድሜ እንዳልኩት ቅኔ የራሱ የትምህርት ይዘት፣ ሥርዐተ ትምህርትና የማስተማር ዘዴ ያለው የትምህርት መስክ (discipline or system) እንጂ በፍጹም ግጥም አይደለም፡፡ ስለዚህ ብሩህ ቅኔን በዚህ ጠባብ ትርጕም ላይ ተመሥርቶ ፍልስፍና ነው/አይደለም በሚለው ክርክር ላይ አቋም መውሰዱ ተገቢ መስሎ አልታየኝም፡፡
ኢትዮጵያዊ ሥርዐተ ትምህርት የሚባለው የንባብ፣ የዜማ፣ የትርጓሜ መጻሕፍትና የሃይማኖት፣ እንዲሁም የሥርዐተ ጽሕፈት ትምህርት ሁሉ በቅኔ ትምህርት ውስጥ ያለ ነው፡፡ አንድ ተማሪ ቅኔ መማር የሚጀምረው ፊደል መማር ሲጀምር ነው፡፡ ዜማ ሲማርም ቅኔን ይማራል፤ ቅኔ ሲማርም ዜማን ይማራል፤ትርጓሜ ሲማርም ቅኔን ይማራል፡፡ ያለ ቅኔ ትምህርት እነዚህን ሁሉ ማወቅ አይቻልም፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ ትምህርት የተወራረሰ፣ እርስ በእርሱ የተሳሰረ እንጂ የተበታተነ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና በቅኔ ትምህርት አለ ወይ? የሚለውን አጠቃላይ ትምህርቱን አጥንቶ አለ/የለም ማለት እንጂ በአንድ ነጠላ ትርጕም ላይ ተመሥርቶ በሂደቱ ያለፉ ሰዎች ስለ ቅኔ ትምሀርት ፍልስፍናነት የሚሰጡትን አስተያየት በተቃራኒ መከራከር ጥልቀት ያለው ሐሳብ መስሎ አልታየኝም።
በኔ አስተያየት ቅኔ አንዱ የኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ምንጭ ነው፡፡ የፍልስፍና ምንነትን በምዕራባዊው አስተሳሰብ መዝነን አንድ ፍልስፍና እናውጣ ማለት እንደማይቻልና ይሄም ሐሳብ እንደ ቀረ ይታወቃል። ኢትዮጵያዊው ፍልስፍናም ሙሉ በሙሉ የተለየ ኢትዮጵያዊ መሆን እንደማይችል አምናለሁ፡፡ በዚህ መሠረት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት በቅዱሳት መጻሕፍት፣ በታሪክ፣ በባህልና በራሳቸው አመክንዮ በደረሱበት ደረጃ ያደራጁት የእምነታቸው፣ የትምህርት ፍልስፍናቸውና ዘዴያቸው፣ የፈጠራ ችሎታቸው፣ የሚገለጥበት የግእዝ ቅኔ ሰፊ የትምህርት ዘርፍ እንጂ ግጥም አይደለም፡፡ ስለዚህ ቅኔ ግጥም ነው በሚል ትርጉም ላይ ተመሥርቶ የግእዝ ቅኔ የፍልስፍና ምንጭ አይሆንም የሚለው አቋም አላሳመነኝም፡፡
ሁለተኛው የብሩህ ምክንያት፣ ቅኔያት የተበታተኑ ብሎም እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ ሐሳቦችን የያዙ ናቸውና ‹‹ቅኔ ፍልስፍና አይደለም›› የሚል ነው፡፡ ቅኔያት የሚላቸው ድርሰቶችን በተናጠል እንደ ሆነ መረዳት ችያለሁ፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ ጉባኤ ቃና ወይም መወድስ ድርሰት በራሱ ቅኔ ይባላል፡፡ ከዚህ አንጻር የአንድ ሰው ቅኔ ከሌላ ሰው ቅኔ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚቃረን አቋም ሊኖረው ይችላል፡፡ የአንድ ሰው ፍልስፍና ከሌላ ሰው ፍልስፍና ሊለይ ቢችል ብሎም ቢቃረን እንኳን ፍልስፍና አይባልም ማለት አንችልም፡፡ ይህን ብሩህም በጽሑፉ በግልጥ አስፍሮታል፡፡
ነገር ግን፣ የአንድ ሰው ሐሳብ በድርሰቶቹ ከተቃረኑ ወጥ የሆነ ፍልስፍና አለው ማለት አንችልም፡፡ ብሩህ እንዳለው፤ ተዋነይ በቅኔዎቹ ወጥ የሆነ ሐሳብ አይታይበትምና ፈላስፋ መባል የለበትም፤ ቅኔውም ፍልስፍና አይባልም ነው፡፡ የተዋነይ ሐሳብ ብሩህ እንዳለው በየቅኔው መሠረታዊ የሚባል ሐሳቡን እየቀየረ የሚመጣ ከሆነ፣ ትክክል ነው ቅኔው ፍልስፍና ለመባል መጀመሪያ ወጥ የሆነ ሐሳብ ሆኖ መገኘት አለበት፡፡
መጀመሪያ ብሩህ የጠቀሳቸው ሁለት የተለያዩና ‹‹እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ›› የተባሉ ቅኔዎችን እንመልከት፡፡
የአምን ወይገኒ
ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ፡፡
ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ፡፡
ለነጽሮ ዝኒ ከመ እስራኤል ይፍርሁ፡፡
ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ፡፡
ወፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ፡፡
(ትርጕም)
ብዙዎች እየተገዙ በፊቱ ይሰግዱ ዘንድ ዓለም ሁሉ ራሱ በፈጠረው ያምናል፤ ይገዛልም፡፡
ይህን ነገር ለማስተዋልም እስራኤል ይፈሩ ዘንድ ሙሴ ፈጣሪውን ፈጠረ፤ ፈጣሪም ሙሴን ፈጠረው፡፡  
ተቃራኒ ብሎ የጠቀሰው ቅኔ ደግሞ በአማርኛው እንደጠቀሰው
ሰው-ባዶ ሰው፣ ራቁት ሰው፤
በረዶ ለበረዶ፣መብረቅም ለመብረቅ ተገዥ እንዳለው፤
በኀጢአተኛው የሚፈርድበት፣
አምላክ በኢዮር (ሰማይ) ላይ መኖሩን ልቡናህ ሲያውቀው፣
የሕይወቱ ዓመት በፍጥነት ለሚያልቅ ለዚያው ለባዶ ሰው፣
አጥንቱ መቃብር ለሚወርድ ለዚህ ለራቁት ሰው፣
በወርቅ ለመገዛት ልብህ እንዴት ከጀለ፣ ነገ አፈር ለባሹ አምላክ እንዲሆነው፡፡
ነገር ግን፣ እኔ እንደተረዳሁት እነዚህ ሁለቱ ቅኔዎች የሚቃረኑ አይደሉም፡፡ ብሩህ በገጽ 13 የጠቀሰው ‹‹ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ፤ ወፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ›› የሚለው ቅኔና በገጽ 15 የጠቀሰው ‹‹ሰው ሁሉ ፈጣሪ (አምላክ) እንዳለ መካድ አይችልም›› የሚል ድምዳሜ ያለው ቅኔ የሚቃረን ሐሳብ የላቸውም፡፡
የመጀመሪያው ቅኔ ‹‹ፈጣሪ የለም›› አይልም። ‹‹ሙሴ ፈጣሪውን ፈጠረ›› ማለት ራሱ ሙሴ አምላክ የሚለውን ወይም ‹‹የደረሰበትን አመለከ›› የሚል ነው እንጂ አንድ ‹‹አምላክ የለም›› አይልም። የመጀመሪያው ቅኔ ዋና ሐሳብ እያንዳንዱ ሰው ፈጣሪን የሚረዳው በራሱ መንገድ ነው የሚል ነው፡፡ ለዚህም “የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ” ባለው ይታወቃል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ‹‹አምላክ ነው ብሎ ባሰበው ነገር ላይ ያምናል›› ማለት አንድ እውነተኛ አምላክ የለም ማለት አይደለም፡፡ ሙሴ የተጠቀሰው አንድን የታወቀ የእምነት መስመር ምሳሌ አድርጎ ለማሳየት ነው፡፡ ሁለተኛው ቅኔ ግን ‹‹አንድ አምላክ አለ፤ ይህም አምላክ መኖሩን ልቡናህ ያውቀዋል፤ ስለዚህ ለወርቅና ለብር ብለህ ለሰው አትገዛ›› የሚል ነው፡፡
በሌላ በኩል እነዚህ ቅኔዎች ተቃራኒ የሆኑ አቋሞችን የያዙ ቢሆን እንኳን ሁለቱም ቅኔዎች ሁለት የአስተሳሰብ መስመርን የሚገልጡ የተለያዩ ሰዎች ቅኔዎች እንጂ የአንድ ሰው ቅኔዎች ለመሆናቸው አፈ ታሪኩን ይዘን ከመከራከር ያለፈ ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም፡፡ ራሱ ተዋነይ የተባለው ሰው ኢትዮጵያዊ ባለ ቅኔን የሚወክል የሆነ አፈ ታሪክ (ፈጠራ) እንጂ ታሪኩ የተረጋገጠ ሰው ላይሆን ይችላል፡፡
እኔ በሁለቱ ቅኔዎች ውስጥ ያየሁት ተቃርኖ፣ ሁለቱ ቅኔዎች የአንድ ሰው የተዋነይ ናቸው ባለ ሰው አእምሮ ውስጥ ያለን የአስተሳሰብ ተቃርኖ ነው፡፡ በቅኔዎች ውስጥ ተቃርኖ አለ ብሎ የሚያምነው ሰው ራሱ ቅኔዎች የአንድ ሰው ቢሆኑ እንኳን ዐሳባቸው እንደማይቃረን አለማስተዋሉን እንጂ በእርግጥም የተዋነይ ሁለት የሚቃረኑ ሐሳቦች አድርጌ አይደለም።
በቅኔ የትምህርት ሥርዐት ውስጥ አንድ ባለ ቅኔ እንዲህ አይነት ተቃርኖን የሚያስወግድባቸው የቅኔ ት/ቤት ሕጎች አሉ፡፡ በአንድ ሰው የሚታይ እንዲህ አይነት የተገለጠ የሐሳብ ተቃርኖ ይቅርና የዘዴ ተቃርኖ እንኳን ቢከሠት ምን ችግር እንዳለበት ትምህርቱ በራሱ ያስተምራል፡፡
ስለዚህ ቅኔዎች የተለያዩና የሚጣረሱ ሐሳቦችን ይዘዋል ቢባል እንኳን በተዋነይ ውስጥ ወጥ የሆነ አስተሳሰብ አለመኖሩን የሚያመለክቱ ሳይሆን ሁለት የተለያዩ ብሎም ብሩህ እንዳለው፣ እርስ በእርስ የሚጣረሱ የአስተሳሰብ መስመሮችን እንጂ የአንድን ባለ ቅኔ እርስ በእርስ የሚቃረኑ ሐሳቦች አድርጌ አላየውም፡፡
ስለዚህ፣ ቅኔን በተመለከተ ‹‹በፍልስፍና ፫›› የተነሡ መከራከሪያ ነጥቦችም ሆነ ድምዳሜው የግእዝ ቅኔን በተመለከተ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም፡፡

Read 2017 times