Saturday, 19 January 2019 00:00

ቃለ ምልልስ ከጋዜጠኝነት እስከ አምባሳደርነት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ተወልደው ያደጉት ሻሸመኔ ነው፡፡ የአንደኛ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሻሸመኔ ካቶሊክ ሚሽንና አብዮት ጮራ ት/ቤት፣ የኮሌጅ ትምህርታቸውን ደግሞ ኩየራ አድቬንቲስት ተከታትለዋል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ቋንቋዎች ያገኙ ሲሆን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን  በዲፕሎማሲና በአለማቀፍ ግጭት አፈታት ከኬንያ ናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ በኒውዮርክና ህንድ በዲፕሎማሲ የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስደዋል፡፡ የዛሬው እንግዳችን አምባሳደር መለስ አለም፡፡
 ወደ ሥራ ዓለም የገቡት  በጋዜጠኝነት ሙያ  ነው፡፡ ሬዲዮ ፋና ትልቁ የጋዜጠኝነት ሙያ ትምህርት ቤቴ ነው ይላሉ፡፡ በዋልታና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም ሰርተዋል፡፡ የማታ ማታ ዲፕሎማት ቢሆኑም የልጅነት ህልማቸው ግን ዲፕሎማሲም ጋዜጠኝነትም አልነበረም። “እውነቱን ለመናገር እኔ የምፈልገው ወታደር መሆን ነበር፡፡” ይላሉ፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአንደኛ ፀሐፊነት የስራ መደብ ተወዳድረው መስሪያ ቤቱን የተቀላቀሉት አቶ መለስ አለም፤ ከተለያዩ የዲፕሎማሲ ስራዎች አንስተው እስከ ቃል አቀባይነት ደረጃ  የደረሱ ሲሆን አሁን ደግሞ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሾመዋል፡፡  
አምባሳደር መለስ አለም ከጋዜጠኝነት እስከ አምባሳደርነት የደረሱበት የስራ ህይወት ምን ይመስላል? በቃል አቀባይነት ሃላፊነታቸው ምን ተግዳሮቶች ገጠሟቸው? በዲፕሎማሲ ስራቸው እንዲሁም በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡


     የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትን እንዴት ነው የተቀላቀሉት?
እኔ ዲፕሎማት እሆናለሁ የሚል ሃሳብ ብዙም አልነበረኝም፡፡ እውነቱን ለመናገር እኔ የምፈልገው ወታደር መሆን ነበር፡፡ ጥሩ ወታደር መሆን፣ ጥሩ መኮንን መሆን ነበር የምመኘው፡፡ እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ ስጠየቅ፣ ወደፊት መሆን የምፈልገው ወታደር ነው ነበር የምለው፡፡
ወታደር የመሆን የልጅነት ፍላጎቱ ከየት መጣ?
አንደኛ አባቴ ወታደር እንድሆን ይፈልግ ነበር፡፡ ቆፍጠን ያለ፣ በትረ መንግስት የያዘ፣ ቀላ ያለ ሸንቃጣ ወታደር እንድሆን ነበር የሚፈልገው፡፡ ሻሸመኔ፣ የደቡብ እዝ የሚል የወታደሮች ካምፕ አለ፡፡ እዚያ የምናያቸው ወታደራዊ መኮንኖች በጣም ፀዳ ያሉ፣ ልብሳቸው የተተኮሰ፣ ዘናጭና ቆፍጣ ናቸው፡፡ እነሱን እያየሁ ስላደግሁ የልጅነት ህልሜ ወታደር መሆን ነበር፡፡ ዲፕሎማት መሆን የሚለው በኋላ ነው ወደ ፍላጎቴ የመጣው፡፡
ወታደርነትን አልመው እንዴት ዲፕሎማትነት ላይ አረፉ?
በአንድ ወቅት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለማቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ተመራቂዎች ይመስሉኛል፣ በቴሌቪዥን አንድ ፕሮግራም ያቀርባሉ፡፡ ፕሮግራሙ ተማሪዎቹ እንደ ሃገር መሪ፣ እንደ ዲፕሎማት ሆነው ክርክር የሚያደርጉበት ነበር። እሱን ያየሁ ጊዜ፣ እንደዚህ መሆን ይቻላል እንዴ? እንዲህ ዓይነት ነገር አለ እንዴ? ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ እንደ ታላቅ ወንድም፣ እንደ መንፈሳዊ አባትም የማስበው የእህቴ ባለቤት ነፍሱን ይማረውና፣ ጌታቸው ቀነኣ ይባላል፤ እሱን አማከርኩት፡፡ እሱም፤ እንደውም ዲፕሎማት ነው መሆን ያለብህ አለኝ፡፡ በዚህ ነው ዲፕሎማት የመሆን ፍላጎቱ ያደረብኝ፡፡ በኋላ ግን ጋዜጠኛ ነው የሆንኩት፡፡ ጋዜጠኛ ከሆንኩ በኋላ ውጭ ጉዳይ እየመጣሁ ቃለ መጠይቅ የማድረግ፣ ዲፕሎማቶችን የማናገር አጋጣሚዎች ነበሩኝ፡፡ ጋዜጠኛ በመሆኔም አለማቀፍ ሁኔታዎችን የመከታተል እድል ስላገኘሁ፣ ቀስ በቀስ ከወታደርነቱ ይልቅ በዲፕሎማሲ ሙያ ላይ ፍላጎት እያደረብኝ መጣ፡፡ በ1995 መጨረሻ አካባቢ ይመስለኛል፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቅጥር ማስታወቂያ አወጣ፡፡ በዚያ ማስታወቂያ ከ300 በላይ ሰዎች እንደተወዳደሩ አስታውሳለሁ። ያው ውድድሩን በብቃት ተወጥተን ጥቂቶቻችን ተቀጠርን፡፡ ከኔ ጋር ተወዳድረው ውጭ ጉዳይን ከተቀላቀሉት መካከል የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ፣ አሁን በህንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ የሆነው ተወልደ ሙሉጌታ ነው፤ ሌላኛው ሳሙኤል ፍፁም ይባላል፤በቤይጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ይገኛል፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡ በወቅቱ ውጭ ጉዳይ እንደገባን የመሥሪያ ቤቱን የፕሬስና ህትመት ክፍል ማጠናከር ይፈለግ ነበር። ዲፕሎማሲያችን የምትባል በእንግሊዝኛም በአማርኛም የምትታም መጽሄት ነበረች፡፡ ስለዚህ ውጭ ጉዳይን ስቀላቀል የገባሁት የፕሬስ ክፍል ባልደረባ ሆኜ ነው፡፡ አንደኛ ፀሐፊ በሚል ደረጃ ነበር የተቀጠርኩት፡፡ ከዚያ በኋላ በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ የመስራት እድል ነበረኝ፡፡ በኋላም አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የቃል አቀባይ ፅ/ቤትን ስራ ለማጠናከር ሲሰራ እኔም ወደ ቃል አቀባይ ፅ/ቤት ገባሁ፡፡ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲፕሎማትነት ስራ የገባሁት በዚህ መንገድ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር እኔ ፍላጎቴ ወታደር መሆን ነው፣ አሁንም ቢሆን፡፡ በኔ ያጣሁትን ወታደርነት በወንድሜ የማገኝ መስሎኝ፣ ወታደር ሁን ብዬው ነበር፤ ግን አልሆነም፡፡ በቀጣይ ልጄ ወታደር ቢሆን ደስ ይለኛል፡፡ በእርግጥ ዲፕሎማሲና ወታደርነት አብረው የሚሄዱ ናቸው፡፡ ወታደርና ዲፕሎማሲ ጀርባና ፊት ናቸው የሚሉም አሉ፡፡ ወታደር በፊት ለፊት ይጋፈጣል፣ ዲፕሎማት ከኋላ የሃገሩን ጥቅም ያስከብራል፡፡
የቃል አቀባይ ጽ/ቤት ቆይታዎ ምን ይመስላል?
ለኔ ጥሩ ጊዜ ነበር፡፡ ተሳክቶልኛል አልተሳካልኝም … የምታውቁት እናንተ ጋዜጠኞች ናችሁ፡፡ በተለይ ክቡር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ወደዚህ ኃላፊነት እንድመጣ ሲያደርጉኝ የሰጡኝ መመሪያ ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ እንዲያውቅ ማድረግ ይገባል፡፡ የውጭ ግንኙነት ወይም የዲፕሎማሲ ስራ በዲፕሎማቶች ብቻ የሚከናወን አይደለም፡፡ በራችንን ከርችመን የምንሰራው ስራ አይደለም፡፡ መስሪያ ቤቱ ፊትም ድምፅም ያስፈልገዋል ነው--- ያሉኝ፡፡ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ በርካታ ሃገራዊ ጉዳዮች ይከናወናሉ፡፡ ያንን ህብረተሰቡ ማወቅ አለበት፡፡ ዘመናዊ ተቋም ማድረግ አለብን---እነዚህን ስራዎች መስራት አለብህ ሲሉኝ፤ በወቅቱ ለኔ ትልቅ ዱብ ዕዳ ነው የሆነብኝ፡፡ ምን ይገጥመኝ ይሆን የሚል ፍርሃት ነበረኝ፡፡ ነገር ግን ትልቁ ተስፋዬ የነበረው የሚዲያውን ዓለም ማወቄ  ነው፡፡ ጋዜጠኛ ምን አይነት መረጃ እንደሚፈልግ ለመረዳት እሞክራለሁ፡፡ ጋዜጠኛ መሆኔ የትኛው ሚዲያ ምን ጉዳይ እንደሚፈልግ ለመረዳት እድል ሰጥቶኛል፡፡ በዲፕሎማሲውም አስር አመት አካባቢ መቆየቴ የትኞቹ መረጃዎች ቢወጡ የተሻለ ይሆናል የሚለውን ለመረዳት አላስቸገረኝም፡፡ እዚህ ጋ ሁሉም ሊገነዘበው የሚገባው፣ ፊት ለፊት የምወጣው እኔ ነኝ እንጂ የቃል አቀባይ ስራ የብዙ ተዋናዮች ድምር ውጤት ነው፡፡ ከአለቆቼ ጋር የትኛው መረጃ እንደሚወጣ፣ ምን ዓይነት ቃላት እንደምንጠቀም ተመካክረን ነው የምንሰራው፡፡ ከባልደረቦቼ ጋር ጋዜጠኞች በዚያ ወቅት ሊያነሷቸው የሚሏቸው ጉዳዮች ምን ሊሆኑ ይችላሉ ብለን ተመካክረን ተዘጋጅተን ነው ወደ ሚዲያ የምንወጣው፡፡ እኛ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ሪፖርቶች ነን ብለን ነው የምናስበው፡፡ ጋዜጠኞች ትልቁ ረሃባቸው መረጃ ነው፡፡ የኛ ትልቁ ሃብት ደግሞ መረጃ ነው፡፡ ስለዚህ ያንን መረጃ እንዴት መስጠት እንደሚገባን በቅጡ ተመካክረን ነው የምንሰራው፡፡
ከጋዜጠኞች ጋር ጠንካራ የሥራ ግንኙነት እንደነበርዎ ይታወቃል፡፡ በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ሁሉ ለጋዜጠኞች መረጃ  ይሰጡ ነበር፡፡ ይሄ ትጋትና ተነሳሽነት ምንጩ ምንድን  ነው?
ትልቁ ነገር እኔ በመጀመሪያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የህብረተሰቡ ቃል አቀባይ ነኝ ብዬ ነው ራሴን የማስበው፡፡ ስለዚህ ጋዜጠኛ ወደ እኔ ሳይሆን መምጣት ያለበት፣ እኔ ነኝ ወደ ጋዜጠኛው መሄድ ያለብኝ ብዬ ነው ራሴን ያሳመንኩትና ያዘጋጀሁት፡፡ ለዚህ ነው ብዙ ጊዜ ጋዜጠኞችን አጭር መልዕክት በየሞባይል ቁጥሮቻቸው በመላክ የምጨቀጭቃቸው፣ አንዳንዴም እስኪታክታቸው ነው ይሄን የማደርገው፡፡ በተደጋጋሚ መረጃ፣ ፎቶ እልክ ነበር፡፡ አንዳንዴ የላኩትን መረጃ ላያወጡልኝ ይችላሉ፤ ነገር ግን ተግባሬን አላቋርጥም፡፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩት ራሴን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የተቀመጠ የህዝብ ሪፖርተር አድርጌ ነው የምቆጥረው፡፡ ጋዜጠኞች በዘገባ ሲሳሳቱ እየወደልኩ የማርመውም፣ ቤተሰባዊ መቀራረብን የበለጠ ለመፍጠር ነው፡፡ ስህተታቸውን እያየሁ ማለፍ አልፈልግም፡፡ ሙሉ መረጃውን ሰጥቻቸው፣ በእርጋታ ስህተቱን እንዲያርሙ ለማድረግ ነው ስሞክር የነበረው፡፡ በዚህ መንገድ የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያን፣ ከአሳዳጅና ተሳዳጅ ወደ አጋርነት የመለወጥ ስራ ሰርተናል ብዬ አስባለሁ። በቃል አቀባይነት ቆይታዬ፣ አንዱ ትልቁ ስራ ይሄ ነበር፡፡ ምን ያህል እንደተሳካልኝ ባላውቅም የምችለውን ሁሉ ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር ሆኜ ለማድረግ ሞክሬያለሁ፡፡
ከጋዜጠኞች ጋር በነበርዎ የሥራ ግንኙነት ምን ታዘቡ?
እኔ ያልተዘጋጀ ጋዜጠኛ ብዙም አይመቸኝም። በተለይ አንድን ጥያቄ ሲጠይቅ በሚገባ ጉዳዩን መርምሮ፣ አንብቦና ተዘጋጅቶ መሆን አለበት፤ ባልተዘጋጀበት ጉዳይ ዝም ብሎ መናገሩ ደስ አይልም፡፡ ስለዚህ ጋዜጠኛ ወደኛ ሲመጣ ጥያቄ ይዞ ተዘጋጅቶ እንጂ ዝም ብሎ የተሰጠውን ተቀብሎ ሲሄድ ደስ አይለኝም፡፡ ጋዜጠኛ ቢያንስ ሰው ፊት በኩራት ሊያቆመው የሚችለውን አለባበስ ቢከተል ደስ ይለኛል፡፡ ቢያንስ የሌላ ሃገር ሰዎች ሲመጡ የሚያከብሯቸው ቢሆኑ ነው የምፈልገው። አለባበስ ሲባል ውድ ልብስ መልበስ አይደለም፡፡ ንፁህ፣ ጥንቁቅ የሆነ አለባበስ ማለት ነው፣ፕሮቶኮል ጠብቁ ሲባል፡፡ ሌላው የታዘብኩት ከኢንተርኔት የተገኘን አሉታዊ ዘገባ ሁሉ የማስተናገድ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ቆመ ሲባል፣ ያንን ተቀብሎ ከማስተጋባት ለምን መንግስትን አይጠይቅም፡፡ ጋዜጠኛው ጥንቁቅ ንቁ ነው መሆን ያለበት፡፡
ሚዲያዎችን  በአካል የጎበኙበት አጋጣሚ አለ… ?
አዎ! ሁሉንም በሚባል ደረጃ ጎብኝቻለሁ፤ የክልል ሚዲያዎችን ሳይቀር፡፡ ይሄን ያደረግሁት ቅርርቦሹንና ወዳጅነቱን ለማጠናከር ነው፡፡
በቃል አቀባይነት ቆይታዎ ወቅት ፈታኝ የሆነብዎ ጉዳይ ምንድን ነው?
ብዙም የቸገረኝ ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም እኔ የራሴን ሃሳብ አይደለም የምናገረው፤ ተሰንዶ ተስተካክሎ የተሰጠኝን ነው የማቀርበው፡፡ ከኔ ጀርባ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ አለቆቼ መረጃዎቹን እንደኔ ሁሉ በሚገባ ተጠብበው ተጨንቀው ያሰናዷቸዋል፡፡ እኔ የመስሪያ ቤቱ ድምፅና ገፅ ነኝ፡፡ እኔ በመጣሁበት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ትኩሳት የተጋጋለበት ነበር፡፡ በቀጥታ ከውጭ ጉዳይ ጋር ባይገናኝም ፍረጃ የበዛበት ወቅት ነው የነበረው፡፡ ማህበራዊ ሚዲያውም በጣም ያየለበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ለተለያዩ ሚዲያዎች መግለጫ መስጠት የራሱ ፈተናዎች አሉት፡፡ ግን ሁሉንም እንደሚገባው የተወጣሁ ይመስለኛል፡፡ በፕሬዚዳንት ክሊንተን ጊዜ ማይክ ማኩሪ የሚባል ቃል አቀባይ ነበር፡፡ ይህ ቃል አቀባይ ወደ ቦታው የመጣበት ጊዜ፣ ክሊንተን ከሞኒካ ቅሌት ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ የገቡበት ጊዜ ነበር። ለኔ በጣም አስቸጋሪው፣ከሞኒካ ጋር በተያያዘ ስለ ክሊንተን የሚነሳው ጥያቄ ነው ይል ነበር፡፡ የተለያዩ ችግሮችና አለመረጋጋት ባሉበት ሁኔታ ቃል አቀባይ መሆን የራሱ ፈተናዎች አሉት፡፡ በእርግጥ እኔ ያን ያህል ፈተና ገጥሞኛል ማለት አልችልም፡፡
ዶ/ር ዐቢይ የስልጣን ሽግሽግ ባደረጉበት ወቅት ለኮሚኒኬሽን ሚኒስትርነት መታጨትዎ በአንድ በኩል ሲነገር፣ በዚያው ሰሞን ደግሞ ማዕከላዊ እስረኛ ገርፈዋል የሚል ወሬ ተሰራጭቶ ነበር። ምናልባት በዚህ ምክንያት ይሆን ለሚኒስትርነት ሳይሾሙ የቀሩት?
እኔ ለሹመት መታጨቴንም እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ አንዳንድ ሚዲዎች ቀጣዩ የኮሚኒኬሽን ሚ/ር መለስ አለም ነው ብለው ነበር፤ ግን እኔ እጩ ሆኜ መቅረቤን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ግን አመራሩ እኔን ለቦታው ቢያስብ ኖሮ፣ ገራፊ ነበር የተባለው እንቅፋት የሚሆንባቸው አይመስለኝም። ምክንያቱም በእንደዚህ ዓይነት ነውረኛና ዘረኛ ተግባር ላይ እንደማልሰማራ ያውቃል፤ መረጃም ካለ በርብሮ ማጣራት ይቻላል፤ እኔን በተመለከተ በቂ መረጃ ይኖራቸዋል፡፡ ስለዚህ በወቅቱ ለሚኒስትርነት እጩነት መቅረቤን አላውቅም፤ ብቀርብም ይሄ ውንጀላ የተለየ ነገር ይፈጥራል የሚል እምነት የለኝም፡፡
የማዕከላዊ ገራፊ ነበሩ የሚለው ውንጀላ የፈጠረብዎ  ችግር አለ?
የፈጠረብኝ ችግር የለም፡፡ ከዚህ ቀደም  ወደዚህ ኃላፊነት እንደመጣሁ፣ አንድ ወዳጄ፣ ኤርትራዊው የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ሆነ የሚል ፅሁፍ አውጥቶ ነበር፡፡ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ የሻሸመኔ ልጅ ነኝ። የሻሸመኔ ልጅ መሆኔን፣ ኢትዮጵያዊነቴን  ማንም አይነጥቀኝም፡፡ ሻሸመኔ ተወልጄ፣ ሻሸመኔ አድጌና ጎልምሼ የኖርኩ ሰው ነኝ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ የ2 ቢሊዮን ዶላር ሃብት አላቸው ብሎ ስም የሌላ፣ ፎቶ ግን የኔ የሆነ ፅሁፍ በሶሻል ሚዲያ ወጥቷል፡፡ 2 ቢሊዮን ሲባል ጓደኞቼም ወዳጆቼም፣ ኧረ ባክህ ትንሽ ብድር ፈልግልን ብለው ቀልደውብኛል፡፡ እኔ እንኳን ሁለት ቢሊዮን ሊኖረኝ፣ ቢሊዮን የማውቀው በወሬ ነው። እኔ ያለፍኩበትን መንገድ ጠንቅቄ አውቃለሁ፤ ቤተሰቤም ወዳጆቼም ያውቃሉ፡፡ ጋዜጠኛ ነበርኩ፣ ዲፕሎማት ሆንኩ፣ ቃል አቀባይ ተደረግሁ፤ አሁን በአምባሳደርነት ተሾምኩ እንጂ ፖሊስም መርማሪም ሆኜ አላውቅም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የገራፊ እጥረት የለም፡፡ እኔን እዚያ የሚወስደኝ ጉዳይ የለም። እኔ የየትኛውም ፓርቲ/የፖለቲካ ድርጅት አባል አይደለሁም፡፡ ይህ ማለት ግን ስለ ሃገሬ አላስብም ማለት አይደለም፡፡ የተሻለች ኢትዮጵያ እንድትሆንልኝ እፈልጋለሁ፡፡ በዚህ ውስጥ የራሴን ማንኛውም አስተዋፅኦ ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡ የመንግስት ሰራተኛ መሆን ማበድ ነው፡፡ ለደሞዝ አይደለም እንዲህ ያለ ስራ የሚሰራው፡፡ እኔ ቤተሰቤም በደብዳቢነት አላሳደገኝም፡፡ ጥሩ ሰብዕና እንዲኖረኝ አድርጎ ነው ያሳደገኝ፡፡ ስለዚህ እንዲህ የማደርግበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ እኔን በጥሩ ሰብዕና የቀረፀኝ ትምህርት አይደለም፡፡ የአባቴ የእናቴ የአስተዳደግ ውጤት ነኝ፡፡ የቀረፀኝ የእነሱ ትምህርት ነው፡፡ እኔ ደስታንም ሃዘንንም በልካቸው ነው የምቀበላቸው፡፡ ይሄ ጉዳይ ሲፈጠርም እንዲሁ ነው የተቀበልኩት፡፡
የአምባሳደርነት ሹመቱን እንዴት አገኙት?
እኔ እውነቱን ለመናገር ይሄን አልጠበቅሁም፡፡ አምባሳደር እሆናለሁ ብዬ አልጠበቅሁም፡፡ ሹመቱ ሲሰጠኝም ደንግጫለሁ፡፡ ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡ 100 ሚሊዮን ህዝብ፣ ትልቅ ሃገር ወክዬ ነው ሌላ ሃገር የምሄደው፡፡ ኬንያ ነው የተመደብኩት፡፡ ኬንያ በዲፕሎማትነት ቆይቻለሁ፡፡ ኬንያውያን ለኢትዮጵያ ያላቸውን ክብር አውቃለሁ፡፡ ይሄን ሃገራዊ ተልዕኮና ግዳጅ ይዤ እንደሚሄድ ወታደር ነው ራሴን የማየው። በዚህ ዝግጁነት ነው ወደ ተልዕኮዬ የማቀናው፡፡ ደግነቱ አምባሳደሩ ብቻ ሳይሆን በርካታ ባለሙያዎች አሉ፡፡ በኬንያ የሚገኙ በተለያዩ አለማቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ከፍተኛ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ነጋዴዎች፣ ሰራተኞች፣ በስደት ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ፡፡ የጋራ ድንበር ላይ የሚኖሩ አሉ፡፡ እስከ 30ሺ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በኬንያ ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ እነዚህን ሁሉ አብረን ለመስራት ነው ጥረት የማደርገው። ብዙ ወዳጆች አሉኝ፤ ከእነሱ ጋር ሁሉ ተባብሬ እሰራለሁ። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አንድ ያሉት ነገር አለ፡፡ ኤምባሲዎች ዜጋ ከሌላቸው መደበኛ ቤት ናቸው ብለዋል፡፡ በእርግጥም ኤምባሲን ኤምባሲ የሚያደርገው ዜጋው ነው፡፡ ለዜጎች የሃዘን ጊዜ መጠለያ፣ የከፋቸው ጊዜ መፅናኛ፣ ደስ ሲላቸውም የሚደሰቱበት የሁሉም ቤት መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ በዋናነት የዜጎቻችንን መብት የማስከበር ስራ እንሰራለን፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ እየተወሰዱ ያሉ የሪፎርም እርምጃዎች ምን ይመስላሉ?
አሁን እኔ ቃል አቀባይ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን እንደ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረባ ነገሩን ሳየው፣ መሥሪያ ቤቱ ከተቀመጠለት ግብና ተልዕኮ እንዲሁም ካለበት ኃላፊነት አንፃር የሚመጥን ማሻሻያ እያደረገ ነው፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ከተቋቋሙ ዘጠኝ መስሪያ ቤቶች አንዱ ነው፡፡ በዕድሜ አንጋፋ ነው። በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ግለሰቦችም ያሉበት ተቋም ነው፡፡ ዶ/ር ወርቅነህ ወደ ኃላፊነቱ ከመጡ በኋላ መዋቅሩ እንደ አዲስ ነው የተሰራው፡፡ የሰራተኛ ምደባና ድልድል ጉዳይም በአዲሱ መዋቅር፣ ሙያን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ የስራ ክፍፍል በመዋቅሩ በጥሩ ተሰርቷል፡፡ የሚመደበው ዲፕሎማት ዋና ስራው፣ ኢንቨስትመንት ማምጣትና ለዜጎች ስራ መፍጠር ነው፡፡ ቱርኮች እንዴት ይመጣሉ የሚል ነው ዋና ስራው፡፡ ዳያስፖራው በሃገሩ ጉዳይ ሙሉ ተሳታፊ እንዲሆን ማመቻቸት ነው ዋና ስራው፡፡ ዳያስፖራው በዚህ ሃገር ኢኮኖሚ ላይ ያለው ድርሻ ቀላል አይደለም፡፡ ለቤተሰቦቻቸው በህጋዊ መንገድ የሚልኩት የውጭ ምንዛሬ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ የዛሬ 15 ዓመት 130 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ነበር፡፡ ገንዘብ ብቻ አይደለም፤ ባሉበት ቦታ ሁሉ ዜጎቻችን አምባሳደሮች ናቸው፡፡ ዋነኛ አምባሳደሮች እነዚህ ዜጎች ናቸው የሚል አስተሳሰብ ነው አሁን የተያዘው፡፡ ስለዚህ በሪፎርሙ ለኢትዮጵያ ምርቶች ገበያ ማምጣት፣ ቱሪስቶችን ማምጣት አንዱ ተልዕኮ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ዜጎችን ማገልገል ነው፡፡ አሁን ውጭ ጉዳይ እያካሄደ ያለው ማሻሻያ፣ የአስተሳሰብም የአሰራርም ለውጥ የሚያመጣ ነው፡፡ ለ1 ሳምንት ለአምባሳደሮች እየተሰጠ ያለው ስልጠናም በዚሁ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ አሁን በአለማቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ጥቅሞቿን እንዴት ነው የምታስጠብቀው የሚለውም ዋናው ጉዳይ ነው፡፡ በአረብ ሃገር ያሉ ዜጎቻችንን እንዴት ነው ማገልገል የምንችለው? የታሰሩትን እንዴት ነው የምናስፈታው? የሚሉት በሙሉ በስልጠናው ተካትተዋል፡፡ ኤምባሲዎች ማረፊያ ቦታ ሳይሆኑ የሥራ ቦታ ናቸው የሚል ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት፡፡      

Read 293 times