Saturday, 19 January 2019 00:00

በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከ2 ወራት በላይ የቆየው የኒጀሩ ስደተኛ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ለስምንት አመታት ወደኖረባትና ህገወጥ ስደተኛ ተብሎ ወደተመለሰባት እስራኤል በድጋሚ ለማቅናት በጉዞ ላይ የነበረው የኒጀሩ ስደተኛ ኢሳ ሙሀመድ፤ ለቀጣይ ጉዞ እረፍት ባደረገበት የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በቁጥጥር ስር ከዋለበት ጊዜ አንስቶ ከ2 ወራት በላይ የስቃይ ኑሮን እየገፋ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ተሳፍሮ ወደ እስራኤል ለመግባት በጉዞ ላይ የነበረውና በህዳር ወር መጀመሪያ ላይ ቦሌ አየር ማረፊያ ውስጥ ለትራንዚት ባረፈበት ወቅት በኢትዮጵያ ፖሊሶችና በእስራኤል መንግስት ተወካዮች ትብብር ህገወጥ ስደተኛ ነህ ተብሎ በቁጥጥር ስር የዋለው ኢሳ መሀሙድ፣ ከአየር ማረፊያው ሰራተኞች የሚሰጠውን ምግብ እየተመገበና ወንበሮች ላይ እያደረ ከሁለት ወራት በላይ የስቃይ ኑሮን በመግፋት ላይ እንደሚገኝ ግሎባል ቮይስስ ዘግቧል፡፡
ኢሣ ሙሀመድ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 2008 ሁለት ጊዜ ከእስራኤል መባረሩን ይናገራል። በመጀመሪያው ተባርሮ አገሩ ኒጀር ሲመለስ የእስራኤል ህጋዊ የጉዞ ሰነድ ስለነበረው፣ ወደ እስራኤል ዳግም ተመልሶ ተጓዘ፡፡ እስራኤል ሲደርስ የጉዞ ሰነዱን ነጥቀው ወደ አገሩ መለሱት፡፡ አገሩ ሲገባ ኒጀርነቱን ወይም እስራኤልነቱን የሚያረጋግጥ ህጋዊ የጉዞ ሰነድ ማቅረብ አልቻለም፡፡ ለ8 ቀናት በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በኢትዮጵያ በኩል፣በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ እስራኤል እንዲመለስ ተደረገ፡፡ ቦሌ ዓለማቀፍ አየር መንገድ ሲደርስ ግን የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከእስራኤል መንግስት ጋር በመተባበር ወደ እስራኤል ተሳፍሮ እንዳይጓዝ አገዱት፡፡
የ24 አመቱ ኢሣ ሙሀመድ ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ፖሊስ ባይታሰርም የሚሄድበት በማጣቱ እስካሁንም በአየር ማረፊያው ውስጥ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ስደተኛው በአዲስ አበባ የሚገኘው የኒጀር ኢምባሲ ድጋፍ እንዲያደርግለት ቢጠይቅም የአገሪቱ ዜጋ መሆኑን የሚያረጋግጥ ህጋዊ ሰነድ ባለመያዙ ሊሳካለት እንዳልቻለ ገልጧል፡፡

Read 1010 times