Saturday, 19 January 2019 00:00

ከ17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በፊት

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 • 251 ቀናት ቀርተዋል፤ በቴሌቭዥን ስርጭት እስከ 6 ቢሊዮን ድምር ተመልካች ተጠብቋል፡፡
  • ኳታር ከ236.2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ አድርጋለች፡፡
  • በ2021 እ.ኤ.አ በአሜሪካ ዩጂን፤ በ2023 እ.ኤ.አ በሃንጋሪ ቡዳፔስት…
  • በ2025 በአፍሪካ ኬንያ ወይስ ናይጄርያ?
  • በ2019 እ.ኤ.አ ውጤታማ ይሆናሉ የተባሉ የኢትዮጵያ አትሌቶች ነፃነት እና ሰለሞን ናቸው፡፡
  • ባለፉት 16 የዓለም ሻምፒዮናዎች ኢትዮጵያ 77 ሜዳልያዎች ሰብስባለች፡፡ (27 የወርቅ፤ 25 የብርና 25 የነሐስ ሜዳልያዎች)


    የኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ለምታስተናግደው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 251 ቀናት ቀርተዋል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው  ከ200 በላይ አገራትን የሚወክሉ ከ2000 በላይ አትሌቶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። በኳታር የዓለም ሻምፒዮና ብሄራዊ አዘጋጅ ኮሚቴ ልዩ እቅድ መሰረት ከመላው ዓለም ከ3ሺ በላይ የሚዲያ ተቋማት እንደሚጋበዙ እየተገለፀ ሲሆን፤ 200  መዳረሻዎችን በሚሸፍን የቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት እስከ 6 ቢሊዮን ድምር ተመልካች ለማግኘት ተጠብቋል፡፡
ዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በ2019 እኤአ የውድድር ዘመን ላይ በሚያካሂዳቸው አጠቃላይ  ሂደቶች ስኬታማ ለመሆን ይፈልጋል፡፡ ከ5 ሳምንት በኋላ በዴንማርክ ፤ አሁሩስ የሚካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና  ከዚያም በጃፓን ዮኮሃማ  የዓለም ዱላ ቅብብል ሻምፒዮና ዋናዎቹ ሲሆኑ፤ ዳይመንድ ሊግ፤ ዎርልድ ቻሌንጅ፤ በዎርልድ ኢንዶር ቱር እና ሌሎች ውድድሮች የተቀሩት  የውድድር ዘመኑ መርሃ ግብሮች ናቸው፡፡ ኳታር ከምታዘጋጀው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 10 ወራት በኋላ  ደግሞ በ2020 እኤአ ላይ ጃፓን የምታስተናግደው 33ኛው ኦሎምፒያድ ነው፡፡
በ17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ላይ ያለ ሚኒማ መሳተፍ የሚችሉት ያለፈው የዓለም ሻምፒዮኖች፤ የ2019 ዳይመንድ ሊግ አሸናፊዎች፤ የተለያዩ የአይኤኤፍ ዙር ውድድር ሻምፒዮኖች ናቸው፡፡ አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ለዓለም ሻምፒዮናው የተሳትፎ ሚኒማ የውድድር ዘመኑን ዓለም አቀፍ ደረጃ ለመጠቀም ከጅምሩ አስቦ ነበር፡፡ ይሁንና ከአትሌቶች፤ አሰልጣኞች፤ ማናጀሮችና ኤጀንቶች በቀረቡ አስተያየቶች አሰራሩን ዘንድሮ ተግባራዊ ላለማድረግ ወሰኗል፡፡ ስለሆነም በተለያዩ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች በመሳተፍ ለሻለም ሻምፒዮናው የሚያበቁ አስፈላጊ ሚኒማዎችን ለማሟላት እንደሚቻል አመልክቷል፡፡ በተለይ  በ10ሺ፤ በማራቶን፤ በርምጃ፤ በዱላ ቅብብል እና ሌሎች ድብልቅ ስፖርቶች ከማርች 15 እስከ ሴፕቴምበር 14 በአይኤኤኤፍ ስር በሚካሄዱ ውድድሮች የሚመዘገብ ሚኒማ ወሳኝ ሲሆን ለሌሎች የስፖርት አይነቶች ደግሞ ከሴፕቴምበር 12,2018 እስከ ሴፕቴምበር 14,2019 በአይኤኤፍ እውቅና በተሰጣቸው ውድድሮች በተመዘገቡ ውጤቶች እና ሰዓቶች ለመመረጥ ይቻላል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ እስከ 15ኛ ደረጃ የሚያገኙ አትሌቶች የ10ሺ ሚኒማን እንዳሟሉ ይወሰድላቸዋል ተብሏል፡፡
የዓለም ሻምፒዮናው ከረጅም ጊዜ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ተጀምሮ ለ10 ቀናት የሚካሄድ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር IAAF ለዓለም ሻምፒዮናው የትኬት ሽያጭ በመጀመርያ ምዕራፍ ከወር በፊት ሲያከናውን በጀርመን፤ በዩናይትድ ኪንግደም በአሜሪካ እና በአውስትራሊያ ከፍተኛ ሽያጭ አግኝቶ ነበር፡፡ ሁለተኛው ምእራፍ የትኬት ሽያጭ በሚቀጥለው ወር የሚቀጥል ሲሆን፤ በዶሃ የዓለም ሻምፒዮናው አዘጋጅ ኮሚቴ እቅድ መሰረት ልዩ ጥቅም የሚያስገኝ ሙሉ የጉዞ ፖኬጅ ለመላው ዓለም ይፋ ከመሆኑም በላይ የውድድሩን ምልክት mascotም ጎን ለጎን እንደሚተዋወቅም ይጠበቃል፡፡
የዓለም ሻምፒዮናን ማዘጋጀት በኳታርና  ከዚያ በኋላ…
ኳታር በዋና ከተማዋ ዶሃ የዓለም ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት ስትነሳ የስፔኗ ባርሴሎና እና የአሜሪካዋ ዩጂን ከተሞች ተፎካክረዋታል፡፡ ምርጫውን በፍፁም ብልጫ በማሸነፍ አዘጋጅነቱን ከ5 ዓመታት በፊት በይፋ ስትረከብ ግን ከብዙ ትችቶች ጋር ነበር፡፡ በ2022 እኤአ እንደምታስተናግደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ሁሉ የ17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናውን አዘጋጅነትን ያገኘችበት ሁኔታ በተለያዩ አጀንዳዎች ተብጠልጥሎባታል፡፡ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ማህበር በ2019 እኤአ የዓለም ሻምፒዮናውን የሚያዘጋጅ አገር ለመምረጥ ባካሄደው ጉባኤ ላይ   የኳታር መንግስትና የኳታር አትሌቲክስ ፌደሬሽን የተለያዩ አባል ፌደሬሽኖችን ድጋፍና ድምፅ ለመደለል ሙከራ አድርጓል የሚለው የውዝግብ አጀንዳ ከሁሉ ትችቶች የመጀመርያው ነበር፡፡ ኳታር የዓለም ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት ባቀረበችው ማመልከቻ በድምሩ ከ236.2 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት መያዟን ይህም በስፖንሰርሺፕ 80 ሚሊዮን ዶላር በቴሌቭዥን ስርጭት እሰከ 29 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የዓለም ሻምፒዮናውን የሽልማት ገንዘብ በመሸፈን እስከ 7.2 ሚሊዮን ዶላር ወጭ እንደምታደርግ አስታውቃ ነበር።  በምርጫው የመጨረሻ ሂደት ላይ መስተንግዶውን ለማግኘት የተፎካከሯትን ሌሎች አገራት ለማሸነፍ በማለት የብሄራዊ ባንኳን የ5 ዓመት ስፖንሰርሺፕ በ30 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት እና ለ21 አባል ፌደሬሽኖች ትራክ መስርያ እስከ 7 ሚሊዮን ዶላር ለመለገስ አይኤኤኤፍን በይፋ ጠይቃለች የሚሉ መረጃዎች መሰማታቸው በከፍተኛ ደረጃ አስተችቷታል፡፡ ለነገሩ በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ ከሚንቀሳቀሱ ግዙፍ የፋይናንስ ተቋማት አንዱ የሆነው የኳታር ብሄራዊ ባንክ የዓለም ሻምፒዮናው አብይ ስፖንሰር ሲሆን ለሚቀጥሉት 4 ዓመታት በአይኤኤኤኤፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች አጋርነቱ ለመስራት መወሰኑ የሙስና ወሬዎቹን አብርዷቸዋል፡፡ በሌላ በኩል የኳታርን የዓለም ሻምፒዮና መስተንግዶ በውዝግብ የጠመደው ሌላው አጀንዳ ደግሞ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከዓለም ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ በተያያዘ የተነሱ እሰጥ አገባዎች ናቸው፡፡ የኳታር መንግስት ለሽብርተኞች ሙሉ ድጋፍ ይሰጣል በሚል አቋማቸው የአረቡ ዓለም ሃያል አገራትና ሌሎችም ዓለም ሻምፒዮናውን ላለማሳተፍ እንደሚወስኑ ሲገልፁ ነበር፡፡ በተለይ ሳውዲ አረቢያ፤ ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ፤ ባህሬንና ግብፅ ይህን አቋማቸውን በይፋ በማስተዋወቅ ተሳትፏቸውን እንደሚሰርዙ በይፋ እስከመግለፅ ቢደርሱም፤ የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ፕሬዝዳንት እንግሊዛዊው ሴባስትያን ኮው በዓለም ሻምፒዮናው ተሳትፎ ላይ ተለዋዋጭ የፖለቲካ ውዝግቦች ተፅእኖ ማሳደር እንደሌለባቸው በመጥቀስ የሁሉንም አገራት ተሳትፎ እንደሚጠበቁ በመናገር ተሳትፎን መሰረዝ ለቅጣት እንደሚያበቃ ማሳሰባቸው ውሳኔያቸውን እንዲያጤኑ አስገድዷቸዋል፡፡ ከዚያም በኋላ  የኳታር ህዝብ ለስፖርት ብዙም ፍቅር ስለሌለው የዓለም ሻምፒዮናውን  የተመልካች ድርቅ ይገጥመዋል በሚል ስጋታቸውን በመግለፅም የተሟገቱም ነበሩ፡፡
ከሁሉም አወዛጋቢ አጀንዳዎች በኋላ የኳታር መንግስት እና ብሄራዊ አዘጋጅ ኮሚቴው የዓለም ሻምፒዮናው በዘመናዊ ስታድዬም፤ ቴክኖሎጂ፤ ምርጥ እና ዘመናዊ ትራክ፤ በልዩ ልዩ ጥቅሞች በተሞላ መስተንግዶ እንዲሁም በቲቪ ነስርጭት ከፍተኛ ድምቅት እንደሚኖረው በልበሙሉነት እየተናገሩ ቆይተዋል፡፡ ዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር የዓለም ሻምፒዮናው 1 ዓመት ሲቀረው የኳታርን አጠቃላይ ዝግጅት በመገምገም ፍጹም መርካቱን የገለፀ ሲሆን  ባለፉት 6 ወራት የ30 አገራት አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን አመራሮችና አሰልጣኞች ዶሃን በመጎብኘት በነበራቸው ተመክሮም መደሰታቸውን በይፋ መናገራቸው ማስተማመኛ ሆኗል፡፡ በኳታር የስፖርት መሰረተልማቶች፤ የአየር ሁኔታ መቆጣጠርያ ቴክኖሎጂ ፤ በተሟላ የትራንስፖርት ፤ የሆቴል እና ሌሎች ዝግጅቶች በማድነቃቸው ነው፡፡
ኳታር ባለፉት 21 ዓመታት ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች በማስተናገድ የተወሰኑ ልምዶችን አካብታለች፡፡ በአትሌቲክስ የመጀመርያው ዓለም አቀፍ የውድድር መስተንግዶዋ በ1997 የተዘጋጀው ግራንድ ፕሪ ሲሆን በ2010 እኤአ ላይም የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናን በተሳካ ሁኔታ ማሰናዳቷም የሚጠቀስ ነው፡፡
በነገራችን ላይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኤሽያ አህጉር ሲዘጋጅ ኳታር አምስተኛዋ አገር ናት። ከኳታር በፊት በ2007 እኤአ የጃፓኗ ኦሳካ፤ በ2011 የኮርያዋ ዳጉ እንዲሁም በ2015 የቻይናዋ ቤጂንግ ሻምፒዮናውን አዘጋጅተዋል፡፡ በዓለም የአትሌቲክስ አስተዳደር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዓለም ሻምፒዮናው በአፍሪካዊ አገር እንዲዘጋጅ እየተመከረ መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ካለፉት 17 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ፊንላንድ በሄልሲንኪ በ1983 እና በ2005፤ ጃፓን በቶኪዮ እና በኦሳካ  ከተሞች በ1991 እና በ2007 እንዲሁም ጀርመን በስቱትጋርትና በበርሊን በ1993 እና በ2009 እኤአ ሁለት ጊዜ የማዘጋጀት እድል የተሰጣቸው አገራት ነበሩ፡፡ በጣሊያን ሮም በ1987፤ በስዊድን ጉተንበርግ በ1995፤ በ1997 በግሪክ አቴንስ፤ በ199 በስፔን ሲቪያ፤ በካናዳ ኤድመንተን በ2001፤ በፈረንሳይ ሴንትዴኒስ  በ2003፤ በደቡብ ኮርያ ዳጉ በ2011፤ በራሽያ ሞስኮ በ2013 ፤ በቻይና ቤጂንግ በ2015 እንዲሁም በእንግሊዝ ለንደን በ2017 ሌሎቹ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ተካሂደዋል፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ከኳታር በኋላ በ2021 እኤአ 18ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን የአሜሪካዋ ዩጂን እንዲሁም በ2023 እኤአ ደግሞ 19ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን የሃንጋሪዋ ቡዳፔስት እንዲያዘጋጁ መርጧቸዋል፡፡  በ2025 እኤአ ላይ ግን  አፍሪካዊ አገር 20ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና  እንዲያዘጋጅ አይኤኤኤፍ ፍላጎት እንዳለው ለማወቅ ተችሏል። ይህን ተከትሎም 6 የአፍሪካ አገራት አልጄርያ፤ ግብፅ፤ ኬንያ፤ ሞሮኮ፤ ናይጄርያ እና ደቡብ አፍሪካ ለመስተንግዶው  ያላቸውን ፍላጎት አስታውቀዋል። ከመካከላቸው ብቁውን አስተናጋጅ አገር ለመምረጥ ሃላፊነቱ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌደሬሽን መውሰዱንም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አንድ አዘጋጅ አገር የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሲያዘጋጅ ከ30ሺ በላይ ተመልካች የሚያስተናግድ ዘመናዊ ስታድዬም፤ ተጨማሪ የልምምድ ማዕከልና ማረፊያ ሆቴሎች፤ ለሽልማት ገንዘብ፤ እንዲሁም ለፀጥታ፤ ለደህንነት እና ለአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት እስከ 30 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደሚያስፈልገው አይኤኤኤፍ ይገልፃል፡፡ በታሪክ የመጀመርያውን የዓለም ሻምፒዮና በአፍሪካ አህጉር ለማዘጋጀት የምስራቅ አፍሪካዋ ኬንያ እና የምእራብ አፍሪካዋ ናይጄርያ ከፍተኛ አቅምና ፍላጎት እንዳላቸው ተሰምቷል፡፡ ባለፈው አመት በሃምሌ ወር አጋማሽ ላይ የአይኤኤኤፍን ሀ 18 የዓለም አትሌቲክሰ ሻምፒዮና ያስተናገደችው ኬንያ በቀጣይነት ሀ 20  የዓለም አትሌቲክሰ ሻምፒዮና በቅርቡ እንድታዘጋጅ እድል ከተሰጣት በኋላ በቀጣይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን የምታዘጋጅበትን እቅድ እንድታስብ አስችሏታል፡፡ ኬንያ በ2007 ላይ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን ከዚያም በኋላ ባለፈው ዓመት እና ዘንድሮ ሁለቱን የታዳጊና ወጣት የዓለም ሻምፒዮናዎች ያስተናገደችበት ልምዷ ምናልባትም በአፍሪካ ምድር ሊዘጋጅ የታሰበውን የዓለም ሻምፒዮና ያለተቃናቃኝ እንድትረከብ ይደግፋታል፡፡ ዋና ተፎካካሪ የምትሆነው በ2018 የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳካ ዝግጅት ያስተናገደችው ናይጄርያ ስትሆን ለአዘጋጅነቱ ያላትን ፍላጎት በተደጋጋሚ እያስታወቀች ነው፡፡
ካሊፋ ዓለም አቀፍ  ስታድዬምና ልዩ ቴክኖሎጂዎቹ…
በኳታር የቀድሞ ኢሚር ካሊፋ ቢን ሃማድ አል ታህኒ መታሰቢያነት ካሊፋ ዓለም አቀፍ ስታድዬም በ90 ሚሊዮን ዶላር ወጭ የታነፀ  የኳታር ብሄራዊ ስታድዮም ሲሆን የዶሃ የስፖርት ከተማ ዘመናዊ ኮምፕሌክስ አካል ነው፡፡ ዘመናዊ ኮምፕሌክሱ ከስታድዬሙ በተጨማሪ አስፓየር አካዳሚ፤ ሃማድ አካውቲክ ማዕከልንና አስፓየር ታወርንም የሚያካትት ነው፡፡ በ2022 እኤአ ላይ ዓለም ዋንጫን ከሚያስተናግዱ ስታድዬሞች ቀድሞ አገልግሎት መስጠት የጀመረውና 48ሺ ተመልካች የሚይዘው ስታድዬሙ ከዓለም ሻምፒዮናው በፊት በሚያዚያ ወር በሚዘጋጀው የኤስያን ጌምስ ሙለሙሉ ብቃቱ የሚፈተሽ ይሆናል፡፡ ላለፉት 42 ዓመታት የኳታር ብሄራዊ ቡድን ዋና ሜዳ ሆኖ ሲያገለግል የቆየው ካሊፋ፤ በ2004 እኤአ የገልፍ ካፕ ኦፍ ኔሽን፤ በ2006 ኤስያን ጌምስ፤ በ2011 ላይ የኤስያ ካፕ የፍፃሜ ጨዋታ፤ በ2011 የፓን አረብ ጌምስን አስተናግዷል፡፡
በዘመናዊነቱ እያነጋገረ የሚገኘው ስታድዬሙ በአየር ማቀዝቀዝ ቴክኖሎጂው፤ ለተመልካች በሚመች ዲዛይኑ ሻምፒዮናውን እንደሚያደምቅ እየተገለፀ ነው፡፡ በስታድዬሙ ዙርያ የተገጠሙት ከ500 በላይ የጄት ሞተር የመሰሉ ማሽኖች የሚሰራው ቴክኖሎጂ ለተመልካች እና ለአትሌቶች ምቹ አየር ንብረት የሚፈጥርና የንፋሱን መጠን የሚቆጣጠር እንደሆነ የገለፁት አዘጋጆች ከሌሎች የማቀዝቀዛ ቴክኖሎጂዎች በ40 በመቶ የሚቀንስ ኃይል የሚጠቀም መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በኳታር ከባድ ሙቀት የተነሳ አንዳንድ የአጭር ርቀትና የማራቶን ውድድሮች በእኩለ ሌሊት ለማድረግ መታሰቡ ግን ጥርጣሬ ፈጥሯል፡፡ በስታድዬሙ የተገጠመው የአየር ማቀዝቀዣ ቴክኖሎጂ በውጭ ያለውን ሙቀት ከ40 ወደ 20 እና 26 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በማውረድ ሙቀቱን ለውድድር የሚመች አድርጎ እንደሚያስተካክል በበርካታ ሙከራዎች ቢረጋጋገጥም የአንዳንድ አገራት ፕሮፌሽናል አትሌቶች ስጋታቸውን ከመግለጽ አልተቆጠቡም፡፡ በውድድር ወቅት በስታድዬሙ ውስጥ አየሩ ሊስተካከል ቢችልም ከውድድር በፊት በሚኖር ቆይታ በብቃታቸው ላይ ተፅእኖ ሊያሳድር የሚችል የአየር ንብረት መኖሩ አሳስቧቸዋል፡፡ በሌላ በኩል የዓለም ሻምፒዮናውን የተሳካ ያደርጋሉ ከተባሉ ቴክኖሎጂዎች የሚጠቀሰው በስታድዬሙ የተነጠፈው ባለወይንጠጅ ቀለም የመሮጫ ትራክ ነው፡፡ ሞንዶ ትራክ Mondotrack WS የተባለው ይህ የመሮጫ ትራክ በዓለም ሻምፒዮናው የአትሌቲክስ ውድድሮች ፈጣን ሰዓቶች እንዲመዘገቡ ያበረታታል ተብሏል፡፡  በኳታር የዓለም ሻምፒዮናው ብሄራዊ አዘጋጅ ኮሚቴ በውድድሩ ሰሞን በዘመናዊ ድሮን ካሜራዎች የሚነሱ ምስሎችና የቪድዮ ቀረፃዎች አዲስ ምዕራፍ የሚከፈትባቸው እንደሚሆኑ ሲገልፅ፤ የሻምፒዮናው አጠቃላይ ሂደት በጥልቅና የተሟላ የብሮድካስት ተግባራት ሰፊ ሽፋን እንደሚያገኝ እና በማህበራዊ ሚዲያው የተጧጧፈ ትኩረት ለመፍጠር ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቋል።  የካሊፋ ዓለም አቀፍ ስታድዬም በግንቦት ወር የዳይመንድ ሊግ ውድድር በሚያዚያ የኤሽያን አትሌቲክስ ሻምፒዮና በማዘጋጀት እነዚህን ልዩ ቴክኖሎጂዎች እና የዓለም ሻምፒዮና መሰናዶዎች ላይ የመጨረሻ ግምገማ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ ከኳታር በፊት እና የዓለም ሻምፒዮና ታሪኳ
በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ በሚካሄደው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በሚኖራት ተሳትፎ መዘናጋት ይስተዋላል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናው መካሄጃ ወቅት መቀየር፤ የኳታር ሞቃታማ የአየር ንብረት፤ የብሄራዊ ቡድን በቂ እና የተሟላ ትኩረት በተሰጠው ዝግጅት አለመስራት እንዲሁም በአትሌቶች ዲስፕሊን ያሉ ችግሮች ስጋት የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ከወዲሁ መጀመር አለበት፡፡
በ2019 የውድድር ዘመን በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ የውድድር መድረኮች ውጤታማ እንደሚሆኑ ከተጠበቁ የኢትዮጵያ አትሌቶች መካከል በተለይ ሁለቱ በተደጋጋሚ ስማቸው እየተነሳ ይገኛል፡፡ በሴቶች አትሌት ነፃነት ጉደታ በወንዶች አትሌት ሰለሞን ባረጋ  ናቸው፡፡ በ2018 የዓለም የግማሽ ማራቶን ሪከርድን በሆነ ጊዜ ያስመዘገበችው አትሌት ነፃነት ጉደታ ከዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በፊት በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ሊሳካላት እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ነፃነት በዓለም ሻምፒዮናው በየትኛው የውድድር መደብ እንደምትሳተፍ ግልጽ ባይሆንም ፤ ከ18 ዓመታት በላይ ሳይሰበር የቆየውን የፓውላ ራድክሊፍ ሪከርድ ማሻሻል ከሚችሉ አትሌቶች ግንባር ቀደም ሆና እየተጠቀሰች ናት፡፡ በሌላ በኩል ባለፈው ዓመት በዳይመንድ ሊግ የ5ሺ ሜትር ሻምፒዮን ሊሆን የበቃው አትሌት ሰለሞን ባረጋ በ2019 ከፍተኛ ስኬት ያገኛል በሚል በአይኤኤኤፍ አዳዲስ ኮከቦች ተርታ ተጠቅሷል፡፡ በውድድር ዘመኑ ከ20 ዓመት በታች ምርጥ የኢትዮጵያ አትሌት ሆኖ የሚቀጥለው ሰለሞን ባረጋ በ5ሺ ሜትር ለዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው የሜዳልያ ውጤት ከመጠበቁም በላይ ሳይሰበር ለ12 ዓመታት የቆየውን የ5ሺ ሜትር ሪከርድ እንደሚያሻሽል ግምት አግኝቷል፡፡
ከ2 ዓመት በፊት የእንግሊዟ ለንደን ባስተናገደችው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በ13 የተለያዩ ውድድሮች 46 አትሌቶችን በማስመዝገብ የተሳተፈች ቢሆንም የሚያስደስት ውጤት አልነበራትም፡፡ ለኢትዮጵያ በሴቶች 10ሺ ሜትርና በወንዶች 5ሺ ሜትር የተመዘገቡት 2 የወርቅ ሜዳልያዎች ብቻ መሆናቸው ከሁለት ተከታታይ የዓለም ሻምፒዮናዎች በኋላ የተመዘገቡ አዳዲስ ስኬቶች ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል በሴቶች 10ሺ ሜትር፤ በወንዶች ማራቶን እና በሴቶች 5ሺ ሜትር  3 የብር ሜዳልያዎች በተጨማሪ ተገኝተዋል፡፡ ከሜዳልያ ውጤቶች ባሻገር ደግሞ በ2 አራተኛ ደረጃዎች፤ በ3 አምስተኛ ደረጃዎች፤ በ1 ስድስተኛ ደረጃ፤ በ3 ሰባተኛ ደረጃዎች እንዲሁም በ2 ስምንተኛ ደረጃዎች 11 ዲፕሎማዎች ለኢትዮጵያ ቡድን ተመዝግበዋል፡፡ ከ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኋላ ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው የተሳትፎ ታሪኳ ያስመዘገበቻቸው 77 ሜዳልያዎች የደረሱ ሲሆን (27 የወርቅ፤ 25 የብርና 25 የነሐስ ሜዳልያዎች) ናቸው፡፡ በተጨማሪ 20 ጊዜ 4ኛ ደረጃዎች፤ 18 ጊዜ 5ኛ ደረጃዎች፣ 14 ጊዜ 6ኛ ደረጃዎች ፣ 21 ጊዜ 7ኛ ደረጃዎች እንዲሁም 15 ጊዜ 8ኛ  ደረጃዎች ተመዝግበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ውጤታማ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አትሌቶች
በወንዶች ኃይሌ ገሥላሴ 4 የወርቅ፣ 2 የብር፣ 1 የነሀስ ሜዳሊያዎች
በሴቶች ጥሩነሽ ዲባባ  5 የወርቅ - 1 የብር፣ 1 የነሐስ ሜዳሊያዎች
በኢትዮጵያ አትሌቶች የተያዙ የዓለም ሻምፒዮና ሪከርዶች
ብርሃኔ አደሬ በ10 ሺ ሜትር 30፡10.18 (2003 እ.ኤ.አ)
ቀነኒሳ በቀለ በ10 ሺ ሜትር 26፡46.31 (2009 እ.ኤ.አ)
አልማዝ አያና በ5 ሺ ሜትር 14፡26.83 (2015 እ.ኤ.አ)
የኢትዮጵያ 27 የወርቅ ሜዳልያዎች በ16 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች
ኢትዮጵያ ከ1983 እሰከ 2017 እኤአድረስ በተካሄዱት 16 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች 27 የወርቅ ሜዳልያዎች አስመዝግባለች፡፡እነዚህን  የዓለም ሻምፒዮና 27 የወርቅ ሜዳልያዎች ያስመዘገቡት 15 የተለያዩ አትሌቶች የተጎናፀፏቸው ሲሆን 14 በሴቶች እንዲሁም 13 በወንዶች የተገኙ ናቸው፡፡ 16 የወርቅ ሜዳልያዎች በ10ሺ ሜትር (9 በወንዶች እና 7 በሴቶች)፤ 7 የወርቅ ሜዳልያዎች በ5ሺ ሜትር (5 በሴቶች  እና 2 በወንዶች)፤ 2 የወርቅ ሜዳልያዎች በማራቶን (1 በወንዶች እና 1 በሴቶች)፤ 1 የወርቅ ሜዳልያ በ1500 ሜትር (በሴቶች) እንዲሁም 1 የወርቅ ሜዳልያ በ800 ሜትር (በወንዶች) ናቸው፡፡
ጥሩነሽ ዲባባ  5 የወርቅ ሜዳልያዎች-በ10ሺ ሜትር 3 የወርቅ ሜዳልያዎች (በ2005 እኤአ ሄልሲንኪ፤ በ2007 እኤአ ኦሳካ እንዲሁም በ2013 እኤአ ሞስኮ) በ5ሺ ሜትር 2 የወርቅ ሜዳልያዎች (በ2003 እኤአ ፓሪስ እና በ2005 እኤአ ሄልሲንኪ)
ቀነኒሳ በቀለ 5 የወርቅ ሜዳልያዎች -በ10ሺ ሜትር4 የወርቅ ሜዳልያዎች (በ2003 ፓሪስ፣ በ2005 ሄልሲንኪ፤ በ2007 እኤአ ኦሳካ እና በ2009 እኤአ በርሊን) በ5ሺ ሜትር 1 የወርቅ ሜዳልያ ( በ2009 እኤአ በርሊን) ሳላዲን
ኃይሌ ገብረስላሴ4የወርቅ ሜዳልያዎች - በ10ሺ ሜትር 4 የወርቅ ሜዳልያዎች (በ1993 እኤአ ስቱትጋርት፤ በ1995 እኤአ ጉተንበርግ፤ በ1997እኤአ አቴንስ  እንዲሁም በ1999 እኤአ ሲቪያ)    
መሰረት ደፋር 2 የወርቅ ሜዳልያዎች- በ5ሺ ሜትር (በ2007 እኤአ ሄልሲንኪ እና በ2013 እኤአ ሞስኮ)
ገዛሐኝ  አበራ 1 የወርቅ ሜዳልያ- በማራቶን(በ2001 እኤአ ኤደመንተን)
ማሬ ዲባባ 1 የወርቅ ሜዳልያ- በማራቶን (በ2015 እኤአ ቤጂንግ)
ጌጤ ዋሚ 1 የወርቅ ሜዳልያ- በ10ሺ ሜትር(በ1999 እኤአ ሲቪያ)
ደራርቱ ቱሉ 1 የወርቅ ሜዳልያ- በ10ሺ ሜትር (በ2001 እኤአ ኤድመንተን)
ብርሃኔ አደሬ1 የወርቅ ሜዳልያ - በ10ሺ ሜትር (በ2003 እኤአ ፓሪስ)
ኢብራሂም ጄይላን 1 የወርቅ ሜዳልያ - በ10ሺ ሜትር (በ2011 እኤአ ዴጉ)
አልማዝ አያና 2 የወርቅ ሜዳልያ - በ10ሺ ሜትር (በ2017 እኤአ ለንደን)
በ5ሺ ሜትር (በ2015 እኤአ ቤጂንግ)
ገንዘቤ ዲባባ  1 የወርቅ ሜዳልያ- በ1500  ሜትር (በ2015 እኤአ ቤጂንግ)
መሐመድ አማን 1  የወርቅ ሜዳልያ- በ800 ሜትር (በ2013 እኤአ ሞስኮ)
ሙክታር ኢድሪስ 1 የወርቅ ሜዳልያ በ5ሺ (በ2017 እኤአ ለንደን)

Read 6369 times