Print this page
Friday, 11 January 2019 00:00

ለታራሚዎች በድብቅ የሚገቡ ሞባይል ስልኮች እየተበራከቱ ነው ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከኃላፊዎች ውጭ ሞባይል ይዞ መግባት አይፈቀድም


     በአዲስ አበባ የቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤትና ቂሊንጦ የቀጠሮ ማረሚያ ቤት ለሚገኙ ታራሚዎች በድብቅ የሚገቡ ሞባይል ስልኮች መበራከታቸውን ምንጮች ገለፁ፡፡
ወደ ሁለቱም ማረሚያ ቤቶች ሞባይል ይዞ መግባት የሚፈቀድላቸው ለአመራሮቹ ብቻ ቢሆንም በርካታ ታራሚዎች ግን ሞባይል አስገብተው እንደሚጠቀሙ የገለፁት ምንጮች፤ አንድ ሞባይል ስልክ ለማስገባት እስከ 20 ሺ ብር እንደሚከፍሉ ተናግረዋል፡፡ ሞባይሎቹን ቻርጅ የሚያደርጉላቸው ደግሞ ቢሮ ውስጥ የሚሰሩ የማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ለአንድ የሞባይል ቻርጅ ማድረጊያ 150 ብር እንደሚያስከፍሉ የጠቆሙት ምንጮቻችን፤ አንድ የመቶ ብር ካርድም እስከ 500 ብር እንደሚሸጥ ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል የማረሚያ ቤቱ ጥቂት ፖሊሶች ለአንድ ደቂቃ 30 ብር እያስከፈሉ ታራሚዎችን ያስደውሉ ነበር ያሉት ምንጮች አሁን ሞባይል የገባላቸው ታራሚዎችም ለአንድ ደቂቃ 20 ብር እያስከፈሉ እንደሚያስደውሉ ታውቋል፡፡
የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገረመው አያሌው ስለ ጉዳዩ ከአዲስ አድማስ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ ስለ ጉዳዩ በጭምጭምታ ከመስማት በቀር የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ጠቁመው፣ ከኃላፊዎች ውጪ ታራሚዎችም ሆኑ ሰራተኞች ወደ ማረሚያ ቤት ስልክ ይዘው እንደማይገቡ ገልፀዋል፡፡

Read 943 times
Administrator

Latest from Administrator