Friday, 11 January 2019 00:00

ህገ መንግስትን ማስተማር ለአገሩ የሚቆረቆርና ያገባኛል የሚል ዜጋ መፍጠር ነው ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 ህገ መንግስቱን ለዜጐች ማስተማር ለአገሩ የሚቆረቆር፣ ያገባኛል የሚልና በአስተሳሰቡና በአመለካከቱ የተቀየረ ዜጋ መፍጠር ነው ተባለ። አገሩንና ወገኑን የሚወድና ለአገሩ የሚቆረቆር ትውልድ ከራሱ ባሻገር ሌሎችን መመልከት ስለሚችል፣ ለአገር ግንባታው አሻራውን ማኖር እንደሚችልም ተገልጿል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውይይት የቀረበውና አባላቱ በስፋት እየተወያዩበት የሚገኘው የህገ መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ እንደተመለከተው፤ ከዚህ ቀደም የነበረው የህገ መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ባልተደራጀ መልኩ የሚከናወን፣ ወጥነት ያለው አሰራርና አደረጃጀት ያልነበረው፣ ዜጐችን ተደራሽ ያላደረገና አሳታፊ እንዳልነበረ ተገልጿል፡፡
ዜጐችን ህገ መንግስት ማስተማር በቅብብሎሽ አገር የመገንባት አንዱ ገጽታ እንደሆነ ያመለከተው ይኸው ረቂቅ አዋጅ የህገ መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮን በስርዓትና በስልት ለመምራት ታስቦ የማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱም ተጠቁሟል፡፡
ዜጐች ህገ መንግስታቸውን እንዲያውቁና እንዲገነዘቡ በማድረጉ ረገድ እስከ አሁን የተሰራው ሥራ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ያልሆነ፣ በቅንጅትና በትስስር ያልተመራ እንደነበር ያመለከተውና ለምክር ቤቱ አባላት የቀረበው የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ እንደሚያመላክተው፤ ባለቤትና ተጠያቂነት ያለው ህጋዊ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ማቋቋም ተገቢ ሆኖ መገኘቱን ይጠቁማል፡፡ ማዕከሉ ተጠሪነቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤትና በፌዴሬሽን ም/ቤት ስር ለሚደራጀውና አስራ ሁለት አባላት ላሉት አማካሪ ኮሚቴ እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡  

Read 609 times