Monday, 14 January 2019 00:00

ሞ ኢብራሂም፤ አልበሽር ስልጣን ከለቀቁ ክሳቸው እንዲቋረጥላቸው ጠየቁ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 የሞ ፋውንዴሽን መስራች ትውልደ ሱዳናዊው ቢሊየነር ሞ ኢብራሂም፤ የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር በፈቃደኝነት ስልጣናቸውን የሚለቅቁ ከሆነ፣ አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የመሰረተባቸውን ክስ እንዲያቋርጥላቸው ጠይቀዋል፡፡
ለሳምንታት በዘለቀውና አልበሽር ከስልጣን እንዲወርዱ በሚጠይቀው ተቃውሞ ዙሪያ ከቢቢሲ ጋር ውይይት ያደረጉት ሞ ኢብራሂም፤ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ፈቃደኛ ሆነው ስልጣናቸውን በመልቀቅ አገሪቱንና ህዝቧን ከእልቂትና ከጥፋት ለመታደግ ከቻሉ በዳርፉር የጦር ወንጀሎችን ፈጽመዋል በሚል በአለማቀፉ ፍርድ ቤት የተመሰረተባቸው ክስ ሊቋረጥላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ሱዳናውያን አልበሽር ስልጣን እንዲለቅቁ በመጠየቅ በአደባባይ ተቃውሞ ማድረግ ከጀመሩ ሳምንታት የተቆጠሩ ሲሆን፣ መንግስት ያሰራቸው ተቃዋሚዎች ቁጥር ከ800 በላይ መድረሱ ተነግሯል። በርካታ ቁጥር ያላቸው ሱዳናውያን አልበሽርን ሲቃወሙ የሰነበቱ ሲሆን ባለፈው ረቡዕ ደግሞ አልበሽርን የሚደግፉ ሱዳናውያን በካርቱም የድጋፍ ሰልፍ አድርገዋል፡፡ አግባብነት የሌለው ተቃውሞ ስልጣናቸውን እንደማያስለቅቃቸው በይፋ ሲያስታውቁ የሰነበቱት ፕሬዚዳንቱም በስፍራው በመገኘት ለደጋፊዎቻቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ካናዳና ኖርዌይ ባለፈው ማክሰኞ ባወጡት መግለጫ፤ የአልበሽር መንግስት የተቃዋሚዎችን መብቶች እንዳይጥስ ጥሪያቸውን ማቅረባቸው የተዘገበ ሲሆን፣ መንግስት ተቃዋሚዎችን በገፍ ማሰሩንና መግደሉን የማያቋርጥ ከሆነ ማዕቀብ ሊጥሉበት እንደሚችሉም አስጠንቅቀዋል፡፡

Read 7723 times