Saturday, 26 May 2012 11:14

‘ሦስተኛዋ እንቁላል…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ‘ተፈላስፎ የበቃለት’ ሰውዬ ሳይቸግረው ሁለቱን እንቁላል “በሎጂክ ሦስት ነው…” ብሎ እንቁላል ሳያገኝ እንዳማረው የመቅረቱን ታሪክ ታውቋት የለ! ፍልስፍናውን ካሰማ በኋላ… “እማዬ ለእኔስ እንቁላል አይሰጠኝም እንዴ!” ሲል እናት “ሎጂክህን ብላ…” አይደል ያሉት! ይኸኔ ሴትዮዋ የኒቼ ሚስት ምናምን ቢሆኑ ኖሮ ይሄ አባባላቸው በየንግግሩ መሀል ይጠቀስላቸው ነበር፡፡ ቂ…ቂ…ቂ (እዚህ አገር ‘ፈረንጅ’ የተናገረው ነገር ሁሉ ከእግዚአብሔር ቃል ቀጥሎ የማይቆረጥ፣ የማይገሰስ ማድረግ አባዜ አለብን አይደል!)እናላችሁ… ዘንድሮ ብዙ ነገር “በሎጂክ ሦስት ነው…” አይነት እየሆነብን ግራ ገብቶናል፡፡ “አንተን አይምሰልህ እንጂ ደልቶሀል…” አይነት ስለ እኛ የማናውቀው ምስጢር ሲነገረን የምር… “ይሄን ያህል ከጊዜና ከዘመን ጋር ተራርቄያለሁ እንዴ!” ያሰኛል፡፡ሀሳብ አለን… የማናየውን፣ የማንዳስሰውን ነገር ሁሉ “በሎጂክ ሦስት ነው…” የሚሉን… አለ አይደል…

ሁለቷን ለእኛ ትተውልን ‘ሎጂክ ያመጣትን ሦስተኛዋን’ እነሱ ይወሰዱልንማ! አሀ… ገና ሦስተኛዋን ማየት የሚችል ዓይን አልተፈጠረልንማ! ልጄ ባዶው ሳህን ላየ የሌለውን ዳቦ ‘ተከምሮ’ ማየት መቻሉ ታላቅ ችሎታ ነዋ! (“አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው…” የሚለው ዘፈን በየመመገቢያ ቦታ በየእኩል ሰዓቱ እንዲዘፈን ይደረግልንማ! አሀ… ሰዋችን እኮ ‘ማን ከማን ያንሳል’ በሚል ኪሱን አራግፎ ጨረሰ!)እናማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… እኛ ‘ሳናየው፣ ሳንዳስሰው’ አለ የሚባለው ነገር ሁሉ የሚገኘው ‘የትኛዋ ሀገራችን’ ላይ እንደሆነ ተደናግሮናል! ልክ ነዋ… የ’ፋንታሲ’ ጉዳይ ከሆነ ከሎጂኳ እንቁላል ሌላ ስንት ምራቅ የምንውጥበት የቀን ህልም እያለን! (እኔ የምለው… ቻይኖቹ “እነኚህ ሰዎች ሌላ አገር አላቸው ወይ?” አሉ የተባሉት’ኮ ህዝቤ ባሌስትራና ማገር በሌሊት እየጫነ ሲሄድ አይተው ነው፡፡ ዘንድሮ ‘የሚጫነው’ ነገር እየበዛ ስለሄደ ጥያቄውን ራሳቸው መልሰውት… “እውነት እውነት እንላችኋለን፤ ነብር ዥንጉርጉርነቱን፣ ኢትዮጵያዊ የማያውቃት ሌላ አገሩን ሊረሱ ይቻላቸዋልን!” ሊሉን ይችላሉ፡፡)ቆይማ… የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ፡፡ እነኚህ ቻይኖቹ የዝሆን ጥርስ ምናምን ሲያሻግሩ የሚያዙት ለየትኛዋ አገራቸው እንደሆነ እነሱም ይግለፁልና! አሀ… እኛ’ኮ ዳግም አረቄያችንን ሲጠጡልን፤ ምስራችንን ሲበሉልን፤እንትናዬዎቻችንን… (ተቆርጦ የወጣ)… በቃ ጓዝ ጠቅልለው የቀሩ መስሎን ነበራ!እናላችሁ… የሦስተኛዋ እንቁላል ነገር ምን ያህል በተመሳሳይ ቋንቋ አውርተንም፤ በተመሳሳይ ቃላት ተጠቅመንም መግባባት እንዳቃተን የምታሳይ አይመስላችሁም! የምር እኮ ነገሩ ሲበዛባችሁ… “እነሱ እንዲህ ቁልጭ ብላ የታየቻቸው እንቁላል ምነው እኔ አላያትምማ!” ብላችሁ… አለ አይደል… ለክፉም ለደጉም ኢንተርኔት ላይ ስለ አልዛይመር በሽታ ምናምን ፅሁፍ ለማንበብ ባይገፋፋችሁ ነው!ጥያቄ አለን… የአማርኛ መዝገበ ቃላት ተከልሶ ይሰራልን፡፡ (‘ይሞታል እንዴ!’ የምትለዋ አባባል ምነዋ ቀረችሳ!) ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… በተመሳሳይ ቋንቋ ተነጋግረን ልንግባባ ያልቻልነው ምናልባት ብዙዎቻችን ‘የቃላት ትርጉም’ መለወጡን ስለማናውቅ ሊሆን ይችላል!እናላችሁ… ነገሩ ሁሉ ተለዋውጦ… እኛ አሁንም “አበበ በሶ በላ…” ላይ የቀረን ይመስላል፡፡ እንደ በፊቱ አተረጓጐምማ… በቃ… “አበበ በሶ በላ…” ጣጣ ፈንጣጣ የለውም… “በቃ በላ” ነው፡፡ ዘንድሮ ግን ‘ከቁንጫ ዓይን ስንጥር’ ለማውጣት የሚሞከርበት ዘመን ስለሆነ… “አበበ በሶ በላ…” ማለት እንደ ድሮ “በቃ በላ” ማለት መሆኑ ቀርቷል፡፡ አባባላችሁን ታስረዷታላችኋ!አለ አይደል… “ምግብ በተትረፈረፈበትና ‘ፔዛንቱ’ ሚሊየነር በሆነበት ጊዜ በሶ በላ ብሎ ነገር ማንን ለማሳጣት ነው?” ሊባል ይችላል፡፡ ወይም… “ከጀርባ ሌላ ስውር ዓላማ ካላዘለ በስተቀር በሰማንያ ሚሊዮን ህዝብ አገር አበበ ማነውና ነው ስሙ የሚጠቀሰው?” ተብሎ የ’ቤተሰብ ዛፋችሁ’ ጃንሜዳን ሊሸጥ ካስማማው ሰው ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡እናማ… የመግባባት ነገር አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ዘንድሮ… “ጨቡዴ ጩቤ ጨበጠ…” ማለት የዓረፍተ ነገር አሰካክ ማሳያ መሆኑ ቀርቶ “ክርክታና ወይራ በሞላበት አገር ሽመል ሳይጠፋ ጩቤን ምን አመጣው?” የሚል ‘ኢንቬስቲጌቲቭ ሪፖርቲንግ’ ነገር ሊያስከትል ይችላል፡፡ ጊዜ ተለውጧላ! የቃላት ፍቺ ተለውጧላ! መጀመሪያ ነገሮች ከ’ስውር ተልእኮ’ ነፃ መሆናቸው መጣራት አለበታ! (እኔ የምለው… ይሄ ሁሉ ለኮሜዲ የሚሆነ ‘ጥሬ ዕቃ’ ሞልቶን ሚስተር ቢን የሚሉት ሰውዬ ፊልም የማይሰራልንሳ! ድሮስ እንግሊዝ…)እግረ መንገዴን… የስፖርት ጋዜጠኞቻችን… ለአቅመ “የግል ተልእኮ…” ምናምን አቤቱታ እንኳንስ ደረሳችሁማ! እኔ’ኮ ገና በፊት “የሩኒ አባትና አጐት በቁማር ተያዙ…” ስትሉ “ይህ ዜና ከጀርባው ምን ተልእኮ አለው!” ብዬ አምቻችሁ ነበር፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…

 

ስሙኝማ… እንደ ልብ ተናጋሪ በዝቷል፡፡ ምን ያሳስብሃል አትሉኝም… ጉልበተኝነት ታች ወዳሉ ‘ወንበሮች’ እየወረደ መምጣቱ! ‘ባለፈው ዘመን’ (አቆጣጠሩን ማለቴ እንደሆነ ይሰመርበትማ!) “አንድ ጉሥ አውርደን ሁለት መቶ ሰማንያ ምናምን ንጉሥ ሾምን…” ነው ምናምን ያሉት ባለስልጣን…

ነገራቸው የሆነ ትንቢትነት ምናምን ያለው አይመስላችሁም! እናማ… ከሰንበቴ ማህበር አባላት ቁጥር ይልቅ ራሳቸው ላይ ዘውድ የጫኑ ንጉሦች ቁጥር ሲበዛ… አለ አይደል… ከግንቡ በሁለቱም ወገን ላለነው አሪፍ አይደለም፡“እስቲ ስትገቢ አይሻለሁ!” ብሎ የሚዝት የጥበቃ ሠራተኛ ባለበት አገር፤ “ከመሰለኝ ነው እንጂ ካልመሰለኝ ያንተን ፋይል የማውጣት ግዴታ የለብኝም…” የሚል የመዝገብ ቤት ሠራተኛ በሞላበት አገር፤ በየመመሪያው ላይ “ዋ! አንተን አያድርገኝ!” የምትለዋ ዛቻ በ’ቃለ አጋኖ’ ምልክት እየወከለ ደብዳቤ የሚበትን ‘ቦስ’ በሞላበት አገር… “ወንበር አካባቢ እስካልደረስክ ድረስ ምንም አትሆንም”

አይነት ‘የልብ ልብ’ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ለስንትና ስንት ጊዜ ሳይፈፀም የቀረን ነገር… “በአምስት ቀን ውስጥ ካላደረስክ ውርድ ከራሴ!” “በሦስት ቀን ውስጥ ጥርግ ብለህ ካልሄድክ ከእቃህ ጋር አብሬ እጠርግሃለሁ!” አይነት ቃና ያላቸው አነጋገሮች የሚጢጢዋን ኃላፊነት ሁሉ… አለ አይደል… ከናፖሊዮን ስርወ መንግሥት ጋር የማያያዝ ነገር ሊመስሉ ይችላሉ!እናማ… ጥራዝ ነጠቅነት እንደ ብዙ ነገሮች የሆነ የ’ጥራዝ ነጠቅነት ቀን’ ተዘጋጅቶለት “በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረ ሲሆን በመላው ዓለም ለማስፋፋት ከዩኔስኮ ጋር ንግግር እየተደረገ ነው…”

ተብሎ ፌሽታ ሊደረግለት ምንም ባልቀረበት ዘመን… “ኸረ ትንሽ እውቀት ያስፈልጋል!” የሚል ሲጠፋ የምር ያሳስባል፡፡ እንዴ… ለመኮረጅም እኮ የኩረጃ ታሪካዊ አመጣጥንና ያለፈው ስርአት እንዴት

‘ለሰፊው ህዝብ ጥቅም እንዳላዋለው’ (ቂ…ቂ…ቂ…) መተንተን ባያስፈልግም ዘዴውን ማወቅ ግን አሪፍ ነው፡፡ ለተርጓሚዎች እንደ ጥቆማ… ‘ሀምሳ ሦስት ምርጥ የአኮራረጅ ዘዴዎች’ የሚል መፅሐፍ ይውጣልንማ!እናላችሁ… ከእኛ በተቃራኒ ለቆመው ሁሉ “ጅራቱን እኮ በኮቱ ደብቆ ነው…” አየነት ነገር ባህል በሆነበት ዘመን የሌለውን ‘ሦስተኛ እንቁላል’ በሎጂክም ይሁን በምን ለማየት ከመሞከር ዓይናተን ሰር የፈጠጠውን መኖሩን ማመን አሪፍ ነው፡፡ እንደውም አሪፍ ብቻ ሳይሆን በዚህ ዘመን ላለነው የትናንቷ አቢሲንያ፣ የዛሬዋ ኢትዮጵያ፤ የነገዋ… (ቃሉ አልመጣልህ አለኝ)… ልጆች ሁሉ ‘የእውቀት ሁሉ መጀመሪያ’ ሊሆንልን ይችላል፡፡እናማ… እንደው ደግሞ “ይችን ሳምንት እንዴት አውለህ እንዴት ታሳድረኝ ይሆን!” በምንልበት ዘመን… “ባታውቀው ነው እንጂ ጠግበህ ተመችቶሀል…” አይነት የ’ሦስተኛ እንቁላል ሎጂክ’ ቃና ያላቸው ነገሮች ሲበዙ… አለ አይደል… ለሀኪምም ለበሽተኛም ደግም አይደል፡፡ድሮ ለታክሲ አሽከርካሪዎች ብቻ የነበረው አጉል ባህርይ ምን የመሳሰለውን መኪና ወደሚያሽከረክሩት ሁሉ እየተዛመተ ሲሄድ “የእኔን አጥር እስካልነቀነቀ ምን አገባኝ!” ማለቱ ጥሩ ነገር አይደለም፡፡ ገና ወጡ እንኳን በቅጡ ሳይወጠወጥ… “ከዓለም ታላላቅ ከተሞች አንዷ እየሆነች ያለችው አዲስ አበባ…” አይነት ‘የሦስተኛ እንቁላል ሎጂክ…’ አሪፍ አይደለም፡፡ እናላችሁ… ነገርዬው “ቦተሊካው ሰፈር ዝር አትበል እንጂ እንደፈለግኸው ሁን!” በሚሆንበት ጊዜ… ከእውነተኛዎቹና ከሚታዩት ሁለት እንቁላሎችና ባይኖርም ‘ሎጂክ ነፍስ ከሚዘራለት’ ሦስተኛ እንቁላል አቀራረብ መምረጡ አሪፍ ነው፡፡እናማ… ከነፋሱ ጋር አብሮ ነፍሶ “እንደውም ሦስት ሳይሆን ሰባት ነው!” አይነት ለአንድ “ጉርምርሜ” ማውረድ በአሥራ አንድ “ያሆ በሌ” መቀበል የብዙዎቻችን አማራጭ ሲሆን በእርግጥም ነገሮች አስቸጋሪ መሆናቸውን ታያላችሁ፡፡ኮሚክ እኮ ነው… የራሳችን ጠረጴዛ ምን ያህል ሳህኖች እንዳሉበት የምናውቀው እኛ ሆነን ሳለ…“ጠረጴዛህ ላይ ያለው ሳህን ሁለት ሳይሆን በሎጂክ ሦስት ነው…” ስንባል “ትያትር ጠፋ የሚሉት ይሄን የመሳሰለ ትያትር እያለ ነው!” ያስብላል፡፡እናላችሁ… ሸረሪቶቹ እንኳን ለድር ማድሪያ በቂ ‘ግብአት’ የለውም ብለው በናቁት ወና ቤታችን… “አንተ ነገሬ አትለውም እንጂ ቤትህ በእቃ ግጥም ብሏል…” አይነት ‘የሦስተኛ እንቁላል ሎጂክ…’ አለአይደል… የእሪ በከንቱን ድልድይ እንኳን ማሻገሩን እንጃ!ስሙኝማ…! በዛሬዋ ቅዳሜ ቀን የ’ሦስተኛዋን እንቁላል ሎጂክ’ በመጠቀም ሁለት ደብል ስቶሊችንያ ምናምን መገልበጥ ስለምችል ‘ፋንታሲው’ ሳይጠፋ ልሂድ መሰለኝ፡፡

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

 

Read 3118 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 11:22