Print this page
Saturday, 12 January 2019 14:39

ቲናዬ ደወለች

Written by  ከቃል ኪዳን
Rate this item
(19 votes)

 ቲናን ወደቀጠርኩበት ካፌ ለመሄድ ታክሲ እየጠበቅሁኝ ነው፡፡ ቲናዬን ያወቅኳት ከሁለት ቀናት በፊት ጠና የሚሠራበት ታክሲ ውስጥ በተፈጠረ ጠብ ምክንያት ነው፡፡ አታውቁትም እንጂ ጠና በአካባቢያችን አንጋፋ የታክሲ ረዳት ነው፡፡ ከሁለት ቀናት በፊት ማታ ላይ ጠና ‹ዲጄ› ሆኖ በሚሠራበት ታክሲ ተሳፍሬ ወደ ሠፈሬ እየተመለስኩ ሳለ፣ ግማሽ መንገድ ላይ ቲናዬ እንደ ትራፊክ ፖሊስ  እጇን ዘርግታ ታክሲውን አስቆመችው፡፡ ሰው በሰው ላይ ጠቅጥቆ አልረካ ያለው ጠና፣ የታክሲውን በር ከፍቶ ከአንዱ ጎረምሳ ጋር ተደላድዬ የተቀመጥኩት እኔን እንድጠጋላት ነገረኝ፡፡ ከወንበሩ ጥበት የተነሳ እግሬን ለማንቀሳቀስና ምላሽ ለመስጠት ስለዘገየሁ በደምፍላት፤
‹‹ወይ ተጠጋላት ወይ ውረድ!›› የሚል ቀጭን ትእዛዝ ሰጠኝ፡፡
ጠና ግዙፍ ሰውነቱን ለማፍታታትና የሰውነት አካላቱን ደኅንነት  ለማረጋገጥ፣ ከተራ አስከባሪና ከተሳፋሪ ጋር ቡጢ ሲቃመስ የሚውል ረዳት ነው፡፡ ብዙ ዕድሜውን ያሳለፈዉ በእስር ቤት ነው፡፡ በፊት በፊት እንደ ሸንኮራ ሻጭ ከእጁ ቢላዋ አይለየውም ነበር፡፡ እንደውም መንደራችን ውስጥ ካሉት አንድ ሃኪምና ሁለት ነርሶች ይልቅ እርሱ ብዙ ሰዎችን እንደወጋ ይነገርለታል፡፡
በጠና እጅ በጥፊ ከመጣጋት፤ መጠጋትን መርጬ ለቲና ግማሽ ቂጧን ማሳረፍያ የምትሆን ቦታ ለቀቅሁላት፡፡ በዓይኗ አመሰግናለሁ አለችኝ፡፡ በተሳፋሪ ፊት በጠና ከፍ ዝቅ ተደርጌ እንድገላመጥ ምክንያት ስለሆነች ከፍ ዝቅ እድርጌ ገላመጥኳት፡፡
ታክሲው መንገድ ከጀምረ በኋላ በድጋሚ ልገላምጣት ፊቴን ወደ እሷ ሳዞር በግማሽ ቂጧ የጎንዮሽ ተቀምጣ፤ በአንድ እጇ ቦርሳዋን አቅፋ፤ አንድ እጇን ደግሞ ቡጢ ጨብጣ የታክሲውን ግርግዳ ተደግፋለች፡፡ እያየኋት እንደሆነ ቀልቧ ነግሯት ዞር ብላ በጨረፍታ ተመለክታኝ ፈገግ አለች። ፈገግታዋ ቀየረኝ፡፡ ፈገግታዋን ሳጣጥም ስታየኝ መሽኮርመም ጀመረች፡፡ ከእሷ ሰስቼ ያስተረፍኩትን ትርፍራፊ ቦታ ከለቀቅሁላት በኋላ ከጎኔ ያለውን ተሳፋሪ እስከ ታክሲው ግርግዳ ገፍቼ ተደላድላ እንድትቀመጥ ጋበዝኋት፡፡ ዳግም ፈገግታዋን ብልጭ ስታደርግልኝ ሰውዬው ከታክሲው ተጣብቆ፤ ታክሲው እስኪለጠጥ ድረስ ተጠጋሁላት፡፡ ፈገግታዋ እንደ ቀትር ጸሐይ እየበረታ ሲመጣ፣ የጠሀይ መነጥሬን ዓይኔ ላይ ከሰካሁ በኋላ ከጎኔ ያለውን ሰውዬ ላስወርድላት ወይስ እኔ ልነሳላት የሚል የሀሳብ ምጥ ያዘኝ፡፡ ከዛም ስለ ምጥ አወራት ጀመር፡፡
‹‹ስሜ ቲና ይባላል›› አለቺኝ ከታክሲ ስንወርድ፡፡
የድምጿ ቅላጼ ከአማርኛ ይልቅ ወደ ፈረንጅኛ ያደላል፡፡
‹‹ስልክሽስ ማን ይባላል?››
‹‹ስልኬ ‹ሳምሰንግ ጋላክሲ› ይባላል›› ሣቅ አለች፡፡
ትንሽ ቆመን ካወራን በኋላ ስልክ ቁጥሬን ተቀብላኝ፤ ፀባዬ ታይቶ ስልክ ቁጥሯ አንደሚሰጠኝ ቃል ገብታልኝ፤ ዛሬ ላገኛት ቀጥራኝ ተለየችኝ፡፡
ቲናዬ ከሄደች በኋላ ድምጿን የሆነ ቦታ እንደማውቀዉ ጠረጠርኩኝ፡፡ ለማስታወስ ያህል ስትሄድ በመቆምና ፈዝዞ በመቆም መካከል ሆኜ ከኋላዋ አስተዋልኳት፡፡ ግና ቄንጠኛ አረማመዷና ዳንኪረኛ ዳሌዋ፣ ድምጿን የት እንደማውቀዉ ምንም ጥቆማ ሊሰጡኝ አልቻሉም፡፡ ቶማስ ኤዲሰን ድምጽ መቅጃን ለመፍጠር ያሰበውን ያህል ካሰብኩ በኋላ ድምጿን የት እንደማውቀው ትዝ አለኝ፡፡ ድምጿ ከተከራየሁበት ግቢ ውስጥ ጠዋት ጠዋት የምሰማው የወፎች የዝማሬን ድምጽ ይመስላል፡፡
የተከራየሁበት ግቢ ውስጥ ዘወትር ጠዋት ጠዋት ያማረ የወፎችን ዝማሬ እሰማለሁ፡፡ ‘ግቢ ውስጥ በድንጋይና በሲሚንቶ አብደዉ ከተሰሩ ቪላ ቤትና ሰርቪስ ቤቶች ውጪ ዛፍ ቀርቶ ቀጫጫ የመፋቅያ ተክል እንኳን የለም፡፡ የድንጋይ ቤት ውስጥ እንሽላሊት እንጂ ወፍ አይኖርም፡፡ እንሽላሊቶች ደግሞ እንደ ወፍ ሊዘምሩ አይችሉም፡፡ ‹ጠዋት፣ ጠዋት የሚሰማው የወፎች ዝማሬ ከየት የመጣ ነዉ?› የሚል ሀሳብ ከቤት ኪራዩ የበለጠ ያስጨንቀኝ ነበር፡፡ እንደውም አንድ፣ ሁለት ቀን የማለዳ ወፎቹን የዝማሬ ድምጽ ተከትዬ ወፎቹን ፍለጋ ግቢዉን አስሻለሁ፡፡ ግን ምንም መረጃ ላገኝ አልቻልኩም፡፡ ምናልባት አከራዮቻችን፣ ተከራዮቻቸውን ለማስደስት ጠዋት ጠዋት እየተነሱ እንደ ወፍ ይዘምሩልን ይሆናል ብዬ ነገሩን ተውኩት። ቲና እኔ በተከራየሁበት ግቢ በር አልፋ ወደ ጀርባ በሚወስደው  ቅያሰ ታጠፈች፡፡ ብዙ ሲያስጨንቀኝ ለነበረ ጥያቄ መልሱንና ማረጋገጫውን አገኘሁ፡፡
የቲናን ተክለ ሰውነትና ፈገግታ ሳስበው ሞልተው እየገላመጡ የሚሄዱትን ታክሲዎች እያስቆምኩ እቅፍ አድርገህ ሳማቸው የሚል ስሜት ወረረኝ። ስሜቴን ያወቁብኝ ስለመሰለኝ በዙርያዬ ያሉትን ሰዎች ተመለከትኩኝ፡፡ ከጠሀዩና በታክሲ ጥበቃ ከመሰላቸታቸዉ የተነሳ ታክሲዎቹን አቅፌ ስሜ ቢሆን እንኳን የታክሲዎቹ በር እስካልተከፈተ ድረስ ቁብ የሚሰጣቸው አይመስሉም፡፡ አንዳንዶቹ ታክሲ ጠባቂው ከመብዛቱ የተነሳ አንድ ወይ ሁለት ተሳፋሪ የጎደለው ታክሲ ቢመጣ እንዴት ተጋፍተው እንደሚገቡ ተጨንቀዋል፤ አንዳንዶቹ ለጠብ እንደተጋበዙ ክናዳቸዉን ሰብሰበው በተጠንቀቅ ቆመዋል፡፡
ሰዓቴን ስመለከት ለቀጠሮዬ ሁለት ሰዓት ይቀረኛል፡፡ የመኪናው መንገድ ውሃና ፍሳሽ በስተግራ፤ ቴሌ በስተቀኝ ባስቆፈሩት ጉድጓድ ምክንያት ስለተዘጋጋ፣ የተቀጣጠርንበት ካፌ ለመድረስ በታክሲ ብሄድ አርባ ደቂቃ፤ በእግር ብሄድ ደግሞ አስራ አምስት ደቂቃ እንደሚፈጅብኝ ገመትኩኝና ከአጀቡ ወጣሁ፡፡ ለስንብትና አይዟችሁ ለማለት አጅበውኝና አጅቤአቸው የነበሩ ምስኪኖችን ዞር ብዬ ቃኘሁኝ፡፡ እራሱን የሚወደው፣ ታክሲ ተደርድረው ከሚጠብቁት እልፍ አዕላፋት መሀል ተነጥቆ ወጥቶ ‹አንድ ሰው ብቻ!› እያለ አመልካች ጣቱን ቀስሮ፣ የታክሲ ረዳቶች እንዲመለከቱትና እንዲመርጡት ይማጸናል፡፡ እራሱን የጠላው ድሮ በስሙኒ ይሸጥ ለነበረ ገመድ አሥር ብር ከፍሎ ገዝቶ እራሱን ሊያጠፋ እያጉተመተመ ያልፋል፡፡
ለፍጥነትና ለጤንነት በእግር መሄዱን መርጬ መንገድ ጀመርኩኝ፡፡ ቲናን እያሰብኩኝ ከቁፋሮው በተረፈ ቀጫጫ መንገድ ላይ በገመድ ላይ እንደሚሄድ የ‹ሰርከስ› ባለሙያ ሚዛኔን ለመጠበቅ እጆቼን እንደ አሞራ እየዘረጋሁና እያጠፍኩ ተራመድኩኝ፡፡ ኋላም ጫማዬን በአቧራ በጽኑ አቆሽሼ፣ በአሥር ደቂቃ ውስጥ ካፌው በር ጋ ደረስኩኝ፡፡ የዘንድሮ ሰው ከፊት ይልቅ እግር እግር ነው የሚያየው ብዬ ቲናዬ ቀድማኝ ወደ ካፌው እንዳልገባች አንገቴን አሾልኬ ካረጋገጥኩኝ በኋላ ጫማዬን ለማስጠረግ አስፋልት ተሻግረው ወዳሉ ሊስትሮዎች አቀናሁ፡፡
ጫማዬን ለሊስትሮው አደራ ሰጥቼ ቲናዬ ስትገባ ለማየት በዓይኔ የካፌውን በር መጠበቅ ጀመርኩ፡፡ የካፌው ባለቤት ይሄንን ቢያውቅ ጥበቃውን እንደሚያባርረው እርግጠኛ ነኝ፡፡ ካፌው ያለበት ሕንፃ ድሮ ተጀምሮ በቅርብ ነው ተሰርቶ ያለቀው፡፡ ይህ ሕንፃ እንደ ብዙዎቹ የአዲስ አበባ ሕንፃዎች ‹በእግዝያብሔር ያውቃል› ተጀምሮ ከዛም የታችኛውን ወለል ለባንክ በማከራየት ፍጻሜውን አሳምሯል፡፡ የባንኩ ደንበኞችም ከአሁን አሁን ብሎኬት ወደቀብን፤ በሚስማር የተንቆጠቆጠ አጣና የአዲሳባ ኑሮ ያጎበጠው ጀርባችን ላይ ተሰካብን፤ ሲሚንቶ ቦነነብን ብለው ከመሳቀቅ ድነዋል፡፡
የባንኩ በር ላይ ‹እንኳን ለበዓሉ አደረሳችሁ› የሚል ባነር ተሰቅሏል፡፡ ለየትኛው በዓል? በቅርብ ያለፈውንና በቅርብ የሚመጣውን በዓላት አስቤ ግራ ተጋባሁ፡፡ ግራ መጋባቴን ያስተዋሉ፤ ከጎኔ ቁጭ ብለው ጫማ የሚያስጠርጉ አዛውንት፤
‹‹ይህቺን በየበዓሉ ከሦስት መቶ እስከ አራት መቶ ብር ልታድን የምትችል የወጪ ቅነሳ ዘዴን ሁሉም ባንኮች ይጠቀሙባታል፡፡ እንደውም በባንኮች የጋራ ጉባዔ የተወሰነች ሳትሆን አትቀርም። ተራ ካፌ እንኳን የበዓላቱን ሥም እየጠቀሰ ‹እንኳን አደረሳችሁ› እያለ ባነር አሠርቶ ሲሰቅልና መስታወት ላይ ሲያጽፍ፤ በዓመት ለኛ ብለው ያተረፉ ይመስል ‘እንኳን ደስ አላችሁ ይሄን ያክል ቢሊዮን ዓመታዊ ትርፍ አተረፍን፤ ይሄን ያክል መቶ ሚሊየኖች የተጣራ ትርፍ አገኘን’ የሚሉት ባንኮች፤ ከዓመት እስከ ዓመት ‘እንኳን ለበዓሉ አደረሳችሁ’ የሚል ጥሁፍ ደጃቸው ላይ ያንጠለጥላሉ፡፡››
‹‹እንደዛ በማድረጋቸው ቢሆንስ ያተረፉት?›› አልኳቸው በሆዴ፡፡
ሽማግሌው ቀጠሉ፤
‹‹ደግሞስ ባለ ንግድ ቤቶች ዶሮና ስጋ ከሚበላባቸው የበዓል ቀናት በተጨማሪ እንኳን ለየካቲት ሃያ ሦስት አደረሳችሁ፤ አንኳን ለሚያዝያ ሃያ ሰባት አደረሳችሁ፤ እንኳን ለመስከረም ሁለት አደረሳችሁ፣ እንኳን ለግንቦት ሃያ አደረሳችሁ የሚሉ መልካም ምኞትን የሚገልጹ ጽሑፎችን ቢለጥፉስ?›› አሉና ወደ ጫማቸዉ ተመለሱ፡፡ ሰውየው ቲናዬን ሊያስመልጡኝ ነው እንዴ?
ድንገት ከእግሬ ስር ኳ ኳ የሚል ድምጽ ሰማሁ። ‹‹ግቢ ቲናዬ!›› አልኩኝ ሳላስበው፡፡ ሊስትሮው ከገላመጠኝ በኋላ እግሬን ገፍትሮ አውርዶ አላስችል እንዳለው፣ ሌላኛውን እግሬን አንከብክቦ አንስቶ ሊስትሮው ላይ ሰቀለው፡፡ ሊስትሮው የሌላኛውን እግሬን ጫማ ጠርጎ ሲጨርስ ድጋሚ አንኳኳልኝ፡፡ ከፍዬው ወደ ካፌው አመራሁ፡፡
ካፌ ውስጥ ሁለት ጥንዶች፤ ሁለት ነጠላዎችና አንድ ቤተሰብ ተቀምጠው ትኩስና ቀዝቃዛ መጠጦችን ከክሬምና ደረቅ ኬኮች ጋር እያዋደዱ ይጠቀማሉ፡፡ ካፌው ሀገራችን ውስጥ ያለውን የጥንድና የነጠላ እንዲሁም የቤተሰብ ቁጥር፣ ስብጥርና ስርጭት የሚያሳይ ‹ቻርት› መሰለኝ፡፡ በሀገራችን ተመጣጣኝ ጥንዶችና ነጠላዎች ቁጥር አለ፡፡ እነዚህ ግን በቂ የሆነ ቤተሰብ መመስረት አልቻሉም፡፡
የቲናን መምጣት ማየት እንዲያስችለኝ ወደዉጪ የሚያሳየዉ መስታወት አጠገብ ካለ ወንበር ላይ ተቀመጥኩኝ፡፡ የሰዉ ምሥጢር መስማት ስለማልወድና ሰዉ ምሥጢሬን እንዲሰማ ስለማልፈልግ ካፌ እጠላለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ካፌ ዉስጥ ለሌላ ሰዉ ለቀለድኩት የማያገባዉ ተስተናጋጅ ሲስቅና አንዳንዴም አብሮኝ ያለን ሰዉ ለጠየቅኩት ጥያቄ የማላዉቀዉ ሰዉ ግሩም መልስና ማብራርያ ሲሰጥ ደርሼበታለዉ፡፡ በዚህ ምክንያት ለስለስ ያለ መዚቃ የሚንቆረቆርበትና ሴት አስተናጋጅ የሌለበት መጠጥ ቤት አዝወትራለዉ፡፡ ሰዉም ስቀጥር እዛ ነዉ፡፡ እዛ እንደጣዎት ማንም ማንንም አያይም፣ አይሰማም፣ ማንም ለማያዉቀዉ አያወራም፡፡ ጨዋታዉ አብሮ ካለ ሰዉ ጋር አልያም ከመጠጥና ከሙዚቃ ጋር ብቻ ነዉ፡፡
አንድ ሻይ አዝዘህ ብዙ ተቀመጥክ አንዳይሉኝና አሥር ጊዜ እየመጡ፤ ጠረጴዛዉን እራሱ መጽዳት ባለበት ፎጣ እንዳያጸዱብኝ በማሰብ ባለሁለት ሌትሩን ዉሃ አዝዤ ዓይኔን ከመስታወቱ ባሻገር ካለዉ መንገድ ላይ ተከልኩኝ፡፡ ለሠላሳ ደቂቃ ያህል መንገዱ ላይ ፈዝዤ ጠበኳት - ብቅ አላለችም፡፡ ያዘዝሁት ዉሃ ሞቀ፡፡ በሰላሳ ደቂቃ ዉስጥ ቲናዬ እንዳታመልጠኝ ዓይኔን ለሦስት ጊዜ ብቻ ነዉ ያርገበገብግኩት፡፡ እሱም ቢሆን የቲናዬን ፈገግታ ዳግም ሳላይ ዓይነ-ዉሃዬ እንዳይደርቅ  በማሰብ ነዉ። ምናልባት በዛ ቅጽበት ቲናዬ ካፌ ዉስጥ ገብታ እንዳይሆን ብዬ ካፌውን ቃኘሁኝ፡፡
ቲና የለችም፡፡ ካፌ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ተለዋውጠዋል፡፡ ቤተሰብ ተቀምጦበት የነበረው ቦታ ላይ ኬክ ያማራት የምትመስል እርጉዝ ሴት፣ ብዙ ልጆችን የመውለድ ልምድ ያላት ከምትመስል ሴት ጋር ቁጭ ብላለች፡፡ እርጉዟ ያዘዘችው ኬክ ላይ የተከለችውን ሹካ ሳትነቅል እጇን እያወራጨች የጦፈ ወሬ ታወራለች፡፡ ሴትየዋ ወሬ ነው ያማራት ወይስ ኬክ? ምናልባት ያስረገዛት ሰው የማውራት እድል አይሰጣት ይሆናል፡፡ የምጠላውን የሰው ምስጢር መስማት ጀመርኩኝ፤
‹‹አይገርምሽም ግን ጉራው? ያቺን የመሰለች ልጅ አግኝቼለት ‹ተማሪ ናት ወይስ ሰራተኛ?› አለኝ። ‹ኧረ! ገና ተማሪ ናት› አልኩት፡፡ ‹ኮሌጅ?› ሲለኝ ‹ገና አሥረኛ ክፍል ናት፤ ብዙ ነገር አለመደችም፤ ላንተ ጥሩ ናት› አልኩት፡፡ ‹የማታ መሆን አለባት!› አለኝ። ‹አንተ የማታ ትሁን የቀን ምን ቸገረህ? ደግሞ የቀን ነው የምትማረው፣ ቢበዛ ይሄን ዓመት እስክትጨርስ ብትታገሳት ነዉ፡፡› እለዋለሁ፣ ምን እንዳለኝ ታውቂያለሽ? ‹ምን ማለትሽ ነው? ላሳድጋት ነው ወይስ ላገባት? የአሁን ዘመን ሴቶች እንደናንተ ጊዜ ትምህርት በአስራ ስምንት አመታቸው የሚጀምሩ መሰለሽ እንዴ? ስንት ዓመቷ ሊሆን እንደሚችል ገምተሻል? እኔ እኮ በትዳር መታሰር እንጂ ለአቅመ ሄዋን ያልደረሰች ሴት በማግባት መታሰር አላልኩሽም› ብሎኝ እርፍ፡፡›› እርጉዟ ተንገበገበች፡፡
ከደቂቃዎች በፊት እንደኔ ሌጣቸውን ከነበሩት ሁለት ነጠላዎች መካከል አንደኛዉ ካፌውን ለቆ ሄዷል፤ ሌላኛው ደግሞ ጓደኛው መጥታ ወደ ጥንዶቹ ጎራ ተቀላቅሏል፡፡ የኔም ዕድል ከሁለቱ አማራጮች አይዘልም፡፡ ቲናዬ መጥታልኝ ጥንድ መሆን ወይም ቀርታ ተነስቶ መውጣት፡፡ እሱን ለማወቅ ደግሞ አንድ ሰዓት የሚሆን አለኝ፡፡ ወጣቱ ጓደኛው በመምጣቷ ከቅድሙ በተለየ ፊቱ ላይ መረጋጋትና እርካታ ይታያል፡፡ በውስጤ በረከትህ ይደርብኝ ብዬ ጸለይኩኝ፡፡
ከሠላሳ ደቂቃ በፊት ካፌ ውስጥ የነበሩት ጥንዶች ወጥተው ሄደዋል፡፡ ብቻ ቲናዬ ትምጣልኝ እንጂ ካፌ ውስጥ የተከሰተውን የጥንዶች እጥረት እንቀርፈዋለን። ዓይኔን ወደ መንገዱ ሰድጄ ቲናን መፈለግ ጀመርኩ - ብቅም አላለችም፡፡ ድንገት መንገድ ላይ የተዋወቁ የሚመስሉ ጥንዶች ወደ ካፌው ዘለቁ፡፡ ሴቲቱ መንገድ ላይ ብዙ ስታወራው ቆይታለች መሰል ጎረምሳው ፊት ላይ መሰላቸት ይታይበታል፡፡
ዓይኖቼን ከመንገዱ ነቅዬ፣ ሰዎቹን አጅቤ አጠገቤ ካለው መቀመጫ ጋ አደረስኳቸው፡፡ አስተናጋጅ መጥቶ ትእዛዝ ተቀብሎ ከመሄዱ ሴቲቱ ወሬዋን ቀጠለች፡፡
‹‹ቅድም እንደነገርኩህ እኔ እንደሌሎቹ ሴቶች አይደለሁም!›› ጎረምሳዉ ፋታ አገኘሁ ብሎ ሊጀምረው የነበረውን ጨዋታ መልሶ ዋጠው። ማንቁርቱ ከፍ ዝቅ አለች፡፡ ልጅቱ ድምጿን ለማሳመር በአፍንጫዋ ነው የምታወራው፡፡
‹‹በቃ እኔ ሴት ነኝና እንክብካቤ ይደረግልኝ ምናምን አልልም፡፡ ‹ላይክ› ሴት ስለሆንኩ አለ አይደል ‹አፈርማቲቭ አክሽን ኦር›…ምናምን አልፈልግም፡፡ ምንም የተለየ ድጋፍ ምናምን አልፈልግም››
‹‹በቃ በአጠቃላይ ምንም ምናምን አትፈልጊም ማለት ነው?›› አላት፡፡
‹‹በቃ ምን መሰለህ! አኔ እራሴን ከወንድ እኩል ነኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ እኩል ስለሆነ ነገር ደግሞ ሁልጊዜ መወራት የለበትም፡፡ ‹ኢቭን› እኛ ሴቶች ከወንዶች እኩል ነን ካልን፣ ‹ዊ ዶን ኢቭን ኒድ ማርች ኤይት ምናምን! ዩ ኖዉ? ዱ ዩ አንደርስታንድ ሚ?› ግን በቃ ለማለት የፈለኩት ሴት ስለሆንን ብቻ ለወንድ የማይደረግ ምንም አይነት የተለየ ድጋፍ አያስፈልገንም-- በተለይ እኔ አልፈልግም፡፡ ‹አም ካፔብል ኦፍ ዱይንግ ኤኒቲንግ!›››
‹‹የሴቶች ሽንት ቤትም ቢሆን መጠቀም አትፈልጊም ማለት ነዋ?››
አሳ አጥማጅ መረቡን ወደ ባህር እንደሚጥለው፣ ዓይኔን መስታወቱን አሻግሬ ወደ መንገድ ወረወርኩት፡፡ የቲናዬ መምጫዋ ወይ መቅርያዋ ሰዓት እየደረሰ ነው፡፡ መንገዱ ላይ ብዙ ሴቶች ሲያልፉና ሲያገድሙ ቢታዩም ቲናዬ ከመካከላቸው የለችም፡፡ ለመጽናናት ስል ዓይኔን ከብቸኝነት ወደ ጥንድነት የደረጃ ዕድገት ያገኘው ጎረምሳ ወዳለበት ጠረጴዛ ላኩኝ፡፡ ጎረምሳው መርዶ በሚያረዳ ድምጽ እያወራ ነው፡፡
‹‹ሃኒዬ የምስራች!››
‹‹ምን? የምን የምስራች ነው? እሺ ምስር ብላ! ግን ደግሞ ምስራ ጨጓራዬን ያመኛል ትላለህ አይደል? እሺ አተር ክክ ብላ! በቃ ደስ ያለህን ብላ!›› ተርበተበተች፡፡
‹‹ችግር የለውም ሃኒዬ!››
ለአፍታ በዝምታ ከቆየ በኋላ፤
‹‹ሃኒዬ አርግዘሻል!››
‹‹ምን?! ማን? እኔ? ከማን?››
‹‹ከእኔ ነዋ! ምን ማለት ፈልገሽ ነው?››
‹‹እንዴት ሊሆን ይችላል? አላውቅልህም! የራስህ ጉዳይ!›› ተመናጭቃ በተቀመጠበት ጥላው ወጣች፡፡ ሴቷ ማርገዟን ካደች፡፡ ወንዱ በእንባ ታጠበ፡፡
ቲናዬ ስትመጣ ምናለ ካፌው እንደ ታክሲው ተጣቦ አስተናጋጁ ‹ተጠጋላት› ብሎ ቢያስጠጋኝ? አስተናጋጁ ግን የጠናን ያህል ልብ ያለው አይመስልም፡፡ እኔ ካፌ አይቀናኝም፡፡ የእኔ እጣ ፈንታ የተቆራኘው ከታክሲ ጋር ነዉ፡፡ ብዙ የሴት ጓደኞቼን የተዋወቅኋቸው ታክሲ ዉስጥ ነዉ። ቲናዬን የመሰለች ልጅ ግን ተዋዉቄ አላውቅም ነበር፡፡ ያውም በግድ ካልተጠጋህላት ተብዬ፡፡ ጠና ባለውለታዬ! ጠና ባለ ሁለት ጸጉሩ አንጋፋው የታክሲ ረዳት!
ከአያቴ በታች በዘር ማንዘራችን የታክሲን ስራ ያልሠራ የለም፡፡ እኔ ብቻ ነኝ የዘሬ አያንዘርዝረኝ! አሻፈረኝ ብዬ የመንግስት ሥራ የምሠራው፡፡ ኮሌጅ የሚያስተምረው አጎቴ እራሱ የታክሲ ስራ ሱስ ተጠናውቶት ጠዋት ወደ ስራ ቦታው ሲሄድ ወደዛ አቅጣጫ የሚሄዱ ተሳፋሪዎችን ይጭናል። ባጋጣሚ ታክሲ ውስጥ ተማሪዎቹን ካገኘ ሂሳብ አንዲቀበሉለት ያደርጋል፡፡ ሂሳብ የተቀበለለት ተማሪን ሂሳብ አያስከፍለውም፤ ‹ግሬድ›ም ከ‹ሲ› በታች አይሰጠውም፡፡ ባለ ሁለት ጠጉሩ የታክሲ ረዳት ጠናም ቢሆን በበፊቱ ወያላነቱን በአሁኑ ረዳትነቱን ከአያቴ ጋር ነው የጀመረው፡፡
እኔ እንደ ቤተሰቦቼ በታክሲ ሥራ ገቢ ባላገኝም ብዙ የሴት ጓደኞችን አግኝቻለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ከሴቶች ሁሉ የምትበልጠውን ቲናዬን አገኘሁ፡፡ ቲናዬ ብቅ አላለችም፡፡ ሰዓቴን ስመለከት ቀጠሯችን አምስት ደቂቃ ቀርቶታል፡፡ ጨነቀኝ፡፡ እናቴ እኔን ለመውለድ ስታምጥ ያለ ዓይነት ላብ ፊቴ ላይ ችፍፍ አለ፡፡ አምስቱ ደቂቃ ዘላለም ሆነብኝ፡፡ መንገዱን አሻግሬ ማየትና ቲናዬን መንገዱ ላይ ፈልጌ ማጣት ፈራሁ፡፡
ጥቁር የጸሀይ መነጥሬን ከሰካሁኝ በኋላ አይኔን ጨፈንኩኝ፡፡ ወደ ካፌው የሚገባ አዲስ ኮቴ ካለ ብዬ ጆሮዬን አንቅቼ ጠበቅሁኝ፡፡ አምስት ደቂቃ ከሚቀረኝ አምስት ሰዓት ቢቀረኝ ተመኘሁ። እንደማይሆን ከማወቅ በተስፋ መጠበቁ ይሻላል። አሁን ግን አማራጭ የለኝም፤ ከደቂቃዎች በኋላ ቲናዬን ከእነ ፈገግታዋ አጠገቤ አገኛታለሁ አልያም ስለሷ አቆሽሼ ባስጠረኩት ጫማዬ ከቴሌና ውሃና ፍሳሽ ቁፋሮ የተረፈውን መንገድ በብስጭት እየቆፈርኩኝ ወደ ቤቴ አዘግማለሁ፡፡
ስልኬ ጠራ፡፡ ቲና ደወለች መሰለኝ፡፡ የጨፈንኩትን አይኔን መግለጥ ፈራሁ፡፡ እየመጣሁ ነው ወይስ ይቅርታ ስላስጠበኩህ ልትለኝ ነው? ደርሻለሁ በሩ ላይ ነኝ ልትለኝ ነው? ወይስ ይኸው ከቤት እየወጣሁ ነው ልትለኝ ነው? እልል ልበል ወይስ…? ደግሞ እርሷ ባትሆንስ የደወለችው? በርግጠኝነት በዚህ ሰዓት የደወለልኝ ሌላ ሰው ከሆነ መቃብሬ ላይ አይቆምም፤ እኔም መቃብሩ ላይ አልቆምም፡፡ ነገር ግን የማንም ቀብር ላይ መቅረት አልፈልግም፤ ማንም ከቀብሬ እንዲቀርም አልፈልግም፡፡ ስልኬን አውጥቼ ማየት ፈራሁ፡፡

Read 5732 times