Saturday, 12 January 2019 14:31

የኢየሱስ ልደትና የሔዋን አመፅ

Written by  ብ.ዓ
Rate this item
(4 votes)

ባለፈው ሰኞ ታህሳስ 29፣ 2011ኛው የኢየሱስ የልደት በዓል ተከብሯል። ለኢየሱስ ሰው ሆኖ መወለድ ምክንያቱ ደግሞ የሔዋን አመፅ ነው። ኢየሱስ የተወለደው አዳምና ሔዋን ከአመፃቸው እንዲመለሱ ነው። ለመሆኑ ሔዋን ያመፀችው ለምንድን ነው? የኢየሱስ መወለድስ እነ ሔዋንን ዳግም ወደ አመፃቸው እንዳይመለሱ አድርጓቸዋል ወይ? ሃይማኖታዊው በሆነው ንባብ የእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች መልስ ምን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ግን ሃይማኖታዊ ከሆነው መልስ በመውጣት፣ ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስን እየጠቀስን፣ ሌላኛውን አተያይ እንመለከታለን፡፡

ሔዋን ለምን አመፀች?
መፅሐፍ ቅዱስ፤ አዳምና ሔዋን ያመፁት በእባብ ላይ ያደረው ሰይጣን አሳስቷቸው ነው ቢልም፣ ዶ/ር እጓለ ግን ‹‹በከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› መፅሐፋቸው ላይ ‹‹የሔዋንን አመፅ በሌላ ነፃ ህሊና ለመረዳት መሞከር አለብን›› በማለት ሌላ ንባብ ይዘው መጥተዋል፡፡ እንደ እጓላ ሐሳብ፤ ‹‹አዳምና ሔዋን ያመፁት የእግዚአብሔር የሞግዚት አስተዳደር ስለ ሰለቻቸው ነው››።
እነ ሔዋን ያመፁት ከውጫዊ ኃይል በሚመጣ ህግ ተንደላቆ ከመኖር ይልቅ፣ ከራሳቸው ከውስጣቸው በሚወጣ ሐሳብ ራሳቸውን ማስተዳደር ስለፈለጉ ነው፣ በራሳቸው ህይወት ላይ የመጨረሻው ባለ ሥልጣን ለመሆንና በዚህም ለሚመጣባቸው ነገር ሙሉ ኃላፊነት ለመውሰድ ነው። ዶ/ር እጓለም እንዲህ ይላሉ፤ ‹‹የአዳምን አመፅ በነፃ ህሊና ለመረዳት ከሞከርን፣ ሰው በስጦታ ወይም በችሮታ በሚገኘው ድሎት የማይደሰት መሆኑንና ከገነት ለመውጣት የደፈረውም ከራሱ ዕውቀት በሚገኘው ጉልበት ራሱን ለማስተዳደር ነው›› (1956፡ 35)፡፡ ይሄም የአዳም ራዕይ ነው፡፡ የአዳም ራዕይ እስከ ዛሬ ሲባል እንደነበረው ‹‹አምላክ የመሆን ፍላጎት›› ሳይሆን፣ ከራሱ ከውስጡ በሚወጣ ሐሳብ ራሱን ማስተዳደር ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ሀጢአት አይደለም፡፡ የአዳም ፍላጎት ይሄ ሆኖ ሳለ፣ ዓለም ግን ‹‹አዳም አምላክነትን ተመኘ፤ ሀጢአትም ሰራ!!›› እያለ ያወግዘዋል፡፡
ያም ሆነ ይህ፣ እግዚአብሔር እነ ሔዋን በራሳቸው ሐሳብ እንዲመሩ ስላልፈለገ እንዲፀፀቱና ‹‹የአንተ መለኮታዊ ሞግዚትነት ይሻለናል›› ብለው እንዲፈርሙ አደረጋቸው። እነ ሔዋንም ይሄ ‹‹ፀፀት›› የሚባለው ነገር እያለ ራዕያቸውን ለማሳካት በአመፃቸው መግፋቱ እንደማያዋጣቸው ስላወቁ ይቅርታ ጠየቁ።

ለመሆኑ አዳምና ሔዋን በአመፃቸው ለምን መግፋት አልቻሉም?
ከእነ አዳም አመፅ አንድ የምንረዳው ነገር ቢኖር፣ የሰው ልጅ በሞግዚት ከሚያገኘው የተንደላቀቀ የገነት ህይወት ይልቅ፣ ራሱን በራሱ ተምኔት እያስተዳደረ ጎስቋላ ህይወት መኖርን እንደሚመርጥ ነው። ለዚህም ነው አዳም ከገነት የሚያስባርር ሪስክ እስከ መውሰድ  የደረሰው፡፡
አዳምና ሔዋንን ‹‹በፀፀት›› ወደ ሞግዚታዊ የገነት ህይወት መመለሱ ጊዜያዊ መፍትሄ ካልሆነ በስተቀር፣ አዳምን ለዘለአለም ከአመፅ እንዲቆጠብ አያደርገውም። ምክንያቱም፣ የሰው ልጅ በራሱ ጥረት በሚያመነጨው እውቀትና ነፃ ፈቃድ ብቻ ህይወቱን የመምራት ፍላጎቱ ተፈጥሯዊና መቼም ቢሆን የማይቀር ስለሆነ ነው። ይሄም ፍላጎት የጊዜ ጉዳይ እንጂ የሆነ ዘመንና ቦታ ላይ መከሰቱ አይቀሬ ነው። ሆኖም ግን አዳም በአመፁ እንዳይገፋ አንድ ችግር ነበረበት፤ ይሄውም የንቃተ ህሊና አለመዳበር ነው፡፡ ምክንያቱም፣ አዳም የሞግዚት አስተዳደርን ካቋረጠ እንዴት መኖር እንዳለበትና ከተፈጥሮ ኃይላት ራሱን እንዴት መጠበቅ እንዳለበት ገና አላወቀም፡፡ ስለዚህ፣ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ከመጀመሩ በፊት ስለ ዓለም በደንብ ማወቅ ነበረበት፡፡
በመሆኑም፣ አዳም በአመፁ እንዳይገፋና ወደ ፀፀት እንዲመለስ ያደረገው ራሱን በራሱ የማስተዳደር ተፈጥሯዊ ፍላጎቱ በእግዚአብሔር ቁጣ ስለተኮላሸበት ሳይሆን፣ የራሱን ህይወት በራሱ ሐሳብ የማስተዳደር የንቃተ ህሊና የዕድገት ደረጃ ላይ ስላልደረሰ ነበር። በመሆኑም፣ አዳም በአመፁ እስከ መጨረሻው ድረስ ለመግፋት ለሚቀጥሉት ተከታታይ ትውልዶች ንቃተ ህሊናውን የማዳበር ሥራ ላይ መጠመድ ነበረበት፡፡

አዳም እንደገና ለ2ኛ ጊዜ አመፀ!!!
አዳም ‹‹በአመፅ ለመግፋት፣ በመጀመሪያ ንቃተ ህሊናን ማሳደግ›› በሚለው ሐሳብ በመፅናት ለሚቀጥሉት 4500 ዓመታት በዚህ ሐሳብ አድፍጦ ቆየ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ግን ፈላስፎችን፣ አስትሮነመሮችን፣ የሒሳብ ሊቃውንትን፣ ፖለቲከኞችን፣ ባለ ቅኔዎችን እየፈጠረ ስለ ዓለም ብቻ ሳይሆን፣ ከገነት ስላባረራቸው ስለ እግዚአብሔርም ህልውናና ባህሪ እየተራቀቀ ቆየ። እናም በሂደት ያከማቸው ዕውቀት በድጋሚ ለማመፅ አስተማማኝ መሆኑ ሲሰማው ሁለተኛውን አመፅ በጥንታዊ ግሪክ ሥልጣኔ ሥር አካሄደ።
ይሄም ሥልጣኔ አርስቶትል የሚባል ፈላስፋ አስነስቶ ‹‹እግዚአብሔር ሞራላዊ ኑባሬ ሳይሆን፣ ስለ ዓለም ግድ የሌለው ‹‹unmoved mover›› ነው›› አስባለው፡፡ በእነ ዲሞክሪተስ በኩል ደግሞ ‹‹ይህ ዓለም ከቁስ አካል ስብስብ ውጭ ሌላ ምንም ዓይነት ስውር ፈጣሪ የለውም›› አስባለ። በዚህም እግዚአብሔር በግሪኮች ተገረመ!! የአይሁዳውያን ሲገርመው የግሪኮቹ ባሰ!!
አይሁዶቹ ከአዳም በተወረሰ ፀፀት ዘመናቸውን በቁዘማ ሲያሳልፉ፣ ግሪኮቹ ግን እንኳን ፀፀት ሊሰማቸው ይቅርና፣ ጭራሽ ራሱ እግዚአብሔርን አንድ የፍልስፍና ርዕሰ ጉዳይ አድርገው አረፉት፡፡ እግዚአብሔር ይሄንን ሲያይ በጣም ተናደደ። ሆኖም ግን፣ እንደ አዳም ዘመን የሰውን ልጅ ‹‹በፀፀት›› መያዝ እንደማያዛልቅ እግዚአብሔር ተረድቷል። እናም ‹‹ከፀፀት ይልቅ ለምን በፍቅር አልመልሳቸውም?›› ብሎ አሰበ። በዚህም ልጁን ኢየሱስን ላከ፤ ከዛሬ 2011 ዓመት በፊትም በታህሳስ 29 ተወለደ። እግዚአብሔር ኢየሱስን ወደ ምድር የላከው አይሁዳውያንን ከፀፀታቸው ለማዳን፣ ግሪኮቹን ደግሞ ከትምክህታቸው ለማስተንፈስ ነው፡፡፡
ሆኖም ግን፣ ኢየሱስ አይሁዶችን ከፀፀታቸው ከፈወሳቸው በኋላ የግሪኩን ተልዕኮ ሳይፈፅም ሰቅለው ገደሉት፡፡ በእስራኤል የነበረውን ተልዕኮ አሳክቶ፣ ከአይሁዳውያን አጠገብ የሚገኙትን ግሪካውያንን መተው አደገኛ ነው፤ ምክንያቱም አመፅ ይዛመታል፡፡ እናም፣ ኢየሱስ በራዕይ ከግሪካዊው ከጳውሎስ ጋር ተማከረ፤ ጳውሎስንም ወደ ግሪክ ላከ። ጳውሎስም ወደ አቴንስ ሄዶ ‹‹የአቴና ሰዎች ሆይ! እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እጅግ እንደምትፈሩ አውቃለሁ፡፡ እኔ ዛሬ የምነግራችሁ ሳታውቁት ስለምታመልኩት አምላክ ነው - ስለ ኢየሱስ!!›› በማለት ፕሌቶና አርስቶትል እያሉ የሚራቀቁት ነገር እንደማያድናቸው በተዘዋዋሪ ነገራቸው፡፡ ግሪካውያንም ከሞት በኋላ ስላለው ህይወት ለረጅም ጊዜ እንቆቅልሽ ሆኖባቸው ስለነበር፣ በጳውሎስ ትምህርት ውስጥ መልስን ከተስፋ ጋር አገኙ፡፡ ቀስ እያሉም ፕሌቶንና አርስቶትልን እየተው ጳውሎስን መከተል ጀመሩ፤ ከአሪዮስፋጎሱም መራቅ ጀመሩ፡፡ በዚህም፣ ታላቁ የግሪክ ሥልጣኔ እየተዳከመ ሄደ፡፡

አዳም ለ3ኛ ጊዜ አመፀ
ሆኖም ግን የአዳም ዘር በመጀመሪያ ከገነት የተባረረባትን ‹‹ራስን በራስ ማስተዳደር›› የምትለዋን ራዕዩን በክርስትና ውስጥም ማግኘት አልቻለም። አዳም በከሸፈው የመጀመሪያ አመፁ፣ ራዕዩን ለማሳካት በመጀመሪያ በዕውቀት መጎልመስ እንዳለበት አምኖ ነበር፡፡ እንዳሰበውም፣ ‹‹በህሊና አርቅቆት›› (Contempletive knowledge) በሚገኝ ዕውቀት ጎልምሶ ሁለተኛውን አመፅ በማካሄድ ታላቁን የግሪክ ሥልጣኔ መፍጠር ችሏል፡፡ በዚህም ራዕዩን አሳክቷል፡፡ ሆኖም ግን፣ ራዕዩ ብዙም ርቀት ሳይሄድ እንደ ገና በክርስትና የእግዚአብሔር ሞግዚታዊ አስተዳደር ራዕዩን ነጥቆታል፡፡ እናም ራዕዩን በድጋሚ ለማስመለስ እስከ ዛሬ ድረስ ያለፈባቸውን የታሪክ ጉዞዎች መለስ ብሎ መገምገም ጀመረ፡፡
በዚህ ግምገማም፣ የህሊና አርቅቆት ላይ ብቻ በተመሰረተ ዕውቀትና ሥልጣኔ ራዕይን ማሳካት እንደማይቻል ደረሰበት፡፡ በሂደትም ያስተዋለው ነገር ቢኖር፣ ከመጀመሪያው አመፅ ጀምሮ እግዚአብሔር ሞግዚታዊ አስተዳደሩን ለመመለስ ዋነኛው የማስፈራሪያና የመቅጫ መሳሪያዎቹ፣ ሲዖልና የተፈጥሮ ኃይላት (መብረቅ፣ ጎርፍ፣ እሳተ ገሞራ፣ አውሎ ንፋስ፣ ድርቅ፣ ወረርሽኝ…) እንደነበሩ አስታወሰ። ሆኖም ግን፣ አዳም በኋላ ላይ የተረዳው ነገር ቢኖር፣ የህሊና አርቅቆቱን ወደ ተግባራዊ ዕውቀት ካለወጠው በስተቀር ራዕዩን በአስተማማኝና በዘላቂነት ማሳካት እንደማይችል ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ተፈጥሮን የሚቆጣጠርበት የንቃተ ህሊና ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ ለ3ኛ ጊዜ ማመፁ ዋጋ እንደሌለው ተረዳ። በዚህም፣ 3ኛውንና የመጨረሻውን አመፅ ከማካሄዱ በፊት ከህሊና አርቅቆት ወጥቶ ተፈጥሮ እንዴት እንደሚሰራ በየዘርፉ እያጠና ቆየ፡፡
ከኢየሱስ ልደት 1400 ዓመታት በኋላ ይሄንን የተፈጥሮ ጥናቱንና ያከማቸውን እውቀት ሲገመግመው፣ 3ኛውን አመፅ ለማካሄድ በቂ የሆነ የንድፈ ሐሳባዊና የተግባራዊ ዕውቀት ዝግጅት ላይ መድረሱን አወቀ፡፡ እናም፣ የሰው ልጅ በአመፁ ዳግም ላይፀፀት ከእግዚአብሔር ሞግዚታዊ አስተዳደር በመነጠል፣ ከ15ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ጀመረ፤ ይሄንንም ዘመን ‹‹ትንሳኤ›› (Renaissance) ብሎ ጠራው፡፡ እናም፣ ከዘመነ ትንሳኤ ጀምሮ የሰው ልጅ ራዕዩ ተሳክቶለት በራሱ ጥረት በሚያመነጨው እውቀትና ነፃ ፈቃድ ብቻ ህይወቱን እየመራ ይገኛል፡፡ በዚህም የአዳም ራዕይ ከ6000 ዓመታት በኋላ ተሳክቷል!!!
ከአዘጋጁ፡- ጽሁፉ የጸሃፊውን አመለካከት  ብቻ የሚያንጸባርቅ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

Read 1159 times