Print this page
Saturday, 12 January 2019 14:29

የ”አንድዬ” ፍልስፍናዊ ትንተና (The One)

Written by  ደረጀ ኅብስቱ
Rate this item
(1 Vote)

 የግሪክ የፍልስፍና የመጨረሻ ዘመናት ላይ እንደተማረ የሚነገርለት ፕሎቲንየስ፤ የአፍላጦንን ሃሳቦች ተንተርሶ ሰፊ ትንታኔ በመስጠትና ከእርሱ በኋላ በመጡ ሃይማኖታዊ እሳቤዎች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ በመፍጠር ስሙ ደጋግሞ ይጠቀሳል፡፡ ኅላዌን በሶስት ዋና መዋቅሮች ይከፋፍልና የአፍላጦን ሪፐብሊክ የተሰኘ ድርሳንን አስፋፍቶ ያስተምራል፡፡
የኅላዌያችን ምንጭ አንድዬ (The One) ነው ይለናል፤ ፕሎቲንየስ፡፡ እያንዳንዱ ነገር መነሻ ምንጭ አለው፤ የሁሉም ነገር አስገኝ፣ አመንጭ የሚሆን ነገር ስለ መኖሩ መጠራጠር አይቻልም፡፡ የኅላዌ ፍልስፍና (Ontology/Methaphysics) የሚባለው የፍልስፍና ዘርፍ ዋና ማጠንጠኛው፤ ይሄንኑ የሁሉ አስገኝ፣ አመንጭ የሆነውን ጉዳይ ስለ መበየን ነው። እናም እውቁ የጥንቷ ግሪክ እርጅና ዘመን ተማሪና የአዲሲቷ ገናና ሮም አስተማሪ የሆነው ፕሎቲንየስ፣ እንደ መምህሮቹ ሁሉ የራሱን ኅላዌያዊ ፍልስፍና ቀምሮ በማስተማር ይታወቃል፤ አንድዬ ይለዋል፤ ለዚህም መነሻ ሃሳብ ያቀበለው አፍላጦን “መልካሙ” (The Good) ብሎ በ”Republic” ድርሳን ውስጥ የተፈላሰፈው እንደሆነ ይጠቁመናል፡፡
እውነት፣ መንገድ፣ ህይወት እኔ ነኝ እንዲል ያባቶቻችን መጽሐፍ፣ ፕሎቲንየስም አንድዬ የእውቀትና የነፍስ አስገኝ ነው ይለናል፤ እራሱን አንድዬን አንድ ክፍል ያደርግና ከውስጡ ግን እውቀትንና ነፍስን እራሳቸውን የቻሉ አካላት ሆነው እንደፈለቁ ይነግረናል፡፡ አንድዬ እራሱን በራሱ ያስገኘ ሲሆን ለሌሎች ፍጥረታት በሙሉ ደግሞ አስገኝ ምንጫቸው ነው፤ በቅድመ ሶቅራጥስ የፍልስፍናና የሳይንስ ባህል መሰረት ብዙ ውስብስብ ነገሮችን ዘር ግንዳቸውን፣ አስመጭ፣ አስገኛቸውን አንድ ቀላል፣ ግልጽ በሚመስል ነገር መመሰል የተለመደ ነበርና ፕሎቲንየስም ይህንኑ ባህል የተከተለ ይመስላል፡፡ እግዚአብሔር ብቻውን በመሆኑ ፈርቶ ይህንን ሁሉ አለም ፈጠረ እንዲል ያባቶቻችን ቅኔ፡፡
የብርሃኖች ሁሉ ቀዳሚ ብርሃን፤ የቀለማት ሁሉ እናት ቀለም አለ፡፡ ቀስተ ደመና እነዚያን ሁሉ ህብረ ቀለማት የሚያስገኘው ከአንድ ብርሃንማ ቀለም ነው፤ በስስ ደመና መካከል የፀሐይ ብርሃን ሲያልፍ ወይም  በስስ የዝናብ ጠብታዎች ጥርቅም ውስጥ ብርሃን ሲያልፍ፤ አልያም በወንዝ ፏፏቴ ፍንጣቂዎች ውስጥ ብርሃን ሲያልፍ የሚያምር እጅብ ያሉ ሕብረ ቀለማት ቀስተ ደመናን ይፈጥራሉ፡፡ ከብርሃንማው ቀለም ብዙ ሕብረቀለማት ይገኛሉ፡፡ የፕሎቲየስ ኅላዌያዊ ፍልስፍናም የሁሉም ነገር አስገኝ የሆነው አንድዬ ነው ሲለን፣ በእንደዚህ ያለ ተምሳሌት ታጅቦ ነው፡፡ ‹‹መጀመሪያ ሰማይና ምድርን ፈጠረ፤ ብርሃን ይሁን አለ፤ ብርሃንም ሆነ›› እንዲል ያባቶቻችን መጽሐፍ፤ ፕሎቲንየስም አንድዬ ማለት ብርሃን ነው፤ አእምሮ ደግሞ በፀሐይ ይመሰላልና፤ ነፍስ ደግሞ በጨረቃ ይለናል፡፡
በአንድዬ (The One) ውስጥ አእምሮ (Intellect) እና ነፍስ (Soul) ይገኛሉ፤ እነዚህ ሦስቱ የኅላዌ መዋቅሮች ደረጃቸው የተለያየ እርከን ላይ የሚገኙ የኅላዌ መዋቅሮች ናቸው፡፡ የሁሉም እናት የሆነው አንድዬ ሲሆን የሚቀጥለው ደግሞ አእምሮ ነው፤ የመጨረሻው ደግሞ ነፍስ ነው ማለት ነው። አንድዬ ሁሉንም ያስገኝ እንጂ እነርሱ ከእርሱ ስለወጡ የእርሱ ማንነት ያንሳል ማለት አይደለም፤ ምንም ሳያንስ ሳይጎድል ልክ እንደ ቀደሞው ማንነቱን ጠብቆ ሁሉንም ግን ይወልዳቸዋል፣ እናት ይሆናቸዋል፡፡ አንድዬ ማለት ኅልውም ኢ-ኅልውም የሆነ ማለት ነው፤ የሁሉንም ፀባይ የያዘ ነው፤ ሁሉም ከእርሱ የሚወጡት ደግሞ ከእርሱ የተለየ የራሳቸው ፀባይና ማንነት ሊኖራቸው አይችልም፤ ምክንያቱም አንድዬ የሁሉ አስገኝ እናት ነውና፡፡ አንድዬ በባህሪው ምልዑ በኩለሄ ነውና እንዲህ ነው ተብሎ ተዘርዝሮ የሚገለጥበት የተለየ ባህሪ ልናመጣለት አንችልም፤ እንደው ብቻ ሁሉን ነው፡፡ እስኪ ይቺን ጥቅስ እንውሰድለት፡-
‹‹The One being beyond all attributes including being and non-being, is the source of the world but not through any act of creation, willful or otherwise, since activity cannot be ascribed to the unchangeable, immutable one….We ought not even to say that he will see, but he will be that which he sees, if indeed it is possible any longer to distinguish between seer and seen, and not boldly to affirm that the two are one.››
ሁሉም ነገሮች ከእርሱ ስለሚገኙ ከተገኙት ይልቅ አስገኝው ቀላልና ግልጽ ነው፤ ብዙ ውስብስብ ነገሮች መነሻቸው ቀላል ነገር ነው፤ ስረ መሰረታቸው የተቀመጠበት መንበራቸው ቀላል ነገር ነው፡፡ ውሃ የምንለውን ፍጡር ብንመረምር እንኳ ሳይንሱ እንደሚለን፤ የሁለት ሃይድሮጅንና የአንድ ኦክስጅን ውህድ ሆኖ ቀልሎ እናገኘዋለን፤ ነገር ግን ውሃ ጠጣር በረዶ ሆኖ መርከቦችን የሚፈረካክስ የክብደት ኃይል መፍጠር ይችላል፤ የአየር ትነት መሰል ባህሪ ወርሶ እንፏሎት ሆኖ የማፈን ኃይል መያዝ ይችላል፤ አሊያም ደራሽ ወንዝ ሆኖ ሰውንም፣ ቁስ አካላትን ሁሉ እያግበሰበሰ ሊወስድ ይችላል፡፡ በቀላሉ ሁለት ሃይድሮጅንና አንድ ኦክስጅን ያልነው ውሃ እንዲህ ያለ ውስብስብ ባህሪ አለው፡፡ አንድዬ ግን የሁሉ አስገኝ ምንጭ ስለሆነ ቀላል እንጂ ውስብስብ አይደለም፤ ውስብስቦች ከቀላሉ ስለሚመነጩ፡፡ አርስጣጣሊስ ደግሞ unmoved mover የሚለው ነገር ነበረው፤ ምናልባትም ፕሎቲንየስ እርሱንም እያሰበ ይሆናል የቀመረልን፡፡
ከአንድዬ ውስጥ የሚመነጨው ቀጣዩ የኅላዌ መዋቅር አእምሮ (Devine Mind) ነው ይለናል ፕሎቲንየስ፡፡ አፍላጦን የዚህ አለም ነገሮች ሁሉ እንደ ጥላ ያሉ ናቸው፤ ዋናዎቹ፣ ቋሚዎቹ፣ አማናዊያኑ የሚገኙት በወዲያኛው አለም ነው የሚለውን ሃሳብ ፕሎቲንየስ ደግሞ አእምሮ ይባላል ይለናል። በፕሎቲንየስ የኅላዌ መዋቅር ሁለተኛውን ተርታ የያዘው አእምሮ፤ ዘላለማዊ፣ አማናዊና ህያው ነው፤ ይህ አእምሮ የመነጨው የተወለደው ከአንድዬ ነው ይለናል፡፡ ስለሆነም ሁሉንም ነገር የመከወን ኃይል አለው፤ በዚህ አለም ላይ ያሉት ህይወት ያላቸውም ሆኑ ህይወት የሌላቸው ፍጡራን በሙሉ የአእምሮ ጥላ ናቸው እንጂ በራሳቸው ዘላለማዊ አይደሉም፡፡ ለአጠቃላይ ተፈጥሮ ለምንለው በሞላ የአምላክ ያህል አስቦ፣ ወጥኖ እንዲፈጠሩ ያስቻላቸው በአእምሮ ውስጥ ስለታሰቡ ነው፡፡ ተፈጥሮ የምንለው በሙሉ በአእምሮ ውስጥ ያሉ ናቸውና አእምሮ አሰበ ብለን ስንል እራሱን በራሱ አሰበ እንደ ማለት ይሆናል፤ ነገር ግን ሁሉንም በአእምሮ ውስጥ ኅልው አድርጎ የያዛቸው አንድዬ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፤ ያለ አንድዬ ሁሉም ነገሮች  አንድነት ኖሯቸው አእምሮ ውስጥ ሊኖሩ አይችሉም፡፡
በአንድዬ ውስጥ ህብረት፣ ስምምነትና አንድነት ያላቸው ነገሮች ወደ አእምሮ ሲመጡ የየራሳቸው መልክ፣ አካል፣ ቅርጽ፣ መለያ እንዲኖራቸው ይሆናሉ፤ ስለሆነም አእምሮ ማለት የማንነትና ምንነት መርህ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ለአንድዬ ደግሞ አእምሮ ማለት ዘላለማዊ መሳሪያው ይሆናል ማለት ነው፤ ምክንያቱም መተግበር መፈጸም የአንድዬ ባህሪይ ስላይደለ፣ በአእምሮ መሳሪያነት ይከውንበታል (ፈጥሮ ፈጠረበት የሚባል ነገረ መለኮት መኖሩን ልብ ይሏል)፡፡ አንድዬ ውስጥ ያሉ ነገሮች በሙሉ ቀላል እንደ መሆናቸው መጠን የየራሳቸውን መገለጫ ለመያዝና ማንነታቸውን ለማረጋገጥ፣ በኅላዌ መዋቅር ውስጥ የአእምሮ አስፈላጊነት ግድ ነው፤ ለአእምሮም ደግሞ ያለ አንድዬ ምንም የለውም፡፡
አንድ የጓደኛችን እህት የስራ ገጠመኝን ላንሳ፤ ጉዳዩ የሆነው በገጠር አካባቢ የጓደኛችን እህት ስታስተምር ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎችን ሳይንስ ትምህርት እያስተማረች፣ ስለ ነፍስ ያላቸው ነገሮችና ነፍስ የሌላቸው ነገሮች ጥያቄዎች እያነሳሳች ነበር፤ እናም “ልጆች፤ ቢራቢሮ ነፍስ አላት ወይስ የላትም?” ብላ ትጠይቃለች፡፡ ከተማሪዎች መካከል ፈጣኑ፤ “እኔ እትዬ! እኔ እትዬ!” እያለ ጮኸ፤ ለመመለስ እድል እንድትሰጠው በመማጸን፡፡ ፈቀደችለት። ተማሪ ሆዬም፤ “አይ እንዴው እትዬ፤ ቢራቢሮ የረባም ነፍስ የላት!” አላት፡፡ የረባም ነፍስ የላት ማለቱ፣ ነፍስ የላትም እንዳይል ስትበር ያውቃታል፤ ነፍስ አላት ለማለት ደግሞ ከሚያውቃቸው እንስሳት በሙሉ እዚህ ግቢ የሚላት አልሆነችለትም፡፡  እናም ቢራቢሮዋም ዝሆኑም በፕሎቲንየስ ኅላዌ መዋቅር፤ አእምሮ ውስጥ የራሳቸው የተከበረ ስፍራ አላቸው፡፡
ሦስተኛው የፕሎቲንየስ ኅላዌ መዋቅር ላይ የሚገኘው ነፍስ ነው፤ አንድዬና አእምሮ ያላቸውን አይነት የግንኙነት መርህ በነፍስ እና በአእምሮ መካከልም አለ፤ መመሪያቸውና ግንኙነታቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ ያለ አእምሮ፣ ነፍስ ምንም ማለት ነው፤ አእምሮ ውስጥ የታሰቡት፣ የታለሙት አማናዊያን ነገሮች ሁሉ በነፍስ አማካኝነት በህልውና በተፈጥሮ ውስጥ ተዘርተው ይገኛሉ፡፡ የነፍስ ጠባዩ በአእምሮ ውስጥ የታሰቡትን የታለሙትን አካል ግዘፍ ይዘው እንዲፈጠሩ ማስቻል ነው፡፡ በአእምሮ ውስጥ ማንነታቸውና ምንነታቸው ታስቦ ታልሞ ሲበየን፣ በነፍስ ውስጥ ደግሞ አካላቸውን፣ ጠባያቸውን፣ መልካቸውን ይዘው ይጠፈጠፋሉ። በአፍላጦን ፍልስፍና “The World of Being” ተብሎ የተሰየመው፣ ለፕሎቲንየስ “The Soul” መነሻ እንደ ሆነው ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለም፤ በአጠቃላይ ተፈጥሮ ብለን የምናውቃቸው ነገሮች በሙሉ ክሱት ሆነው የሚገኙት ነፍስ ውስጥ ነው። እዚህ ውስጥ የምናገኛቸው በሙሉ አማናዊ፣ ቋሚ ሳይሆኑ ጊዜያዊና እውነት ያልሆኑ ጥላዎች ናቸው፤ የሚጠፉ፣ የሚበሰብሱ፣ የሚረሱ ናቸው፡፡ አንዱ ሲሄድ ሌላኛው ሲመጣ ዘመናትን የሚያፈራርቁ ናቸው፤ ዋና ማንነታቸው አእምሮ ውስጥ ነው (ነብዩ ሙሴ በግብጻዊያን ላይ አምላክ አድርጌ ሾምኩህ እንደተባለ ሁሉ፣ በፕሎቲንየስ ፍልስፍና ውስጥ በነፍስ አለም ለሚገኙ ሁሉ አእምሮ አምላክ ሆኖ ተሸሞባቸዋል)፡፡
የኅላዌ ፍልስፍና፣ የሁሉም ፍልስፍና መነሻ ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፣ አይ የሁሉም ፍልስፍና መነሻ የእውቀት ፍልስፍና ነው በማለት የሚሞግቱም አሉ፡፡ ለማንኛውም እስካሁን ያየነውን የፕሎቲንየስ የኅላዌ መዋቅሮች፣ እንደ የፖለቲካ ፍልስፍና መነሻ አድርገን ብንወስዳቸው፣ እንዲህ ማለት እንችላለን፤ የሁሉም አስገኝ ገዢ እንደ ሆነው አንድዬ ሁሉ አገሬ የምንለው ያስፈልገናል፤ ልክ እንደ አእምሮ ደግሞ ተቋማት ያስፈልጉናል፤ ከዚያ በተረፈ እንደ ነፍስ አገልጋይ ሰዎችን ማተካካት እንችላለን፡፡ አንዳንዴ መዋቅሮችን አልረዳ ስንል በእጅ የያዙት ወርቅ መዳብ ይመስላል እንደሚባለው ይሆንብናል፡፡ የኛም አባቶች እንዲች እንዲች ያለችውን ፍልስፍና፣ በቅኔ ምጣኔ ቀንብበው ስለሚያስቀምጧት ለኛ ‹‹ለተመራማሪ›› ልጆቻቸው ተሰውሮብናል፡፡ አንድዬ አእምሮን ወለደ፤ አእምሮ ደግሞ ነፍስን ወለደ እያልን የፕሎቲንየስን ውልደቶች ስንቆጥር ቆይተናል፤ እናም መልካም የልደት በዓል ለሁላችሁም ይሁን!! ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም ‹‹ተዋነይ›› በሚል ርዕስ ባሳተመው የጥንታዊያን አባቶች ቅኔ ስብስብ ውስጥ የመልአከ ፀሐይ ዘቴዎድሮስን ቅኔ ለመሰናበቻ ጋብዣችኋለሁ።
‹‹ማርያም እም ዘኢትፈርህ ሐሜተ፤
ፍርፋሪተ ኅብስት ሰአለት፣ በፍና እንዘ ትፀውር ኅብስተ››

Read 1399 times