Saturday, 12 January 2019 14:16

አባገዳዎች ዛሬ ኦነግ እና መንግስትን ያሸማግላሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

በኦሮሚያ ክልል መንግስትና በኦሮሞ ነፃነት ግንባር መካከል ተፈጥሮ የቆየውን ግጭትና ውዝግብ  በእርቅ ስርአት ለመፍታት የአባገዳዎች ም/ቤት ለዛሬ  ቀጠሮ መያዙን የቀድሞ የአባ ገዳዎች ም/ቤት ሠብሳቢ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
በዚህ የእርቅና ሽምግልና ሂደት ላይ ከመንግስት በኩል የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ ከፍተኛ ኃላፊዎች እንዲሁም ከኦነግ መሪው አቶ ዳውድ ኢብሣና አጋሮቻቸው ፊት ለፊት ተገናኝተው አባገዳዎች ባሉበት ከዚህ ቀደም የተስማሙባቸውን ጉዳዮች ይነጋገራሉ፤ ስምምነታቸውንም ያድሳሉ ተብሏል፡፡  
የሃይማኖት አባቶች ጉዳዩን በእርቅ ይፈታሉ ብለን በማሰብ ነበር ጣልቃ ሳንገባ የቆየነው ያሉት አባገዳ በየነ ሰንበቶ፤ አሁን ግን አባገዳዎች ወሳኙን ድርሻ ሊወጡ ይገባል በሚል መተማመን ወደ ሽምግልናው ሂደት እንደተገባና ከሁለቱም ወገን በጐ ምላሽ እንደተገኘ ጠቁመው፣ በሁለቱ ወገኖች  መካከል የቆየው ውዝግብና አለመግባባት ዛሬ በእርቅ እንደሚፈታ እተማመናለሁ ብለዋል፡፡ የእርቅና ሽምግልና ሥነ ስርዓቱም በኦሮሞ ባህል ማዕከል እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡  
በምዕራብ ወለጋ ከኦነግ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ያለውን ሁኔታ ሰሞኑን ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያብራሩት የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ፤ በታጠቁ ሃይሎች  ከፍተኛ ኢ- ሰብአዊ ተግባራት ሲፈፀሙ መቆየታቸውን አስታውቀዋል፡፡
በታጠቁ ሃይሎች በአካባቢው የተፈፀመው ድርጊት ዘግናኝና በጭካኔ የተሞላ መሆኑን የጠቆሙት ጀነራሉ፤  ሴቶች በባላቸው ፊት ተደፍረዋል፣ የግለሰቦችና የመንግስት ንብረት ተዘርፏል፣ ሰዎች ተገድለዋል፣ ዜጐች በጅምላ በጉድጓድ ውስጥ ተደብቀው ቆይተዋል፣በርካቶችም ታግተው ነበር ብለዋል፡፡
“ሃገሬን በውትድርና ማገልገል ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ በራስ ህዝብ ላይ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ተፈጽሞ ያየሁት በምዕራብ ወለጋ ነው” ብለዋል - ጀነራሉ፡፡
በአካባቢው የመከላከያ ሠራዊት እንዲሰማራ ከታዘዘ ጊዜ ጀምሮ በተወሰዱ የሠላም ማስከበር እርምጃዎች በአሁኑ ወቅት አካባቢው መረጋጋት እንደሰፈነበት ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ጠቁመዋል፡፡
በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የኦነግ ታጣቂዎች መሣሪያቸውን ለመንግሥት እያስረከቡ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን 170 ያህል ተጠርጣሪዎችም ግጭቱን በማቀጣጠልና በግጭቱ ተሳታፊ በመሆን በሚል መታሠራቸውን  የክልሉ መንግስት አስታውቋል፡፡
ኦነግ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፤ ዘለቄታዊ ሰላም እንዲመጣ ለህዝቡ በተለይም ለኦሮሞ ህዝብ ጥሪ አቅርቧል። “ሁሉም ሰላም ወዳድ ወገኖች፣ በተለይ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ፣ ይህ መንግሥት እያካሄደ ያለውን ጦርነት እንዲያቆም አስፈላጊ ጫና ማድረግ ያስፈልጋል” ብሏል።  በኦነግና በመንግሥት የተደረሱት ስምምነቶችንም ለማደስና ዘላቂነት እንዲኖረው፣ ሶስተኛ ወገን በሚገኝበት ድርድር እንዲካሄድ ጥሪ አቅርቧል፡፡  

Read 9526 times