Print this page
Saturday, 12 January 2019 14:10

መኢአድ፤ በደቡብ ክልል አባሎቼ ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እየተፈፀመ ነው አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 በደቡብ ክልል ሰገን ህዝቦች ዞን፣ በአባሎቼ ላይ የግድያ ሙከራን ጨምሮ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እየተፈፀመ ነው ያለው መኢአድ፤ ድርጊቱን የፈፀሙና ያስፈፀሙ የክልሉ ፀጥታ ኃይሎችን ጨምሮ የዞንና የወረዳ አመራሮች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል፡፡
“ለውጡን የማይደግፉ የዞንና የወረዳ አመራሮች በአባሎቻችን ላይ እያደረሱ ያለው ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን” በሚል መግለጫ የሰጠው ፓርቲው፤ የሰገን ህዝቦች ያነሱትን የልማት ጥያቄ ተከትሎ ጥያቄውን ያስተባበሩት የመኢአድ አባላት ናቸው በማለት አባላቱ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ማድረግ አለብን በሚል መነሻ፣እስርና ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ጠቁሟል፡፡  
በዚህ ጥቃት ከክልሉ የፀጥታ ኃይል በተተኮሰ ጥይት 3 ሰዎች በፅኑ ቆስለው  ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን፣ 22 ሰዎች ደግሞ መታሰራቸውንና መደብደባቸውን መኢአድ አስታውቋል፡፡ መንግስት ለውጡን በተቀላጠፈ መልኩ ለማስቀጠል እየሰራ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ለውጡን የማይፈልጉ የዞንና የወረዳ አመራሮች በህዝብ መካከል ክፍፍልና መጠራጠሮችን እየፈጠሩ ነው ያለው ፓርቲው፤እነዚህ አመራሮች ላይ መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡
መኢአድ በህዝቡ የተገኘው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያልተቋረጠ ድጋፍ ያደርጋል ያሉት የፓርቲው አመራሮች፤ ለውጥን የማይቀበሉ በየአካባቢው ያሉ ባለስልጣናት ግን የህዝቡን የመብት ጥያቄ ባልተገባ መልኩ እየተመለከቱ ችግር እየፈጠሩ ነው ብሏል፡፡
በሰገን ህዝቦች ዞን ደራሼ ወረዳም ህዝቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥያቄን ማቅረቡን ተከትሎ፣ ይሄ የመኢአድ ጥያቄ ነው በሚል የፓርቲው አባላት ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ተፈፅሟል ብሏል፡፡ የአካባቢው ነዋሪ መብቱን እንዳይጠይቅ ከፍተኛ አፈና እየተፈፀመበት ነው  ያለው ፓርቲው፤ “ማንኛውንም የመሰረተ-ልማት ጥያቄ ከፈለጋችሁ ዶ/ር ዐቢይ ይመልስላችሁ” የሚል ያልተገባ መልስ እየተሰጣቸው ነው ብሏል፡፡
ይሄን ጉዳይ የፌደራል መንግስት ተገንዝቦ አፋጣኝ ፍትህን በአካባቢው እንዲያሰፍን እንዲሁም በህዝብ ላይ በደል የሚፈፅሙ አመራሮችን ለህግ እንዲያቀርብ፣ ተጎጂዎችም ህክምና እንዲያገኙና የታሰሩ አባሎቹ እንዲፈቱ መኢአድ ጠይቋል፡፡

Read 1390 times