Saturday, 12 January 2019 14:07

ብ/ጀ ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ ስምንት ግለሰቦች ከ319 ሚሊዮን ብር በላይ የሙስና ክስ ቀረበባቸው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ብ/ጀነራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ ሌሎች ኃላፊዎችና ግለሰቦች 319,475,287 (ሶስት መቶ አስራ ዘጠኝ ሚሊዮን አራት መቶ ሰባ አምስት ሺህ ሁለት መቶ ሰማኒያ ሰባት) ብር በማባከን የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
አቃቤ ህግ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የመሰረተባቸው ሜ/ጀነራል ክንፈ ዳኘው፣ የቀድሞ ም/ዋ/ዳይሬክተርና የግብይትና ሽያጭ ኃላፊ ብ/ጀነራል ጠና ቁርንዲ፣ የአዳማ እርሻ መሳሪያዎች ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ የቀድሞ ዋና ስራ አስኪያጅ ኮ/ል ደሴ ዘለቀ፣ የአዳማ እርሻ መሳሪያዎች ኢንጂነሪንግና ኢንዱስትሪ የቀድሞ ም/ዋ/ዳይሬክተርና የኮርፖሬሽኑ ማርኬቲንግ ሰፕላይ ኃላፊ ኮ/ል ጌትነት ጉድያ፣ የአዳማ እርሻ መሳሪያዎች ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ የቀድሞ ም/ዋ/ዳይሬክተርና የኮርፖሬት ኒው ቢዝነስ ዋና ስራ አስኪያጅ ኮ/ል ጎይቶም ከበደ እንዲሁም በንግድ ስራ የሚተዳደሩት ቸርነት ዳና፣ እሌኒ ብርሃንና ረመዳን ሙሳ ናቸው፡፡
በእነዚህ ስምንት ባለስልጣናትና ግለሰቦች ላይ ሰባት ክስ የቀረበባቸው ሲሆን ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም የመንግስት ህዝብን ሃብት አባክነዋል፣ የሙስና ወንጀልም ፈፅመዋል ብሏል - አቃቤ ህግ በክሱ፡፡
ኃላፊዎቹ ለአዳማ እርሻ መሳሪያዎች ኢንዱስትሪ አገልግሎት የሚውሉ ትራክተሮችና የትራክተር መለዋወጫ እቃዎችን ያለግልፅ ጨረታ ያለግዥ ፍላጎት ግዥ ፈፅመዋል ይላል - የክሱ ዝርዝር፡፡
ከዚህም ጋር በተያያዘ 319,475,287 ብር ማባከናቸው በክስ መዝገቡ ተመልክቷል፡፡
ከተከሳሾቹ መካከል ኮ/ል ጌትነት ጉድያ፣ ኮ/ል ጎይቶም ከበደ፣ እኔሊ ብርሃኔ በሌሉበት ነው ክሱ የቀረበባቸው፡፡ ሌሎች ተከሳሾች በክሱ ላይ ያላቸውን መቃወሚያ ከጠበቆቻቸው ጋር ተመካክረው ማቅረብ እንዲችሉ ተለዋጭ ቀጠሮ የጠየቁ ሲሆን ፍ/ቤቱም በእንግሊዝኛ የቀረቡ የሰነድ ማስረጃዎች ወደ አማርኛ ተመልሰው በ10 ቀናት ውስጥ ለፍ/ቤቱ እንዲቀርቡ አዝዟል፡፡ ተለዋጭ ቀጠሮም ለጥር 17 ቀን 2011 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡     

Read 1977 times