Saturday, 12 January 2019 14:06

“አዴፓ” እና “አብን” በአማራ ህዝብ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት ተስማሙ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአማራ ክልል ገዢ ፓርቲ “አዴፓ” እና አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ህዝብ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የተስማሙ ሲሆን ከሁለቱ ፓርቲዎች ስራ አስፈፃሚ አባላት የተውጣጣ የጋራ ኮሚቴ አቋቁመዋል፡፡
ሁለቱ ፓርቲዎች በስራ አስፈፃሚ ደረጃ የመከሩ ሲሆን በአዴፓ በኩል የፓርቲው ሊቀ መንበርና ም/ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም በአብን በኩል ሊቀመንበሩ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ስብሰባውን መርተዋል፡፡
በዚህ ስብሰባ ላይ የአዴፓ አስራ አንዱም የስራ አስፈፃሚ አባላት የተገኙ ሲሆን በተመሳሳይ የአብን ዘጠኙም ስራ አስፈፃሚዎች መገኘታቸው ታውቋል፡፡ ውይይቱ በዋናነት አሁን ያለውን የፖለቲካ አሰላለፍ ታሳቢ ያደረገ ነው የተባለ ሲሆን በፀጥታ፣ በሰላምና ደህንነት እንዲሁም በልማትና በአማራ ህዝብ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል፡፡
ሁለቱ ፓርቲዎች በአማራ ህዝብ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት የጋራ ኮሚቴ አቋቁመዋል፡፡ ከሁለቱ ፓርቲዎች ስራ አስፈፃሚዎች የተመረጡት የጋራ ኮሚቴው አባላት ወደፊት ዝርዝር መግለጫ ይሰጣሉ ተብሏል፡፡

Read 1454 times