Print this page
Saturday, 12 January 2019 14:06

የኢዜአን አደረጃጀት በማፍረስ እንደ አዲስ የሚያቋቁም ረቂቅ አዋጅ ለምክር ቤት ቀረበ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አደረጃጀትን በማፍረስ እንደ አዲስ ለማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡ ለም/ቤቱ የቀረበው ይኸው ረቂቅ አዋጅ እንደሚያመለክተው$ የድርጅቱን አስተዳደራዊና የአሰራር ነፃነት በማረጋገጥ ሥራውን በአግባቡ እንዲያከናውን ለማድረግ ታስቦ በ1987 ዓ.ም ተጠሪነቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሆን በማድረግ ተቋቁሟል፡፡ ይህ ሁኔታም ለድርጅቱ የተሻለ አስተዳደራዊ ነፃነት ስለሰጠው የአሰራር ስርዓቱን ለማዘመንና የባለሙያዎቹን ሙያዊ ክሕሎት ለማሳደግ እንዲችል አድርጐት ነበር፡፡
ይህን የማሻሻያ ስራም በ1999 ዓ.ም በአዋጅ ፈርሶ በመምሪያ ደረጃ እንዲደራጅ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ኢዜአ በመምሪያ ደረጃ እንዲደራጅ ከተደረገ በኋላ የጀመራቸው ፕሮግራሞች እንዲቋረጡና የገነባው ሙያዊ ስምን እንዲያጣ አድርጐታል፡፡ ይህንን ሁኔታ ለማሻሻልና ተቋሙን በተሻለ ደረጃ፣ በአዲስ መንገድ ለማደራጀት ታስቦ በአዋጅ ቁጥር /097/2011 በቅርቡ ድርጅቱ ተጠሪነቱ በቀጥታ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህም ተቋሙ ተጠሪነቱ ለአስፈፃማው አካል በነበረበት ወቅት የገጠሙትን ዋና ዋና ችግሮች እንደሚቀርፍና ተቋሙን ለማሳደግ የተሻለ እድል እንደሚፈጥር የታመነበት መሆኑ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተገልጿል፡፡
ድርጅቱ አብዛኛውን ወጪዎቹን በራሱ መሸፈን እስከሚችል ድረስ በዋናነት በበጀት የሚተዳደር የመንግስት መስሪያ ቤት ሆኖ እንዲቀጥል እንደሚደረግ የሚጠቁመው አዋጁ፤ መንግስት በጀት ከመመደብ ባለፈ ተገቢ የስራ ድጋፍና ቁጥጥር እንዲያደርግ ያስችለዋልም ተብሏል፡፡
ኢዜአን እንደገና እንዲቋቋም ማድረጉ በየጊዜው የሚለዋወጠውን የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በየጊዜው አሰራሩንና አደረጃጀቱን እንዲያሻሽልና የሰው ሃይሉንና የቴክኖሎጂ አቅሙን እንዲያዳብር እድል እንደሚሰጠው ተገልጿል፡፡

Read 709 times