Sunday, 06 January 2019 00:00

ሕጻናት…ኤችአይቪ…ኤይድስ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)


ሕጻናት ለምን በኤችአይቪ ቫይረስ ይያዛሉ?
ሕጻናት በኤችአይቪ ቫይረስ መያዛቸውን እንዴት ማወቅ ይቻላል?
የሚደረግላቸው እርዳታ ምንድነው?
ሕጻናት ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው እያለ ጤናማ ሆነው ማደግ የሚችሉበት መንገድ ምንድን ነው?
Jonathan E. Kaplan, MD የተባሉ የህክምና ባለሙያ June 12 /2017/ ለንባብ ያበቁት መረጃ እንደሚገልጸው በአለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ በኤችአይቪ ቫይረስ የሚጠቁ ልጆች ቁጥር እየቀነሰ ነው፡፡ እንደውጭው አቆጣጠር በ2015/መጨረሻ ወደ 2.6/ሚሊዮን የሚሆኑ እድሜ ያቸው ከ15/ አመት በታች ያሉ ሕጻናት ቫይረሱ በደማቸው እንደነበር እና ከእነዚህም መካከል 1/3ኛው ያህል ብቻ የህክምና እርዳታ እንዳገኙ መረጃው ይጠቅሳል፡፡
አብዛኛው ክሕጻናት ጋር የሚያያዘው የኤችአይቪ ቫይረስ ጉዳይ ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት በተለይም በደቡብ አካባቢ በርት ብሎ ይታያል፡፡ ኤችአይቪ በእነዚህ ሀገራት ታዳጊዎችንና ለታዳጊነት እድሜ ያልደረሱትን በመግደል እንዲሁም የህጻናቱን የበሽታ መቋቋም ኃይል በመቀነስ በኩል ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ ያለ ነው። ስለዚህም እንደ ኢንፌክሽን እና  ካንሰር የመሳሰሉ ሕመሞችን ለመቋቋም ሕጻናቱ ይሳናቸዋል፡፡
ነገር ግን በጊዜው ተደርሶ በትክክለኛው ሕክምና ተደርጎላቸው አስፈላጊውን መድሀኒት እንዲወ ስዱ በማድረግ የህክምና እርዳታውን ካገኙ ሕጻናቱ ቫይረሱ በደማቸው ቢኖርም ለረጅም ጊዜ በተሙዋላ ጤንነት በሕይወታቸው ማድረግ የሚገባቸውን ነገር እያደረጉ መኖር ይችላሉ፡፡   
ሕጻናቱ የኤችአይቪ ቫይረስ እንዴት ያገኛቸዋል?
አብዛኞቹ ልጆች የኤችአይቪ ቫይረስ የሚይዛቸው ፤
በእርግዝና ወቅት እናቶቻቸው ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ካለ፤
እናትየው በደምዋ ውስጥ ቫይረሱ ካለ እና በወሊድ ጊዜ፤
ወይንም ቫይረሱ በደምዋ ውስጥ ያለ እናት ጡት በምታጠባበት ወቅት ሊሆን ይችላል፡፡  
ሴቶች በእርግዝና ወቅት የኤችአይቪ ምርመራ ካደረጉ እና እራሳቸውን ካወቁ በሁዋላ በሕክም ናው ዘርፍ የሚነገራቸውን የህይወት መመሪያ እና ጥንቃቄ እንዲሁም ላረገዙት ልጅ ጭምር የሚረዳ ማንኛውንም ሕክምናና የምክር አገልግሎት በትክክል ከተጠቀሙበት የተረገዙት ልጆች በቫይረሱ የመያዝ እድላቸው እጅግ የቀነሰ ይሆናል። ምክንያቱም ቫይረሱን ወደልጆቹ የማስተ ላለፍ እድሉ በእጅጉ የቀነሰ ስለሚሆን ነው፡፡
ከላይ ከተገለጸው በተጨማሪ  ወላጆቻቸውን ወይንም ቤተሰቦቻቸውን በሞት የተነጠቁ ሕጻናት ለቫይረሱ ተጋላጭነታቸው ሲጨምር ይታያል፡፡ ለዚህም በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል ተንከባካቢ ማጣታቸው ወይንም ወደትምህርት ቤት እንዲሄዱ ስለማይደረግ ወይንም ልጆቹ ለመብታቸው መቆም እና እራሳቸውን መከላከል ስለማይችሉ ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም የተለያዩ ችግሮች ይደርሱባቸዋል፡፡
ሕጻናት ተገዶ መደፈር ወይንም ወሲባዊ ጥቃት ሊደርስባቸው እና ለቫይረሱ ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡
ሴት ልጆች ካለእድሜ ጋብቻን እንዲፈጽሙ ስለሚደረጉ ለቫይረሱ የመጋለጥ እድላቸው ይጨምራል፡፡
ወጣቶች ወይንም ህጻናት በመጀመሪያው የወሲብ ግንኙነታቸው ለኤችአይቪ ቫይረስ የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ነው፡፡
አንዱ በተጠቀመበት መርፌ ወይንም ምላጭ የመሳሰሉ ስለታማ ነገሮች ከተጠቀሙ እንዲሁም ቫይረሱ ያለበት ሰው በተወጋበት መርፌ ካለምንም ጥንቃቄ ወይንም መርፌው ሳይለወጥ ሌላው ሲወጋ ቫይረሱ የመተላለፍ እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ይህ በተለይም ገቢያቸው አነስተኛ በሆኑ ሀገራት የሚታይ እውነታ ነው ጆናታን እንደሚሉት።
ሕጻናት በኤችአይቪ ቫይረስ የመያዝ ምልክታቸው ምንድው?
በእርግጥ ሁሉም ሕጻናት በኤችአይቪ ቫይረስ ስለመያዛቸው በአፋጣኝ የሚታይ ምልክት አይኖርም። ምልክቶቹ በእድሜ እና በአንዳንድ ምክንያቶች ልዩነት ይኖራቸዋል፡፡ በአብዛኛው የሚስተዋሉት ምልክቶች ግን የሚከተሉት ናቸው፡፡
እድገታቸው ከተጠበቀው ወይንም በእድሜያቸው መሆን ከሚገባው በታች መሆን ፤
በእድሜያቸው ተመጣጣኝ የሆነ አስተሳሰብ ወይንም ብስለት ማጣት እና ተገቢውን ድርጊት አለመፈጸም፤
የአእምሮ ወይንም የነርቭ ስርአት ችግር፤ …በእግር ለመሄድ መቸገር፤ በትምህርት ቤት ውስጥ ሊሳተፉባቸው ከሚገቡ ነገሮች ወደሁዋላ መቅረት…ወዘተ
ባልተጠበቀ መንገድ መታመም፤ (እንደጆሮ ኢንፌክሽን ወይንም ጉንፋን ወይንም የሆድ ሕመም ተቅማጥ…) የመሳሰሉት ሕመሞች ሕጻናቱ ሊታዩባቸው ይችላል፡፡
ሕጻናቱ የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ሲኖር የሚደረግላቸው ሕክምና፤
ሕጻናቱ በደማቸው ውስጥ ቫይረሱ ሲገኝ ልክ እንደአዋቂዎች ጥሩ ሕክምና ይደረግላቸዋል፡፡ አዋቂዎቹ የሚወስዱትን ART ይወስዳሉ፡፡ በእርግጥ እንክብሉን ለመስጠት በሚያስቸግርበት እድሜ ማለትም በጣም ሕጻናት ከሆኑ በፈሳሽ መልክ ካልተገኘ እና እንክብሉን ሕጻናቱ ስለማ ይውጡት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዴም መድሀኒቶች ለህጻናቱ የጎንዮሽ ጉዳት የሚያስ ከትሉበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ገና የተወለዱ ጨቅላዎች በመጀመሪያው በተወለዱበት ቀን መድሀኒቱን ስለማይጀምሩ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ካለባቸው ጨቅላዎች ግማሽ ያህሉ 2ኛው ቀን ላይ ሳደርሱ ይሞታሉ፡፡ ከዚህ በተረፈ እድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ መድሀኒቱን እየተጠቀሙ ጤናማ ሕይወትን እንዲኖሩ ያስችላቸዋል፡፡  በእርግጥ ART በመውሰድ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ እንደ…የምግብ ፍላጎት ማጣት…ጉንፋን…ተቅማጥ…የመሳሰሉት ሕመሞች ሕጻናቱ ቢታይባቸውም እንደማንኛውም የህጻናት ሕመም በሕክምና ክትትል ሊደረግላቸው እና ሊታከሙ ይችላሉ፡፡  
ህጻናት ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እያለ በጤናማነት እንዲያድጉ ምን ያስፈልጋል?
ህጻናት በደማቸው ቫይረስ መኖሩ ከታወቀ ወላጆች ወይንም ቤተሰቦችና ሌሎችም የሚመለከታ ቸው ሰዎች ሁኔታውን ለልጆቹ በእርጋታ ማስረዳት አለባቸው። ሕጻናቱ ሕመሙ ስላለባቸው እንዳይደናገጡ እና እንዳይጨነቁ ለማድረግ የቻሉትን መንገድ ሁሉ በመጠቀም ልጆቹን ከፍርሐት ስሜት ማጽዳት ትልቁ ቁምነገር ነው፡፡
ሕጻናቱ ከሌሎች ልጆች በተለየ በየቀኑ መድሀኒት ለምን መውሰድ እንዳስፈለጋቸው እና የታመሙትም በእነሱ ጥፋት ወይንም በመታመማቸው ምክንያት ኃላፊነት መውሰድ እንደሌለባቸው ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡
ሕጻናቱ ብቸኝነትን አይፈልጉትም፡፡ ማህበራዊ ግንኙነታቸው እንዳይቋረጥ፤ የገንዘብ ፍላጎታቸው እንዲሟላ እና መላው ቤተሰብ ሞራሉ የተገነባ እንዲሆን በተለይም አቅም በሌለው ሕብረተሰብ ዘንድ በጣም ያስፈልጋል፡፡
ሕጻናቱ ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ቢኖርም እንደማንኛውም ልጅ ካለምንም ችግር እና ፍርሀት ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በትምህርት ቤት ውሎአቸው ከሌሎች ልጆች ጋር እንዳይቀራረቡ የሚያደርጋቸው አድሎና መገለል እንዲሁም ዝቅተኛ ተደርጎ መታየት እንዳ ይደርስባቸው ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ይህን ለመከላከልም አስተማሪዎች እንዲሁም መላው የትምህርት ቤት ማህረሰብ ተማሪዎችን ጨምሮ የኤችአይቪ ቫይረስ እንዴት እንደሚተላለፍ እውቀቱ እንዲኖራቸው ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ንቃተ ሕሊናን ማሳደግ ከተቻለ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ሕጻናት ወይንም ተማሪዎች በቤተሰብ ውስጥ ግልጽ ውይይት የሚደረግበትና ሕጻናቱ ሞራላቸው የሚገነባበትን መንገድ ማመቻቸት ይቻላል፡፡ እንዲሁም የንቃተ ህሊና መዳበር ካለ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ህጻናት በትምህርት ቤት ውስጥ በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ እና ትምህርት እንዲከታተሉ ስለሚያስችላቸው ለእድገታቸው ወሳኝ መሆኑን Jonathan E. Kaplan, MD አክለው ገልጸዋል፡፡  

Read 567 times