Sunday, 06 January 2019 00:00

‘ከጠፋ’ በኋላ ሳይሆን ‘ከመጥፋቱ በፊት’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

  እንኳን ለብርሀነ ልደቱ አደረሳችሁ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…ዘንድሮ የበዓል መዳረሻ ሰሞን ትንሽ ቀዝቀዝ አለ ልበል! ለነገሩ አይገርምም። ውስጣችን ሰላም ሳይሆን፣ ውስጣችን ብዙ ስጋቶች ባሉበት፣ የግድ “አሀ ገዳዎ” እንበል ብንልም ሙሾ እንጂ ዘፈን አይሆንማ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የበዓል ወጪን አስመልክቶ ሲፈጠሩ የነበሩ መለስተኛ የባልና ሚስት ፍልሚያዎች… አሁን፣ አሁን ‘ጊዜው አለፈባቸው’ እንዴ! ወይስ “ለማን ደስ ይበለው!” በሚል በየቤቱ ‘ሳይለንት’ ፍልሚያዎች እየተካሄዱ ነው! ለነገሩ በዓልን አስታከው አይምጡ እንጂ ዘንድሮ እኮ በትንሽ፣ በትልቁ መፋለም እየተለመደ መጥቷል፡፡
እግረ መንገድ የሆነ ነገር ትዝ አለኝ…ይሄ የኳሳችን ነገር እንዴት ሆነ?!  ጨዋታ ካለፈ በኋላ ግጥሚያው እንዴት እንደነበረ፣ ማን ማንን እንዳሸነፈ ሳይሆን … “ጨዋታው በሰላም ተጠናቋል?” ሆኗል፤ ጥያቄው። የምር ከዚህ የባሰ ሽንፈት የለም እኮ! “ጨዋታው በሰላም ተጠናቋል” የሚለው የጨዋታው ዘገባ ዋናው ሀረግ ሲሆን ነገሮች ምን ያህል ፈር እየለቀቁ እንደሄዱ ማሳያ ነው፡፡ በተመልካቾች መሀል ከስንት አንዴ ረብሻ በፊትም ነበር፡፡ ከአንዳንድ ጨዋታዎች በፊት ስጋቶች የሚያንዣቡበት ጊዜ ነበር፡፡
ስሙኝማ... የኳስ ነገር ካነሳን አይቀር፣ አንድ ጊዜ በቅዱስ ጊዮርጊስና መቻል መሀል ይደረግ ከነበረ ወሳኝ ግጥሚያ በፊት በነበረው ሳምንት ከተማው ላይ አንዣቦ የነበረው ስጋት ልክ የሙሶሎኒ ዘሮች ለሦስተኛ ዙር የመጡ ይመስል እንደነበር ትዝ ይለናል። የጄኔራሎቹ ሁሉ መወያያ ሆኖ ነበር፡፡ ያኔ ኳሱም የተቃውሞ መግለጫ ስለነበር ካምቦሎጆውም “ሆድ ያባውን ኳስ ያወጣዋል” አይነት ነበር፡፡ አንደ ዘንድሮው የዘር፣ የትውልድ ስፍራ፣ አፍ መፍቻ ቋንቋ … ምናምን ነገር አልነበረም፡፡
እዛ ማዶ የጦሩ ደጋፊ “ይናዳል ገደሉ፣” ሲል እዚህ ማዶ “እኛው ነን፣ እኛው ነን” ይባል ነበር። ግን ኳሱ የምር ኳስ ነበር፡፡ ተጫዋቾቹም እንደ ዘንድሮ በየወሩ መለስተኛ ፋብሪካ እንኳን ማግኘት የሚያዳግተው ደሞዝ እየተከፈላቸው ሳይሆን ኳሱ ሲያልቅ ቤታቸው የሚሄዱበት የአውቶብስ ፍራንክ የሚያጡበት ነበር። የዘንድሮ ኳሳችን ‘ትራጄዲ’ እኮ ነው፡፡ አለ አይደል… ገንዘቡ ይፈሳል … ‘የኳስ ደጋፊ ነኝ’ የሚለውም ይፈሳፈሳል፡፡
ብዙ ጊዜ ሜዳ ላይ በዳኝነት ውሳኔዎችና በመሳሰሉ በሚፈጠሩ ክስተቶች፣ በተመልካች መሀል ብጥብጥ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ካምቦሎጆ ውስጥ ወይም በአካባቢው ለጥቂት ጊዜ ትርምስ ይሆንና ነገሩ በዛው ያበቃል፡፡ እንደውም ብዙዎቹ የጸጥታ አባላት ጣልቃ ገብነት ሳያስፈልግ ሁሉም በዚህ በኩል፣ በዚያ በኩል ወደ ቤቱ ሮጦ በዛው ያልቃሉ። በወሩ ወይም በሁለት ወሩ እነኛው ቡድኖች ደግመው ሲገናኙ ፍጹም ሰላማዊ ጨዋታ ይካሄዳል፣ ይኸው ነው ሂሳቡ! እንደ ዘንድሮ በቀደም “እንዲህ አድርጋችሁንማ ከተውናችሁ ሞተናላ!” አይነት ነገር የለም፡፡ ሌላው የኳሳችን ትልቅ ‘ትራጄዲ’ ብጥብጦች ዋናው ሰበባቸው ኳስ አለመሆኑ ነው፡፡ ይኸው ነው ዘንድሮው ሂሳቡ!
እናማ…በዚህ በፍቅርና በሰላም በዓል ሰሞን የኳስ ሜዳዎቻችን ሰላም ይመለስልን እንላለን። ችግሩ ሁሉንም የሚመለከት ስለሆነ፣ ሁሉም ለዘላቂ መፍትሄ ይሥራ እንላለን፡፡ ገና ለገና ፊፋዎች ያኮርፋሉ፣ ይቆጣሉ እየተባለ የአገር ሰላም በኳስ የተነሳ ሲታመስ ዝም ብሎ ማየቱ በምንም መለኪያ ልክ አይሆንም፡፡ ቡድኖች “ለደህንነታችን ስለምንሰጋ እንትን ከተማ ሄደን አንጫወትም” አይነት ነገር ሲበዛ ዝም ብሎ ስለ ስፖርት የሰላም መሳሪያነት እየደሰኮሩ መቀጠል ይቻላል እንዴ!
ኳስ ሜዳዎቻችን የፍቅርና የሰላም ስፍራዎች የሚሆኑበትን ጊዜ ያፍጥንልን፡፡ አለበለዛ ከዚች መከራ ከማያጣት አገር ደህንነትና ከዚህ መከራ ከማያጣው ህዝብ ሰላም የሚበልጥ ምንም ነገር ሊኖር አይችልም…ኳስም ቢሆን፡፡
 አሁን ግን በጣም የሚያስጠላ ደረጃ ላይ ደርሷል። በሻይ ማንኪያ ገቢ የማያስገባ ስፖርት፤ በቡልዶዘር መአት ብር እየተዛቀበት፣ ለምንድነው በህዝብ መሀል መቃቃርን የሚፈጥሩ ነገሮች ሲበዙ፣ ፈጣን እርምጃ መውሰድ ያልተቻለው እንላለን፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ የበዓል ሰሞንም አይደል፡፡ የሴት ልጅ  የምግብ አሠራር ባለሙያነት የሚለካው ዶሮ መሥራት ትችላለች፣ አትሠራም በሚል ነው፡፡ ዶሮ መሥራት ካልቻለች ለፕሬሚየር ሊግ አትመጥንም ማለት ነው፡፡ አሥራ ሁለቱን ብልት ሳታዛንፍ መለያየት አለባት፡፡ (በነገራችን ላይ…አሁንም የዶሮ ብልት አሥራ ሁለት ነው… አይደል! አይ…የሚቆረሱና ሊቆረሱ ስለት እየተሳለላቸው ያሉ ነገሮች ስለበዙብን ነው፡፡ ፈረሰኛ “የእኔ ስጋ የዶሮዋን አንድ አራተኛ ስለሆነ..” ምናምን አይነት የ‘ሰልፍ ዲተርሚኔሽን’ ጥያቄ አንስቶ ወይም ሊያነሳ አስቦ ከሆነ ማን ያውቃል! እናላችሁ… እዚሀ አገር ምንም ነገር ቢሠራ መደነቅ ትተናል፡፡)
እናላችሁ… የዶሮን ነገር ካነሳን አይቀር … አንዲት ሴት ከአንድ ዶሮ አሥራ ሶስት ብልት ስለማውጣቷ ሰምተን ነበር፡፡ “አይ የእኛ ገልቱ” ተብሎ ተሳቀባት አሉ፡፡ አሀ… ‘ሊበራሊዝምን’ በመሰላት መልክ ብትተረጉመው መብቷ አይደል እንዴ! ቂ…ቁ…ቂ… (እንደ ዘንድሮ ቢሆን “የኮፒራይት ቢሮ የት ነው?” ብዬ እጠይቅ ነበር፡፡
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እንደ ዘንድሮ ‘ፖለቲካ የሚመስሉ’ ነገሮቻችን፣  እነኚህ አሥራ ሁለት የዶሮ ብልቶች መናገር ቢችሉና ‘የልምድ ልውውጥ’ ቢያደርጉ፣ ሊከተሉት የሚችሉትን ፖለቲካ ስታስቡት…አለ አይደል…ተጨማሪ ራስ ምታት ባይሆኑ ነው! መላላጫው “እኔን ለብቻዬ አንድ ሳህን ላይ የማታስቀምጡኝ፣ እነ አጭሬ ከእኔ በምን በልጠው ነው!” ቢል አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
ደግሞላችሁ…እንግዲህ ፈረሰኛው የሆነ አባወራ አይነት ነገር አይደል…ያገባኛል የሚል  ‘አክቲቪስት’ ነገር…“ፈረሰኛው ትንሽ ሞላ ያለ ስለሆነ ፍትሀዊ የሥጋ ክፍፍል እንዲኖር ለአንድ ሰው ብቻ መሰጠቱ ቀርቶ ለሶስት ሰዎች ይከፋፈል” የሚል ‘ካምፔይን’ ነገር ሊጀምር ይችላል፡፡ አንድ ጊዜ ሆነ ብለው የነገሩን ነው። የሆነ ስታንድ አፕ ኮሜዲ የሚመስል ነው፡፡ እሱና እሷ በሆነ ነገር ሳይጋቡ ይቀራሉ፡፡ እና እሷ ምን አለች አሉ… “ዋ ዲቪ እንዳልሞላ!” ይቺ እንኳን ‘ፌክ ኒውስ’ ትመስላለች፡፡
ስሙኛማ… በቀደም ‘ጩኸቱን የተነጠቀው’ና ጭርታ የበዛበት የ‘ድሮው ቦሌ’ አካባቢ እያለፍን ሳለ፣ ግፋ ቢል ከሀያና ሀያ ሁለት የማትበልጥ ልጅ ፊት ለፊት ትመጣለች፡፡ ከመሀላችን አንዱ “እዩዋት” ይላል። አለባባሷ አሪፍ ሱሪ፣ አሪፍ ጫማ፣ አሪፍ ጃኬት ምናምን ይሆንና፣ ሆድ አካባቢ ነገርዬው ለየት ይላል፡፡
ልብስ ያልሸፈነው ስፍራ ቢያንስ አስራ አምስት ምናምን ሴንቲሜትር ሊሆን ምንም አይቀረው፡፡ የሚገርመው ነገር. ..አይደለም ወንዶች ወጣት ሴቶች ሁሉ ዘወር እያሉ ያዩዋት ነበር፡፡ እዛ አካባቢ ባለው የሰውነቷ ክፍል “እንዲች ብለሽ ጨርቅ የሚባል ነገር ታስነኪኝና ወይ እኔ ወይ አንቺ!” የተባለች ነው የሚመስለው፡፡
እኔ የምለው…ታጥረው የቆዩ ስፍራዎች አጥር እየፈረሱ ስናያቸው፣ ታጥረው የከረሙ የሰውነት ክፍሎችም የመብት ጥያቄ አነሱ እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ…!
በነገራችን ላይ አንድ ሰሞን እምብርት እንቁልልጭ በዝቶ ነበር፡፡ ምን ግርም ይልሀል አትሉኝም… እንደዛ ‘ፌመስ’ ሆና የነበረችው እምብርት፣ ለአቅመ ፕሮፋይል ፒክቸርነት አለመብቃቷ!
አውቆም፣ ሳያውቅም የሚያጠፋ በበዛበት ዘመን ይቺን ስሙኝማ…
ሴትየዋ በሆነ ጥፋት ተከሳ ዳኛ ፊት ትቀርባለች። ዳኛውም ይጠይቋታል…
“ጥፋተኝነትሽን ታምኛለሽ?”
“አዎ ክቡር ዳኛ፣ አምናለሁ፡፡”
“ታዲያ መጀመሪያውኑ ለምን አላመንሽም?”
“ክቡር ዳኛ፤ የምስክሮቹን ቃል ከሰማሁ በኋላ ጥፋተኝነቴን አመንኩ፣” አለችና አረፈችው፡፡
‘ከጠፋ’ በኋላ ሳይሆን ‘ከመጥፋቱ በፊት’ መከላከል የምንችልበትን ብልሀቱንና ትእግስቱን ይስጠንማ!
መልካም የበዓል ሰሞን!
ደህን ሰንብቱልኝማ!

Read 2750 times