Sunday, 06 January 2019 00:00

ቃለ ምልልስ በውዝግብና በስጋት የታጀበው የዘንድሮ “ጉዞ አድዋ”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  “ማንም እንዳይነካን በጠመንጃ ተጠብቀን ማለፍ አንፈልግም”

    ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ የሚካሄደው “ጉዞ አድዋ”፤ ከሌሎች ጊዜያት በተለየ ከሃረር በመነሳት፣1540 ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጦ፣ ፍፃሜውን የካቲት 23 ቀን 2011 ዓ.ም አድዋ ሶሎዳ ተራራ ላይ ያደርጋል። “ፍቅር ለኢትዮጵያ” በሚል መርህ የሚደረገው ጉዞ አድዋ፤ በውዝግብና በስጋት የታጀበ ይመስላል። አንዳንድ አክቲቪስቶች “ወደ ትግራይ ድርሽ እንዳትሉ” የሚል ማስጠንቀቂያ በማህበራዊ ሚዲያ ሲያሰራጩ መቆየታቸውን የሚገልጸው የጉዞው መስራችና አስተባባሪ አርቲስት ያሬድ ሹመቴ፤ አዝማሚያው ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ጎጂ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ባለፉት ዓመታት በክብር የተቀበሏቸው የትግራይ እናቶች፤ ዘንድሮም  ተመሳሳይ አቀባበል እንደሚያደርጉላቸው በእርግጠኝነት ተናግሯል፡፡
ከጉዞው መሥራቾች መካከል ጥቂቶች ተከፍለው በመውጣት፣በ”ጉዞ አድዋ” ስም የበጎ አድራጎት ማህበር ፈቃድ ማውጣታቸው ታውቋል፡፡ ሆኖም የተለመደው ዓይነት ውዝግብና እንካ ሰላንቲያ አልተፈጠረም፡፡ እንዴት አልተፈጠረም? የያሬድ ሹመቴ ቡድን፣ጉዳዩን እንዴት አስተናገዱት? የአክቲቪስቶች ቅስቀሳ በተጓዦቹ ላይ የፈጠረው ፍርሃትና ስጋት ይኖር ይሆን? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ከፊልም ባለሙያው ያሬድ ሹመቴ ጋር በጉዞውና በእነዚህ ውዝግቦች ዙሪያ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡  


    የዘንድሮ “ጉዞ አድዋ” ከዚህ ቀደም ከነበሩት በምን ይለያል?
የዘንድሮ ጉዞ ለ6ኛ ጊዜ ነው የሚካሄደው፡፡ ሁልጊዜ እንደምለው፣ ከመጀመር በላይ ትልቅ ዋጋ ያለው የተጀመረው ነገር ሳይቋረጥ ማስቀጠሉ ነው። የተጓዥ ቁጥርም ጨምሯል፡፡ ሌላው የዘንድሮውን ለየት የሚያደርገው ጉዞው ከአዲስ አበባ ውጪ (ሃረር) መጀመሩ ነው፡፡ የእስከዛሬ ጉዞአችን 1010 ኪሎ ሜትር ነበር፤ ዘንድሮ 1540 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍን ጉዞ ሆኗል፡፡ በተጨማሪም ያለንበት ወቅት እንዲህ ያለውን ጉዞ ለማካሄድ ጭንቀትና ስጋት የሚፈጥሩ ብዙ አለመረጋጋቶች ባሉበት፣ እንዲሁም የብሔራዊ ስሜት የደፈረሰበት የሚመስል ወቅት ላይ በመሆኑ፣ ይሄንንም ፈተና ለማለፍ አስቦ መነሳት በራሱ ምን ያህል ቁርጠኝነት ያላቸው ተጓዦች እንደተፈጠሩ የሚያሳይ ነው፡፡
ለምንድን ነው በዘንድሮ ጉዟችሁ ከሃረር መነሳትን የመረጣችሁት?
እንደሚታወቀው የዛሬ 123 ዓመት፣ የአድዋን ድል ታሪክ እውን ለማድረግ፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው ከያሉበት ወደ አድዋ የዘመቱት፡፡ ስለዚህ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ስብስብ አድዋ ላይ መግባት ማስታወስ የሁልጊዜ ህልማችን ነበር፡፡ የወደፊት ህልማችሁ ምንድን ነው? ተብለን ስንጠየቅ፤ “ጉዞ አድዋን ጉዞ አድዋ ማሳከል ነው” ብለን እንመልስ ነበር፡፡ አድዋን ለማከል ደግሞ ከአዲስ አበባ ብቻ መነሻን አድርጎ መጓዙ በቂ ስለማይሆን፣ ከሁሉም አካባቢዎች መጓዝ መጀመር አለበት፡፡ ስለዚህ ይሄኛው ከሃረር እንዲጀመር ያደረግንበት ትልቁ ምክንያት፣ የዛሬ 123 ዓመት ወደ አድዋ የዘመተውን የሃረርን ጦር ሲያስተባብሩ የነበሩት ራስ መኮንን፣ በታሪክ ውስጥ የነበራቸውን ሚና ስናይ፣ “ቀዳሚው ጦር” የሚል ስያሜ የተሰጠውን ጦር የሚመሩ ነበሩ። ቀዳሚ ጦር ማለት ከንጉሰ ነገስቱ ጦር በፊት ቀድሞ ሄዶ ሁሉንም መንገድ እየጠረገ፣ አድዋ ድረስ የደረሰ ጦር ነው፡፡ ስለዚህ ዘንድሮ ቀዳሚ ጦሩን ለማስታወስ ከሃረር ተነስተናል፡፡ ተጓዦቹ አዲስ አበባ ከደረሱ በኋላ፣ ከአዲስ ተጓዦች ጋር ጉዞው ይቀጥላል ማለት ነው፡፡
ከአዲስ አበባ ተጓዦች ጋር መቼ ነው የምትቀላቀሉት? በአጠቃላይ ስንት ተጓዥ ይሳተፋል?
የሃረር ተጓዦች ብዛት 5 ነበሩ፡፡ ነገር ግን አንድ ልጅ በዋዜማው በጤና ምርመራ ከጉዞው ተሰርዟል። አሁን አራት ናቸው፡፡ ጥር 5 ቀን 2011 ዓ.ም አዲስ አበባ ይደርሳሉ፡፡ ከዚያም ጥር 6 ቀን የሽኝት መርሃ ግብር ይደረጋል፡፡ ጥር 7 ጉዞ ይጀመራል፡፡ ከአዲስ አበባ 30 ወጣቶች ለጉዞ የተዘጋጁ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ወደ አድዋ የሚጓዙት 35 ናቸው፡፡ በመጨረሻ ላይ ከትግራይ- ሽሬ የሚነሱ 5 ተጓዦች አሉ፤እነሱ ሲጨመሩ 40 ተጓዦች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡
በዚህ ጉዞ ላይ ምን አይነት ክንውኖች ይኖራሉ?
የ”ጉዞ አድዋ” ዋና ዓላማ፤ የአድዋን ድል ታሪኩን እያጠኑ ለመጓዝ ስለሆነ፣በተቻለ አቅም በታሪክ የተጠቀሱ ቦታዎችን በሙሉ እየዳሰስን ነው የምንሄደው፡፡ አዳማ ላይ ትልቅ አቀባበል ይደረጋል። የድሉን ስሜት የማስታወስ ስነ ስርአት ይከናወናል። ይህም ሁሉም ኢትዮጵያውያን የአድዋን ድል በመዘከር የአንድነት ስሜትን ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ቢሾፍቱ ላይ ትልቅ ዝግጅት ይኖረናል፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ አድዋ ድረስ ከ28 በላይ ከተሞች ነው የምናቆራርጠው። የአዲስ አበባ ነዋሪ ለገጠሩ ህዝባችን የሚልከንን በአደራ እናደርሳለን፡፡ ለዓመቱ አጋማሽ የትምህርት ዘመን ደብተር መግዛት ለማይችሉ የገጠር ተማሪዎች የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ያሰባሰቡትን የደብተር ስጦታ ይዘን በመሄድ፣ በምናድርባቸው ት/ቤቶች ውስጥ ለርዕሰ መምህራኑ እያስረከብን እናልፋለን፡፡ ይሄን ግን ስናደርግ መታወቅ ያለበት፣ እኛ መልዕክተኛ ነን እንጂ ከራሳችን ኪስ የገዛነው አይደለም፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ ሰብስቦ የሚሰጠንን ነው የምናደርሰው፡፡
ዋናውና ትልቁ ቁም ነገር፤ አሁን ያጠላብንን የመራራቅና የጥላቻ መንፈስ እንዴት አድርገን ነው መስበር ያለብን? እንዴት አድርገን ማስታረቅ እንችላለን? የሚለውን ታሳቢ በማድረግ፣ ፍቅርንና አንድነትን እየሰበክን፣ በተቻለን መጠን የሰላም ሃሳብ እየዘመርን፣ አድዋ በመግባት፣ የብሔራዊ አንድነት ሃሳብ እንዳይሞት አስተዋፅኦ ማበርከት እንፈልጋለን። ይሄን እናሳካለን ብዬም አምናለሁ፡፡
በየቦታው ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ከመኖራቸው አንፃር፣ችግር ይገጥመናል ብላችሁ አልሰጋችሁም?
በየዓመቱ የተለያዩ ፈተናዎች በየመንገዱ ይገጥሙናል፡፡ ዘንድሮ የሚጀመረው ከሃረር ነው። እስካሁን ባለው ጉዞ ጉዳዩ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ የፀጥታ አካላት በተደጋጋሚ አስቁመው፣ እነማን ናችሁ? የት ነው? ወዴት ነው? የሚለውን ጥያቄ፣ በጣም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነው የሚጠይቁት፡፡ ስናስረዳቸውም፣  በጥሩ ሁኔታ ነው ሃሳቡን የሚቀበሉት፡፡ እኛም የፍቃድ ወረቀቶችን በማሳየት ነው የምናልፈው፡፡ ከዚህ በኋላም ብዙ ችግር ያጋጥመናል የሚል ስጋት የለንም፡፡
በማህበራዊ ሚዲያ አንዳንድ አክቲቪስቶች “ወደ አካባቢው ዝር እንዳትሉ” የሚል ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውስ---?
የዘንድሮውን ዘመቻ በይፋ ከገለፅን ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ አክቲቪስቶች ወደ አድዋ የመምጣትን ጉዳይ በጥርጣሬ እንደሚመለከቱትና እንድንሄድ ፍላጎት እንደሌላቸው የሚገልፁ ቅስቀሳዎች በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያካሂዱ ነበር፡፡ እነዚህ ትልቅ ፈተናዎች ናቸው፤ ምንም ጥርጥር የለውም። ነገር ግን በኛ እምነት እስከ ዛሬ ተቀብሎ በደስታ ሲያስተናግደን የኖረው የትግራይ ህዝብ፣ እንዲህ ያለ ሃሳብ አለው ብለን አናምንም፡፡ ምክንያቱም የ5 ዓመቱ ልምዳችን የሚያሳየው፣ ህዝቡ ልጆቹን ተቀብሎን በጥሩ ሁኔታ ሲያስተናግደን ነው፡፡ ምንም ስጋት አልነበረንም፡፡ የዘንድሮው የተለየው እንግዲህ ወቅታዊ የፖለቲካ ግለቱ በፈጠረው ተፅዕኖ ነው። ይሄን ግለት ምን ፈጠረው የሚለውን መመርመር ማስተካከል ይገባል፡፡ መንግስትም ይሄን በተመለከተ የሚገባውን ስራ መስራት አለበት፡፡ እኛ የችግሩን አሳሳቢነት ማሳያ እንሆን ይሆናል እንጂ እኛን ለማዳን ብቻ አንድ ነገር መደረግ አለበት ብለን ለመጮህ አይደለም፡፡ “ይሄ የኔ ብቻ ነው፤ ማንም እንዳይደርስ” የሚለው አመለካከት ሲታይ፣ ለወደፊት ኢትዮጵያን ችግር ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ስለዚህ ይሄን ለማረም “እንደዚህ አትበሉ” ማለት ብቻ ዋጋ የለውም። እንዲህ የተባለበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚለውን አጥንቶ፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ በተለይም ይሄን ጥያቄ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በተደጋጋሚ የሚያነሱ አካላት፤ ጥያቄያቸው ምንድን ነው? በሚል አይቶ መንግስት ችግሮችን እየፈታ መሄድ አለበት፡፡ ከማዕከላዊ መንግስቱ ጋር እየሻከረ የመጣ የሚመስለውም ግንኙነት  መታረም አለበት፡፡ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ የሚመጣው ጥያቄያችን በለዘበ መንገድ፣ ማስከን የሚቻልበት ጥበብ ሲኖር ነው፡፡ አንዳንድ ጥሩ አያያዝ ያላቸውን ጥበቦች መንግስት አካባቢ እናያለን፣ ግን በመሃል ደግሞ ሲሰራ ሁሉንም አካል ማስደሰት አይቻልም፡፡ በጅምላ ብዙ ሰዎች የሚቀየሙበት ወይም ጥርጣሬ ውስጥ የሚገቡበት አካሄድ ካለ፣ መንግስት ራሱን መፈተሽ አለበት፡፡ ያ ሲሆን ነው ሰላም ተመልሶ መምጣት የሚችለው፡፡
በዚህ አጋጣሚ መናገር የምንፈልገው በጥበቃ አናምንም፡፡ የጥበቃ ኃይል ተመድቦ፣ እየተጠበቅን አድዋ መግባት ለኛ ሽንፈት ነው፡፡ ለኢትዮጵያም ኪሳራ ነው፡፡ እኛ የምንፈልገው ሰው አቀባበል፤ አሸኛኘት እንዲያደርግልን ነው እንጂ ማንም እንዳይነካን በጠመንጃ ተጠብቀን ማለፍ አንፈልግም። የኛ ፍላጎት ሃገራችን ሰላም መሆኗን ማረጋገጥ እንጂ በጠመንጃ አፈሙዝ ተከበን፣ ሰላም ሆነን መግባት አይደለም፡፡ ይሄ የሽንፈት ሰላም ነው፡፡ ታዋቂዋ ዘፋኝ ማሪቱ ለገሰ “ከሽንፈት ሰላም ሞት ይሻላል” ትላለች፡፡ የሽንፈት ሰላም የሚባለው በጠመንጃ ተጠብቆ ምንም ያለመሆን ነው፡፡ እኛ ጥበቃ ሳይሆን የተረጋጋ ሃገር ነው የሚያስፈልገን፡፡ ሰላምን፣ ፍቅርን እየሰበክን፣ ከህዝቡ ጋር ያለን መስተጋብር የተቃናና ሰላም እንደሆነ አድዋ እንገባለን የሚል ነው እምነታችን፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በእርግጥም መልካም ህዝብ ነው፤ ስለዚህ መልካም ነገር ይገጥመናል፡፡
አድዋ ሲነሳ አንዱ የሚያከራክረው የአፄ ምኒልክ ከድሉ ጋር ተያይዞ መነሳት ነው….
ዳግማዊ አፄ ምኒልክን በተመለከተ በዚህ አምስት ዓመት ውስጥ በየዓመቱ ያየናቸው ለውጦች አሉ። ለውጦቹ በአዎንታዊም በአሉታዊም መንገድ ነው። ቀደም ባለው ጊዜ የዳግማዊ አፄ ምኒልክን ስም ማንሳት አስቸጋሪ የነበሩባቸው ቦታዎች፣ አሁን ካለው ቦታ ውጪ ነበሩ፡፡ ዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ፤  ባለፉት 150 ዓመታት ከዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ መነሳት ወዲህ ያለው ነው፡፡ በአፄ ቴዎድሮስ ተጀመረ፣ በአፄ ዮሐንስ ቀጥሎ፣ እስከ አፄ ምኒልክ ዘመን ድረስ ያለው ጊዜ፣ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ቅርፅ መፍጠርያ ነበር። በዘመናዊ ኢትዮጵያ መፈጠር ውስጥ የእነዚህ ነገስታት ስም በተደጋጋሚ ይነሳል። አፄ ምኒልክ ስማቸው ከሚነሳባቸው ጉዳዮች አንዱ፣ የግዛት አንድነትን በማስጠበቅ፣ የዘመናዊ ኢትዮጵያን ቅርፅ ያመጡ ንጉስ ናቸው የሚለው ነው፡፡ በዚህ የግዛት ማጠቃለል ሂደት ውስጥ የተጎዳ አካል አይኖርም ማለት አይቻልም፡፡ በዚህ መነሻ ቅራኔና ቅሬታ የተፈጠረባቸው ሊኖሩ ይችላሉ። አፄ ምኒልክን የመጥላት ጉዳይ ኢትዮጵያዊነትን ከመጠራጠርና ካለመቀበል ጋር ተያይዞ የሚነሳ ነው፡፡ ስለዚህ የአፄ ሚኒልክ ስም አይነሳብን የሚለው ጥያቄ ጎልቶ በሚታይባቸው ቦታዎች አብሮ መፈተሽ ያለበት፣ ኢትዮጵያዊነት እዚያ አካባቢ ችግር ውስጥ እየወደቀ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህን ምልክቶች ይዞ ደግሞ መንግስት ትልቅ ስራ መስራት ነው ያለበት፡፡
ባለፉት 5 አመታት ውስጥ ይህ ስሜት በየቦታው ተፈራርቆ ተመልክተነዋል፡፡ ሌላው ከአድዋ ታሪክ ጋር በተያያዘ አፄ ምኒሊክ ለአፍሪካም የነፃነት አባት እየተባሉ ስማቸው የሚጠራበት ትልቁ ምክንያት የአድዋ ድል ነው፡፡ የነጭ ወራሪ አሸንፈው ማባረራቸው፣ ብዙ አፍሪካውያን አንገታቸውን ቀና እንዲያደርጉ ያስቻሉበት ታሪክ ነው፡፡ ይሄንን ታሪክ የአንድ ቀን ጦርነት ብቻ አድርገው የሚያስቡ አሉ። ይሄ ታሪክ አለማወቅ ነው፡፡ አድዋን ለማሸነፍ ኢትዮጵያን አንድ ማድረግ ያስፈልግ ነበር፡፡ ምክንያቱም የተበታተነ ህዝብ፤ የተደራጀን ኃይል ማሸነፍ አይችልም፡፡ ስለዚህ የተበታተነውን ህዝብ አሰባስበው፣ በአንድ ቦታ ላይ ለማስቀመጥ የተሰራው ታሪክ፣  የ7 አመት ተጋድሎ ነበረው፡፡
ሌላው ደግሞ ለምሣሌ ራስ አሉላ ታላቅ ጀግና ናቸው፡፡ አለም በጀግንነታቸው ነው የሚያውቃቸው። የአፍሪካ የመጀመሪያው ጀነራል የሚል ስያሜ ሁሉ ያላቸው ናቸው፡፡ በጉንደት፣ በጉራ፣ በዶጋሊ፣ በኩሪት… ታግለው ጀግና መሆናቸውን ያስመሰከሩ፣ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ናቸው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የሚመሰገኑበት ትልቅ ሃቅ፣ አፄ ዮሐንስን አገልግለው፣ በኋላ አፄ ምኒልክ ሲመጡም፣ ጦርነቱ አይመለከተኝም ብለው የተቀመጡ ሰው አልነበሩም፡፡ በሀገር አንድነት የሚያምኑ በመሆናቸው፣ ከአፄ ምኒልክ ጋር አብረው ዘምተው፣ ተዋግተው ድል እንዲመጣ ካደረጉ ግንባር ቀደም የኢትዮጵያ ጀግናዎች ውስጥ ስማቸው የሚጠራ ጀግና ናቸው፡፡ እኚህ ታላቅ አባታችን የአንድ ጐሣ ወይም ህዝብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ወገን ናቸው፡፡ ስለዚህ ጀግኖቻችንን፣ የአንድነታችን ድልድይ እንዲሆኑ መጠቀም እንጂ ለልዩነታችን ምክንያት እያደረግን ማሳበብ አያስፈልግም፡፡ የራስ መኮንንን ስም ከሀረር እንደጠቀስነው ሁሉ፣ ራስ አሉላና ራስ መንገሻ ለሀገር የከፈሉትን ዋጋ የሚዘክሩ ወጣቶች ደግሞ ከዚያው አካባቢ (ከሽሬ) ተነስተው ጉዞ የሚያደርጉ ይሆናል፡፡ ይሄን እያስተሳሰርን፣ የኢትዮጵያን አንድነት እያጐላን መሄድ እንችላለን፡፡
በ“ጉዞ አድዋ” ላይ የይገባኛል ጥያቄዎች ተፈጥረዋል፡፡ ጥያቄው ምንድነው? እናንተ በዚህ ጉዳይ ያላችሁ አቋም ምንድን ነው?
“ጉዞ አድዋ” እንግዲህ ባለፉት አመታት በሙሉ በህጋዊነት ሲንቀሳቀስ የቆየ ሁነት ነው እንጂ ራሱን የቻለ ተቋም አይደለም፡፡ ይሄን የሚያስተባብሩ ተቋማት ግን አሉ፤ በጋራ ተሰባስበን የመሠረትነው ድርጅትም ነበር፡፡ አሁንም ይሄን የሚያስተባብር ለረጅም ጊዜ አብሮን የነበረ ተቋምም አለ፡፡ እንግዲህ ጓደኞቻችን የፈለጉት ራሱን የቻለ ከአመት አመት የሚሠራ ተቋም ለመፍጠር ነው፡፡ ጥሩ ሃሳብ ነው። ግን እንዲህ አይነት ነገር የሚሠራው በድብቅ አይደለም፤ ተደብቆ ይሄን ነገር ማድረግ ያው የተደከመበትን ነገር ዝም ብሎ የመቀማት ልምድ ስላለን ነው፡፡ ይሄ በጣም ደካማ ጐናችን ነው፡፡ እኛ ብቻ ጉዞ አድዋን ለማዘጋጀት አንበቃም የሚል እምነት አለን፡፡ ብዙ ተቋማት ቢፈጠሩ ደስ ይለናል፡፡ ለምሣሌ ሀረር ላይ ጉዞውን በማነሳሳት ጭምር ሃላፊነት የወሰዱት “ቃል የኪነጥበብ ማህበር” አባላት ናቸው፡፡ የአድዋ ድል ከትንሽ ተጀምሮ ነው ሁሉም ከያለበት ተሰባስቦ መጨረሻ ላይ ትልቅ ታሪክ የተሠራው፡፡ ስለዚህ ብዙ ሰዎች መምጣታቸውን እኛ እንወደዋለን፡፡ ምክንያቱም ስራችንን ያግዙናል፡፡ የተናጠል እንቅስቃሴ ማድረግ ግን ጥቅም የለውም፡፡ እነዚህ ባለቤትነቱ የኛ ነው የሚሉ አካላት፣ የተናጠል እንቅስቃሴን ነው የመረጡት፡፡ እኛን ሳያማክሩ የሄዱበት አካሄድ፣ እኛ ላይ ያልተገቡ ውንጀላዎችን በመፈፀም ጭምር ነው፡፡ እስካሁን እኛ መልስ አልሠጠንም፤ አሁንም አንሰጥም፡፡ ምክንያቱም ጭቅጭቁ የአድዋ ታሪክን አይመጥንም፡፡
መጨረሻ ላይ “ጉዞ አድዋ በጐ አድራጐት ማህበር” በሚል ስሙን ከያዙት በኋላ ያዘጋጅነት መብት የኛ ብቻ ነው የሚል፣ በህግ ሲታይ ድጋፍ የሌለው ነገር ማራመድ የተገባ አይደለም፡፡ ይሄ ማለት አክሱም ፂዮንን ለመሳለም መንገዱ በኔ በኩል ብቻ ነው እንደማለት ነው፡፡ እንዲህ አይነት ነገር አይሠራም፡፡ የአድዋ ታሪክንም አይመጥንም፡፡ እኛ ለነሱ መልስ እየሠጠን መጨቃጨቅ አንፈልግም። ጉዟቸው የተሳካ እንዲሆን እንመኛለን፡፡ የጉዞው አካላትም የኛው ቤተሰቦች ናቸው፡፡ ምክንያቱም መጨረሻ ላይ ሁላችንም የምንገናኘው ሶሎዳ ተራራ ላይ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የተናጠል ጉዞ አይጠቅምም፣ ከውዝግብ  ወጥተን በአንድነት መንፈስ ብንራመድ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡
በመጨረሻ --- መልዕክት--ምስጋና----?
የዘንድሮ ጉዞ አድዋን ለማካሄድ ከማሰብ ጀምሮ ለመሳተፍ የቻሉ፣ ልጆቻቸው እንዲሳተፉ የፈቀዱ ቤተሰቦች ጭምር መመስገን አለባቸው፡፡ በየአካባቢው አቀባበል የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከወዲሁ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ የመንግስትም እገዛ ምስጋና የሚያሻው ነው፡፡ ከኢትዮጵያም ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን፣ በተለያዩ ማህበራትና እንቅስቃሴዎች፣ የኛን ጉዞ ለማገዝ የሚያደርጉት ድጋፍ በራሱ በጣም ምስጋና የሚያስፈልገው ነው፡፡ ሁሉንም ጠቅልዬ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ የኛ ራዕይ ራዕያቸው እንዲሆንና ወደፊትም አብረን እንድንቆም ነው ጥሪ የማቀርበው፡፡ ለእናቶቻችን፣ ለአረጋውያኑ በሙሉ ደግሞ በፀሎት አስቡን እላለሁ፡፡ “ፍቅር ለኢትዮጵያ” ነው የዘንድሮ መፈክራችን፡፡ ፍቅር ለኢትዮጵያ እያልን፣ሁላችንም እየዘመርን አድዋ እንገባለን፡፡ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!    

Read 534 times