Saturday, 26 May 2012 10:33

እርካታ እጦት በረከት ነው!

Written by  ሶፎንያስ
Rate this item
(2 votes)

እርካታ ማጣት ሰላም ማጣት ሊሆን ይችላል፡፡ ሰላምህን የምታጣው የተሻለ ሰላም ፍለጋ ከሆነ ግንየዛሬ እረፍትህን ለነገ ጠብደል ትርፍ ኢንቨስት እያደረግህ እንደሆነ ማሰብ ይገባል፡፡ኢንቨስትመንት ከሌለ ልማት የለም፡፡ በሚሊዮኖች ሊያወጣ የሚደፍር ነው፣ በሚሊዮኖች ሊያተርፍ የሚችለው፡፡ በትንሽ የገንዘብ ፈሰስ ብዙ ብር ለመሳብ መሞከር ቢያንስ የቀን ህልም ነው፡፡በትንሽ ነገር ትልቅ እርካታ የሚሰማው፣ ከትልቅነት ጋር ሊተዋወቅ አይችልም፡፡ ትልቅ እርካታ ትልቅ ድክመት ነው፡፡ የውድቀት መነሻ ነው ሊባልም ይችላል፡፡ በትንሹ የሚረካ ሰው ውሎ አድሮ የራሱን መቃብር መቆፈሩ አይቀርም፡፡ የመቃብሩ ጥልቀት በእርካታው የከፍታና የዝቅታ መጠን ይወሰናል፡፡

እርካታ እጦት ግን የትጋት ምንጭ ነው፡፡ የእርካታ እጦት ባለቤት የሆኑ ሰዎች የስኬት ጥመኞች ናቸው፡፡ የስኬት ጌቶችም ናቸው፡፡ ታዲያ አንርሳ፤ ጥማታቸው ነው ወደ ጌትነት የሚጠራቸው፡፡ በቀላሉ የሚረካ በቀላሉ ይቆማል፡፡ በቀላሉ የመርካት ‘ተሰጥኦ’ ያለው ሰው መድረሻው ከመነሻው
ብዙም የላቀ አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡ዛሬው ከትላንቱ የተለየ ነገር አይኖረውም፡፡ ዛሬው ከትላንቱ ሲናፀር ከ”አልሸሹም ዞር አሉ” ተረት
የሚያልፍ አይሆንም፡፡እርካታ ማጣት እርጋታ የማግኘትን ያህል በህይወት ውስጥ አስፈላጊ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ እርጋታ ከሌለህ በዙሪያህ የሚከናወነውን የማገናዘብ አቅም አይኖርህም፡፡ አፍንጫህ ስር አንድ ሺ አንድ ተአምር እየተፈጠረ፣ እርጋታ ስለራቀህና ስለምትናጥ ብቻ ነገሩን እያደመጥክ እውነታውን ትስታለህ፡፡ ስለዚህ እርጋታ አስፈላጊ ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ “ረካሁ!” ካልክ ባለህበት መርገጥ ሊሆንብህ ነው፡፡ ቀና ብለህ አታይም፡፡ አርቀህ አታስብም፡፡ “ረካሁ!” ማለት “በቃኝ!” የማለት ወንድም ስለሆነ እድሎችን አትጠቀምም፡፡ ቁጭ ባልክበት ብዙ መልካም የእድገት አጋጣሚዎች ያልፋኻል፡፡ “ረካሁ!” ማለት የትኛውም ሃሳብ ወዳንተ እንዳይገባ በር መከርቸም ነው፡፡ የረካ ለመርካት አይንቀሳቀስም፡፡ የጠገበ ምግብ ፍለጋ እንደማይሯሯጠው ሁሉ ማለት ነው፡፡ለመርካታ የማይንቀሳቀስ ደግሞ አንዲት ጋት አያድግም፡፡ ሳይንቀሳቀሱ ማደግ የለምና፡፡የውሃ ጥም ያላስቸገረው ወይም ያልገጠመው ምንጭ ፍለጋ ስለመነሳት ሊያስብ አይችልም፡፡ከመኖርያው በኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ምንጭ አግኝቶ “ረካሁ! ከእንግዲህ ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ!” የሚል ከደጁ ላይ የውሃ ቧንቧ አይገኝም፡፡“አሁንም ገና ነው!” ያለ ወይም የሚል ነው፤ ከወንዝና ከምንጭም መገኘት በኋላ ውሃን በቧንቧ ቤት ስለማድረስ ሊያስብ የሚተጋው፡፡ እርካታ እጦት አንዱ የእድገት መሰረት ነው፡፡ ቶሎ የሚረካ ቶሎ ይወድቃል፡፡ ከአንድ ስኬት ወይም ድል ማግስት በፍጥነት የእርካታ እጦት የሚሰማው በፍጥነት ወደ ሌላ ስኬት ወይም ድል ይሻገራል፡፡“ረክቻለሁ!” የሚለው ቃል አቻ ትርጉም “ሩጫዬን ጨርሻለሁ!” ከሚለው የመካነ-መቃብር ሐውልት ፅሁፍ የሚርቅ አይደለም፡፡ “ሩጫዬን ጨርሻለሁ!” ባይ ማን እንደሆነ መግለፅ ቃላትንና የአንባቢን አይን ማድከም ይሆናል፡፡ ስለዚህ “ረክቻለሁ” ወይም “ሩጫዬን ጨርሻለሁ!” የሚሉ ሟቾች ናቸው አልላችሁም፡፡ ይልቁኑ እላችኋለሁ “እርካታ እጦት ሲሰማኝ እርካታ ይሰማኛል” የሚል ህያው ነው፡፡ እርካታ እጦቱ ጠፍቶ እርካታ ብቻ የሚሰማው ግን ከህያውነት ክልል ለመውጣት የጉዞ ቪዛ በመጠየቅ ላይ የሚገኝ መሆኑን እንመን፡፡ ከእርካታ በኋላ ስኬት አይኖርም፡፡በአንድ ግጥም የሚረካ ገጣሚ ሌላ ግጥም አይደግምም፡፡ ስሜቱን ገና አለመግለፁን፣ ፍላጐቱን አለማርካቱን የሚያምንና እርካታ እጦት የሚሰማው ገጣሚ ነው፣ “ገጣሚ!” ተብሎ ሊጠራ የሚችለው፡፡ እንደ ፑሽኪን የክብር ሐውልት እንዲቀረፅለት አድናቂዎቹን በውዴታ የሚያስገድደው፡፡ በአንድ መፅሐፍ ታላቅነት የሚሰማው ደራሲ ከታናሽነት ድንበር ሳያልፍ አፈር ይለብሳል፡፡በእርካታ እጦት እየተገፉ እርካታ ለማግኘት ወይም ወደ ከፍተኛው እርካታ ለመድረስ ህይወትን የሚቧጥጡ ናቸው፤ በሰው ልብ ወስጥ ተተክለው ዘላለም ለመኖር የሚታደሉት፡፡ እርካታ ፍለጋ ደምና ላባቸውን ለስራቸው የገበሩ ናቸው፤ ዓለምን የሚያስገብሩት፡፡ ፊዮዶር ዶስቶቭስኪ ስለ አንድ ድርሰቱ ሲናገር “ስጋዬን ደሜንና ነፍሴን ገብሬበታለሁ” እንዳለው፡፡ለአንድ ስራ ሁሉ ነገርህን ልትሰጥ የምትችለው እስካሁን በሰራኸው የእርካታ እጦት ተሰምቶህ ሌላ እርካታ ለማግኘት ስትታትር ነው፡፡ እንጀራህ ስለሆነ ብቻ ለስራህ ደምና ስጋህን አትከፍልም፡፡ ግፋ ቢል ጊዜህን ብትገብር ነው፡፡ እርካታ እጦት ሲሰማህ ግን አንድ ሺ ነገር ትሞክራለህ፡፡ አንድ ሺ ነገር አንድ ሺ አንድ ጊዜ እየሞከርክ ለእርካታ ወድቀህ ትነሳለህ፡፡ዶክተር ማይልስ ምኑር እንዲህ ይላል፤“When you have a vision, you are sad about where you are because you want to be where your true joy is. People who are satisfied with a lesser existence, however, will never go where they need to be.”   (ራዕይ ሲኖርህ፤ እውነተኛው ደስታህ ወዳለበት ለመድረስ ስለምትሻ ባለህበት ቦታ ታዝናለህ፡፡ በአናሳ ህላዌ እርካታ የሚሰማቸው ሰዎች ግን ሊገኙ ወደሚፈልጉበት ቦታ በጭራሽ አይደርሱም እንደማለት)በትንሽ ነገር እርካታ የሚሰማው ሰው ከትንሽነት የኑሮ ክልል የሚያልፍ ሰው አይደለም፡፡ ታላቅነት፤ እርካታ እጦት በሚወልደው ታላቅ ጥረት የሚገባበት የስኬት ግዛት ነው፡፡ ወደዚህ ግዛት ለመግባት ባሉበት ያለመደላደል እና በትንሽ ትልቁ ያለመርካታ ፀጋ ያስፈልጋል፡፡ በደረሰበት በሚረካና ባለበት በሚረጋ ሰው ላይ ሸረሪት ያደራበታል፡፡ የውድቀት ሸረሪት!ቤን ስዊትላንድ፤ በአሜሪካ ፓተንት ቢሮ የተመዘገበ እያንዳንዱ ፈጠራ የእርካታ እጦት ውጤት ነው
ይላል፡፡ የፈጠራ ባለሙያው አንድ ነገር ባለበት ደረጃ ወይም ሁኔታ ባለመርካት፣ ያንን ወደተሻለ ደረጃ የሚወስድበት ወይም ወደተሻለ ነገር የሚለውጥበትን መንገድ ይፈልጋል፡፡ ይፈልግና የተሻለ ፈጠራ ያስገኛል፡፡“If people were satisfied with horse and buggy transportation, we would not have automobiles, trains and planes.If people were satisfied with ordinary postal communication, we would not have telephones and telegraph.Every improvement of any kind reflects discontent with things as they were.”“ሰዎች በፈረስና ጋሪ መጓጓዣ ረክተው ቢሆን፣ መኪና ባቡርና አውሮፕላን ባልኖረን ነበር፡፡በፖስታ አገልግሎት ረክተው ቢሆን ስልክና ቴሌግራፍ ባልኖረን ነበር፡፡እያንዳንዱ መሻሻል ነገሮች ባሉበት ሁኔታ ካለመርካት ይመነጫል፡፡”
እርካታ እጦት በረከት ነው ማለት ነው፡፡ በረከቱን ያብዛልን እንበላ!

 

 

 

Read 2854 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 10:49