Sunday, 06 January 2019 00:00

“ከእርቅና ይቅርታ በፊት ኑዛዜ ያስፈልጋል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 (የታሪክ ምሁሩ የሚያዋጣን “ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት” ነው ይላሉ

    “ሁላችንም የአንድ አባት ልጆች ነን” የሚሉት ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሣ፤ የታሪክ አረዳዳችን መታረቅ አለበት ይላሉ፡፡ ቋንቋችን መግባቢያ እንጂ ዘራችን አይደለም ሲሉ የሚሞግቱት ፕሮፌሰሩ፤ ”በዘርማ ሁላችንም የኢትዮጵያ ልጆች ነን” ባይ ናቸው፡፡ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ እንዲህ አውግተዋል፡፡

    በሀገሪቱ ከተደረጉ ለውጦች ለእርስዎ ጉልህ ትርጉም ያላቸው የትኞቹ ናቸው?
ሁላችንም እንደምናውቀው ለውጥ ተካሂዷል። ዝርዝር ውስጥ ሳልገባ ለምሣሌ ለመጥቀስ ያህል፤ እስረኞች ተፈተው ወህኒ ቤቶች ከፖለቲካ እስረኞች ነፃ መሆን አንዱ ነው፡፡ ይህ በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያው ሊሆን ይችላል፡፡ በንጉሱ ጊዜም ቢሆን የፖለቲካ እስረኞች አሉ፡፡ አሁን ከዚያ የተለየ ሁኔታ ነው ያለው። በውጪ ሆነው ሲታገሉ የነበሩ፣ የሀገራቸውን መሬት ረግጠው የማያውቁ ሰዎች፣ ሀገራቸው ገብተው በነፃነት ለመኖርና ለመታገል መቻላቸውን ማየት አስደሳች ለውጥ ነው፡፡ ምንም እንኳ አንዳንዶቹ ይህን ነፃት አግባብ ላልሆነ ተግባር በማዋል፣ ሁከት ለመፍጠር ቢጠቀሙበትም፣ ይሄ መብት መገኘቱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በአሸባሪነት የተፈረጁ ሁሉ በነፃነት መንቀሳቀስ መቻላቸው፣ ከቶውንም የማይታመን ውጤት ነው። ከየአቅጣጫው ያለው የሪፎርም እንቅስቃሴም በዋዛ የሚታይ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ሰውን ሲያሰቃዩ፣ ሀገርና ህዝብ ሲበድሉ የነበሩ ሰዎች በህግ መጠየቃቸው፣ በፍፁም ይሆናል ተብሎ የማይጠረጠር ነበር፡፡ የደሀውን የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የትውልዱን ገንዘብ የዘረፉ ሰዎች ጉዳይ መጣራትና ህግ ፊት መቅረብ መጀመሩ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ሴቶች በብዛት መሾማቸው ትልቅ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ታሪክ ሴቶች ንግስተ ነገስታት፣ የጦር መሪ ሆነውም ያውቃሉ፤ አዲስ አይደለም፡፡ ጥንትም ቢሆን የኢትዮጵያ ሴቶች ተራማጅ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል በወታደሩ ውስጥ የሀገር ፍቅር ስሜት እንዲያብብ፤ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት እንዲፈጠር የሚደረገው ጥረት ጥሩ ነው፡፡ በሰብአዊ መብት አጠባበቅ እየተደረገ ያለው ለውጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ ባልተገመተ መልኩ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በቀጣይ ለሚደረገው ምርጫ የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነው እንዲሠሩ መደረጉ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ወ/ት ብርቱካን ስለ እውነት ብላ ግፍ የተቀበለች ነች፡፡ የፍርድ ሚኒስትሯ ወ/ሮ መአዛ አሸናፊም ሆኑ አቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ትልቅ ስራ የሚሠሩ ናቸው። በየሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ ለውጥ እንዲኖር የሚደረገው ሙከራ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ሰው የነፃነት ስሜት እንዲሰማው፣ የሀገር ባለቤትነት ስሜት እንዲያድርበት ማስቻሉ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ይሄ ለውጥ በህዝብ ትግል የመጣ ነው፡፡ ይሄ ትግል ደግሞ የትናንት ብቻ አይደለም፤ ከደርግ ጀምሮ ህዝብ ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲ ለነፃነት---ያፈሰሰው ደም ውጤት ነው፡፡
በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ምን ያህል ቦታ አግኝቷል?
አሁን ህዝቡ የሚያዋጣው ኢትዮጵያዊ መሆን እንጂ ዘረኛ ወይም ጐሰኛ መሆን እንደማያዋጣ ገብቶታል። እንደ ህዝብ ልንተርፍ የምንችለው ኢትዮጵያዊነትን ካቀነቀንን ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ያለው ህዝብን እንደሚያፈናቅልና እንደሚያጋድል መረዳት አለብን፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ፕሬዚዳንት ለማ መገርሣ፤ “ሱስ ነው” ብለው ከገለፁት በኋላ፣ ዶ/ር ዐቢይ ደግሞ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን” በሚል የተናገሩት ተደምሮ ዛሬ ጥሩ መንገድ ተጀምሯል፡፡ እኔ በተለይ ባለፉት ሁለት አመታት ኢትዮጵያዊነትን ሳቀነቅን ነው የከረምኩት፤ አሁንም እሱኑ ነው የምሠራው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ነው የሁላችንም መሠረት። ጐሰኝነት ቋንቋ ነው፤ ጐሣ ማለት ቋንቋ ነው፡፡ ቋንቋ የንግግር ክፍል እንጂ የዘር ወይም የስነ ፍጥረት ክፍል አይደለም። ቋንቋ የንግግር ክፍል ስለሆነ ያግባባል እንጂ አያዛምድም። ቋንቋ የስጋ ዝምድና አይፈጥርም፡፡ ሰው ቋንቋ ሊያጠና ይችላል፤ ግን የቋንቋው ተናጋሪ ዘመዶች መሆን አይችልም፡፡ እኛ ሀገር ለምሣሌ አንዱ አፋር ነኝ ሲል፣ አፋርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሆነ እንጂ ዘሩ አይደለም። በዘሩማ “የኢትዮጵያ” ልጅ ነው፡፡ አንድ ሰው አማራ ነኝ ሲል፣ አማርኛ ቋንቋ ከሚናገሩ ሰዎች ቡድን ውስጥ ነኝ ማለቱ እንጂ ዘሩን አይደለም የሚያመለክተው፤ በዘሩማ የኢትዮጵያ ልጅ ነው። ተጋሩም ኦሮሞውም፣ ሶማሌውም፣ ጉራጌውም ሌላውም እንደዚሁ ቋንቋውን እንጂ የስነፍጥረት (ባይሎጂካዊ) ዘሩን አይገልጽም፤ በዘር ሁላችንም የኢትዮጵያ ልጆች ነን፡፡ ስጋችን ዘራችን አንድ ነው፡፡
ሰዎች “ቋንቋዬን ነኝ” ሲሉ፣ ስህተት እየሠሩ ነው፡፡ ቋንቋቸውን አይደሉም፤ ዘራቸውን ናቸው። ዘራቸው ደግሞ አንድ ነው፤ እሱም ኢትዮጵ ነው። ሁላችንም ኢትዮጵያውያን፤ “የኢትዮጵ ልጆች ነን”። ቋንቋ መግባቢያ ነው፤ ሌላ ትርጉም የለውም። ለምሣሌ በአሜሪካን ሀገር ጥቁር አሜሪካውያን አሉ። ቋንቋቸው ወይም ጐሣቸው  እንግሊዘኛ ነው፡፡ (ጐሣ ማለት ሌላ ትርጉም የለውም፤ አገሣ ከሚለው ወይም ከውስጥ አፈለቀ ከሚለው የመጣ ቃል ነው፤ ትርጉሙም ቋንቋ ማለት ነው፡፡ “አገሣ” እና “ጐሣ” አንድ ነው፡፡ ጐሣ የንግግር ክፍል እንጂ የስጋ ዝምድና መለያ አይደለም።) ጥቁር አሜሪካኖች ዘራቸው ግን ጥቁር ነው፡፡ እንግሊዘኛ ስለተናገሩ እንግሊዝ ነን አላሉም፤ አይሉም፡፡ ዘራቸው አፍሪካ ነው፡፡ የኛም እንዲሁ ነው፡፡ ጐሣችንን እንደ ዘር ከመቁጠር የሁላችንም ግንድ “ኢትዮጵ”ን መሠረት በማድረግ፣ ኢትዮጵያዊነታችንን ብናጠናክር ነው የሚሻለው። አሁን ኢትዮጵያዊነት ለማበብ ጥሩ ጅምር ላይ ነው፡፡ አሁንም ግን ቋንቋቸውን መሸሸጊያ ያደረጉ ሰዎች ስላሉ ብዙ ስራ ይቀራል፡፡ እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያዊነታቸውን ቢቀበሉ ነው የሚያዋጣቸው። ከተቀበሉ በሠላም ከህዝቡ ጋር መኖር ይችላሉ፡፡ ሁሉም ዘራቸው ኢትዮጵ ነው፡፡
“የአማራ እና የኦሮሞ እውነተኛ የዘር ሀረግ ምንጭ” የሚለው መጽሐፍዎ ለንባብ ከበቃ በኋላ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡ በመጽሐፉ ያቀረቡትን ታሪክ ብዙዎች ተቀብለውታል ብለው ያምናሉ?
አዎ በሚገባ ብዙዎች ተቀብለውታል፡፡ አሁን ለተፈጠረው የኦሮሞ አማራ ጉድኝትም አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በእርግጥ ከዚያ በፊትም ይህ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን ከመጽሐፉ በኋላ የበለጠ ተጠናክሯል፡፡ ለለውጡ መጽሐፉ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ህዝቡም በተለያየ አጋጣሚ የመጽሐፉን አስተዋጽኦ ይነግረኛል፡፡ እንደውም እነ ዶ/ር ዐቢይን፣ ወደ ኢትዮጵያዊነት እንዲመጡ ያደፋፈራቸው ይህ መጽሐፍ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ አቶ ገዱ መልዕክት ልከውብኛል፡- ያንተ መጽሐፍና አስተምህሮ ኢትዮጵያዊነቴን ስላሳወቀኝ ምስጋናዬ የላቀ ነው ብለውኛል፡፡ ዶ/ር ዐቢይም በአደባባይ፣ የፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሣ ምርምር የምስማማበት ነው ብለዋል፡፡ አቶ ለማም መጽሐፉን እንደወደዱት በተለያየ መንገድ አውቄያለሁ፡፡
እርስዎ “አዳም ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የተፈጠረው” ያሉትን ብዙዎች እንደ ቀልድ የቆጠሩት ይመስላል ---
እንዲያውም የምርምር ግኝቴ ያንን የሚያጠናክር ሆኗል፡፡ በወቅቱ አንዳንዶች እኔ ያላልኩትን ነው ለራሳቸው በሚመቻቸው መንገድ ተርጉመው፣ “አዳም ጐጃሜ ነው” የሚለውን ቀልድ የፈጠሩት። አዳም የኖረው የዛሬ 10ሺህ አመት አካባቢ ነው። ጐጃም የሚለው ቃል ከተፈጠረ 3ሺ500 አመት ቢሆነው ነው፡፡ ጐጃም የአንድ ንጉስ ስም ነው፡፡ ይህ ንጉስ የኖረው ከዛሬ 3ሺ500 አመት በፊት ነው። ከሱ ቀደም ብሎ ቦታው ጐጃም አይባልም ነበር፡፡ አዳም የኤደን ገነት ዜጋ ነው። ኤደን ገነት ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል፡፡ ኤደን ገነት ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረ የት ነው? ለሚለው ማስረጃዎች ቀርበዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ፤ ሁለት ወንዞች ኤደን ገነትን ያጠጡ ነበር ይላል፡፡ እነዚህ ወንዞች እነማን ናቸው? በኔ ጥናት አንዱ አባይ ነው፣ ሌላኛው ዋቢ ሸበሌ ነው፡፡ ስለዚህ ሁለቱ ወንዞች የሚያጠጡት ኤደን ገነት ከኢትዮጵያ ውጪ የትም አይኖርም፡፡ ጣና አካባቢ ነው የተፈጠረው ብንል ያስኬዳል፡፡ ብዙ ማስረጃዎች አሉት፤ ይሄ ምርምር፡፡
ወደ ወቅታዊ የሀገራችን ጉዳይ እንመለስና---እርስዎ ደጋግመው የሚያነሱት የእርቀ ሠላም ጉዳይ በመንግስት ትኩረት አግኝቶ፣ የእርቅ ኮሚሽን ተቋቁሟል፡፡ እርቁ እንዴት ነው መፈፀም ያለበት ይላሉ?
በመጀመሪያ ወደ እርቅ ከመደረሱ በፊት የሚያስፈልጉ ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛ ያጠፉ ሰዎች፤ አጥፍተናል ብለው ሃጢያታቸውን ተናዘው፣ ”ተፀጽተናል ማሩን፤ ይቅርታ አድርጉልን” ብለው መቅረብ አለባቸው፡፡ ይቅርታ የሚያስፈልጋቸው አካላት ይሄን ሳይጠይቁ፣ እየተዞረ “እባካችሁ ምሬያችኋለሁ፤ ይቅርታ አድርጌላችኋለሁ” እየተባለ አይለፈፍም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይም፤ ምህረትና ይቅርታ የሚገባው፣ ይቅርታና ምህረትን ተፀጽቶ ለጠየቀ ነው፡፡ በኑዛዜ ሃጢያትህን ሳትታጠብ፣ ከእነ ሃጢያትህ፣ ከእነ ወንጀልህ እየተንገላወድክ፣ በቃ ምሮኛል ብትል እግዚአብሔር አይምርምህ፡፡ እንኳን ሰው እግዚአብሔር እንኳ በሃጢያታችን እንድንፀፀት ይፈልጋል፡፡ ከልብህ ስታዝንና ይቅር በለኝ ስትል ነው እንጂ ይቅርታ የሚኖረው፣ ይሄ በሌለበት ከመሬት ተነስቶ ይቅርታና ምህረት አይደረግም፡፡ ያጠፉና ያልተፀፀቱ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው፡፡ ስለዚህ ከእርቅ በፊት ኑዛዜ ያስፈልጋል፡፡ እኔ የእርቁን ጉዳይ በዚህ መልኩ ነው የማየው፡፡
በአገራችን ለሚፈጠሩ የእርስበርስ አለመግባባቶችና ጥርጣሬዎች አንዱ ምክንያት በታሪክ ጉዳይ መግባባት ላይ አለመደረሱ ነው የሚሉ ወገኖች  አሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
የታሪክ አረዳዳችን መታረቅ አለበት፡፡ እኔ ሀቁን ጽፌያለሁ፡፡ በአንዳንድ የፖለቲካ ልሂቃን እንደሚነገረው፤ አማራ እውነት በድሏል ወይ? ሌላውስ ተበዳይ ነበር ወይ? አማራስ ተበድሏል ወይ? እኔ ባደረግሁት ምርምር፤ አማራ ያጠፋው ምንም አይነት ጥፋት በታሪክ የለም። የኢትዮጵያን ልዕልና ለማስከበር ሲዋጋና ሲዋደቅ የኖረ ህዝብ ነው። ይሄን ሲያደርግ በአንፃሩ ምንም ጥቅም ያላገኘ ይባስ ብሎ የተንከራተተ የተሰቃየ ህዝብ ነው፤ የአማራ ህዝብ፡፡ እውነቱ ይሄው ነው፡፡ ሌላው ቢያንስ ራሱን የሚመግብበት አረንጓዴ መሬት ነበረው፡፡ አማራው ግን እየተሰቃየ የኖረ ህዝብ ነው፡፡ እናቱ እንደሞተችበት ልጅ፣ ማንም የሚከላከልለትና አለሁ የሚለው ሳያገኝ ቆይቷል፤ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፡፡ ይሄ ሁሉ የሆነው በኢትዮጵያዊነት ፍቅር እየነደደ፣ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ስላለ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ስላፈቀረ ነው የተንከራተተው። አማራነቱን ሳያጐላ ኢትዮጵያዊነቱን ስላስቀደመ ብዙ ጥቃትም ደርሶበታል፡፡ ስለዚህ ይሄ እውነተኛ የታሪክ ሃቅ ተዘርዝሮ፣ ሁሉም አውቆት ተረድቶት፣ እንዲያውም አማራው ይቅርታ ተጠይቆ፣ ካሣ ሊሰጠው እንደሚገባ ነው እኔ የሚታየኝ፡፡ በህሊናዬ ይሄ ነው ያለው። ይሄን የህሊናዬን ሙግት ልቃወመው አልችልም። ከምንም በላይ ሁላችንም የኢትዮጵያ ልጆች ነን፡፡ ኢትዮጵያዊነት ይሻለናል፡፡ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያዊ፤ በቋንቋው ምክንያት መገደልም መሞትም የለበትም። መቆም አለበት፡፡
ከአገራዊ ለውጡ ምን ተስፋ ያደርጋሉ?
በለውጡ ላይ ብዙ ተስፋ አለኝ፡፡ ምርጫ ተካሂዶ አሸናፊው የመንግስትን ስልጣን በታማኝነት ይዞ እንደሚሠራ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ዶ/ር ዐቢይም ቃላቸውን ይጠብቃሉ የሚል እምነት አለኝ። የፖለቲካ ድርጅቶችም በቋንቋቸው ወይም በጐሣቸው ሃይል ተንተርሰውና ተመክተው ስልጣን ለመያዝ መመኘታቸውን ትተው፣ የሃሳብ ልዕልናቸውን አቅርበው፣ ሞግተውና አሣምነው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲመርጣቸው ማድረግ ነው ያለባቸው። ከዚህ ውጭ ማንም በአምባገነንነት ወደ ስልጣን እንዳይመጣ መጠንቀቅ ያሻል፡፡ ረብሻ፣ መገዳደልና መፈራረጅ የሌለባት፣ የአንድ አባት ልጆች በሰላም የሚኖሩባት አገር እንደምትኖረን ተስፋ አደርጋለሁ። ኢትዮጵያዊነት ላይ ማተኮር የመዳኛ መንገዳችን ነው። ለሁሉም የሚያዋጣው የኢትዮጵያ ልጆች መሆናችንን አምነን፣ ኢትዮጵያዊነትን ማጠናከር ነው፡፡ ሌላው መንገድ አያዋጣም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ይለምልም! ኢትዮጵያዊያነት ያብብ! ኢትዮጵያዊነት ለዘለአለም ይኑር!        

Read 1807 times