Monday, 07 January 2019 00:00

በጉለሌና በቦሌ የግዴታ ጋብቻ በብዛት ይፈጸማል ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 በአዲስ አበባ ከሚገኙ ክፍለ ከተሞች ውስጥ ጉለሌና ቦሌ የግዴታ ጋብቻ በብዛት እንደሚፈፀምባቸው ተገለጸ፡፡  ባለፈው ሐሙስ በኢንሽየቲቭ አፍሪካ አዘጋጅነት፣ “ለውጥን በመለወጥ መተግበር” በሚል መሪ ሃሳብ በሞዛይክ ሆቴል ለአንድ ቀን በተካሄደ ስብስባ ላይ 20 የሁለተኛ ደረጃና የልዩ ፍላጐት ትምህርት ቤቶች መምህራን፣ ርዕሰ መምህራንና ሴት ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
የኢንሽየቲቭ አፍሪካ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ክቡር ገና በስብሰባው ላይ እንደገለጹት፤ድርጅታቸው ከኢትዮጵያ መምህራን ማኀበር ጋር በመተባበር ባካሄደው ጥናት፤40 በመቶ በሚሆኑት ተማሪዎች ላይ ልዩ ልዩ ፆታዊ ጥቃት እንደሚፈጸም አረጋግጠዋል፡፡ ጥቃቱ በሁለቱም ፆታዎች ላይ የሚደርስ ቢሆንም ይበልጥ ተጐጂዎች  ልጃገረድ ተማሪዎች ናቸው ብለዋል፤ጥናቱን በመጥቀስ፡፡   
የስብሰባው ዋና አላማ በትምህርት ቤት አካባቢ በተማሪዎች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለመቀነስ ምን ማድረግ እንደሚቻል ሃሳብ ለማመንጨት መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ችግሩን ፈጥኖ መከላከል ካልተቻለ የሚያስከትለው ጉዳት ቀላል እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡   
ለተሰብሳቢዎቹ የውይይት መነሻ መረጃዎችን ያቀረቡት፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ ፆታ ኃላፊ፣ ወ/ሮ አበባ ዘውዴ፤የግዴታ ጋብቻ በአንዳንድ ክፍለ ከተሞች የሚታይ ቢሆንም በቦሌና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች በብዛት እንደሚፈጸም  አስረድተዋል፡፡
በ2010 የመጨረሻዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ በአዲስ አበባ 7 ሴት ተማሪዎች በግዳጅ እንዲያገቡ መደረጋቸውን የጠቆሙት ኃላፊዋ፤ በ35 ሴት ተማሪዎችና በ17 ወንዶች ላይ የፆታ ጥቃት መፈፀሙንና ከጥቃት አድራሾች ውስጥ አባትና አጐት እንደሚገኙበት አስምረውበታል፡፡  
“ለውጥን በመለወጥ መተግበር” በሚል መርህ የሚካሄደው የኢንሽየቲቭ አፍሪካ ፕሮግራም 20 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘለትና አዲስ አበባ በሚገኘው የስዊድን ኤምባሲ የሚደገፍ መሆኑ ታውቋል፡፡


Read 6206 times