Print this page
Tuesday, 01 January 2019 00:00

“ዘመናዊ” ትምህርትና ኢትዮጵያ

Written by  ተስፋ ሥዩም
Rate this item
(1 Vote)

መነሻችን ይታወቅ - ርዕያችን ይተርጎም!
            
    እንደ መነሻ
የትምህርት ነገር ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ እምብዛም ፍሬ ካላፈሩላት፣ ነገር ግን ብዙ ከደከመችባቸው ዘርፎች የሚመደብ ነው፡፡ መንግስት ቢለወጥ፣ ፖሊሲ ቢቀየር፣ በጀት ቢጨመርም የተማረ ከተባለው ክፍል ለኢትዮጵያ ጠብ ያለ፣ ይህ ነው የሚባል ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አስተዋጽኦ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ይህን ችግር ተመልክተን ነገሩን ለማጥናት ስንነሳ፣በትምህርት ዙሪያ የሳትናቸው መሠረታዊ ቁምነገሮች እንዳሉ እናስተውላለን፡፡ በዚህና ተከታይ ጽሑፎች፤በትምህርት ሥርዓታችን ምስረታና ቀጣይ ጉዞዎቹ ወቅት የሳትናቸውን መሠረታዊ አንጓዎች ለማሳየት እንሞክር፡፡
መነሻችን ይታወቅ
“በዓለም መጀመሪያ ወይም በስልጣኔ ታሪክ መጀመሪያ አይደለንም፡፡ በዓለም መጨረሻም አይደለንም፡፡”
እጓለ ገብረ ዮሐንስ
እጓለ እንደነገሩን፤ በዓለም መጀመሪያ ስላይደለን መነሻ አለን፡፡ መልኩና መጠኑ ምንም ዓይነት ሊሆን ይችላል፣ መነሻ ግን አለን፡፡ ኃይለ ቃሉ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ሀገር ሲነገር ደግሞ መነሻው ብዙ የተደከመበትና ሀገሪቱን ለሺህ ዓመታት በዓለም ፊት ያጸና መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ከእነዚህ መነሻዎቻችን አንዱ የትምህርት ሥርዓታችን ነው፡፡ ሀገራችን የትምህርትን አስፈላጊነት ተረድታ ከአውሮፓዊው ትምህርት አስቀድማ ለሺህ አመታት የዘለቀ፣በሥርዓት የተደራጀ የትምህርት ስርዓት ዘርግታ ነበር፡፡ “The education traditionally offered by the Ethiopian church on the highlands should not be ignored…. It had produced many wise men the like of whom had served Ethiopia well during the regime of many kings.” በማለት ሪቻርድ ግሪንፊልድ እንደገለጸው፤ የትምህርት ሥርዓቱ በራሱ መልክ ፍሬያማ ነበር፡፡
ለቤተ መንግስቱም ሆነ ለቤተ ምልክናው የተዘጋጀ የሰው ሃይል የሚያቀርብ፣ ከማኅበረሰቡ ማንነትና የአኗኗር ዘይቤ፣ ባህል፣ በአጠቃላይ ማኅበረሰቡ የኔ የሚላቸውን ቁሳዊና መንፈሳዊ እሴቶች የሚያከብር ትውልድ ለማፍራት ችሎ ነበር፡፡ ይህን መሠረታችንን ማወቅና መነሻችንን በዚህ መሠረት ላይ መጣል ሲገባን፣ ትናንት እንደተፈጠረ ሀገር ድንገትም እንደመጣ ህዝብም ከዜሮ ለመጀመር መጣደፋችን፣ ዛሬ ላይ ለደረስንበት ውድቀት የመጀመሪያው መነሻ ነጥብ ነው።  
ከአውሮፓ የተቀዳው አዲሱ የትምህርት ስርዓት መንገዱን የጀመረው፣ ራሳችንን ምንም እንደሌለን በመቁጠርና የቀደመውን ሁሉ በመጣል፣ ለሀገሩ እንግዳ ለህዝቡ ስነ ልቦናም ባዳ በሆነ ሥርዓት መተካት ነው፡፡ ይህ ወደ አውሮፓ ስልጣኔ በአቋራጭ ይወስዳል የተባለላት አዲሱ የትምህርት ሥርዓት ግን ለነባሩ ኢትዮጵያዊ ህይወት የራሱ የሚለውን ከማስጣል በመጀመሩ ቅሬታን፣ ለአዲሱ ትውልድ ደግሞ እንዴት ወደ አዲሱ እንደሚወስደው አጥርቶ ባለማሳየት ብዥታን አምጥቷል፡፡ ውጤቱም በብዙሃኑ ዋጋ ከፋይነት፣ጥቂት ምሁራንን ማፍራት ሆኗል፡፡ መነሻችንን በመዘንጋታችን በራሳችን ላይ ተደራራቢ በደል ፈጽመናል፡፡
ከትንሹ ስንጀምር የራሳችን የሆነውን ነባር የእውቀትና የምርት መንገዶችን  ማሳደግንና ቢያንስ በተወሰኑ መስኮች ላይ ራሳችንን መቻል አልሆነልንም፡፡ ስልጡን ህዝብ ራሱን የቻለ ህዝብ ነው፡፡ ጥገኛና ተረጂ ሆኖ ስልጡንነት ለይስሙላ ነው፡፡ በትምህርት የሸማ ስራችንን አሳድገን ከውጭ አልባሳት፣ የእርሻና የከብት እርባታ ስራችንን አበልጽን ከስንዴ ልመና እንዳንላቀቅ ያደረገን፣ምንም አይነት ነባር እውቀት የለንም ብለን ስለተነሳን ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ ይህ ከመነሻችን ጋር ያለን ጸብ፣ እንደ ሀገር ሊገልጡንና ሊያሳውቁን፣ እርስ በርሱ የሚጠፋፋ ያይደል የሚከባበር ሊያደርጉን ይችሉ የነበሩ ማኅበረሰባዊ እሴቶቻችንን ወራሽ አልባ አድርገናቸዋል። ትምህርት፤ ማኅበረሰብ ራሱን የሚተካበት መሳሪያ (social reproductive system) ነው የሚባለው ለዚህ ነበር፡፡ በዚህም አልሆነልንም። ይህም ሀገሪቱ የለውጥ ምጥ ላይ በምትሆንበት ጊዜ ሁሉ፣(ለምሳሌ በ1966 እና አሁን) ብቅ በሚለው አውሬነታችን ውስጥ ይገለጣል፡፡
የዚህ መነሻችንን የመካድ ሌላው ጦስ፣ የተደላደለ መንፈስ አልባ መሆናችን ነው፡፡ ይህም አዲሱን የስልጣኔ መንፈስም በቅጡ ለመያዝ (ለመቀበል) የተዘጋጀ ሰብዕና እንዳይኖረን አድርጎናል፡፡ አዲሱ መንገድ እስከ ዛሬ ምን ሰጠን፣ ምንስ አጎደለብን ብለን እንኳን አልተቸነውም፡፡ ለምን ቢባል? ከማንጸሪያችን፣ ከመሰረታችን ተነቅለናልና ነው፡፡ መጨረሻውም አሁን እንደሚታየው፣ ትናንት የሌለው የሚመስል፣ ነገ የሚባለውም ድንግዝግዝ ያለበትና ምን እንደሚፈልግ ግራ የገባው ትውልድ ሀገሪቱን አስታቅፏታል፡፡
ሌላው ችግር ራሳችንን የምንመለከትበት መነጽር ውጫዊ ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ታሪካችንን የምንመረምረው፣ በፈረንጅ ጽሑፎችና በጸሐፊዎቹ አስተሳሰብ ላይ ተመስርተን ሆኗል፡፡ የራሳችን የታሪክ ምንጮች በሙሉ የተዘነጉ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ከመሰረት መነቀል ነው፡፡ ታሪኩ በምሁሮቻችን ሲጻፍም  የሚጻፋው በባዕድ ቋንቋ መሆኑን ስንመለከት ደግሞ ችግሩ ከቅኝ ሐሳቦች ጋር ያጋፍጠናል፡፡ በአጠቃላይ የእኛነታችን ታሪክ በሙሉ የታሪኩ አካል ካልሆኑት ላይ ለመቅዳት በመሞከር፣ ምን ዓይነት ማኅበረሰብ እንደፈጥርን ስንመለከት፣ ዳግም መነሻችንን መፈተሽ ምን ያህል አንገብጋቢ እንደሆነ እንረዳለን፡፡
በአጭሩ አንድ ሰው የሚኖረው በአባቱና በልጁ አዝማናት መካከል በመሆኑ፣ ለአባቱ ስራ እውቅና በመስጠት ካልጀመረና በመሰረቱ ላይ መገንባት ካልቀጠለ፣ ለልጁ የሚሆን ቅርስ የማያስቀምጥ ባካና የመሆኑ እውነት በእኛ ተገልጧል፡፡ ልጁም ለአቅመ ማስተዋል በደረሰ ጊዜ፣ ልክ እንደዚህ ትውልድ መነሻ ፍለጋ አባቱን ትቶ አያቱን በመመልከት የወላድ መካን ያደርገዋል፡፡ የትውልዴ ታሪክ ይኸው ነው፡፡
ከላይ ለመመልከት እንደሞከርነው፤ እንደ ሀገር ዛሬም ቆም ብለን ፍኖተ ካርታውን ተከትሎ በሚመጣው አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ ልናካትታቸው ከሚገቡን የእኛ የሆኑ እሴቶቻችን መምረጥና መሰረታችንን ማደስ ያስፈልጋል፤ የራሱን እሴቶች በትምህርቱ የማያካትት ህዝብ ዝርው ይሆናል፡፡ ሙሉጌታ ወዳጆ የተባሉ ምሁር፤ “If the schools are to preserve their identity, the Ethiopian national system of education must be both a reflection of the past and a guide to the future. The educational system must in the first place aid in the transmission of the nation’s cultural heritage from one generation to the next and in addition, it must train capable persons who have the ability to interpret, enrich, and adopt the heritage to new needs and to changing conditions as they may arise… any system of education in Ethiopia that fails to satisfy those demands bound to make the country a lost nation, a nation living in darkness…” በማለት እንደገለጹት፡፡ ጆሮ ያለው ነው ነገሩ፡፡
 ርዕያችን ይተርጎም
ሊቁ እጓላም በዋነኝነት የሚጠይቁት ይህንኑ ነበር፤ “አንድ ሀገር በትምህርት ላይ ሀብቱን ለማፍሰስ ሲነሳ መመለስ የሚገባው ጥያቄ አለ፤ ይህም ምን፣ ለምንና እንዴት የሚለው መሆን ይገባዋል፡፡ ያለዚያ ነገሩ ፍሬ ቢስ እንዳይሆንበት ያስፈራዋል፡፡” የሚለው ሊመረመር ይገባዋል፡፡
ምን ዓይተን፣ የት ለመድረስ ጉዞ ጀመርን? የዚህ ጥያቄ መልስ፣ ነገራችን ሁሉ የሚፀናበት ወደ የሚፈርስበት ሚዛን ነው፡፡ “Education cannot be planned in a vacuum” JC AGGARWAL እንዲል ህንዳዊው፣ የትኛውም ህዝብ ትምህርትን የሚያክል ግዙፍ ሀብት የሚውልበትና ትውልድን አሳልፈው የሚሰጡትን ቁምነገር ለሀገሩ ለመተግበር የሚሞክር መሪ በመጀመሪያ ሊያስቀምጠው የሚገባው መልስ፣ ምን ላተርፍበት እሻለሁ ለሚለው ጥያቄ  ነው፡፡
በመሰረቱ ትምህርት ሀገራዊ ርዕይን ከታሰበለት ማድረሻ መሳሪያ እንጂ በራሱ ግብ አይደለም፡፡ በመሆኑም ከትምህርት ዓላማ አስቀድሞ ሀገራዊ ግብ (national goal) በቅጡ መቀመጥ አለበት፡፡ ይህ ሀገራዊ ግብ በንጉሡ ዘመን ማብቂያም ላይ በጠራ ሁኔታ የነበረ አይመስልም፡፡ ለዚህም ማሳያ እ.ኤ.አ በ1974 የታተመ የአ.አ.ዩ መጽሔት ላይ ጥናታቸውን ያሳተሙት እነ ግርማ አማረም፣ የኢትዮጵያን የትምህርት ዓላማ ለመግለጽ (ለመቀመር) ባደረጉት ጥረት የገጠማቸው ዋነኛ ችግር ይኸው ከሀገራዊ ርዕይ (National goal) አለመኖር ጋር የተያያዘ እንደነበር ሲገልጹ፤“Such is the intimate connection between educational aims and national aims that the former is fact assume a clear formal and well articulated statement of the latter. Such a formal statement of national aims or a political economic and social ideology does not exist for this country” ብለው ነበር። ታዲያ የንጉሱ ህልም ምን ነበር ሲባል፣ ኢትዮጵያን ማዘመን (Modernization) የሚል የጅምላ መልስ እንደሚሰማ፣ ሳይታለም የተፈታ ነውና፣ እሱን ወደ መመልከት እንለፍ፡፡  
ዝመና?
“ስልጣኔ የሠውን ክብር ከፍ አድርጋ የምታሳይ ትልቅ ዋጋ ያላት መሆኑዋን በማሰብ ከልብ ልንወዳት ይገባል፡፡ ይህንንም ለማድረግ እንድንችል የተወደደች ለመሆን የተገባች የሚያደርጋት ጠባይዋ፣ ምን እንደሆነ ለማወቅ ከመጣጣር አለማቆም ያሻል፡፡” ከበደ ሚካኤል
ክቡር አቶ ከበደ ሚካኤል እንደመከሩን፤ የስልጣኔ ጠባይዋን (የወደድንላትን ነገር) በሒደትም ቢሆን ለማወቅ፣ ለመተንተን መጣር አለብን፡፡ ቀዳሚው ጥያቄ መሆን ያለበትም፣ ዝመና ለንጉሡ ያለው ትርጉም ምን ነበር? የሚለው ነው፡፡ እስካሁን ባለው ንባቤ፤ ንጉሱ ሐሳቡን በጠራ ሁኔታ ሲተነትኑት አልገጠመኝም፡፡ በዘመነኛቸውም ተጠይቀው አልመለሱትም፡፡
 ይህን ጥያቄ ራስ ኃይሉ ለአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን በግልጽ አቅርበው ነበር፡፡ አልጋ ወራሹ በአውሮፓ ጉብኝታቸው መጨረሻ፣ ለሀገሬ ከአውሮፓውያን ምን ልጠይቅላት ብለው አብረዋቸው የተጓዙትን 12 ሹማምንት እንደጠየቁና መልሱንም ተማክረው እንዲያመጡ እንደታዘዙ፣ የንጉሱን ታሪክ በሰፊው የፃፉልን አምባሳደር ዘውዴ ረታ ይነግሩናል። አስራ ሁለቱም መክረው፣ በሁለት ሀሳብ ስምንትና አራት ሆነው፣ በሁለት ቡድን ተከፍለው፣ ከአልጋ ወራሹ ፊት ሲቀርቡ፤ ባለ አራቱ ቡድን “ዘመናዊ” ትምህርትን ይጠይቁ ብሎ ሲመክር፣ ባለ ስምንቱን በመወከል የተናገሩት ራስ ኃይሉ ግን ንግግራቸውን የጀመሩት በጥያቄ ነበር፤ “ከሁሉ አስቀድሞ አልጋ ወራሽ ሌት ተቀን የሚጨነቁበት ይኼ ስልጣኔ የሚባለው ነገር፣ እውነተኛ ትርጓሜው ምን ማለት እንደሆነ ለኔም ለጓደኞቼም የተገለፀልን አይመስለኝም፡፡”
አልጋ ወራሹ ለዚህ ጥያቄም ሆነ ራስ ኃይሉ በቀጣይ ለሰነዘሯቸው ሀሳቦች ቀልባቸውን እንዳልሰጡ ከዛ በኋላ በወሰዷቸው እርምጃዎች አስመስክረዋል፡፡ ራስ ኃይሉ ግን ስልጣኔ የሚታዩ መገለጫዎች ብቻ ያይደል ከማኅበረሰብም ምግባር፣ ጨዋነት፣ ታሪክና የአኗኗር ባህል አንጻር የሚታይ ገጽ እንዳለው በመግለጥ፣ እነዚህን አክብሮ ይዞ፣ ከአውሮፓ የኢትዮጵያን ህዝብ አኗኗር ዘይቤ ያማከሉና የወደፊት ጉዞውን ሊያቀኑ በሚችሉ በጨርቃ ጨርቅ ልማት፣ በዘመናዊ ከብት እርባታና ራሳችንን ለመከላከል በሚያስችለን የጦር መሳሪያ ማምረቻ ላይ እንዲያግዙን እንጠይቅ የሚል፣ ዘመናቸውን የዋጀ ነጥብ አንስተው ነበር፡፡ አልጋ ወራሹ አልሰሟቸውም፡፡
ዘመናዊነት/አውሮፓዊነት?
የንጉሱ ዘመን ተማሪ የሆኑት የተከበሩት ፕሮፌሰር ሺፈራው በቀለ፣ በማኅበራዊ የጥናት መድረክ በታተመ አንድ ጥናት መድበል መግቢያ ላይ እንዳሰፈሩት፤ የዘመናዊነት ጽንሰ ሀሳብ በአውሮፓውያ ከተቀረው ዓለም ጋር በስፋት መገናኘት ሲጀምሩ እንደተጠነሰሰና መሰረቱንም ራሳቸውን ስልጡን፣ ሌላውን ያልሰለጠነ በማለት ላይ የጣለ እንደሆነ ይነግሩናል፡፡ ይህ ሀሳብ የቅኝ ግዛት ዘመን መሪ ሀሳብ እንደነበረም አይዘነጋም፡፡
በዚህ ሳይገደቡ የዘመናዊነት ባህርይን በዝመና ቲኦሪ (Modernization theory) ላይ በመመስረት ሲገልፁት፤ “ዝመናም ተባለ ልማት ለውጡ እጅግ ስር ነቀል፣ ሁሉንም የተወረሱ የኑሮ፣ የባህል፣ የርዕዮተ ዓለም፣ የምርት፣ የውጊያ፣ የግንኙነት ዘርፎችን ወደ ጎን አድርጎ፣ በቦታቸው “ዘመናዊ” የኑሮ፣ የባህል፣… ወዘተ ሁነቶችን የሚተካ መሆኑን ነው… በጥቅሉ ዝመና ለምዕራባዊነት (Westernization) የተሰጠ ሌላ ሀሳብ ነው”  በማለት ያብራሩታል፡፡  
በአጭሩ ዘመናዊነት መለኪያውን የአውሮፓን የኢኮኖሚ ለውጥ በማድረግ፣ የአንድን ሀገር ህዝብ በማዘመን ስም ወደ አውሮፓዊነት በማስጠጋት ዛሬ ለሚቀነቀነው ሉላዊነት (Globalization) ቀዳሚው የሆነው የማኅበረሰብ ማመሳሰል (Homogenization) ላይ የሚተጋ ጽንፀ ሀሳብ ነው፡፡ ይህም ዝመናን የተረዳንበት መንገድ መሰረታዊ ስህተት እንዳለው ያሳብቅብናል፡፡
የዝመና መረዳታችን ስህተቶች
በዘመናዊነት ሁሉን ዓቀፍ ሐሳብ እንጂ በቁሳዊ ብዕል ወይም ኢኮኖሚያዊ እድገት ብቻ የሚመነዘር አለመሆኑን መዘንጋቱና መንፈሳዊ፣ ባህላዊ፣ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ሌሎች ብዙ መሻሻሎችን ከሚያካትተው አጠቃላይ ሀገራዊ እድገት (national development) ጋር መምታቱ ነው፡፡
ዘመናዊ ማህበረሰብ እንዴት ይፈጠራል የሚለው ላይ የጠራ መረዳት ማጣት፡፡ መቼም አፍሪካውያን ከፈረንጅ የምንቀዳቸው ጽንሰ ሐሳቦችን ወደ ተግባር ስንለውጥ ካሉብን ፈተናዎች አንዱ ስለ ሒደቱ ያለን ግንዛቤ ቁንጽል መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ዲሞክራሲንና ዘመናዊነትን መውሰድ እንችላለን፡፡ እነዚህ ሐሳቦች አንድም ከመንግስት የሚሰጡ ፀጋዎች አድርገን ነው የምንመለከታቸው፣ ካልሆነም እንደ ሃይማኖት በጅምላ ጥምቀት የምናደርሳቸው እናስመስላቸዋለን፡፡ ሁለቱም ሐሳቦች ግን አንድ ማኅበረሰብ በተለያዩ የሕይወት ዘርፎች ለተከታታይ ብዙ ዓመታት በሚያደርገው ለውጥ ህልው የሚሆኑ መሆናቸው ነው፡፡ የሀገራችን የዘመናዊነት ሒደት ጅማሮ፣ ሀገራዊ እውቀትንና ማኅበረሰባዊ ማንነትን የተላበሱትንና ሀገሪቱን ለብዙ ሺህ ዓመታት ያገለገሉትን ሀገር በቀል ምሁራን ከጨዋታው በማግለል የጀመረው በዚህ ስህተት ምክንያት ይመስላል፡፡
የአንድን ህዝብ ኋላቀርነት (የአኗኗር እና የአመለካከቱን) ዘመናዊ አለመሆን ለማሳየት ከሌላው ባህል በተወሰዱ መለኪያዎች መጠቀም የችግሩ ሌላው መሠረት ነው፤ መጀመሪያ ሁሉም ሰው አንድ አይነት የአኗኗር ዘይቤን ሊመርጥ ይችላል ብሎ እንደማሰብ ነውና፣ ይህ ከሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ልዩነት ጋር በእጅጉ የተቃረነ ሀሳብ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ማህበረሰብ የሚከተለው የኑሮ መንገድ በዘመናት ሂደት ባለፈበት ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ማህበረሰባዊ ሁነቶች የተቃኘ  ነውና፣ ሁለት በተለያየ መንገድ የተሰራ ማህበረሰብ የግድ አንድ አይነት የአኗኗርና የአመለካከት ዘይቤ ላይ መገኘት አለበት በማለት የራስን ከመጣል መጀመር በፈቃደኝነት ቅኝ መገዛት ነው፡፡ የምዕራቡን ባህልም እንደ ዓለም አቀፋዊ ባህል በመውሰድ፣ የሌሎች ባህሎች መመዘኛ፣ ስታንዳርድ አድርጎ መቀበልን ያመለክታል፡፡
የአፄው መንግስት ዘመናዊነትን ቢሮክራሲውን በማዘመን እውን ማድረግ እንደሚቻል በማመን፣ የትምህርት ሥርዓቱን ቢሮክራሲውን የሚያዘምን የሰው ኃይል በማፍራጽ ላይ እንዲያተኩር አድርጓል፡፡ ነገር ግን ዘመናዊነት በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በማኅበረሰብ የኑሮና የአስተሳሰብ እድገት ላይ እንዲመሰረት ካልሆነ፣ የጥቂቶች የአኗኗር ዘይቤ ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡
ዘመናዊነት እንደወረደ ካስገባነው በአንድ ሀገር በሚኖሩ ትውልዶች መሐከል ቅራኔን የመፍጠር ተፈጥሯዊ ባህርይ እንዳለው አለመረዳት፡፡ የዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ በትውልዶቹ መካከል ያለው በመኖር የሚገኘው እውቀት ልዩነት ነው። አዲሱ ትውልድ “ዘመናዊ” ተብሎ የቀረበውን ሁሉ ለመቀበል የተጋ፣ በዚህም ተቀባይነቱ የአባት እናቶቹን ልዩ ልዩ እሴቶች የዘነጋ ወይም የሚያቃልል የመሆን እድሉ እጅግ ሰፊ ነው። ይህን ክፍተት ሊደፍን የሚገባው ደግሞ ትምህርት ነው፡፡ ትምህርት፤ ማህበረሰብ የኔ የሚላቸውን እሴቶችን ወደ ቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ፣ ማህበረሰብ ራሱን እንዲተካ የሚያስችል (Social reproduction system) መሳሪያ ሊሆን ይገባው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ይህ አልሰመረም፤ ይልቁንም ለራሱ ባዳ፣ ለቀደምቶቹም እንግዳ የሆነ ትውልድ መፍጠሪያ መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል፡፡
እንግዲህ ከላይ እንደተመለከትነው፣ በዘመናችን ከመነሻችን የመታረቅና ርዕያችንን በአግባቡ የመቀመር ድርብ ስራ ይጠብቀናል፡፡ ከንጉሡ በኋላ በመጡትም መንግስታት፣ ይህ ስራ ባለመደፈሩ፣ የዚህ ትውልድ ተንከባላይ የቤት ስራዎች ሆነዋል፡፡ አዲሱን ፍኖተ ካርታ እየቀረጹ ያሉ ምሁራን፣ የንጉሡ ዘመን ተማሪዎች መሆናቸው ችግሩን ለማየትም ላለማየትም እድላቸው ሃምሳ ሃምሳ መሆኑን ስንገምት፣ ዛሬም ችግሩን ተሸክመን እንዳንሔድ ያሳስበናል፡፡ ለምሳሌ ፍኖተ ካርታውን ተከትሎ ይቀረጻል ተብሎ የሚገመተው የትምህርት ፖሊሲ፣ ለአስራ አምስት ዓመታት እንደሚያገለግል ተነግሯል፡፡ ጥያቄው ሀገሪቱ የዛሬ 15 ዓመት የት መድረስ እንደምትፈልግ ፣ ምን ዓይነት ማኅበረሰብ መፍጠር እንደምትሻ  የሚያሳይ ሀገራዊ ርዕይ ወይም ግብ አስቀምጠናል ወይ ነው፡፡ ከሆነ ደግ፤ካልሆነ ግን አዙሪታችን እንዳይቀጥል ከመነሻችን እንታረቅ፡፡ ርዕያችንን እንደ ሀገር እንቀምር፡፡ የ20/20 እቅዳችን እንደሁ በደጅ ቆሟል፡፡

Read 1281 times