Saturday, 05 January 2019 11:13

“ኢትዮጵያዊነት ሲፈተን …”

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

 ወጣቱ ገጣሚ አሌክስ አብርሃም፤ ልባችን ላይ የሚጉላሉ፣ አደባባይ ላይ የተጣዱ ፍልቅልቅ ስሜቶችን በዜማ ነክሮ ለንባብ በማብቃት ለነፍሳችን ቀረብ ያለ ነው፡፡ ብዙ ግጥሞቹ ለልብ ጆሮ ቀርበው የሚያወሩት፣ ልብ ላለው የሚነግሩት ግዙፍ ሀቅ አለ፡፡ ስለዚህም ስንኞችን ከርሱ መዋስ ለኔ የሁልጊዜ ምርጫ ነው፡፡ ዛሬም ለሀሳቤ ማሄጃ፣ ለዐላማዬ መነሻ እንዲህ አሀዱ ብያለሁ፡-
ባዕድ ደጃችን ሲረግጥ - አንድ ሆነን እየደቆስን፣
ከድል መልስ በየጎጣችን - እልፍ ጥል እየፈጠርን እልፍ - አንድነት ስናቆስል
በጋራ ሸራ ወጥረን - በየራሳችን ቀለም - የጓዳ ገድል ስንስል
ሸራው የኔ ነው፣ የኔ ነው - ስንጓተት ስንራኮት - ስንቧቀስ ስንዋቃ፣
ቀለማችንን ከንብለን - ስንቴ ለወስነው በጭቃ!
ይህ ግጥም የኢትዮጵያውያንን የእርስ በርስ ሽኩቻና ፉክክር፣ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥና ጠላት የመጣ ቀን ብቻ በአንድ ድንኳን ከትቶ ባንድ የመሞትን ልክፍት ያሳያል፡፡ ይህንን የታሪክ አካሄድ አንዳንዴ እንደ ጥሩ ነገር ብንኮራበትም፣ በሌላ በኩል ስናየው ግን ከጤናማነቱ ይልቅ ዕብደቱ ቁልጭ ብሎ እንደሚታይ አይካድም፡፡  
ብዙ ጊዜ የውጭ ወራሪ ሲመጣ ብቻ አንድ ሆኖ መሞገትና ጠላትን መመከት፣ የታሪካችን አካልና በጎ ገፅታ ቢሆንም የመጨረሻ ውጤቱ ሲመዘን ግን ራስን ላለማሳደግና አቅምን አንድ አድርጎ ለብልፅግናና ስልጣኔ ከፍታ ላለመታደል ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ብንታደል ኖሮ በየጎራውና በየሰፈሩ፣ ሽለላና ቀረርቶዎችን ይዘን፣ በየወንድማችን ላይ ከምንዳክር፣አሊያም ጦር ከምንሰብቅ፣ ችግሮቻችንን ፈትተን፣ ከሰለጠነው ዓለም ጋር ለመቀላቀል፣ አንድ መዝሙር እየዘመርን ለጋራ ብልፅግና እንተጋ ነበር፡፡ ምናልባትም ቀደም ባሉት ጊዜያት ያየናቸውን አበሳዎችና ሰቀቀኖች በየመንደራችን ባላየን ነበር፡፡ ተፈጥሮም ክፍተታችንን ተጠቅማ በረሀብ ባልቀጣችን ነበር፡፡
አናስተውል ብለን እንጂ ታሪካችን ውስጥ ከሚያኮሩት ታሪኮች ይልቅ የሚያሳፍሩት ብዙ ናቸው። በርግጥ የስልጣኔ ጀማሪ ነበር፡፡ በጧቱ የታሪክ ገበያ ቱባ ሰነዶች የተሰነዱልን፣ እልፍ ተረኮችና መዝሙሮች የተነገሩልን ነበርን፡፡ ከዚያም በኋላ ለጠላቶቻችን ትንታግ ሆነን፣ ከመዳፋቸው እያመለጥን፣ በክብር ድንበራችንን ጠብቀን የኖርን አልበገሬዎች ነን፡፡
እውነት ነው ሜዳና ተረተሩ፣  በጠላት አልተደፈረም። አደባባዮቻችን ላይ ባዕድ አልደነፋበትም፡፡ ባንዲራችንና ክብራችን በባዕድ አልተቀደደም፡፡ ዘወር ስንል ግን ጓዳዎቻችንና እልፍኞቻችን ብዙ እንባ ፈስሶባቸዋል፤ ባንድ ተጣምረን፣ በፍቅር ተጋግዘን ስላልሰራን፣ ረሀብ ድንበራችንን ሳይሆን ጓዳችንን ደፍሮታል፡፡ “ኧረ ጎራው!” እያልን ስጋ ለባሽ ላይ ስናቅራራ፣ ረቂቁ ድህነትና ረሀብ ረግጦናል፤ ተባብረን ስላልሰራን በሽታና ድህነት ቀጥቅጦናል፡፡ በጠመንጃ ያልተበገርንላቸው ጠላቶቻችን፣ በአካል ባያሸንፉንም መንፈሳችን ረግፎ፣ ነፍሳችን ስትቃትት፣ ከረጢት ይዘን ለልመና ስንወጣ፣ በሽሙጥ ስቀውብናል፡፡ ጀግኖች ነን አልን እንጂ፣ በረሀብ እግር ተረግጠን ስናለቅስ ኖረናል፡፡
ይሁን እንጂ ምን አዚም እንደወደቀብን ባላውቅም፣ ዛሬም ልመናችን አያሳፍረንም፡፡ ዛሬም ረሀብን ለማሸነፍ ማጭድና ዶማ ከመያዝ ይልቅ ወንድማችንን ለማጥፋት ጦር እንሰብቃለን፣ ቢላ እንሞርዳለን። ወደ ስልጣኔና ዕድገት ከማማተር ይልቅ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩትን ግጭቶች እየቆሰቆስን ለመጠፋፋት እንተጋለን፡፡ በተለይ ላለፉት 27 ዓመታት ኢሕአዴጋዊው መንግስት፤ በልማት ጥሩንባ ግን የጥፋት ፅላት ጽፎ ሲመጣ፣ የዘፈነውም ያለቀሰውም ልዩነቱ እስኪጠፋ ድረስ ሀገሩን ሳይሆን መንደሩን የሙጢኝ እንዲል ተደርጓል፡፡ ይህ ሴራ በጥልቀት ተቆፍሮ በመተከሉ፣ ብዙዎቻችን መንደርተኝነት ተጠናውቶን፣ ለጋራ ሀገራችን ማሰብ እንዳንችል ተፈርዶብናል፡፡
ቀደም ያሉት መንግስታት ብሔራዊ አንድነት ላይ ጠንካራ አቋም ቢኖራቸውም፣ የሕዝባችንን ስስ ብልት ያዩትና ይህንኑ ስሱነት ለሥልጣናቸው ማጣፈጫ አድርገው የቀመሙት ሰዎች “አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት” የሚለው ስያሜ እንደ ሰይጣን ሲያስበረግጋቸው ኖሮ፣ በፍርሃት አርቀው ሊቀብሩት ሌት ተቀን ተግተው ነበር፡፡ ይሁንና ለእነርሱም ለኛም አልጠቀመም፡፡ የሳሱላትን ስልጣን፣ በመረረ እንባና ሰቀቀን ተነጥቀው ተሸኝተዋል፡፡
በዚህም ምክንያት በዶ/ር ዐቢይ የሚመራው የተሀድሶ መንግስት፤ይህንን የተጣለና የተረሳ የአንድነት መዝሙር ይዞ ማቀንቀንና መታገል ጀምሯል፡፡ መለያየትን የጠላነው ኢትዮጵያውያንም፣ መዝሙሩ ለአንድ ሰሞን የጣፈጠን ብንመስልም፣ ቀስ እያለ ግን ውስጣችን ሲፈተሽ፣ የምንቃወመው ወያኔ መራሹ መንግስት፣ አብስሎ የሰጠን የዘር ፖለቲካ ፓስቲ ጣፍጦናል፡፡ በየጓዳው ያጫወተንን ቁማር አስበልቶናል፡፡
“ኢትዮጵያዊነትና አንድነት ይጠቅመናል፤ መለያየታችን ያጠፋናል!” የሚለው አዲሱ መንግስት፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው አማራጭ የሌለው ነው በሚል ያልጠበቅናቸውን አኩሪ ተግባራት ቢከውንም፣ የኛ ልብ ግን ከሰፈራችን ተሻግሮ ማሰብ የቻለ አይመስልም፡፡
“እስረኞች ይፈታሉ፣ የፖለቲካው ምህዳር ይሰፋል!” የተባለው ምኞት እውን እየሆነ፣ አሸባሪና አማፂ የተባሉና የተሰደዱ ፖለቲከኞች ሳይቀር ወደ ሀገር ሲገቡ፣ እውነት እንዳይናገሩ፣ ነፃ መረጃ ለህዝብ እንዳያቀርቡ የተከለከሉ ስደተኛ ሚዲያዎች ወደ ሀገር ገብተው ቢሰሩም አልደነቀንም፡፡ እንዲያውም እኛ ይህንን አስደናቂ ዕድል መጠቀም ያቃተን ይመስላል፡፡
ባለፉት ጥቂት ወራት እንዳየናቸው፤ ብዙዎቻችን አዲሱን የለውጥ ዕድል ተጠቅመን፣ በነፃነት የተሻለች ሀገር ለመፍጠር ከመትጋት ይልቅ፣ ለግላችን ኑሮና ለቀበሌያችን ጥቅሞች በመቆም አሳፋሪ ሰልፋችንን አሳይተናል፡፡ ሌላው ቀርቶ በቀድሞው አምባገነን መንግስት፣አንገታቸውን ደፍተው የቆዩ፣ዞኖችና ወረዳዎች፤ “ክልል ይሰጠን! ዞን እንሁን!” እያሉ መንግስትን በማዋከብ ሌላ አፍራሽ ሚና ለመጫወት መሰለፋቸው፣ አሳዛኝና አስተዛዛቢ ይመስለኛል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ ለበርካታ ዓመታት በሰላምና በፀጥታ ስራቸውን ሲሰሩ የነበሩ ሲቪል ሰራተኞች ሳይቀር “የደሞዝ ጭማሪ ካልተደረገልን ሥራ እናቆማለን” በማለት እንጭጩን የለውጥ ጉዞ ለመግታትና ለማጨንገፍ ሰልፍ ያዙ፡፡ ለመሆኑ ትንሽ ጊዜ ታግሦ፤ ቀጣዩን የተስፋ እሸት ከመጠበቅ ይልቅ፣ ግርግሩን ተጠቅሞ አንዴ ጎርሶ ሲጥ ማለት ይሻላል የሚለውን ሀሳብ ከየት አምጥተው ይሆን? “ሀገሬን እወዳለሁ” እያሉ አደባባይ ላይ መንተክተክስ፣ ያለ ተግባር ምን ውጤት ይኖረዋል? ኢትዮጵያዊነትም የተፈተነው ይኼኔ ነው፡፡ የሀገር ጉዳይ ያንገበግበናል የሚሉና ሰልፍ ለመውጣት ግንባራቸው ላይ ባንዲራ አስረው፣ ክንዳቸው ላይ ተነቅሰው፣ በእንባ ስለ ኢትዮጵያዊነት የደሰኮሩ ዳያስፖራዎች፤ ለሀገር አንድ ዶላር አዋጡ ቢባሉ፣ እንደ ኤሊ አንገታቸውን ቀብረው ጠፉ፡፡ ስለዚህም 3 ሚሊዮን ገደማ ከተገመተው ዳያስፖራ፤ ቃላቸውን የጠበቁት 2800 ሰዎች ብቻ ሆነው ተገኙ ተባለ፡፡  
የእውነት ሀገሩን የሚወድድ ሰው ብዙ መሰናክሎች ከፊቷ የተጋረጡ ሀገር ውስጥ ቆሞ፣ በእጅጉ በተንኮል የረቀቁ ባላንጣዎች ከእነ አቅላቸው ቆመው ሳሉ “ባንዲራው ይቀየር፣ ባንዲራው ልሙጥ ይሁን!” እያለ በችግር ላይ ችግር ይፈጥር ነበር? ምናልባት ቀጣዩ የአሌክስ አብርሃም ግጥም፣ ሁኔታውን ይገልጠው  ይሆን?
ባመድ አፋሽ እጅሽ አጥልቀሽ ካቴና
በጭቆናችን ላይ ቆመን እንዝናና!

ከጭቆና እጮኛ የተጫጨንበት …
ሽክ ብሏል ሕዝብሽ አምሮበታል ጌጡ…
ያንችው ውዶች ብቻ - ከዝምታወ ክታብ በጩኸት የወጡ!
ቀን አንቆጥራለን አርግዘናል ተስፋ፣
ዜናውም ጭንግፍ ነው - ወይ ተስፋ አያወርድ ወይ ተስፋ አያፋፋ!
ነገሩ እንዲህ ነው የሚመስለኝ፡፡
ያለፈው ዘመን ጭቆናም በወያኔ ግንባር ቀደም መሪነት፣ የተወሳሰበና ሀገር የማፍረስ ሴራ ይቀኝ እንጂ በየመንደራችንና በየጐጣችን ያሉት “ጅቦች” ሁሉ ተባብረው እንደበሉን የሚካድ አይደለም፡፡ እነዚህ በሊታዎች ደግሞ ለውጡ ሲመጣ ደንግጠው ወደ ጓዳ አልገቡም፡፡ ወይም እንደ ዋናዎቹ ፍርሀት እንኳ አላሳዩም፡፡ እዚያው ቀለማቸውን ቀይረው፣ ሌላ ተንኮል ሲሰሩ፣ ወንበራቸውን ላለማጣት ህዝብ ሲያፋጁ እያየን ነው፡፡
በዚህ ጊዜ የሰይጣን ዕጣ የደረሰው “ወያኔ” የሚሰማው ስለሌለ፣ ሁሌ ማሳሰቢያ ቢሆንም በየክልሉና ዞኑ፣ ዋናውን የመገዳደል ድራማ የሚሠሩት ግን መለያቸውን “የብሔር ተቆርቋሪ” አድርገው የተነሱ ሌቦች ናቸው፡፡ የህዝቡን የልብ ትርታና የሃያ ሰባት ዓመታት የጠባብነት ስነልቡና በመጠቀም፣”ቀበሌያችን ተወሰደ፤ መሬታችንን ይልቀቁልን” ወዘተ--በማለት ህዝቡን ለማናጨት ታጥቀው ተነስተዋል፡፡
በተለይ ደግሞ የዶ/ር ዐቢይ አሕመድን የሰለጠነና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ራዕይ ለመቀበል ያልተዘጋጁትና ጠመንጃ ብቻ ችግር የሚፈታ የሚመስላቸው ደካሞች ስለበዙ፣ የመንግሥትን ልዕልናና የሀገር አንድነትን ለመገዳደር ጥቂትም አልፈሩም፡፡ እንደ ድሮው ጥይት ባለመተኮሱ ህግን ማክበር አልተዋጠላቸውም፡፡ ስለዚህም ሀገሪቱ ያልተረጋጋች፣ መንግሥትም አቅምና ብልሀት ያነሰው ለማስመሰል፣ ዋነኞቹ ወዳቂዎች የወጠኑትን ውጥን ለማገዝ፣ የየሠፈራችን ከሃዲዎች የሚቻላቸውን እያደረጉ ነው፡፡  
አሳዛኙ ነገር ደግሞ አብዛኞቻችን በሠፈራችን የሚደረገውን የሴረኞች ተንኮል ከመቃወም ይልቅ በየሠፈራችን ተሰልፈናል፡፡ ለብሔራዊ አንድነታችን የምንታገል የምንመስለው ሰዎች፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀድሰናል ብለን የምንዘምር ሃይማኖተኞች፣ ዞረን ዞረን በሠፈራችንና በጐጣችን ተደምረን ፣ ደረት ስንደቃ፣ ሙሾ ስንደረድር ተገኝተናል፡፡
ቀድሞውንም 27 ዓመታት ሙሉ በሌቦች መሶብ ላይ እጃቸውን ሰድደው፣ ለምቾታቸውና ለምኞታቸው የተገዙ የሃይማኖት ሰዎች፤ለአምላካቸው ታማኝ በመሆናቸው ከካድሬ የተሻለ ቦታ በልባችን ማግኘት ባለመቻላቸው፣ በእርቅ ጉዳይ ላይ መግባት ስለተሳናቸው፣ ጦራቸውን ሰብቀው ወንድማቸውን ለመግደል ሲነሱ፣ ታሪክን ቀርቶ ፈጣሪያቸውን አልፈሩም፡፡ ይህ ደግሞ የሀፍረታችን መደምደሚያ ነው። ከጥቂቱ በስተቀር “መብታችንን ያስከብሩልናልና” ተብለው በህዝብ የተደገፉ፣ ነፃነት ያመጡልናል ተብለው በየአደባባዩ ዋጋ የተከፈለላቸውና የተሞተላቸው ተፎካካካሪ ፓርቲዎች ሳይቀሩ፣ በሀብት በጥቅም ተጠላልፈው ስለወደቁ፣ ሕዝቡ ልቡን ከእነርሱ ላይ አንስቶ፣ ወደ ሰማይ ሲያንጋጥጥ፣ ያገኘውን ተስፋ ለማስጠነቅ የተጉም አልጠፉም፡፡  
ታዲያ የኢትዮጵያ ነገር የሚያገባው ማን ይሆን? አቶ ለማ መገርሳ? ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ? ወይስ ማ? የጊዜው ሁኔታ ይህንን አጥብቀን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡ ማነው ኢትዮጵያዊነትና አንድነት፣ ዴሞክራሲና ልማት የናፈቀው?-- መቼም በየሠፈሩ ተበታትነን፣ ዕድገትና ሥልጣኔን መመኘት አይቃጣንም፡፡
ጀምስ ዴቪድ ባርበር፤ ”ዘላቂነት ላለው ዴሞክራሲ የሚስፈልጉት ነገሮች አሉ፤ እውን የዴሞክራሲና የልማት ፍላጐት ካለን ማድረግ የሚገባን እንዲህ ነው፤ ሕዝቦች በመተማመን ላይ የተመሰረተ መከባበርና መቀባበል ያስፈልጋቸዋል (ለ
ዴሞክራሲ ግንባታ መነጋገር እንጂ አመጽ መፍትሔ አይሆንም!!” ይላል፡፡
 በመንግሥቱ መዋቅርና ሥርዓት ላይ አመኔታ ሲኖራቸው፣ መንግሥት የሀገር ሥርዓት መሪ እንጂ እንደ ገዢና መቆጣጠሪያ መሳሪያ ካልታየ፣ ሕዝቡ የፖለቲካው ሥርዓቱ ለአሁኑና ለቀጣዩ ተስፋ እንደሚሰጥ ሲያምን፣ ከዚያም ባለፈ በአንድ ጊዜ ሁሉንም ነገር መለወጥ እንደማይቻል ተረድቶ፣ በምክንያታዊ መንገድ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ሲቀበል ነው፡፡
በአብዛኛው በእኛ ሀገር ለውጥ የታየው ግን ይሄ አይደለም፡፡ ብዙዎቻችን ከጅማሮው አንስቶ እስካሁን ሁሉን ነገር “ሱሪ ባንገት” እያልን ምጥ አብዝተናል፡፡ ለሀገራችን የምናስብ መሆናችንን፣ አንዳንድ ችግሮችን በመታገስ አለዚያም “ምናገባኝ” ብለን እንደ ትርዒት ተመልካች ዳር ቆመን ከማየት በመቆጠብ፣ ለልጆቻችን እንኳን የተሻለች ሀገር ለመፍጠር አልተጋንም፡፡ ከሁሉ የሚበልጠው ሠላም የሀገራችንን አድማሥ እንዲሸፍንና የልማት መሠረቶች የሚጣሉበት ዕድል እንዲፈጠር አልተጋንም፡፡ “ኢትዮጵያዊነት” ብለን የዘመርንለት ጥንካሬ፣ በገቢር ባለመታየቱ በአደባባይ ላይ ወድቀናል!
ይሁን እንጂ የለውጡ ግንባር ቀደም መሪዎች በያዙት ራዕይ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር የምትሆንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ ከፈተናዎቻችን ይልቅ ህልሞቻችን አቅም ስላላቸው፣ ተስፋ የሚያስቆርጥ ስሜት ሳይሆን፣ የድልና የበረከት መዓዛ ከደጃችን እንደቆመ  ይሰማኛል።


Read 2652 times