Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 26 May 2012 09:50

“እውነተኛ ጋብቻ በኮንትራት? ትዳር እንደ አክሲዮን ገበያ?”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አንተ... ቴዲ አፍሮ ነህ ወይስ አፈወርቅ ተክሌ! እነሱም አላደረጉትም”

ገና ወደ ግቢው ስገባ ታውቆኛል። የሆነ ችግር ተፈጥሯል። ሲሟሟቅ የሰነበተው የሰርግ ዝግጅት፤ ዛሬ ደርሶ ቅዝዝ የሚልበት ምክንያት የለማ። በእርግጥ፤ ሳቅና ጨዋታው፤ የሰርግ ዘፈን ጩኸትና ወከባው አለ። ሁሉም ሰው፤ አዲስ የተፈጠረ ነገር እንደሌለ ለማስመሰል ይሞክራል። ሰላምታውን እንደወትሮው ለማጯጯህ ይተጋል። ነገር ግን፤ ቁልጭ ብሎ ባይታያችሁም፤ አንዳች የተለወጠ ነገር እንዳለ ይሰማችኋል።

ስለ ሰርጉ ዝግጅትናና ስለ ቀለበት ስነስርአት ወሬ ሲጀመር፤ ለምንድነው ሚዜዎቹ እርስ በርስ የተያዩት? አንደኛው አንገቱን ሲደፋ፤ ሌላኛው ጎልማሳ ሚዜ ምንም እንዳልሰማ ድንገት ወደ ሰማይ አንጋጥጦ የጨረቃዋን ውበት ማድነቅ ያሰኘውስ ምን ነሽጦት ይሆን? ሙሽራው ወሬ ለመቀየር መሞከሩ ደግሞ ይገርማል። ምናልባት በፊርማ ቀለበት የሚያስርበትና የጋብቻው ቀን ሲቃረብ ፍርሃት ፍርሃት ይል ይሆናል።

ግን... ጠቅላላ ሁኔታቸው ሲታይ ግር ይላል። ሁለቱ ሚዜዎች ሊያንሾካሹኩ ሲሞክሩ አይቻለሁ። የሌላኛው ሚዜ ስልክ ሲጮህ፤ ሁሉም አፈጠጡበት። ሲጠብቁት የነበረ ድምፅ ይመስላል። የሚጮኸውን ስልክ ለአፍታ ገልመጥ አድርጎ፤ ከሙሽራውና ከሌሎቹ ሚዜዎች ጋር ተያየ። በቃላት አልተነጋገሩም፤ ግን ተግባብተዋል። በምን እንደተግባቡ ነው ያላወቅኩት። ስልክ ማናገር የጀመረው፤ ራቅ ካለ በኋላ ነው። ንግግሩን ለመስማት እየጓጉ፤ ግን ደግሞ ሮጠው ላለመሄድ ከራሳቸው ጋር የሚታገሉ ይመስላሉ። “የተፈጠረ ነገር አለ?”

“ምን?”፤ “ምን ተፈጠረ?”፤ “ኧረ ምንም የለም”፤ “ምን መስሎህ ነው?” ....እርስ በርስ እየተያዩ አጣደፉኝ። ግራ ገባኝ። በዚህ መሃል ነው፤ ስልክ ለማነጋገር ወደ አጥሩ ጥግ ሄዶ የነበረው ሚዜ የተመለሰው። ተናዷል። “ዘጋችብኝ፤ ራሷ ደውላ ዘጋችብኝ። ሁለተኛ እንዳትደውል ልነግርህ ነው የደወልኩት ብላ ዘጋችብኝ...”

ከዚህ በኋላ፤ “ኧረ ምንም አልተፈጠረም” እያሉ መቀጠል አልቻሉም። ግን ግልፅ አድርገውም አልነገሩኝም። ብቻ... በሆነ ምክንያት፤ ሙሽሪትና ሙሽራ ተኮራርፈዋል፤ መነጋገር አቁመዋል። ሚዜዎች በየተራ ለማግባባት ሞክረው አልሆነላቸውም። “እንዴ፤ ታዲያ ምን ችግር አለው?...” አልኳቸው። እንዴት እንዳላሰቡት እንጃ። ሁለት እህቶቹኮ (አንዷ የኔ ፍቅረኛ ነች)፤ የሙሽሪቷ የቅርብ ጓደኞች ናቸው፤ በጣም የቅርብ ጓደኛ። “ጓደኞቿ እዚህ አጠገብህ እያሉ...” ንግግሬን አላስጨረሱኝም።

ተስፋ የሌለው ሃሳብ የተናገርኩ ይመስል አጣጣሉብኝ። የዚህ ምክንያት ገብቶኛል። እህቶቹና ሙሽሪት፤ ጓደኝነታቸው እንደድሮው አይደለም። የወንድማቸው ሚስት እንድትሆን ስላልፈለጉ፤ ተደባብረዋል። “አንተ ብትሞክር... ትሰማሃለች፤ ዝምተኛ ስለሆንክ ታከብርሃለች። ደውልላት” ... ለማሰብና መልስ ለመስጠት ጊዜ ሳይሰጡኝ፤ ከኪሴ ስልክ አውጥተው እያዋከቡ እንድደውል አደረጉ። የሙሽሪት ስልክ መጥራት ሲጀምር ነው፤ የተደናገረኝ። ለመሆኑ በምን ምክንያት ነው የተኳረፉት? መልስ ሳላገኝ፤ ስልኩ ተነስቶ ከሙሽሪት ጋር መነጋገር ጀመርን።

ሰላም፤ ጤንነት... ከተባባልን በኋላ፤ ምን ችግር ተፈጠረ ብዬ ጠየቅኳት። “እሱን ጠይቀው፤ እኔን ተወኝ” .... ሙሽራውን ማለቷ ነው። ሙሽራውን ምን እንዳጠፋ በግልፅ ልትነግረኝ አልፈለገችም። ያንኑን ጥያቄ፤ ቃላት እየቀያየርኩ ሃያ ጊዜ ጠይቄያታለሁ፤ “ምን አጠፋ?”፤ “ምን ጥፋት ሰራ?” ... እያልኩ። እሷም ትናገራለች። አስር ደቀቂ ባይሞላ ነው? ግን አንድም የተጨበጠ ነገር አላገኘሁም። ንዴቷ ደግሞ እየጨመረ ነው። በመጨረሻ፤ “ይሄውልህ ልንገርህ። አዋርዶኛል፤ ንቆኛል። የእህቶቹን ምክር እየሰማ አዋርዶኛል፤  ለፍቅር ብዬ ስቀርበው እሱ ስለ ገንዘብ ያወራል። ለዚያውም በሌለ ገንዘብ። ግድ የለም። ለማንኛውም ቻው” ... ብላ ስልኩን ዘጋችው።

መቼም፤ እሷ ባትናገረውም፤ ሙሽራው እዚው አጠገቤ ስለሆነ፤ ሁሉንም ነገር ለማወቅ አያስቸግረኝም። ግን እንደገመትኩት ቀላል አልሆነም። ከሙሽራውም በጭራሽ በቀጥታ መልስ ላገኝ አልቻልኩም። እጠይቃለሁ፤ እሱም “መልስ” ብሎ ይናገራል። ግንም ምኑም አይጨበጥም። ግን ይናገራል ...”እስቲ አስበው፤ የሷ ቤተሰቦች እኔን ቢጠሉኝ ጋብቻችን ሰላም ይሆናል? የኔ ቤተሰብ እሷን ቢጠሏት ሰላም ታገኛለች? ለሷ አስቤ ያደረግኩት ነው። ሰላም መፍጠር ብዬ ነው። እሷ ግን በቃ አኮረፈች። በእኔ ላይ እምነት የላትም ማለት ነው ...”

እነዚህ ሰዎች፤ ስለ ምንድነው የሚያወሩት? አንድ የታዘብኩትን ነገር ልንገራችሁ። ሰዎች በግልፅ ከምታቀርቡላቸው ጥያቄ ወይም ሃሳብ ጋር ምንም የማይገናኝ ምላሽ የሚሰጧችሁ ከሆነ፤ ወይም አንዱን ነገር እየደጋገሙና እየመላለሱ የሚናገሩ ከሆነ፤ ... ያኔ “ነገር አለ” ማለት ነው። ግራ መጋባት የለባችሁም። ሊናገሩትና ሊመልሱት ያልፈለጉት ነገር አለ። ይህንን እያወቅኩም፤ ደጋግሜ መጠየቄ አልቀረም። ምናልባት አጠያየቄ ግልፅ ስላልሆነ ነው? ብላችሁ እንድትጠራጠሩ ያስገድዷችኋል። ለማረጋገጥ፤ በረዥሙ መጠየቅ ጀመርኩ።

“እሺ። ለሷ አስበህ ያደረግከው ነው። ምንድነው ያደረግከው? ሰላም ለመፍጠር ብለህ ምን አደረግክ? ምንህን ነው ያላመነችው?” ...

ሙሽራው ያንኑን ሃያ ጊዜ የሰማሁትን መልስ ደገመልኝ - የተወሰኑ ቃላትን ቀይሮ፤ ጨምሮ ወይም ቀንሶ። “እንደምወዳት ታውቃለህ። ለሷ አስቤ ያደረግኩት ነው። የቤተሰብ ስምምነትና ሰላም ለመፍጠር ብዬ ነው፤ በእኔ ላይ እምነት ከሌላት አልወደደችኝም ማለት ነው፤ በእህቶቼ የምመራ ከመሰላት እንደ ጋሪ ትቆጥረኛለች ማለት ነው” ይላል። ከዚህ በኋላ መጠየቅ ዋጋ የለውም። ለነገሩ ሙሽሪቷንም በአካል አነጋግሬያት፤ ምንም የተሻለ ቁምነገር አላገኘሁም።

“ምን ተናግሮ ምን አድርጎ ነው ያዋረደሽ? ከእህቶቹ የሰማው ምክር ምንድነው? እንዴት ነው ከፍቅር ይልቅ ገንዘብ የመረጠው?” ... እንዴት ተንትና እንደምታስረዳኝ ለማወቅ ከጓጓችሁ፤ እንዳማራችሁ ይቀራል። “ከምንም በላይ ክብሬን እፈልገዋለሁ እሺ?” በሚል መግቢያ ጀምራ፤ የቅድሙን ደገመችልኝ “እሱ ግን አዋረደኝ፤ ንቆኛላ። ፍቅርን ትቶ ስለ ገንዘብ ያወራል፤ ሴተኛ አዳሪ መሰልኩት እንዴ? ወይ ከገንዘብ ወይ ከፍቅር አንዱን ይምረጥ፤ ወይ ከእህቶቹ ወይ ከኔ ይምረጥ” አለች።

ፍሬ ነገሩን፤ ቁም ነገሩን፤ ጭብጡን... እንዲነግሩኝ በጠየቅኳቸው ቁጥር፤ ነገሩን ይበልጥ እያወሳሰቡ እንቆቅልሽ ያደርጉብኛል። እንዴት ነው ነገሩ! የሚሰጡኝ “መልስ” ግን፤ በፍፁም “መልስ” አይደለም። “መልስ” ላለመስጠት የሚደረግ ቀሽም ሙከራ ነው። ሙሽሪትን ለሁለተኛ ጊዜ  ሙሽራውን ለሶስተኛ ጊዜ ካነጋገርኩ በኋላ፤ “በቃኝ” አልኩ። ለዝባዝንኬ የድብብቆሽ ጨዋታ፤ ከዚህ በላይ ትእግስት የለኝም። ታጋሹ የሚባለው ጻድቁ ኢዮብም እንዲህ የታገሰ አይመስለኝም።

ነገሩን ማወቅ ፈልጌያለሁ። ግን ተናድጃለሁ። እንደገና ላላናግራቸው ለራሴ እየማልኩ በንዴት ተነስቼ ስሄድ ነው፤ አንዱ ሚዜ ውጭ ጠብቆ “ጉዱን” የነገረኝ። ሙሽራው፤ የጋብቻ ኮንትራት እንፈራረም ብሎ ሙሽሪትን ስለጠየቃት ነው ችግር የተፈጠረው። ሃሳቡ የመጣው ከእህቶቹ እንደሆነ ግን ገና አላወቅኩም፤ አልተነገረኝማ - የአንዷ ፍቅረኛ ስለሆንኩ፤ ፈርቶ ይሆናል ያልነገረኝ። የዛሬን አያድርገውና፤ የሙሽራው እህቶችና ሙሽሪቷ በጣም የሚዋደዱ ጓደኛሞች ነበሩ። የሚገርመው ነገር፤ ወንድማቸውን ያወቀችው ከነሱ ጋር በነበራት ጓደኝነት ነው።

ጓደኝነታቸው ተራ ጓደኝነት እንዳይመስላችሁ። አብረው ተምረዋል፤ አብረው ጨፍረዋል። ሚስጥር የማይደባበቁ ጓደኛሞች ናቸው (ጓደኛሞች ነበሩ፤ ከወንድማቸው ጋር ፍቅር ጀምራ የጋብቻ ሃሳብ እስኪመጣ ድረስ)። ለነገሩ ጓደኝነቷን አይጠሉትም፤ ከሷ ጋር ሚስጥር መካፈልና አብሮ መጨፈሩን ይወዱታል። ወንዶችን መማረክና ማማለል፤ በዚህም ግብዣና ስጦታ መሰብሰብ፤ ወንዶችን ማታለልና ማሞኘት እንደ አዝናኝ ጀብድ (እንደ “አድቬንቸር”) እየቆጠሩ አብረው የሰሩት ነገር ሁሉ ያስደስታቸዋል። በየጊዜው እያስታወሱ ይስቃሉ። በዚህ በዚህ ጓደኝነቷን ይወዱታል።

ነገር ግን ወንዶችን በማሞኘት ስታስቃቸው የነበረችው ሴት፤ የወንድማቸው ፍቅረኛ እንድትሆን አልፈለጉም። ምን ዋጋ አለው? ተከራክረው ሊያለያዩዋቸው አልቻሉም። “አትሆንህም” ብለው ወንድማቸውን በየቀኑ ሲወተውቱ ወራት ተቆጠሩ። ጭራሽ የእህቶቹ ጭቅጭቅ ሲሰለቸው፤ አንደኛውን በጋብቻ ልገላገል ብሎ ሲወስን ደግሞ አበዱ። “አትሆንህም፤ ዱርዬ ነች፤ ልትበላህ ነው” የሚል ውትወታ አልሰራም። ሲጨንቃቸው፤ የመጨረሻ ሙከራ አደረጉ። “ገንዘብህን ፈልጋ ካልሆነ፤ የጋብቻ ኮንትራት ፈርማ ታሳየን። አለበለዚያ ግን ጋብቻህ ላይ አንገኝም” አሉ።

ይሄን ሁሉ ታሪክ ገና አላወቅኩም። ስለ እህቶቹም ምንም የተነሳ ነገር የለም። በቃ የጋብቻ ኮንትራት እንፈራረም ሲላት ችግር እንደተፈጠረ ነው የተነገረኝ። ለነገሩ፤ ለመጠየቅም ጊዜ አልነበረኝም። የውዝግቡን መነሻ መጀመሪያኑ በግልፅ ሳይነግረኝ በመቆየቱ የተሞኘሁ መሰለኝ። በተለይ በሙሽራው ተናድጃለሁ። “ዙሪያ ጥምጥም መዘብዘብ እንጂ፤ በቀጥታ መናገር ትተሃል? የምን ኮንትራት ነው? ልታገባት ካልፈለግህ፤ ሃሳብህን ከቀየርክ በቀጥታ አትነግራትም?” ብዬ ስጮህበት እሱም ተናደደ። ሃሳብ መቀየርና ጋብቻ አለመፈለግ... ብዬ በማይመለከተኝ ነገር ውስጥ መግባት አልነበረብኝም። ቶሎ ብዬ ስህተቴን ለማረም ሞከርኩ። “እሺ እሱን ተወው። የምን ኮንትራት ነው የምታወራው?”

ሚዜዎቹ አጉረመረሙ። “እኔም ብያለሁ፤ እኔም ብያለሁ” በሚል ስሜት። “እኔ ምንም አልጣመኝም። እንደዚህ አይነት ነገር አጋጥሞኝ አያውቅም” አለ ተለቅ ያለው ጎልማሳ ሚዜ። ካሁን በፊት አራት ጊዜ “በሚዜነት ያገለገለ” ስለሆነ፤ እንደ አዋቂ ነው የሚታየው። እስካሁን ታፍኖ የቆየ ስሜቱን ለቀቀው - “ጋብቻ በኮንትራት? በጣም ያሳፍራል።... ህግ ውስጥ ገብቷል እያለ ይከራከራል፤ እኔ ግን በህይወቴ እንዲህ አይነት ነገር አይቼም ሰምቼም አላውቅም። ሁሉም ሰው በማዘጋጃ ቤት፤ ማለቴ በክፍለ ከተማ ተፈራርሞ ነው የሚጋባው። ኮንትራት የሚባል ነገር የለም”

ደግነቱ፤ ሙሽራው አንድ ቲፎዞ የሚሆንና የሚከራከርለት ሚዜ አላጣም። “ኮንትራት መፈራረምም ይቻላል። ያለ ኮንትራት ወይም ኮንትራት ተፈራርመህ ማዘጋጃ ቤት መሄድ ትችላለህ። ኮንትራቱን ተቀብለው ያፈራርሙሃል” ... የሙሽራው ቲፎዞ፤ በደንብ ለማስረዳት የቻለ አይመስልም። ጎልማሳው ሚዜ ተመቸው።

“ኮንትራት ምን ያደርጋል? ምንም ጥቅም የለውም። በፍቺ መለያየት ከመጣኮ፤ እስካሁን የነበራችሁ ንብረት የየግላችሁ ይሆናል በቃ። ከዚህ በላይ ምን ትፈልጋለህ? ደግሞስ ለየትኛው ሃብት ነው የምትጨነቀው? አንዲት ያረጀች አይሱዙ... እና በቃ። ሌላ ምንም የለህም። 10 ሄክታር የእርሻ መሬት ... ይሄ እንደ ንብረት አይቆጠርም። ከእርሻ መሬት የሚገኘው ትርፍ በግል ሂሳቤ ይቀመጥ ብለህ የጋብቻ ኮንትራት ስታዘጋጅ አታፍርም? በአመት ከአስር ሺ በላይ አተረፍኩ ስትል ሰምቼ አላውቅም። የሷ ደሞዝ የዚህ አራት እጥፍ አይሆንም?” ጎልማሳው ሚዜ ሰሞኑን በሙሉ በቁጭት ሲንገበገብ የሰነበተ ይመስላል። “ደግሞስ፤ ከማን በልጠህ ነው ኮንትራት ምናምን የምትለው... አንተ ቴዲ አፍሮ ነህ ወይስ አፈወርቅ ተክሌ! እንኳን አንተ ሚሊዬነሮቹና ቢሊዬነሮቹ እንደዚያ አላደረጉም”

“እንዴት አወቅህ?” ብሎ አፋጠጠው የሙሽራ ቲፎዞ።

“በቃ፤ ከባህላችን ውጭ ነው። ማንም እንደዚህ አያደርግም” ... ዛሬ ቀኑ የጎልማሳው ሚዜ ነው። አልተቻለም - “ይሄኮ ግልፅ ነው። ጋብቻ ማለት፤ ሁለት ሰዎች እንደ አንድ ተዋህደው ለመኖር የሚገቡበት ነው። ፍቅር አይደለም እንዴ? በጣም ያሳዝናል። የገና በጋብቻ ከመጋባትህ በፊት፤ በፍቺ ለመለያየት ታቅዳለህ። ኮንትራት ማለትኮ፤ ወደ ፊት በፍቺ ስትለያዩ እንዴት ንብረት እንደምትከፋፈሉ መፈራረም ማለት ነው። ታዲያ እሷ ስለ ጋብቻና ሰርግ እያሰበች፤ አንተ ስለፍቺና ስለ ገንዘብ ክፍፍል ላስፈርምሽ ትላታለህ? እንዴት ሰው በጋብቻው ዋዜማ፤ በፍቺ ስለመለያየት ያቅዳል?” ጎልማሳው ሚዜ ክርክሩን በማህተም የዘጋ ያህል ጭንቅላቱን እየነቀነቀ ቢራውን ተጎነጨ። የሙሽራው ቲፎዞ ሆኖ ለመናገር ሞክሮ ብዙም ያልተሳካለት ሌላኛ ወጣት ሚዜ፤ በዚህች ፋታ ገባ።

“በፍቺ መለያየትማ ያለ ነገር ነው። ከጋብቻዎች መካከል ግማሾቹ በፍቺ ይፈርሳሉ። በንብረት ክፍፍል እየተጣሉ የሚናከሱ ባልና ሚስት ለማየት ከፈለግህ ፍርድ ቤት መሄድ ነው፤ ፍርድ ቤት የተጣበበው በነሱ ነው። ባለፈው ሳምንት አልነገርኩህም? ባልና ሚስት ተጣልተው ንብረት ሲከፋፈሉ... ይታያችሁ፤ መጨረሻ ላይ አንድ መኪና ቀረ። መኪናውን ሸጦ ገንዘቡን መካፈል ቀላል ይመስላል። እልህ ለተጋቡ ባልና ሚስት ግን ቀላል አይደለም። ሴቷ፤ መኪና የሚገዛ ሰው አፈላልጋ አመጣች። በ260ሺ ብር ለመግዛት ተስማምቶ ማለት ነው። የድሮው ባለቤቷ ሊያመሰግናት መሰላችሁ? በጭራሽ። እሱም ገዢ አፈላልጓል። ግን በ200ሺ ብር እንኳ የሚገዛ ሰው አላገኘም። ግን አላመሰገናትም። እንዲያውም አልስማማም አለ። እልህ ነዋ። ቤትና ሚኒባስ፤ ፍሪጅና ቴሌቪዥን፤ የመጠጥ ግሮሰሪውና አሳ መሸጫው... ይሄን ሁሉ ለመከፋፈል ሲጨቃጨቁ፤ በእያንዳንዷ ቀን፤ አንዱ ሌላውን ማብገን እንደ ስራ ይዘውታል። ጥላቻና እልሃቸው ጣራ ደርሷል። በመኪናው ሽያጭ ላይ ስላልተስማሙ፤ የመጨረሻው አማራጭ ለሃራጅ ጨረታ ማቅረብ ነው። በሃራጅ ጥሩ ዋጋ እንደማይገኝ ቢነገረውም፤ የድሮው ባል ምንም አልመሰለውም። መኪናዋ በሃራጅ የተሸጠችው ከ180ሺ ብር በታች መሰለኝ ... ብቻ በኪሳራ ተሸጠች።

ለእልህና ለጥላቻ ብለው፤ ሁለቱም ይከስራሉ። ...ግማሹ ጋብቻ በፍቺ እየፈረሰ፤ ከዚያ ደግሞ በንብረት ክርክር መጣላትና መክሰር...። ባል ወይም ሚስት የቢዝነስ ድርጅቶችን የሚመሩ ከሆነ አስቡት። በክስና በክርክር ጊዜያቸው ሲቃጠል፤ ስራቸው ተመልካች አጥቶ ይበላሻል። ስራ ላይ ቁጭ ሲሉም፤ ሃሳባቸው ሌላ ቦታ ነው - እልህና ጥላቻ ጋ። አርቲስት ለሆነ ሰውማ ተወው፤ በጭራሽ አእምሮውን ሰብሰብ አድርጎ መስራት አይችልም። እድሜው ባክኖ ይቀራል። እድሜያቸው ከ40 በላይ የሆኑ አርቲስቶች እንደ ወጣትነት ዘመናቸው አስደናቂ ፈጠራ ይሰራሉ? ብዙዎቹ አይሰሩም። እንደ ወጣትነታቸው ዝነኛ ይሆናሉ? አይሆኑም። እየተረሱ፤ እየጠፉ፤ ዝናቸው እየደበዘዘ በትዝታ ብቻ የሚወደዱ ይሆናሉ”

“ተው እንጂ!” እስካሁን በዝምታ የቆየው ሌላኛው ሚዜ ገና አሁን ነቃ። ስልቹ ይመስል እንዳልነበረ ሁሉ አሁን ፊቱ በርቷል ...”40ኛ አመታቸውን የደፈኑ አርቲስቶች ጉዳቸው ነዋ። አንተ እንዲህ አስቤ አላውቅም። ግን በደንብ ስታየው ግን እውነት ነው... በጣም የሚገርም ነው” ... የአርቲስቶችን ስም መዘርዘር ጀመረ።

የሙሽራው ቲፎዞ ሆኖ ሲናገር የነበረው ሚዜ፤ የሌሎችን ትኩረት መሳብ በመቻሉ ተደስቶ፤ ማብራሪያ ጨመረበት።

“እድሜ ሲገፋ፤ እውቀት ሲጨምር፤ አእምሮ ሲበስል ... አርቲስቶቹ በፈጠራ ስራም ማደግ ሲገባቸው፤ ወደ ታች ይወርዳሉ። ለምን ብትሉኝ፤ በዚሁ የጋብቻ፤ የፍቺና የንብረት ጣጣ ሊሆን ይችላል። እዚህ ሁሉ ጣጣ ውስጥ ከመግባት፤ አስቀድሞ የጋብቻ ኮንትራት መፈራረም ይሻላል”

“ቆይ፤ ቴዲ አፍሮ ኮንትራት ተፈራርሟል?” ... ጠየቀ ከስልቹነቱ የተነቃቃው ሚዜ።

“እኔ ምን አውቃለሁ? ደግሞ ገና አላገባም። ጋብቻ አልፈፀመም” የሙሽራው ቲፎዞ ተነጫነጨ። ክርክሩ መስመር የሳተ መስሎት ነው የተናደደው። “አሁን የአርቲስቶችን ነገር እንተወውና፤ እዚህ የጀመርነው ጉዳይ ...”

“ለምድነው የምተወው?” ስልቹ መሳዩ ሚዜ፤ በቀላሉ ክርክሩን ለመተው አልፈለገም። “ማንም ሰው ቢሆን፤ ለሚወዳቸው አርቲስቶች ያስባል። የፈጠራ ስራቸውኮ፤ ለሁላችንም ነው። ለኔ ደግሞ በተለይ የቴዲ አፍሮ... ቆይ ግን፤ ከማግባቱ በፊት ኮንትራት የሚፈራረም አይመስልህም? ለማንኛውም ቢጠነቀቅ አይከፋም። በአንድ አልበም 5 ሚሊዮን ብርኮ ቀላል አይደለም። በኋላ በፍቺ መለያየት ሲመጣ፤ ወድ የፈጠራ ጊዜው በጭቅጭቅና በንትርክ እንዳይጠፋ ነዋ”

“ጤና የላችሁም እንዴ?” ጎልማሳው ሚዜ እንደገና ተነሳበት፤ “ይሄ የናንተ ሟርት ነው። ለመሆኑ እናንተ ምን እንደሆናችሁና የት እንደሆናችሁ ታውቃላችሁ? ሚዜዎች ናችሁኮ፤ ሰርግ የሚደገስበት ግቢ ውስጥ ነው ያለነው። ለምታፈቅሯትና የምታገቧት ሴት አታስቡም? ፈርሚ ስትሏት፤ እንደማታምኗትና እንደምትጠረጥሯት እየነገራችኋት ነው”

“ኮንትራቱና ፊርማውኮ ለሁለቱም ነው” መለሰ የሙሽራው ቲፎዞ፤ “ማንኛውም ሰው ኮንትራት የሚፈራረመው፤ ታማኝነትን በመጠራጠር አይደለም። ድርሻ ድርሻቸውን በግልፅ እንዲያውቁና አላስፈላጊ ጭቅጭቅ እንዳይፈጠር ለመከላከል ነው። ሰላም ለማግኘት ነው”

ጎልማሳው ሚዜ ገነፈለ። “ስለዚህ፤ ጋብቻ እንደንግድ፤ በኮንትራት ይሁን? የገቢ ምንጭና የገቢ አይነት ብለህ መዝገብ ታዘጋጃለህ? ከዚያኛው የገቢ ምንጭ እኔ 70% አንቺ 30%፤ ከዚህኛው የገቢ አይነት ስድሳ እና አርባ ፐርሰንት እያልክ ድርሻ ድርሻ ትመድባለህ። የአክሲዮን ሽያጭ አደረጋችሁትኮ። ጋብቻኮ ኩባንያ አይደለም። በዚህ የምንስማማ መሰለኝ። ይሄኮ የፍቅር ጉዳይ ነው። በፍቅር መሃል ስለ ገንዘብ ድርሻ ማሰብ .... በጣም ያሳዝናል”

“ወንድሜ፤ ሙሽራና ሙሽሪት ሰርጉን የሚደግሱት፤ የየድርሻቸውን አዋጥተው እንደሆነ ታውቃለህ” አለ የሙሽራው ቲፎዞ።

“የየድርሻቸውን የሚያዋጡትማ ለጋብቻ ነው። ለመልካም ነገር ነው። አንተ የምታወራው ድርሻ ግን የመለያየት ድርሻ ነው። ያልገባኝ ነገር አለ። ሰው እንዴት በጋብቻው ዋዜማ፤ በፍቺ ስለመለያየት ያቅዳል? ደግሞም በፍቺ የማይለያዩ ብዙ ናቸው” ጎልማሳው ሚዜ ተማረረ።

የሙሽራው ቲፎዞ ጎልማሳውን ሚዜ ተከራክሮ እንደማይችለው ገብቶታል መሰለኝ፤ ነገረኛ መልስ ሰጠ፤ “የማይፋቱ ብዙ ናቸው? እንግዲህ ስለፍቺና ስለጋብቻ ከኔ ይልቅ አንተ ታውቃለህ። ሶስት ነው አራት ጊዜ... ሚዜ ሆነሃል። ሁሉም ሁለት አመት ሳይሞላቸው ተለያይተዋል አይደል? ራስህ ነህ የነገርከኝ”

ጎልማሳው ሚዜ በድንጋጤ ተቁለጨለጨ። ለካ፤ ሙሽራው ይህን አያውቅም ነበር። የጭቅጭቁ ርእስ ተቀየረ። “እንዴት አትነግረኝም?”፤ “ነግሬሃለሁ”፤ “ሚዜ ሆነህ እንደምታውቅ እንጂ ሌላውን ታሪክ አልነገርከኝም”፤ “ስላልጠየቅከኝ እንጂ...”

ጭቅጭቁ ወደ ሌላ ርእስ ቢሸጋገርም፤ የኔ ሃሳብ ግን ከጋብቻ ኮንትራት ላይ አልተላቀቀም። ከሁሉም በላይ ገንኖ የታየኝ ነገር፤ ህይወታችን ምን ያህል “በይሉኝታ” ተሳስሮ መጠፈሩ ነው። የጋብቻ ኮንትራት፤ አሳማኝ ምክንያቶች እንዳሉትና ጠቃሚ እንደሆነ ለመካድ ባልችልም፤ “ጥሩ ነገር ነው” ብዬ ለማመን ግን ከስሜቴ ጋር ትግል ሆነብኝ። ሁለት ሰዎች እንዴት ህይወታቸውን መምራት እንዳለባቸው ተነጋግረው ቢስማሙና ቢፈራረሙ ምን ችግር አለው? መቼም፤ ሁለት ሰዎች ሺ ጊዜ ቢፋቀሩ፤ ሺ ጊዜ ቢጋቡ... ያው ሁለት ሰዎች ናቸው። ተጨፍልቀው አንድ ሰው፤ አንድ ሃሳብ አይሆኑም። በእውን የምናየው የሰዎች ህይወት እንዲህ ግልፅ ነው።

ነገር ግን፤ “ሁለት ሰዎች በትዳር አንድ ይሆናሉ” የሚለውን አባባል በጥሬው ይዘን ለማመን እንፈልጋለን። ባልና ሚስት፤ የተለያየ አእምሮና ሃሳብ፤ የተለያየ አካልና ዝንባሌ እንዳለቸው ለመካድ ይሞካክረናል። ለምን? በይሉኝታ ነዋ። ለፍቅርና ለጋብቻ ብዙም ክብር የሌለን መስለን እንዳንታይ እንፈራለን። “ሰው ምን ይለኛል?” በሚል ስሜት፤ “ሁለት ሰዎች በጋብቻ አንድ ልብ ይሆናሉ”... ብለን እንናገራለን። ግን፤ ፍቅርና ጋብቻ የሚኖረው ሁለት ሰዎች፤ ሁለት ልቦች፤ ሁለት አእምሮዎች ሲኖሩ ነው። ሙሽሮች የምር ተዋህደው አንድ ከሆኑ፤ “መፋቀርና መጋባት፤ ሚስትና ባል” የሚባል ነገር አይኖርም። ፍቅርና ጋብቻ ማለት፤ ባልና ሚስት አንድ አይነት ሃሳብ ይኖራቸዋል ማለት አይደለም። ፍቅርና ጋብቻ ማለት፤ እሱ የሷን የተለየ ሃሳብ፤ እሷ የሱን የተለየ ሃሳብ ያደንቃሉ፤ ቢያንስ ቢያንስ በሃሳብ ይግባባሉ፤ በማይግባቡት ጊዜም በእርጋታ ተነጋግረው የሚያስማማ ሃሳብ የመፍጠር ፍላጎቱ አላቸው ማለት ነው። ያኔ ደስተኛ የቤተሰብ ህይወት ለመምራት እድል ይኖራል።

“ለይሉኝታ” ብለን እውነታውን ስንክድ፤ ባልና ሚስት ሁሌም “አንድ ሃሳብ” እንዲሆኑ ስንመኝ ግን ጣጣ እናመጣለን፤ “ለምን እንደኔ ሃሳብ አልያዝሽም፤ ለምን እንደኔ ሃሳብ አልያዝክም” የሚል አላስፈላጊ ቅራኔ ይወለዳል። ያው፤ በንግዱ አለም እንደምናየው ነው። በይሉኝታ ሳቢያ ግልፅ የሽርክና ወይም የኮንትራት ውል መፈራረም ከብዷቸው፤ “እንተሳሰባለን፤ አብሮ አደግ ጓደኛሞች ነን፤ ዘመድ አዝማድ ነን” በሚል ስሜት የሚጀመሩ ቢዝነሶች፤ በከፍተኛ ኪሳራና በእድሜ ልክ ጥላቻ ይጠናቀቃሉ።

በሰዎች መካከል አለመግባባት እንደሚፈጠርኮ ያለጥርጥር እናውቃለን። ግን አለመግባባቶችን የምንፈታበት፤ ካልሆነም የምንዳኝበት የስራ ወይም የቢዝነስ ውል አንፈራረምም - ውል ለመፈራረም ማሰብ ጓደኝነትን የሚያበላሽ ስለሚመስለን በይሉኝታ እናልፈዋለን። በዚያው ልክ በጋብቻ ውስጥ አለመግባባትና የፍቺ ጥያቄ ሊፈጠር እንደሚችል አሳምረን እናውቃለን። ነገር ግን ልናስበው አንፈልግም።

አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያግዝ፤ ካልተቻለም አላስፈላጊ ጣጣዎችንንና መዘዞችን በሚያስወግድ መንገድ እልባት ላይ ለመድረስ የሚረዳ ኮንትራት መፈራረም አይሻልም? ኮንትራት እንፈራረም ብሎ መጠየቅም፤ በፍቅር ላይ ታላቅ ክህደት እንደመፈፀም ይቆጠርብናል ብለን እንፈራለን - በይሉኝታ ታስረን። አሳዛኙ ነገር ምን መሰላችሁ? ከ”ይሉኝታ” የምናተርፈው ነገር ቢኖር፤ አላስፈላጊ ጣጣዎችን ነው።

 

 

Read 2889 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 10:31