Tuesday, 01 January 2019 00:00

‹‹ውሃ ወደ ወሰዱት ይሄዳል››

Written by  ነጋሲ
Rate this item
(0 votes)

‹‹ማይ ኀበ ወሰድዎ የሐውር›› ይላሉ የቅኔ ተማሪዎች፡፡ (ውሃ ወደ ወሰዱት ይሄዳል ማለታቸው ነው፡፡) አንድ ባለ መስኖ ውሃውን ወደፈለገው አቅጣጫ እያዞረ አትክልቱን ያጠጣበታል፡፡ ውሀው ወደ ምሥራቅ እንዲፈስለት ከፈለገ፣ በምሥራቅ በኩል አጎድጉዶ ይቆፍርለታል፡፡ ወደ ምዕራብ እንዲፈስለት ከፈለገ እንዲሁ በምዕራብ በኩል ይቆፍራል፡፡ ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ እንዲዞርለት ከፈለገም፣ የምዕራቡን ቦይ ዘግቶ በምሥራቅ በኩል ይቆፍርለታል፡፡  
በሳይንስ የሰውነታችን 75 ከመቶው ውሃ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አውሮፓውያን ሳይንሱን በማግኘት ይበልጡናል፡፡  እኛ ደግሞ በተግባር ሆነን በመገኘት እንበልጣቸዋለን፡፡ ውሃ በአትክልተኛው ወደ አራቱ አቅጣጫዎች እንደሚፈስ፣ እኛም ጥቅመኞች ወደ ፈለጉት አቅጣጫ እንደ ውሀ እንጎርፋለንና። ውሀ መሬቱን እየደረመሰ ግንዱና ድንጋዩን እያተራመሰ ይወርዳል። በፊቱ ያለውን ማሳ እንዴት እንደሚያወድመው ግን አይገነዘብም። ውሀ አያስብምና፡፡ እኛም አሁን በምንናገረውና በምናደርገው፣ ለነገው ትውልድ እንዴት ያለ የዕዳ ክምር እየተውንላቸው እንደሆነ መገንዘብ አቅቶናል፡፡ 75 ከመቶ የሰውነታችን ክፍል ውሀ ነውና፡፡
ግን ውሀ አንድ ነገር ማድረግ አይችልም፡፡ ወደ ላይ አይፈስም፡፡ እኛ እንደ ውሀ ወደ ላይ መሄድ አንችልም። አንድም ወደ ላይ ከሄድን ትዕቢት ስለሚመስለን፣ በሥልጣኔ ወደ ላይ አንሄድም፡፡ በዕውቀት ወደ ላይ አንሄድም፡፡ በፍቅር ወደ ላይ አንሄድም፡፡ የቁልቁለት መንገድ ግን እንችልበታለን፡፡ ልክ እንደ ውሀ፡፡ ፊት ለፊታችን ገደል ካለ ፏፏቴ ሠርተን እንወርዳለን፤ እንደ ውሀ፡፡ ስለዚህ እንደ ተፈጥሮአችን በመሆን አውሮፓውያንን እንበልጣቸዋለን፡፡ እነሱ ከውሀ ተፈጠሩ እንጂ እንደ እኛ የውሀ ፀባይ የላቸውም። ጥሩ ነው ብለው ለቆሙበት ዓላማ ዐለቶች ይሆናሉ። አካሄዳቸው ሁሉ የውሀ ተቃራኒ ነው፡፡ ስለዚህ ተፈጥሮአቸውን ስተዋል፡፡ ውሀ ወደ ላይ አይሄድም። እነሱ ግን ወደ ላይ ይሄዳሉ፡፡ በኢኮኖሚ ወደ ላይ ይሄዳሉ፡፡ በዕውቀት ወደ ላይ ይምዘገዘጋሉ። በፈጠራ ዓለማትን ይዳስሳሉ፡፡ ለእኛም ‹‹ዛሬስ ጉድ ነው የማይሰማ የለም›› የሚለውን ቃለ በረከት ያካፍሉናል። ነገር ግን ሁሉም ጎደሎ ነው፤ የዚህ ዓለም ነገር። አውሮፓውያንም ሰው መሆናቸው አይቀርምና፣ እንደኛ በሁለት ምክንያቶች ቁልቁለት ይወርዳሉ። በሞት ቁልቁለት ይወርዳሉ፤ እንደ እኛ፡፡ በጽድቅ ቁልቁለት ይወርዳሉ፤ እንደ እኛ፡፡   
በስነ ምግብ ተመራማሪዎች መሠረት፤ ወተት በብዛት ጠጥቶ ያደገ ቀጭን ግን ደግሞ በጣም ጠንካራ ይሆናል፡፡ ሥጋ በብዛት የሚበላ ደግሞ የሥጋ ስብስብ ይበዛበታል፡፡ አእምሮም እንዲሁ ነው፡፡  ጠማማ ሐሳብ የተጋተ  አእምሮ ጠማማ ይሆናል፡፡ ‹‹ምሰለ ጠዋይ ትጠዊ›› ነውና ነገሩ፡፡  ቀናነት የተመገበ አእምሮ ቀና አመለካከት ይኖረዋል፡፡ ‹‹ምስለ ኅሩይ ኅሩየ ትከውን›› እንዲል መዝሙረ ዳዊት፡፡ ጠማማነት ሳይቀድም ጥሩ ሐሳብ ይግባ በአእምሮ፡፡ እየተቆላ የሚበቅል ጥሬ የለም፡፡ ውሀ እየጠጣ የሚያር ተክል የለም፡፡ ለማብቀል መሬትና ውሀ ያስፈልጋሉ፡፡ ለማሳረር እሳት ያስፈልጋል፡፡ ህዝብ እንዲያርለት የፈለገ በየቀኑ እሳት ያቀብላል፡፡ ሌላኛው ማገዶ በላዩ ላይ ይጨምራል፡፡ ህዝብ እንዲለመልምለት የፈለገ ውሀ ያቀብላል፡፡ ገጸ ዜና ሆይ፤እሳቱን አስቀርተህ ውሀውን አሳልፍ፡፡ እኛም የለመለመ መስክ እናያለን፡፡
የባህል ግሽበት
ባለፈው የገጸ ዜና እትማችን፤ ስለ ዋጋ ግሽበት ጭራቅነት አይተን ነበር፡፡ በአንድ አገር ውስጥ የተሻለና ዘመኑን የሚዋጅ የኢኮኖሚ አስተሳሰብ መገንባት ለድሀ ምግብን፣ ለነጋዴ ሰላምን ይሰጣል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ባለመኖሩ ግን ድሀ ምግብን፣ ነጋዴም ሰላምን አጥተው፣ ሁሉም በሌሊቱ ጨለማ ሌላ የጨለማ ብርድ ልብስ ደርበው ሲገለባበጡ ያድራሉ፡፡ የሰው ልጅ ጥጋብ ብቻ አይደለም ራሱን እንዳይገዛ እንቅፋት የሚሆነው፡፡ ሰው ሲያጣ፤ በኑሮ ቀንበር ሲማቅቅ ራሱን መግዛት ያቅተዋል። እንኳን ሰው የሠራውን ሕግ፣ መለኮታዊ ሕግንም ለመሻር ወደ ኋላ አይልም፡፡ ‹‹እምነ ረኃብ ይኄይስ ኲናት›› የሚለው ብሂለ ሐዋርያት ለዚህ ምስክር ነው፡፡ ጉልበተኛ ነኝ ባይ ከእሱ የበረታ እስኪመጣ ደካማውን ይዘርፋል፡፡ ደካማው ከሱ የባሰ ደካማውን ይዘርፋል። በመጨረሻ ለመከላከል ይቅርና ለመጮህ እንኳ አንደበት የሌለው ምስኪን የዘረፋው ሰለባ ይሆናል፡፡ የዋጋ ግሽበት ይዞት የሚመጣው ችግር እንዲሁ በሆድ ብቻ የሚገደብም አይደለም። ከአንድ ሀገር ህልውና ጋር ቀጥተኛ  ግንኙነት ያለው ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሀኪም ለታካሚው ደምህ 120/150፤ ሙቀትህ ደግሞ 50 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ነው ብሎ ቢነግረው፣ ምን እንደሚሰማው ታውቃላችሁ? በሞት አፋፍ ላይ እንደሆነ እየታየው ድንግጥ ድንግጥ ማለቱ አይቀርም፡፡ ለአንድ ሰው እስከዚህ ድረስ “መልአከ ሞት” ነው የዋጋ ግሽበት። ሌላም ጣጣ አለው፡፡ የዋጋ ግሽበት ዛሬ በልተው ነገ ለመክፈል የሚፈልጉ ተጠቃሚዎችን ይፈጥራል፡፡ ምክንያቱም የዛሬው አሥር ብር፣ ከነገው አሥር ብር እንደሚሻል ስለሚያውቁ፡፡ ስለዚህ ነው የዋጋ ግሽበት የአንድ አገር ቁጥር አንድ ጠላት ነው የሚባለው። እኛ ግን ጠላት የምንለውን በቃላችን መዝለፍ፣ በሥራችን መደገፍ ልማዳችን ሆኗል፡፡ ለዚህ ነው ስንፍና፣ ዝብርቅርቅ የሆነ ምጣኔ ሀብታዊ ሥርዓት፣ ሙስና፣ ድህነትና ሌሎች ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጠንቆች  በጉያችን ታቅፈን፣ እነሱን የሚያበረታና ጉልበት የሚሆናቸው ሌላ ጠላት ለመፈብረክ የምንኳትነው፡፡ ምስኪኖች! አሁን እየገጠመን ያለው ማኅበራዊ ቀውስ የገጠማቸው አገሮች (ሩዋንዳ)፣ ከመፍትሔ ማማ ላይ ሆነው፣ በንስር አይን ሲመለከቱን፣ በገደል አፋፍ ሆነው ኳስ የሚጫወቱ እምቡቃቅላ ህጻናት እንመስላቸዋልን፡፡ ‹‹አይ ምስኪኖች! ተያይዘው ገደል ሊገቡ ነው” እያሉም ያዝኑልናል፡፡  
በእርግጥ በአሁኑ ዘመን አገሪቱ በዋጋ ግሽበት ብቻ አይደለም እየተመታች ያለችው፡፡ በባህል ግሽበትም ጭምር እንጂ፡፡ ተመለስ ባይ የሌለው የዋጋ ግሽበት ህዝቧን እየበላ እንዳለ ሁሉ፣ መረን አልባ የሆነ የባህል ግሽበትም እየተፈታተናት ይገኛል፡፡ የዋጋ ግሽበት በድሀው አናት ላይ፣ የባህል ግሽበት ደግሞ  በኢትዮጵያ አናት ላይ ሜዳ ሠርተው ይጨፍራሉ፡፡ ተስፋ መቁረጥ፤ ዘረኝነት፣ ጥላቻ፣ ጥርጥር፣ አለመተማመን ደግሞ ዙርያቸውን ከብበው ያጨበጭባሉ፡፡ ሰይጣንም ተጨማሪ እጆችን ከእኛ ተበድሮ ለእኛ ያጨበጭባል፡፡ ለዚህ ሁሉ ውድቀት የሁሉም አጋንንት እጆች ተሰብስበው ቢያጨበጭቡ፣ ጭብጨባው አይደምቅም ብሎ ሰግቷልና፡፡ መላእክት ግን ክለባቸው የተሸነፈባቸው የኳስ ደጋፊዎች ጾማቸውን እንደሚያድሩ፣ እነሱም አክሊላቸውን ከራሳቸው አውርደው ተፈጥሮአቸው ያልሆነውን እንቅልፍ ይተኛሉ፡፡ የዘረኝነት ድምጽ ሰልችቷቸዋልና፡፡
ዕውቀትና ንግድ
እኔ የምላችሁ ንግድ ማለት ምን ማለት ነው? ንግድ የዕቃ ልውውጥን ያመለክታል፤ በዐይነ ስጋ ብቻ ሲመለከቱት፡፡ ውጫዊው ዐይንና ውስጣዊው ዐይነ ህሊና አዋህደው ሲያስተውሉት ግን ትልቅ የሕይወት ምሥጢር ይዟል በውስጡ፡፡ የሰው ጎዶሎነትን፡፡ የሰው ልጅ በሁሉም ነገር ጎዶሎ ነው፡፡ ይህም ፍጡርነቱን ያሳያል፡፡ በሁሉም ዘርፍ የፍጹምነት ጫፍ ንክች የማድረግ ዐቅም የለውም፤ የሰው ልጅ፡፡ በበላዩ ያለውን ካለማየት የተነሳ ግን  ሁሉም እኔ፤ ሁሉም በእኔ፤ ሁሉም ለእኔ እያለ ሲሸልልና ሲመካ ይደመጣል፡፡ ይህ ሁሉ ትምክህት፣ የውሱንነቱና የደካማነቱ ውጤት ነው። ለምሳሌ ሰማይ ላይኛውን የዘንዶ መንጋጋ ቢሆን፤ ምድር ታችኛውን የዘንዶ መንጋጋ ብትሆን፤ የሰው ልጅ ሁሉ በዘንዶ አፍ ውስጥ ሆና ወዲያና ወዲህ የምትራወጥ አይጥ ይመስል ነበር፡፡ ዘንዶው ምራቁን ለመዋጥ መንጋጋዎቹን ቢገጥም፣ የሰው ልጅ እየሸለለ ወደ ዘንዶ ሆድ ይዋጣል፡፡ ሰው ጎደሎ ነው፡፡ ንግድም የጎዶለነቱን ምሥጢር አምቆ ይዟል፤ በምጣኔ ሀብት ፍልስፍና መሠረት፡፡
 አንድ ሰው የሚለብሰውን ልብስ በራሱ መሸመን አይችልም፡፡ የሚመገበውን ምግብ በራሱ ብቻ ማምረት አይችልም፡፡ የሚነዳውን መኪና በራሱ መሥራት አይችልም፡፡ ከፍ ሲል አውሮፕላን ኮምፒውተርና ሌሎቹም የቤት ቁሰቁሶች እንዲኖሩት ይፈልጋል እንጂ እነሱን ሁሉ በራሱ የማምረት ዐቅም የለውም። አውሮፕላን ለመሥራት ስንት ዐመት የሚፈጅበት ይመስላችኋል? ሲታመም ለመፈወስ መድኃኒት ማምረት ይፈልጋል፡፡ ይህንን ለመሥራት እንኳን ይህች የጽላሎት አምሳል ያላት ዕድሜን ይዞ፣ ማቱሳላ ከእነ ዕድሜው በዚህ ዘመን እንደገና ቢፈጠር ያሉበትን የኑሮ ቀዳዳዎች ለመሸፈን ዕድሜ ያንሰዋል፡፡ ንግድም ይህን የሕይወት ምሥጢር ያስረዳል፡፡ እያንዳንዱን ቁሳቁስ ዝም ብለን ብናስተውለው የሰው ዕውቀት ፈሶበታል። ዥንጉርጉር ልብስ የለበሳችሁ ሰዎች፤ ልብሳችሁን እስኪ አስተውላችሁ ተመልከቱት፡፡ እንዴት ያለ ንድፍ አለው? ንድፉን ለመሥራት ቀለም ያስፈልጋል? ቀለሙን ለመሥራት አበባ ወይም ሌላ ነገር ይጠይቃል? ቁርኝቱ ይቀጥላል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ እናንሳ፡፡ በአገር ውስጥ የሚካሄድ ንግድ አገራዊ ሀብትን ያሳድጋል? ሰው ይገምታል እንጂ አያውቅም፡፡ ግን በምጣኔ ሀብት መሠረት፤ ነገሩ እንዲህ አይደለም፡፡ ምሥጢረ ንግድን ለመረዳት ይህንን ምሳሌ እንካችሁ፡፡ አንዲት እናት ከእነ ልጆችዋ በአንድ ቤት ውስጥ ትኖራለች፡፡ ይህች እናት በመሶቧ አንድ እንጀራ ብቻ አላት፡፡ ለሁለቱም ልጆቿ ግማሽ ግማሽ እንጀራ ትሰጣቸዋለች፡፡ ግማሽ የሰጠቸውን ኩርማን ልትጨምርለት ትፈልጋለች፡፡ ነገር ግን ግማሽ ከሰጠችው ልጇ ለመቀነስ ትገዳደለች። ምክንያቱም ያላት እንጀራ አንድ ብቻ ነውና፡፡ በአገር ውስጥ ብቻ የሚደረግ ንግድም ምሥጢሩ እንዲህ ነው። አፋር የተመረተው ጨው አዲስ አበባ ይሸጣል። ጎጃም የተመረተው ጤፍ ድሬዳዋ ይሸጣል፡፡ ጅማ የተመረተው ቡና ደሴ ይሸጣል፡፡ ሑመራ የተመረተው ሰሊጥ ሀረር ይሸጣል፡፡ የትም የተመረተ በለጬ የትም ይሸጣል፡፡ ግን ለአገርየው አዲስ ነገር ጠብ እንዳላለ ኢኮኖሚክስ ያረጋግጣል፡፡ አዲስ ነገር ካልመጣ ደግሞ ሀብት አላደገም ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው በቀኝ ኪሱ የነበረውን ብር ወደ ግራ ኪሱ ቢያሳልፈው፣ ሀብቴ ጨመረ ብሎ መናገር አይችልም፡፡ ልክ እንዲዚሁ ነው በአገር ውስጥ የተገደበ የንግድ ሀብትነት፡፡ ሀብት የሚያድገው በዕውቀት ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጆች ዕውቀትን ተጠቅመው ምንም ያልነበረ አዲስ ነገር ይፈጥራሉ፡፡ ይፈጥራሉ ሲባል እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ አይደለም፡፡ ከአሁን በፊት ተገናኝተው ተዋህደው የማያውቁ ንጥረ ነገሮች ያዋህዳሉ፤ ያቀነባብራሉ፤ ይቀምማሉ ለማለት ነው፡፡ ያኔ ሀብት አደገ ይባላል። በተለይ ደግሞ ሰዎች ዕውቀታቸውን ተጠቅመው በአገር ውስጥ ያመረቱትን ወደ ውጭ መሸጥ ሲጀምሩ፣ ያኔ ሀብት ማደግ ጀመረ ይባላል፡፡ በዕውቀት ደካማ የሆነ ምጣኔ ሀብት፤ ዕውቀት የሌለው ነጋዴና ገንዘብ የሌለው ምሁር እንደ አሸን ይፈላበታል፡፡ ገንዘብ የሌለው ምሁር፣ በአእምሮው ያለው የካበተ ልምድ አንድም ሳይፈይድለት ወደ መቃብር መውረዱን ይጠባበቃል፡፡ ሞት ለማይቀር ብሎ ህሊናው ለማይወደው ነገር ተገዢ እንዲሆን ኑሮ ታስገድደዋለች፡፡
ታዳጊ ወጣቶችም የምሁሩን ድህነትና ሞራል ዝቅጠት እየተመለከቱ፣ ዕውቀት የማይፈይድ መሆኑን ያስባሉ፡፡ አንድም አእምሮአቸውን ከዕውቀት ያሸሻሉ። ዕውቀት የሌለው ነጋዴም፤ የያዘው ሀብት መብራት ሲጠፋ እንደሚጠፋ ሳይገነዘብ፣ ቢዝነስ ነው እንጂ ትምህርት ምን ዋጋ አለው እያለ ንጹሕ አእምሮን ይበክላል፡፡ በመጨረሻ ምሁሩ ድህነቱን ለመርሳት፣ ነጋዴው ሀብቱን ለማሳየት ሁለቱም አንድ ቦታ ይገናኛሉ፡፡ ጠንካራ ምጣኔ ሃብት፤ ዕውቀት ያለው ምሁርና ገንዘብ ያለው ነጋዴ ተጣምረው እንዲሠሩ ምቹ መንገድ አለው፡፡ ንግድ ነውና ነጋዴው በገንዘቡ ዕውቀት ይገዛል፡፡ ዕውቀት ገዝቶ ድንገት ሽው በሚል ነፋስ የማይወድቅ ህንጻ ለመገንባት ዐቅም ይኖረዋል፡፡ ካለህበት ተነስ ያላለው ምጣኔ ሀብት ደግሞ በምሁር መቃብር ላይ ለነጋዴ ህንጻ ይገነባለታል፡፡ ሀብት የሚያድገው የተማረ ገንዘብ ሲኖረው ወይም ሀብታም ነጋዴው ዕውቀት ሲኖረው ብቻ ነው፡፡ ካልሆነ በዚህ ዐለም አዲስ ነገር የለም የሚለው ብሂል፣ በዚች አገር አዲስ ነገር እንጂ አዲስ ሀብት ሊኖር አይችልም፡፡ አራት ነጥብ፡፡ ስለዚህ ዕድገት- በዕውቀት!

Read 973 times