Saturday, 22 December 2018 13:35

የፍቅር ክፈፎች

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(11 votes)


     ባለቤትዋ መምጫው ስለደረሰ ቤትዋን በተለመደው ዐይነት ሁኔታ እንዲቆይ አልፈለገችም። ስለዚህ ሠራተኛ ቀጥራ ቀለም አስቀብታ፣ ግቢውን አስውባ፣ በእንግዳ ሰው ዐይን ለማየት ሞከረች። አንዳች ነገር ቅር አሰኛት። አዲሱ ቴሌቪዥን፣ የመጽሐፍት መደርደሪያው፣ ሌሎችም የሳሎን ዕቃዎች ብዙ አያስጠሉም፡፡ ሶፋዎቹ ግን ልብዋን አላሳረፉትም፡፡ ቤቱ ቀለም ከተቀባ በኋላ፣ ሶፋው አልጣጣም አላትና እረፍት አጣች፡፡
ሳሮን- ድሮም እረፍት የላትም፡፡ ለልብዋ ያልተስማማት ነገር ካለ፣ ሳንቲም ምኗም አይደለም። ከባለቤትዋ ጋር የሚጣሉት በዚህ ነው፡፡ ገንዘብ አትበትኚ ይላታል፡፡ አሁን አሜሪካ የሄደችው እርሷ ብትሆን ኖሮ፣ የማታመጣው ዕቃ፣ የማታመጣው የልብስ ዓይነት አልነበረም፡፡ ግን ምን ያደርጋል? ባለቤትዋ ሦስትና አራቴ ሄዶ ያመጣው ልብስም ሆነ ዕቃ፣ እሷ አንዴ ብትሄድ የምታመጣውን አያህልም።
“ቆይ አንዴ ብቻ ልሂድ አሳይሃለሁ!” ትለዋለች፡፡
“ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት ይል ነበር አባቴ፣ አንቺ ያየሺው ሁሉ ያምርሻል፤ ሁሉን ነገር ባንድ ጀንበር ለማሟላት ትፈልጊያለሽ፡፡ ሁሉን ባንዴ የሚያሟላው መድሃኒዓለም ብቻ ነው፡፡” ይላታል፡፡
አይዋጥላትም፡፡ ውድ እቃ፣ ውድ ቤት፣ ውድ ቤት፣ ውድ መኪና፣ ውድ ኑሮ--ትወዳለች፡፡
“ያንቺ ዓይነቷ ሴት ዝም ብላ ትበትናለች!” ይልና የአብርሃም ሊንከንን ሚስት ይጠቅስላታል፡፡
“እሰይ ደግ አረገች…ሁለቴ አይኖር!” ብላ ትስቃለች። ሳቋ ቶሎ አይቋጭም፡፡ ሰውነቷ ድንቡሽቡሽ  ያለ፣ ጉንጫም ናት፡፡ መንበሽበሽ የምትወድድ፡፡
ሶፋውን መቀየር አሰበች፡፡ ምናልባት እልፍነህ ደስ ላይለው ይችላል፡፡ ይነጫነጫል፡፡ ግን ዐይኑ ያማረ ነገር ይይ፤ አለችና- ሶፋውን ልትቀይር አሰበች። ከሆነ አይቀር ውድ ሶፋ፣ ዘመኑን የሚመጥን ዕቃ - መግዛት አለባት። ለአቅመ ሔዋን ካልደረሰች ልጇ ጋር መከረች። ልጇ ደስታውን አልቻለችም፡፡ ተስማሙና ገበያ ወጡ፡፡
እቃ መጫኛ መኪናዋን ይዛ ወጣች፡፡ ፒያሳ - መርካቶ - ቦሌ - ሃያ ሁለት - ብዙ ቦታ ሄዳ መረጠች። የወደደቻቸውን እንደገና አወዳደረች፤ ልጇኝ ጠየቀች፡፡ ሌሎችን ሰዎች አማከረች፡፡
አንዳንዶቹ፤ “የሰው የቀለም ምርጫ ይለያያል” አሏት፡፡
ሌሎቹ፤ “ብዙ ሰዎች ይወዱታል” ብለው የተስማሙበትን አሳዩዋት፡፡ አንዱን መርጣ ወደ ቤት ጫነች፡፡ መጋረጃም መጨመር አማራት፡፡ ትንሽ የምታውቀው የቀለም እውቀት ትዝ አላት። ሰማያዊ - ለመንፈሳዊ መነቃቃት፣ ብርቱካንማ - ለሃይል፣ ጠሊቅ ብርቱካን- ኩራት፣ ሙላት፣ ቢጫ - ዕውቀት እያለች-- በብርሃን ጨረሮች ሃሳብ ጥቂት ሄዳ፣ ልቧ የወደደውን አደረገች፡፡ ባለቤትዋ ሳይወደው እንደማይቀር ገምታለች፡፡ በፍቅረኝነት ዘመናቸው ስትለብሳቸው የሚያደንቅላትን ቀለሞች አስታወሰችና ፈገግ አለች። ቀይ ቀለም አይወድድም። አንድ ቀን ምሳ ጋብዟት፣ ቀይ ቀሚስ ለብሳ የወጣች ቀን፣ ዐይኑ ቀሚስዋን መስሎ ስታየው፣ የደነገጠችውን ድንጋጤ አትረሳውም፡፡
“ምን ሆንክ?”
“አስጠላሽኝ!”
“ለምን? ምን ሆኜ?”
“ቀይ ለብሰሽ ትመጫለሽ! የሆነ ኮሚኒስታዊ በሽታ አለብሽ?”
ከት ብላ ሳቀችበት፡፡ ይበልጥ ተናደደ፡፡
ብዙም አላወሩ፡፡ ሳቅ የለ፤ ጨዋታ የለ፡፡ በኩርፊያ ተለያዩ፡፡
ሌላ ቀን ሮዝ ሸሚዝ ለብሳ ስትመጣ፣ እንዴት እንደሳማት አትረሳውም፡፡
ያኔ- ያኔ- ስሜቱን መደበቅ አይችልም ነበር። ምናልባት ለፖለቲካው ትዝታ ቅርብ ስለነበረ ይሆን? ኢሕአፓም ደርግም ቀይ ስለሚወዱ፣ ቀይን ይጠላል። እርሱ ሃይማኖተኛ ነው፡፡ ቤተ ክህነት አድጐ በኋላ የመንግሥት ትምህርት ቤት ጐበዝ ተማሪ ሆኗል፡፡ ፖለቲካ ግን አይወድድም። ቀዩ ባንዲራ፣ ወንድሙን በልቶበታል፡፡ አካሉን ነጥቆታል፡፡
በፍጥነት ወደ ቤት ነዳች፡፡
“እንዴት ነው ሜሮን--ጥሩ አለመረጥንም?!”
“አሪፍ ነው እማዬ”
“አባትሽ የሚወድድው ይመስልሻል?”
“የእርሱ ነገር አይታወቅም፤ ግን የብዙ ሰው ምርጫ ነው፡፡ በዚያ ላይ ቤቱ ከተቀባው ቀለም ጋር ማች ያደርጋል”
“እንግዲህ ባወጣው ይውጣው፤ Surprise ላደርገው ፈልጌ ነው፡፡ አሜሪካ ሄዶ ሲመጣ ቤቱ እንዳያስጠላው፡፡ እኛም ፊታችን ቢቀየር ኖሮ፣ ቀይረን እንጠብቀው ነበር፡፡”
ሳቀች፡፡ የመጀመሪያ ልጇ ስለሆነች እንደ ጓደኛም፣ እንደ እህትም ታያታለች፡፡
 “ያ- ትንሹ ጐረምሳ ከደበረው ለንቦጩን ይጥላል” አለቻት፡፡
 ተሳሳቁ፡፡
ሁለተኛ ልጇ ወንድ ነው፡፡ ያልተመቸው ነገር ካለ፣ ፊቱን አርዝሞ፣ የታች ከንፈሩን ያንጠለጥለዋል።
“እማዬ አታስቂኝ--” አለቻት ሜሮን፡፡
“የወንድምሽን ፀባይ አጣሽው እንዴ! - የአባቱ ቢጤ!”
“ይወድደዋል ባክሽ--”
“እኔ ባሌ ከወደደው የራሱ ጉዳይ! እርሱ ወደፊት ከሚስቱ ጋር ይምረጥ፤ የኔ ዋናዬ ባሌ ነው፡፡ ሁሉም ወደየቤቱ ይሄዳል፣ ቀሪ ሀብቴ እርሱ ነው፡፡”
“እኛስ?”
“አንቺም ወደ ባልሽ ትሄዳለሽ፣ ወንድምሽም ወደ ሚስቱ! መሄጃ የሌለን እኔና እልፍነህ ነን፡፡”
“ገና ገና የትናየት!”
“መስሎሻል! ጊዜው እንደ ነፋስ በርሮ፣ አሁን ይደርሳል”
“ሲ-ያ-ስ-ፈ-ራ!”
“ም---ኑ?”
“መለያየቱ ነዋ!”
“አያስፈራም፤ ደስ ይላል ትደርሷበታለሽ ጊዜው ሲደርስ ከዚህ ቤት እስክትወጪ ይጨንቅሻል፡፡ ፍቅር እናትና አባትን ያስረሳል፡፡ ያንቺ አባት እኔን ያደረገኝን ብታውቂ፣ ለዚያውም የኔ እናት ወርቅ ነበረች፡፡ እርሷን እንኳ አስረሳኝ፡፡”
እየተሳሳቁ ቤት ደረሱ፡፡
ዘበኛው በሩን ከፈተና ገቡ፡፡
“እትዬ! የሚያምር ሶፋ ገዝተዋል፡፡”
“ወደድከው?”
“አዎ! በጣም!”
“አመሰግናለሁ!” አለችና ወደ ልጇ ዞረች፡፡
“የወንዶች ምርጫ ተመሳሳይ ነው፡፡ እልፍነህም ሊወደው ይችላል፡፡ ያው በቀለም ምርጫ እኛ እንደምንበልጣቸው የታወቀ ነው፡፡”
ተሳሳቁ፡፡
እልፍነህን ከአየር ማረፊያ ሄዳ ከተቀበለችው በኋላም የምታስበው፣ ስለ ቤቱ ቀለምና ስለ ሶፋው የሚሰጠውን አስተያየት ነበር፡፡ ስለ አሜሪካ፣ እዚያ ስላገኛቸው ሰዎች፣ ስለሄደበት ጉዳይ ሲያጫውታት ሁሉ-- እርሷ ልቧ እቤት ውስጥ ስለሚገጥመውና ስለሚፈጠርበት ስሜት ነበር፡፡
የቀድሞውን ሶፋ አብረው ሲገዙት በጭቅጭቅ ነበር። እርሱ የወደደውን እርሷ አልወደደችም። ቢሆንም ግድ ነውና ገዛችው፡፡ ሰሞኑን አሮጌ ዕቃ መሸጫ ቤት እስከሸጠችው ጊዜ ድረስ ቀልቧ አይወድደውም ነበር። የሚገርመው ግን በሸጠችለት በማግሥቱ ሌላ ሰው ወድዶ ገዝቶታል፡፡ ተገርማ ባለ ሱቁን ስትጠይቀው፣ የገዛው ሰው ወንድ ነበር። ወንዶች ዐይናቸው አንድ፣ ምርጫቸው አንድ ነው የምትለውም ለዚህ ነው፡፡
ቤት ደርሳ ጥሩንባ አጮኸች፡፡ ዘበኛው ቆመጡን እንደያዘ ተወርውሮ ወጣ፡፡
“ጋሽዬ!” ዘሎ አቀፈው፡፡
“ሠላምታው ይቆይና፣ ዕቃውን አገባባ፡፡”
“አማሪካ ቆይተው ሲመጡ፣ እሳቸውን ሠላም ሳልል--”
“ግድ የለም---ይደርሳል!”
ዕቃውን አገባቡና ወደ ጓጓችው ትዕይንት ደረሱ። በሩን ከፍቶ ገብቶ፣ መጀመሪያ የተቀባውን ቀለም አየ። ከዚያም ሶፋውን፡፡ ስለ ሶፋው ሃሳብ ይሰጣል ብላ ስትጠብቅ፤ “የቀድሞው ሶፋ የት ሄደ?” አለ በከፍተኛ ድንጋጤ አይነት፡፡
“እርሱ ናፈቀህ?”
“አይደለም የት ሄደ?”
“ተሸጠኣ!”
እልፍነህ ሰከንድ አልቆየም፡፡ ወደቀ፡፡
“በስመአብ ወልድ! በስመአብ!” ብላ አብራው ስታጐነብስ፤
“ለማን ተሸጠ?”
ግራ ተጋባች፡፡ ዘበኛውን፤ “ና..ሀኪም ቤት! ሀኪም ቤት!” አለችው፡፡
“ወይኔ - ፖለቲካ ነክ ትርጉም አለው ይሆን…?” ስትል
በሰመመን፤ “…ብዙ ዶላር ውስጡ ነበረ” አላት፡፡
“ከኔ የደበቅኸው?---ያንተ የገንዘብ ፍቅር?! ገንዘብና ፍቅር!
 ጩኸቱ ቀለጠ…

Read 3460 times