Print this page
Sunday, 23 December 2018 00:00

የዶ/ር ዐቢይ መንግስትና የጸረ-ለውጥ ኃይሉ ተቃርኖ!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(23 votes)

 - “ዶ/ር ዐቢይ የተመረጠው በአሜሪካ መንግስት ጣልቃ ገብነት ነው-” - አቦይ ስብሃት
       - “ኢህአዴግ እንኳንስ ህገ መንግስት፣ ህገ ደንብ አክብሮ አያውቅም” - የአረና አመራር
       - “ኢትዮጵያ ውስጥ እየገረፉ መግዛት መቆም አለበት” - ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
       


    ሰሞኑን በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው አገራዊ ውይይት ላይ እርጅና የተጫጫናቸው የሚመስሉት  የህወሓት መስራችና ታጋይ አቦይ ስብሃት፤ “ዶ/ር ዐቢይ የተመረጠው በአሜሪካ መንግስት ጣልቃ ገብነት  ነው- በአምባሳደር ያማማቶ!” ሲሉ ሰማኋቸው፡፡ ምን ማለታቸው ነው? (ወጣት አመራር ቢተኩ እኮ-- ከአንዳንድ ስህተት ይድኑ ነበር!) እርግጠኛ ነኝ---አቦይ ድንገት አዳልጧቸው ነው ይሄን የተናገሩት፡፡  የህወሓት አመራሮች በዚህ ንግግራቸው ሳያፍሩ አይቀርም። እኛም ህወሓትም፤ ዶ/ር ዐቢይ የተመረጡት በኢህአዴግ መሆኑን ነው የምናውቀው - ያው በህዝብ ግፊት! (አምባሳደር ያማማቶ ከየት መጡ ታዲያ!?) ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፤ ሁለት ጊዜም ለኢህአዴግ ሊቀ መንበርነት የተመረጡት እኮ በህወሓትም ድምጽም ጭምር ነው፡፡ (በተለይ ሁለተኛው በሙሉ ድምጽ እኮ ነው!) በእርግጥ ኢህአዴግም የዛሬ 29 ዓመት ገደማ ደርግን ገርስሶ፣ ሥልጣን ሲይዝ፣ በአሜሪካ (እንደውም ሲአይኤ!) ጣልቃ ገብነት ነው ተብሎ ነበር። (አቦይ፤ እሱ ትዝ ብሏቸው ይሆን!?)
ሌላም ነገር ጠረጠርኩ፡፡ ምናልባት እነ “ዋሺንግተን ፖስት” እና “ዘ ኢኮኖሚስት” ሸውደዋቸው እንዳይሆን ብዬ አሰብኩ፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ በዓመት አንዴም የዘገባ ሽፋናቸውን የማታገኘው አገራችን፤ በወር አንዴ ሰፊ ሽፋን ማግኘት ችላለች። በተደጋጋሚ የለውጡን ሃይል፣ በተለይም የዶ/ር ዐቢይን---ሪፎርመርነት! የዲሞክራሲ ፋና ወጊነት! የአፍሪካ ቀንድ ተፅዕኖ ፈጣሪነት!… እያደናነቁ ሲጽፉላቸው---አቦይ ስብሃት ጥርጣሬ ሳይገባቸው አልቀረም፡፡ “ዶ/ር ዐቢይ የተመረጡት በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ነው!” ያሉት ከዚህ ተነስተው ሊሆን ይችላል፡፡ ግን እኮ የዶ/ር ዐቢይን አመራር አድንቀው የሚዘግቡት እነ ዋሺንግተን ፖስት ብቻ አይደሉም፡፡ በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዶ/ር ዐቢይንና ሪፎርማቸውን ደጋግመው ሽፋን ሰጥተውታል፡፡ ደግሞም ይገባቸዋል። ጠ/ሚኒስትሩ፤ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም እየተረፉ ነው!! (አቶ በረከት፤”የዐቢይ መንግስት ደካማ ነው!”ብለው ቢያብጠለጥሉም!!) እኔ የምለው፤ የዐቢይ መንግስት “ደካማ ነው!” ወይስ “ትዕግስተኛ”?? አቶ በረከት “ደካማ” ለሚለው ቃል፣ ፍቺ ቢሰጡት ጥሩ ነበር፡፡ እርግጥ ነው “ጠንካራ” የሚባለውን የቀድሞውን የኢህአዴግ መንግስት አሳምረን እናውቀዋለን፡፡ አደባባይ ለተቃውሞ የወጡ ዜጎችን በጥይት የሚበትን ጀብደኛ መንግስት ነው!! (ልዩነቱ እዚህ ላይ ነው!) የአሁኑ የዶ/ር ዐቢይ መንግስትስ? “ኢትዮጵያ ውስጥ እየገረፉ መግዛት መቆም አለበት” ባይ ነው፡፡ (ደካማነት ይሆን?)   
በኢህአዴግ የሦስት አስርት ዓመታት የስልጣን ዘመን፣ ከሞላ ጐደል በሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩል ድጋፍ የተቸረው መንግስት የተፈጠረው ዛሬ እኮ ነው - በዶ/ር ዐቢይ ዘመን!! ያለ ምክንያት ግን አይደለም- ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ክብር በመስጠቱ ነው። በአሁኑ ወቅት አንድም ነፍጥ አንግቦ፣መንግስትን የሚታገል የታጠቀ ሃይል የለም፡፡ (በአውሮፓም በኤርትራም!) ሁሉም መሳሪያውን ጥሎ ወደ አገር ውስጥ በመግባት፣ በመጪው ምርጫ ለመሳተፍ፣ እራሱን እያዘጋጀ ነው፡፡ (ቤተ መንግስት ገብቶ ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር የሰለጠነ ድርድርም ጀምሯል!) ይሄስ ከደካማነት ያስቆጥር ይሆን? (ወይስ “ተንበርካኪነት” ነው!)
እንደመታደል ሆኖ…ዛሬ ኢትዮጵያ በአሸባሪነት የፈረጀቻቸው የፖለቲካ ድርጅቶች የሏትም! (አንድም እንኳን!) ለዓመታት በወህኒ ቤት ታጉረው የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞች…ከእስር ተፈተዋል፡፡ ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያደረገው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ቡድን (CPJ) በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት፤ ኢትዮጵያን “አንድም ጋዜጠኛ በእስር ቤት የሌላት አገር” - ብሏታል፡፡ ልብ አድርጉ! ላለፉት 13 ዓመታት፣ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር ከዓለማችን ቀዳሚ አገራት ተጠቃሽ ነበረች፡፡ (በየዓመቱ Top 10 ውስጥ አንጠፋም ነበር!) በሰብአዊ መብት አያያዝም አስደማሚ ለውጥ መታየቱን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት እየመሰከሩ ነው። (የ27 ዓመት የሰብአዊ መብት ጥሰት ታሪካችን ግን ይዘገንናል!)
አንዳንድ ወገኖች ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ በብርሃን ፍጥነት ያስመዘገቧቸው ለውጦች የማይታመን ቢሆንባቸው አያስገርምም፡፡ አንዳንዱ እኮ እንኳን ለዓለም ለኛም አይታመንም፡፡ የቀድሞው ኢህአዴግ፣ ለ27 ዓመታት የፈጸመውን ጥፋትና ብልሹ አሰራር እኮ ነው፣ አዲሱ መንግስት በ7 ወራት ውስጥ ለማረምና ለማሻሻል የታተረው፡፡ መከላከያና የደህንነት ተቋሙ ከፓርቲ ወገንተኝነት ጸድተው፣ ለህገ መንግስቱ ብቻ እንዲቆሙ---የሪፎርም ሥራ መሰራቱን ሰምተናል። ከኤርትራ ጋር የተፈጠረው ሰላምና ዕርቅ፣ፍቅርና መደመር እኛን ብቻ ሳይሆን ዓለምን አስደምሟል፡፡ ይሄን ተከትሎም ኤርትራ ለረዥም ዓመታት ተጥሎባት የነበረው ማዕቀብ፣ በዶ/ር ዐቢይ ጥረት ተነስቶላታል። አሁን ከጅቡቲና ከሶማሌ ጋር ሰላም አውርዳለች- ኤርትራ! ፕሬዚዳንት ኢሳያስም ከሰሞኑ ጅቡቲንና ሶማሌን ሲጐበኙ አይተናል፡፡ አያችሁልኝ… የዶ/ር ዐቢይ የለውጥ እርምጃ፤ በአንድ ጊዜ ለ4 አገራት በጎ ውጤት አምጥቷል - ለኢትዮጵያ፣ ለኤርትራ፣ ለሶማሌና ለጅቡቲ (በአንድ ድንጋይ 4 ወፍ በሉት!)
ይሄን ሁሉ የምዘረዝረው ለናንተ አይደለም፡፡ ዓይኑን ለጨፈነውና ጆሮውን ለደፈነው የጸረ-ለውጥ ሃይሉ ነው፡፡ የዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግስት በአገሪቱ ላይ ስላመጣቸው ለውጦች ሲጠየቁ፤ “የለውጡ ባለቤት እኛ ነን” ይላሉ፡፡ (የየትኛው ለውጥ?) በሌላ በኩል ደግሞ “የዶ/ር ዐቢይ መንግስት ለውጥ አላመጣም፤ጸረ-ዲሞክራሲ ነው፤ ህገ መንግስቱን ይጥሳል“ ሲሉ ያብጠለጥሉታል፡፡ “ደካማ መንግስት በመሆኑ የህግ የበላይነት ማስከበር አልቻለም፤ ሰላም ደፍርሷል፡፡” በሚል ይተቹታል፡፡ አሁንም እንደገና ልጠይቅ፡፡ የዶ/ር ዐቢይ መንግስት “ደካማ” ነው ወይስ “ትዕግስተኛ”? (ሁለቱ ልዩነታቸው የትየለሌ ነው!)
በቅርቡ በከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰትና በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የቀድሞ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች (የሜቴክን ዋና ዳይሬክተር ጨምሮ) በተያዙ ወቅት፣ የትግራይ ክልላዊ መንግስት፤ “በአንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ነው” “የፖለቲካ ድራማ ነው!” ምናምን--በሚል እርምጃውን ተቃወሙት - ሚዲያ ጠርተው፡፡ (በኢህአዴግ ታሪክ እኮ ሆኖ አያውቅም!) ያኔ የፌደራል መንግስቱ የሰጠው ምላሽ በአጭር ቋንቋ፤ “መብታቸው ነው!” ነበር ያለው፡፡ (የዶ/ር ዐቢይ መንግስት!)
“በማይስማሙበት ጉዳይ በግልጽ የሚቃወሙና የመሰላቸውን የሚናገሩ የክልል መንግስታት… ያስፈልጉናል…” ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ (ይሄስ ደካማነት ነው ወይስ ህገ መንግስት መጣስ?)
ዝም ብዬ ሳስበው---የዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግስትና ጸረ-ለውጥ ሃይሉ፤ሁለት ተቃራኒ ቡድኖች ነው፡፡ እንደ ጥፋትና በጎነት፣ ፍቅርና ጥላቻ፣ ጨለማና ብርሃን፣ ነጻነትና አፈና፣ ድህነትና ብልጽግና፣ ሥልጣኔና ኋላቀርነት፣ ዲሞክራትና አምባገነን፣---- ወዘተ፡፡ የዚህን ያህል ነው ርቀታቸው፡፡ ስለዚህ ቢያወግዙት፣ ቢረግሙት፣ቢያብጠለጥሉት፣ቢያሴሩበት----አይገርምም! (ቢጤታቸው አይደለማ!)
 እናላችሁ… የዶ/ር ዐቢይ መንግስት ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ የተመዘገቡ አስደማሚ ለውጦች፣ በመቀሌ ለከተሙት “ጡረተኛ ኢህአዴጋውያን” ላይታቸው ይችላል፡፡ ለምን ቢሉ? የዶ/ር ዐቢይ ሪፎርሞች ለአብዮታዊ ዲሞክራሲያውያኑ የሚዋጡ አይደሉም፡፡ ከምሬ ነው---እንዴት ብሎ ነው የመደመር፣ የፍቅርና የይቅርታ ፍልስፍና፣ መፈረጅ ለሚወዱት ጸረ ለውጥ ይሎች የሚገባው!? (አይገባምም!! አይታይምም!!) ዶ/ር ዐቢይ እኮ ባለፉት ወራት እነሱ ያሰሯቸውን ሲፈቱ፣ ከአገር ያሰደዱትን… ወደ አገር ቤት ሲመልሱ፣ ያወጣቸውን አፋኝ ህጐች ሲያሻሽሉ፣ ፍትህ የነጠቋቸውን  ሲያስመልሱ! ወዘተ ነው የቆዩት፡፡ መቼም የቀድሞዎቹ ገዢዎቻችን፤ ሥራዬ ብለው የዘጓቸውን ከ200 በላይ ድረ ገፆች፣ የዶ/ር ዐቢይ መንግስት በመክፈቱ ፌሽታ ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ (ተጫወትን ብለው ይቆጫሉ እንጂ!) እነ ኢሳትና ኦኤምኤን በአዲስ አበባ ቢሮ በመክፈታቸውም “ወንዳታ” አይሉም፡፡   
የዶ/ር ዐቢይን መንግስት፤ ህገ መንግስት በመጣስና በኢ-ዲሞክራሲያዊነት የሚወነጅሉት የአቦይ ስብሃት ቡድኖች፤ በዚያው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጉባኤ ላይ እውነተኛ ማንነታቸውን (ፖለቲካዊ ባህርያቸውን!) የሚያጋልጥ አሳፋሪ ተግባር ፈጽመዋል፡፡ (የማፍያ ቡድን የሚመስል!) የ“አረና” አመራር አምዶም ገብረሥላሴ በህወሓት ላይ እንቅልፍ የሚነሳ ግን ሂስ ሲሰነዝር፣ አቦይ ስብሃት አላስቻላቸውም፡፡ የለመዱትን ዘዴ ተጠቀሙ- አፈና!! እያጨበጨቡ ደጋፊዎቻቸውን አስተባበሩ - እነሱም በጭብጨባ አጀቧቸው፡፡ የአምዶምን  እርቃን የሚያስቀር የሰላ ሂስ በአየር ላይ አስቀሩት፡፡ አቶ በረከት ስምኦን ከመድረኩ ሆነው “ኧረ ይጨርስ!” ቢሉ ማን ይስማቸው!… ሃሳቡ በኋላቀር የአድማ ሴራ የታፈነበት የ“አረናው” አምዶም፤ “ይሄ እኮ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው ስብሰባ እንጂ የህወሓት ጉባኤ አይደለም!” ለማለት ብቻ ነው የቻለው፡፡ እነ አቦይ ስብሃት ከ29 ዓመት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በኋላም የራሳቸውን  መናገር እንጂ የሌላውን የማድመጥ ባህል አላደበሩም፡፡
የቀድሞው የአየር ሃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖት፤ “የ60ዎቹ ትውልድ ታግሎ ነፃ ሊያወጣ ይችላል፤ ዲሞክራሲ ሊያሰፍን ግን አይችልም!!” ያሉት ትዝ አለኝ፡፡ ይሄ ቡድን ነው እንግዲህ ስለ ህገ መንግስት ጥሰት አፉን ሞልቶ… በድፍረት የሚናገረው፡፡  አምዶም ገ/ሥላሴ… የህወሓት ቡድን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያመጣው የ“ህገመንግስት ይከበር” ጥያቄ ግራ ቢገባው፤ “…ኢህአዴግ እንኳን ህገ መንግስት፣ ህገ ደንብ አክብሮ አያውቅም፤ ባለፉት 27 ዓመታት ህገ መንግስቱ ሲፈርስ ነበር… ምርጫ ሲጭብረበር ነበር፡፡
በዳኝነት ላይ ጣልቃ ሲገባ ነበር…በጣም አምባገነኑ ኢህአዴግ ያለው ትግራይ ውስጥ ነው” በማለት  የሰላ ትችቱን ሰንዝሯል (በጭብጨባ እስኪታፈን ድረስ!)፡፡ በመጨረሻ ለጸረ-ለውጥ ሃይሉ አንድ ምክር ጣል ላድርግ፡- “እባካችሁ ከሁሉ በፊት ከራሳችሁ ጋር ታረቁ!”

Read 8670 times