Saturday, 22 December 2018 13:18

“ባቄላ ማለት ምን ማለት ነው?”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(8 votes)


    እንደምን ሰነበታችሁሳ!
ቀደም ባሉት ጊዜያት የጥንት ወዳጅ ማግኘት ደስ ይል ነበር፡፡ ማለት ክላስሜት፣ አብሮ አደግ፣ የሰፈር ልጅ ማግኘትን የመለሰ ነገር የለም፡፡ ብዙ ‘አድቬንቸር’ ይወራ ነበራ! ‘ዘ ጉድ ኦልድ ዴይስ’ የሚባሉት ጊዜያትን እያነሳን፣ ከዘመኑ ኑሮ ጫና ለጥቂት ሰዓታት እንኳን ራሳችንን ነጻ ማድረግ እንችላለና! የጥንቱን አኗኗራችን በሳቅ አጅቦ ማውራቱ የመተቻቸት ጉዳይ ሳይሆን ባለማወቅ በተሳሳትናቸው ስህተቶች፣ አውቀን በሠራናቸው ተንኮሎች ፍርስ እያልን የምንስቅበት ነበር፡፡ (አሁን በሳቅ ሳይሆን በብስጭት ፍርስ የሚያደርጉ ነገሮች እንዲህ ሊበዙ!) እና ምንም ነገር በሌላ የማይመነዘርበት ጊዜ ነበር፡፡
እናላችሁ…ዘንድሮ ግን ነገሮች ተለዋውጠዋል፡፡ ‘ዘ ጉድ ኦልድ ዴይስ’ የምንላቸው ነገሮች በሙሉ ፖለቲካዊ ቅብ እየተቀቡ ጥቂት መሳሳቅም እኮ ቸገረን! አንድ መቶ አንድ እመጫት ቃላት እየተቸነከሩ… አለ አይደል… ሳቁም ፖለቲካ፣ መኮሳተሩም ፖለቲካ እየሆነላችሁ ነው፡፡ እናላችሁ… ብዙዎቻችን ልክ ‘ትናንት’ የሚባል ነገር እንዳልነበረ ሰሌዳውን ሙልጭ አድርገን አዳዲስ ታሪክ እየጻፍን ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ከአገር ውጪ ራቅ ብሎ ከተከረመማ “ይቅርታ አላስታወስኩህም!” አይነት ወሽመጥ ብጠሳ በሽ፣ በሽ ነው፡፡
እናላችሁ… ‘አዲሱ ቦሌ’ አካባቢ ከሆነ የሦስት ብርጭቆ ሻይ ዋጋ፣ መርካቶ ምን የመሰለች ሱሪ ለመግዛት ምንም ከማይቀርበት ካፌ ሲወጣ ታገኙታላችሁ፡፡  (በማይከፈልበት መንገድ እየሄዳችሁ ሳለ ማለት ነው፡፡)
“አንተ፣ እኔ አላምንም! እንዴት ነህ?” ፈገግታችሁ እኮ በስንትና ስንት ወር ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡
ኮስተር ብሎ ከፍ ዝቅ አድርጎ ያያችኋል፡፡ አለ አይደል… ልክ ‘ሱፕ’ ውስጥ የገባች ዝምብ የሆናችሁ ይመስል! ሁለተኛ ዙር ሙከራ…
“ረሳሁህ እንዳትለኝ! ጩኒ ከላይ ሰፈር እንኳን---እንዴት እጠፋሀለሁ!” አሁንም ‘ግራ እንደገባው’ ነው፡፡ «ዮሴፍ ነኝ፣ የቆንጆዋ አልማዝ ወንድም፡፡” ይፍለቀለቃል! የምስጢሩ ቁልፍ ቃል ተገኛ! የምስጢሩ ቁልፍ ‘አልማዝ’ ነው!
“ኦ ዛትስ ኩል፡፡ አልማዝ…አስታወስኩ፡፡ ኢዝ ሺ ስቲል አራውንድ?” ይቺን ይወዳል---የድሮው ጩኒ የዛሬው ‘ትናንትን ናፋቂ!’ (ቂ…ቂ…ቂ…) እናንተን ትከሻ ለትከሻ ባያጋጭ እንኳን እጃችሁን ጨብጦ ሰላም ሳይል ስለ አልማዝ ይጠይቃል!
“ደህና ነች… ስማ ነስሩ ሻይ ቤት ሶስት፣ ሶስት ፓስቲ በልተን፣ የአንድ ብቻ ከፍለን ሽል የምንለው ትዝ አይልህም?” በሳቅ ሲንፈቀፈቅ አደናቅፎት እንዳይወድቅ እጃችሁን አንከርፍፋችሁ ትጠብቃላችሁ፡፡ እሱ ሆዬ ወይ ንቅንቅ! ትቀጥላላችሁ… “ያኔ እኮ ተበላ፣ ኮሌስትሮል ብሎ ነገር የለ፣ ነጭ የደም ሴል ቆጠራ የለ፣ ምግብ የሚመዘነው ሆድ በሞላና በጎደለ እንጂ የካሎሪና ፕሮቲን አልጄብራ የለ…” ከአሁን አሁን ሳቅ ይላል ያላችሁት ሰው…አለ አይደል… የመረቀነ ቀራጺ የጨበሰበት ጥርብ ሆኖ ቆሞላችኋል፡፡
“ሶሪ..አይ ሀቭ ቱ ጎ…” ብሎ ድሮ የኮከበ ጽባኋ እንትና፣ የዘጠኝ ቁጥርን ፌርማታ አስደግፋችሁ እንደቀረችው ገትሯችሁ ይሄዳል፡፡ ስሙኝማ….እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የእንቁጣጣሽ ሰሞን ከአስራ ምናምን ዓመት በኋላ የተመለሰች ልጅ የሚያውቋት ሰዎች እንዳገኟት፣ የአደገችበትን ሰፈር በኪሎ ሜትሮች ርቃ ስትዘዋወር ከረመች ሲሉ ሰምተናል። ምክንያቱም የሰፈር ሰው ትናንትን ለትችት ብሎ ሳይሆን ለመሳሳቅ ብሎ ማንሳቱ አይቀርማ! “በሌሊት አበባየሆሽ እያለች እንቅልፍ ስትነሳን እንዳልኖረች አሁን እንዲህ ሊያምርባት…” ምናምን የሚል ምስጢር አዋቂ ጎረቤት ይኖራላ! በዘንድሮ ሂሳብ ደግሞ ትናንት ለዘመኑ በሚመች መልኩ ይጻፋል እንጂ ለሳቅና ለትዝታ ተብሎ አይነሳማ!
እናላችሁ… ስለ ነስሩ ፓስቲ ያነሳችሁበት ሰው ምናልባት በሆነ አገር አክቲቪስት ሆኖ ከርሞ የመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ እንኳን የእሱን አክቲቪስትነት ልናውቅ፣ መጣባት የተባለችው አገር በዓመት አንዴም ትዝ አትለንም እኮ! እና በነጻነት ታጋይነት ማንዴላን ከወንበራቸው ሊገፋ ምንም ያልቀረውን ሰው “ድሮ ፊትህን ሁሉ በፓስቲ ዘይት ስትለቀልቅ የነበረው ትዝ ይልሀል?” ማለት ክብረ ነክ ይሆናል፡፡ ለታሪክ አይመችም፣ ለቴሌቪዥን ቃለ መጠይቅ አይመችም፣ “ገና ልጅ ሳለሁ ጀምሮ የሌላ ሰውን ጥቃት ስቃወም ነው የኖርኩት» ለማለት አይመችም፡፡
“ስማ፣ እንደው እዛ ለንደን ቁጭ ብለህ፣ እየተጋፋህ ትበላ የነበረው የበኒን ሰፈር ፉል ትዝ አይልህም?”
“ፉል፣ ሁዋትስ ፉል?”
“ፉል እንዴት ይረሳሃል! እንደውም ሳህኗን ጥርግርግ አድርገህ መጨረሻ ላይ ጣትህን ሁሉ ትልስ አልነበረም እንዴ! በኒን ሰፈር እንዳይታዘብህ!”
“በኒን ሁዋት..ዱ ዩ ሚን ቦሌ?”
አይ ምነው፣ አልበዛም! ምሳውን ሳይቀር ፉሉን እየዋጠ “እሱ እኮ የሚተነፍሰው ባቄላ ብቻ ነው!” ሲባል እንዳልነበረ የምን መዘባነን ነው!
“አሁን ማን ይሙት ያቺን የባቄላ ክትፎ ረሳሁ ልትል ነው?”
“ሶሪ… ሁዋት ዲድ ዩ ሴይ? ባቄላ ማለት ምን ማለት ነው?”
በቀን አስሬ የሚመላለስበትን በኒን ሰፈር አያውቅም፣ ያሳደገውን ባቄላ አያውቅም...ግን እኛ በቀን ሦስቴ እንድንበላ እየታገለልን ነው…ምንም እንኳን በማህበራዊ ሚዲያ ቢሆንም፡፡ የምር እኮ… አለ አይደል… ‘ደስ የምንል’ ዜጎች መአት ነን፡፡
እናላችሁ...ጊዜው ይሁን፣ አየራችን ላይ የተበተነ ነገር ይኑር… ብቻ ራሳችንን ሆነን እንዳንቀርብ እየሆንን ነው። አሁን ትልቁ ሩጫ የበርሊን ማራቶን፣ የእንትን የጎዳና ሩጫ ሳይሆን… ከትናንት ማንነት ለመሸሽ የሚደረገው ሩጫ ነው፡፡ ዛሬያችን የትላንትናችን ውጤት እንዳልሆነ ሁሉ፣ የዛሬው ዋልታና ማገር በትናንቱ መሰረት ላይ የተገነባ እንዳልሆነ ሁሉ…ሽሽት ላይ ነን፡፡
ዘንድሮ ሩጫው ‘ሂሮ’ የመሆን ሩጫ ነው፡፡ “ይቺ ስምን ሰማይ የማድረሻ ጊዜ እንዳታመልጥህ ተሯሯጥ” የተባለ ነው የሚመስለው፡፡ 
“ስሚ፣ ትዝ ይልሻል…ጩጬ ሆነሽ ባለ አበባ የሻማ ቀሚስ የተገዛልሽ ጊዜ እንኳን የጨፈርነው ጭፈራ!”
“የሻማ ምንድነው ያልሽው? ደግሞ ቀሚስ በሻማ ይሠራል እንዴ?!”
“እማዬ ድረሽ!” ትላለች ጠያቂዋ በሆዷ፡፡ “እንዲህማ ሙድ አትይዥብኝም!”
 ጭማሪ ትዝታ…
“ግን ያቺ ቀዳዳዋ ሸራ ጫማሽ የቀሚሷን መልክ አጠፋቻት እንጂ!”
ሴትዮዋ… ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የሚባል ነገር መኖሩን ብታውቅ ኖሮ፣ ይሄኔ ሻንጣዋን ማዘጋጀት ትጀምር ነበር፡፡  ልክ ነዋ… «ገና የስድስት ወር ሕጻን ሳለሁ ጀምሮ ልብስና ጫማዬ ሁሉ ከፈረንሳይና ከጣልያን ብቻ ነበር የሚመጣልኝ” እያለች ፕሮፋይሏን ስታወፍር ከርማ፣ የምን አበባ ቀሚስ ብሎ ነገር ነው! አሁን እኮ ሞዴል (ወይም ‘በተሻሻለው’ አገርኛ አጠራር ‘ሞዴሊስት’) ሆናለች! በእሷ ስሌት ደግሞ የአበባ ቀሚሷና ቀዳዳዋ ሸራ ጫማ ትዝታ ፋሺን ‘ዋን ኦ ዋን’ ከእናቷ ማህጸን ለጀመረች ‘ወንደርገርል’ ፕሮፋይል አይመችማ! እናላችሁ… ትናንትናችንን ለዛሬ ጥንካሬ እንደመጠቀም ከታሪክ ገጽ ለማጥፋት መሞከር (አንዳንድ ታሪኮቻችንን ለማጥፋት እንደሚሞከረው ማለት ነው) ፕሮጀክት ፕሮፖዛል የጻፍንለት ተግባር ነው የሚመስለው፡፡
 “ስማ ትዝ ይልሀል…ቱሪስቶቹ እንኳን በሰፈራችን ሲያልፉ አንተ እንግሊዝኛውን የዝንጀሮ መንጋ የፈነጨበት ማሳ ስታስመስለው...አይ ልጅነት!” እንዲህ የምትሉት ሰው እኮ “ገና ከእናቴ ሆድ ስወጣ መጀመሪያ ‘ጉድ ሞርኒንግ ማሚ’ እንዳልኩ ነግረውኛል” ሊል ምንም የማይቀረው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ሊቀ ጠበብት ነገር እኮ ነው!
የባስ አስራ ሳንቲም አጥቶ ከሽሮ ሜዳ እስከ ስጋ ሜዳ በእግሩ ‘ሲያቀጥን’ እንዳልኖረ (የድሮ አራዶች የሚሉትን ለማስታወስ ያህል) አሁን “ይገርምሀል የቶዮታ ኤክስኪዩቲቭ ወንበር አይመቸኝም፣ ይቆረቁረኛል” አይነት ነገር ሲላችሁ በ“ይቆረቁረኛል የሚነገር እርግማን ስለማታውቁ ነው እንጂ ብታዘንቡበት ደስ ይላችሁ ነበር፡፡
ስሙኛማ… አንዱ ‘ፈረንጅ’ ምን አለ መሰላችሁ… “ብዙ የአፍሪካ መሪዎች ስልጣን ሲይዙ፣ ድሮ እነሱም በባዶ እግራቸው እንደነበሩ ይረሳሉ፡፡” እኛም መገናኛ ብዙሃኖቹን ላጨናነቋቸው ፖለቲከኞች እንላቸዋለን... ስለ ነገ ስታወሩልን  ትናንትን ትምህርት መቅሰሚያ (ከተቻለም ንስሀ መግቢያ) አድርጉት እንጂ ከሰሌዳው ሙሉ ለሙሉ አትፋቁትማ፡፡  ዘንድሮ እኮ ትናንት ‘በጣም ቅርብ’ እየሆነ ነው፡፡ እናማ…“ባቄላ ማለት ምን ማለት ነው?” አትበሉንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 7499 times