Sunday, 23 December 2018 00:00

በአለማቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ገቢ ያገኙ ፊልሞች ይፋ ተደረጉ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

    “አቬንጀርስ - ኢንፊኒቲ ዎር” በ2.04 ቢሊዮን ዶላር ቀዳሚ ሆኗል

    በፈረንጆች 2018 አመት በአለማቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ገቢ ያገኙ የአለማችን ምርጥ ፊልሞች ዝርዝር ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ አቬንጀርስ - ኢንፊኒቲ ዎር የተሰኘው ፊልም በ2.04 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ገቢ የአንደኛነት ደረጃ ላይ መቀመጡ ተነግሯል፡፡
300 ሚሊዮን ዶላር ያህል ፈጅቶ የተሰራው አቬንጀርስ - ኢንፊኒቲ ዎር፣ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በማግኘት በታሪክ አራተኛው ፊልም ሆኖ መመዝገቡን የዘገበው ዴይሊ ሚረር፣ ፊልሙ በአመቱ በአሜሪካ ብቻ 678.8 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አመልክቷል፡፡
ዋካንዳ በተባለችና የኢትዮጵያ ተምሳሌት ናት ተብሎ በሚነገርላት የምናብ አገር ላይ ተመስርቶ የተሰራውና ጥቁር ተዋንያን የሚበዙበት ብላክ ፓንተር በአመቱ 1.34 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
210 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት ብላክ ፓንተር በፈረንጆች 2018 አመት በአሜሪካ ብቻ ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ፊልሙ በርካታ ክብረ ወሰን መስበሩንና በአለማቀፍ ደረጃ ተወዳጅ በመሆን በወረፋ መታየቱን መቀጠሉን ገልጧል፡፡
ዡራሲክ ወርልድ - ፎልን ኪንግደም የተሰኘውና በዩኒቨርሳል ፒክቸርስ ፕሮዲዩስ የተደረገው ፊልም በበኩሉ፤ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት የሶስተኛነት ደረጃን መያዙ ተነግሯል፡፡
ኢንክሪዲብልስ ቱ በ1.2 ቢሊዮን ዶላር፣ ቬኖም በ853 ሚሊዮን ዶላር፣ ሚሽን ኢምፖሲብል - ፎልአውት በ787.4 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደ ቅደም ተከተላቸው፣ ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡


Read 7351 times