Saturday, 22 December 2018 13:07

በ2018 ብቻ 63 ያህል ጋዜጠኞች ተገድለዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ጋዜጠኞችን በማሰር ቻይና ቀዳሚነቱን ይዛለች

     ስራቸውን በማከናወን ላይ ሳሉ ግድያ የሚፈጸምባቸው ጋዜጠኞች ቁጥር እያደገ መምጣቱንና በ2018 ብቻ በአለማችን የተለያዩ አገራት 63 ያህል ጋዜጠኞች መገደላቸውን ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ ባወጣው ሪፖርት እንዳስታወቀ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በስራ ገበታቸው ላይ እያሉ የተገደሉ ጋዜጠኞች ቁጥር ከአምናው በ15 በመቶ የጨመረ ሲሆን በአለማችን ለጋዜጠኞች እጅግ አደገኛ የተባሉት የመጀመሪያዎቹ ሶስት አገራትም አፍጋኒስታን፣ ሶርያና የመን ናቸው፡፡
በአመቱ በአፍጋኒስታን 15፣ በሶርያ 11፣ በየመን 8 ጋዜጠኞች መገደላቸውን የገለጸው ተቋሙ፣ በአመቱ 6 ጋዜጠኞች የተገደሉባት አሜሪካም ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ለጋዜጠኞች እጅግ አደገኛ ከሆኑ አስር አገራት ተርታ መሰለፏን አመልክቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአለማችን የተለያዩ አገራት በድምሩ 348 ያህል ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ የጠቆመው ተቋሙ፣ ቻይና 60፣ ግብጽ 38፣ ቱርክ 33 ጋዜጠኞችን በማሰር ከአለማችን አገራት ቀዳሚነቱን እንደሚይዙ አስታውቋል፡፡
በአለማችን የተለያዩ አገራት ታግተው የሚገኙ ጋዜጠኞች ቁጥር 60 ያህል መድረሱን የጠቆመው ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ፣ ሶርያ 31፣ የመን 17፣ ኢራቅ 11 ጋዜጠኞችን አግተው እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡
ባለፉት 10 አመታት በመላው አለም የተገደሉ ጋዜጠኞች ቁጥር 702 ያህል መድረሱን የገለጸው ተቋሙ፣ ባለፉት አስርት አመታት በርካታ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞች የተገደሉት በፈረንጆች አመት 2012 እንደነበርና በአመቱ 87 ጋዜጠኞች መገደላቸውንም አክሎ አስታውቋል፡፡

Read 1312 times