Sunday, 23 December 2018 00:00

ለንግድና ለድርጅት የሚከራዩ የመንግስት ቤቶች ላይ እስከ 2ሺ ፐርሰንት የሚደርስ አስደንጋጭ የዋጋ ጭማሪ ተደረገ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

ከ6ሺ ብር ወደ 71 ሺ ብር፣ ከ7 ሺ ብር ወደ 140 ሺ ብር አሻቅቧል

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን፤ ለንግድና ለድርጅት አገልግሎት በሚያከራያቸው ቤቶች ላይ ከ500 እስከ 2200 ፐርሰንት የሚደርስ የዋጋ ጭማሪ ያደረገ ሲሆን ከሁለት ሺህ በላይ ተከራዮች ጭማሪው ፍትሃዊ አይደለም ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡   
የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በበኩሉ፤ የክፍያ ተመን ማስተካከያውን ያደረገው ቤቶቹ በሚገኙበት አካባቢ የሚገኙ ተመሳሳይ የግለሰብ ህንፃዎች የሚከራዩበትን ዋጋ ግምት ውስጥ በማስገባት ለረጅም ጊዜ ሲያካሂድ የቆየውን ጥናት ተንተርሶ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የዋጋ ጭማሪው ከሚቀጥለው ጥር ወር 2011 ጀምሮ የፀና እንደሚሆን የገለጸው ኮርፖሬሽኑ፤ በማስተካከያ ዋጋው ላይ ቅሬታ ያላቸው አካላት ደብዳቤው በደረሳቸው በ5 ቀናት ውስጥ ቅሬታ ማቅረብ እንደሚችሉ አስታውቆ፤ ደንበኞች እስከ ታህሳስ 15 ቀን 2011 ድረስ በተሻሻለው ዋጋ መሠረት አዲስ ውል እንዲዋዋሉ አሳስቧል፡፡
“የዋጋ ጭማሪው ወቅቱን ያላገናዘበና የቤቶቹን ውስጣዊ ገጽታ ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው” ያሉት ማሻሻያውን የተቃወሙ ተከራዮች፤ መንግስት አቅማቸውን ታሣቢ ባደረገ መልኩ ጉዳያቸውን በድጋሚ እንዲያጤን  ጠይቀዋል፡፡
አዲሱ የታሪፍ ማሻሻያ በአፄ ኃይለስላሴና  በደርግ  ዘመን  የተሠሩ ቤቶችን በደረጃ በመከፋፈል የተዘጋጀ መሆኑ የታወቀ ሲሆን፤ በቤቶቹ ኪራይ ላይ ከ500 እስከ 2ሺ200 ፐርሰንት የሚደርስ የዋጋ ጭማሪ ተደርጓል፡፡ በወር 6ሺህ ብር ይከፍሉ የነበሩ የጨርቃ ጨርቅ ነጋዴ፣ አሁን 71 ሺህ ብር በወር እንዲከፍሉ ተጠይቀዋል፡፡ ለቢሮ ኪራይ በወር ከ2ሺ እስከ 3ሺ ብር ይከፍሉ የነበሩ ደንበኞች፤ በአዲሱ ማሻሻያ ከ15ሺ እስከ 88ሺ ብር ጭማሪ ተደርጎባቸል - በተሻሻለው ታሪፍ፡፡   
በወር ከ6ሺ እስከ 7ሺ ብር ኪራይ ሲከፍሉ የቆዩ ደንበኞች፤ እስከ 140ሺ ብር እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን ኮርፖሬሽኑ ለደንበኞቹ ከላካቸው የማሳወቂያ ደብዳቤዎች ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፒያሣ አካባቢ 650 ብር ሲከፍል የነበረ  አንድ ሬስቶራንት፤ 140ሺ ብር እንዲከፍል ተወስኖበታል - በወር፡፡
የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሚያስተዳድራቸው ለቢሮና ለንግድ የተከራዩ ቤቶች በፒያሣ፣ መርካቶ፣ አራት ኪሎ፣ ቦሌ፣ ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ፣ ተክለሃይማኖት እንዲሁም ካዛንቺስ በብዛት እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡   


Read 8497 times