Saturday, 22 December 2018 08:07

16 የፖለቲካ ፓርቲዎች የህወሓትን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አወገዙ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

     በፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው የኢትዮጵያ ሶሻል ፓርቲና ኢህአፓን ጨምሮ 16 የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰሞኑን በጋራ ባወጡት መግለጫ፤በትግራይ ክልል “በህውሓት” የሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎችን አውግዘዋል፡፡
ባለፉት 27 አመታት ህወሓት/ኢህአዴግ አገሪቱን ሲያስተዳድር፣ከ1 ትሪሊዮን ብር በላይ በላይ ከኢትዮጵያ በህገ ወጥ መንገድ ወጥቶ፣ በውጭ ሃገር ባንኮች መከማቸቱን መረጃዎች እንደሚያመለክቱ የጠቆሙት ፓርቲዎቹ፤"በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ዲሞክራሲና ነፃነታቸውን በመጠየቃቸው ምክንያት አካላቸው ጎድሏል፣ ተገድለዋል፣ ተሰቃይተዋል" ብለዋል፤በመግለጫቸው፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ አገሪቱን በሚያስተዳድርበት ወቅት ለማመን የሚያዳግቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውንና ከፍተኛ የሆነ የሃገሪቱ ሃብት መመዝበሩን የጠቆሙት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ፤ ሁለቱም የተፈጸሙት በዋናነት "በህወሓት ዘራፊዎችና ገራፊዎች ነው” ብለዋል፡፡ "የድርጊቱ ፈፃሚዎች ግን ፈጽሞ የትግራይን ህዝብ አይወክሉም" ብለዋል - ፓርቲዎቹ፡፡
"ገራፊዎችና ዘራፊዎች" የትግራይ ህዝብን ጋሻ ለማድረግ "የትግራይ ህዝብና ህውሓት አንድ ናቸው" የሚለውን ለማስረገጥ ታህሳስ 5 ቀን 2011 ዓ.ም የተቀነባበረ ሰልፍ በማድረግ፣"እኛን ከነካችሁ ሃገር ትበታተናለች" እያሉ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ መሆኑን አጥብቀን እንቃወማለን፤በቁርጠኝነት እንታገላለን ብለዋል - በመግለጫቸው፡፡
"በተቃዋሚ ፓርቲ ስም ተደራጀተው ከህውሓት ዘራፊዎችና ገራፊዎች ጎን ቆመው ለውጡን ለማደናቀፍ የሚሯሯጡትን እናወግዛለን" ያሉት ፓርቲዎቹ፤ "ህወሓትና አጋሮቹ ምኞታቸው እንዳይሳካ በፅናት እንታገላቸዋለን" ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲከበር የተዘረፉና በሰብአዊ መብት ጥሰት የሚጠየቁ ሁሉ በአፋጣኝ ወደ ህግ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን ሲሉም መንግስት ህግን ለማስከበር እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ አስገንዝበዋል፡፡
ህዝብን ከህዝብ የሚከፋፍሉ ሃሳቦችን በሃሳብን በነፃነት መግለፅ ስም በማህበራዊ ሚዲያዎች እና በተለያዩ መገናኛ አውታሮች የሚያራግቡ ከድርጊቸው እንዲቆጠቡም የፓርቲዎቹ የጋራ መግለጫ ጠይቋል፡፡
ይህን መግለጫ ካወጡት ፓርቲዎች መካከል የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት፣ የጋምቤላ ክልላዊ ንቅናቄ፣ የገዳ ስርአት አራማጅ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ፣ የኦሮሚያ ነፃነት ብሔራዊ ንቅናቄ፣ የሲዳማ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄና ኢህአፓ ይገኙበታል፡፡    

Read 5660 times